በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“አሁን በራሴ አላፍርም”

“አሁን በራሴ አላፍርም”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1963

  • የትውልድ አገር፦ ሜክሲኮ

  • የኋላ ታሪክ፦ የጎዳና ተዳዳሪና የበታችነት ስሜት ይሰማው የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 የተወለድኩት በሰሜናዊ ሜክሲኮ በሚገኘው ስዩታት ኦብሬጎን ሲሆን ከዘጠኝ ልጆች አምስተኛ ነኝ። ያደግነው ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ነው፤ አባቴ እዚያ ትንሽ እርሻ ነበረው። ደስ የሚል ቦታ ነበር፤ ቤተሰባችንም አንድነት ያለውና ደስተኛ ነበር። የሚያሳዝነው ገና የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ከባድ አውሎ ነፋስ ተነሳና እርሻችንን አወደመው፤ በዚህም የተነሳ ወደ ሌላ ከተማ ሄድን።

 አባቴ በቂ ገንዘብ ያገኝ ነበር። ሆኖም የመጠጥ ሱሰኛ ሆነ። ይህ ደግሞ በትዳሩም ሆነ በእኛ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከአባታችን ሲጋራ ሰርቀን ማጨስ ጀመርን። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰከርኩት የስድስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ ተለያዩ፤ የእኔም ሱስ እየተባባሰ ሄደ።

 እናቴ ከሌላ ሰው ጋር መኖር ጀመረች፤ እኛንም ይዛን ሄደች። ሰውየው ገንዘብ አይሰጣትም ነበር፤ እሷ የምታገኘው ገንዘብ ደግሞ እኛን ለማስተዳደር በቂ አልነበረም። ስለዚህ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ ያገኘነውን ሥራ መሥራት ጀመርን፤ ግን የምናገኘው ገንዘብ መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ አያሟላም ነበር። ጫማ እጠርግ እንዲሁም ዳቦ፣ ጋዜጣ፣ ማስቲካና ሌሎች ነገሮችን እሸጥ ነበር። በተጨማሪም ሀብታሞች ከጣሉት ቆሻሻ ውስጥ ምግብ እፈልግ ነበር።

 አሥር ዓመት ሲሞላኝ አንድ ሰው በከተማው የቆሻሻ መጣያ አብሬው እንድሠራ ጠየቀኝ። እኔም በሐሳቡ ስለተስማማሁ ትምህርቴን አቋርጬ ከቤት ወጣሁ። በቀን የሚከፍለኝ ገንዘብ አንድ የአሜሪካ ዶላር እንኳ አይሞላም ነበር፤ የምበላው ደግሞ ከቆሻሻ መጣያው ውስጥ የተሰበሰበ ምግብ ነበር። ከወዳደቁ ዕቃዎች በሠራኋት ጎጆ ውስጥ እኖር ነበር። እዚያ የነበሩት ሰዎች የብልግና ቃላት ይናገሩ እንዲሁም የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። ብዙዎቹ የዕፅና የመጠጥ ሱሰኛ ነበሩ። በሕይወቴ ውስጥ በጣም አስከፊውን ጊዜ ያሳለፍኩት ያኔ ነው፤ በጣም ስለምፈራ በየቀኑ ማታ ማታ አለቅስ ነበር። ድሃ ስለሆንኩና በትምህርቴ ስላልገፋሁ በጣም እሸማቀቅ ነበር። በዚያ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ለሦስት ዓመት ከኖርኩ በኋላ ወደ ሌላ ከተማ ሄድኩ። እዚያም እርሻ ውስጥ አበባና ጥጥ እለቅም፣ ሸንኮራ እቆርጥ እንዲሁም ድንች እሰበስብ ነበር።

ለሦስት ዓመታት እንዲህ ባለ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ኖሬያለሁ

 ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ስዩታት ኦብሬጎን ተመለስኩ። እዚያም ጠንቋይ የሆነች አክስቴ ቤቷ ውስጥ አንድ ክፍል ሰጠችኝ። በዚያ ስኖር ቅዠት ያስቸግረኝ ጀመር፤ በመንፈስ ጭንቀት ከመዋጤ የተነሳ ራሴን ለማጥፋት ጭምር ያሰብኩበት ጊዜ ነበር። አንድ ምሽት እንዲህ ብዬ ለአምላክ ጸለይኩ፦ “ጌታዬ፣ በእርግጥ ካለህ ላውቅህ እፈልጋለሁ፤ ለዘላለም አገለግልሃለሁ። እውነተኛ ሃይማኖት ካለ እባክህ አሳውቀኝ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 ከልጅነቴ አንስቶ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች የማወቅ ጉጉት ነበረኝ። በጣም ልጅ እያለሁ እንኳ ወደ ብዙ አቢያተ ክርስቲያናት ሄጃለሁ፤ ግን አንዳቸውም አላረኩኝም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረኝም ሆነ መንፈሳዊ ጥማቴን የሚያረካልኝ ቤተ ክርስቲያን አላገኘሁም። አንዳንዶቹ ትኩረታቸው ያረፈው ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ የፆታ ብልግና በሚፈጽሙ ሰዎች የተሞሉ ነበሩ።

 አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ የእህቴ ባል የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ሥዕሎችን መጠቀምን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ያሳዩትን ነገረኝ። ዘፀአት 20:4, 5ን አነበበልኝ። ጥቅሱ የተቀረጸ ምስል ሊኖረን እንደማይገባ ይናገራል። ቁጥር 5 “አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ” ይላል። ከዚያም የእህቴ ባል “አምላክ በምስሎች ተጠቅሞ ተአምር የሚሠራ ወይም ምስሎችን ለአምልኮ እንድንጠቀም የሚፈልግ ከሆነ በምስል አትጠቀሙ ያለን ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ጥያቄው የማወቅ ጉጉቴን ቀሰቀሰው። ከዚያ በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ተወያየን። የምናደርገው ውይይት በጣም ስለሚያስደስተኝ ጊዜው ሲሄድ ራሱ አይታወቀኝም ነበር።

 በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ወሰደኝ። እዚያ ያየሁትና የሰማሁት ነገር በጣም አስደነቀኝ። ልጆች እንኳ ከመድረክ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር! ‘የሚያገኙት ሥልጠና በጣም ያስደንቃል!’ ብዬ አሰብኩ። ፀጉሬና አለባበሴ የተዝረከረከ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። እንዲያውም አንድ ቤተሰብ ከስብሰባው በኋላ ራት ጋበዙኝ።

 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ይሖዋ አምላክ አፍቃሪ አባት እንደሆነና ዘራችን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ እንዲሁም የኑሮ ወይም የትምህርት ደረጃችን ምንም ዓይነት ቢሆን እንደሚያስብልን ተማርኩ። አምላክ ፈጽሞ አያዳላም። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) በዚህ ሁኔታ መንፈሳዊ ጥማቴን ማርካት ቻልኩ። ውስጤ የነበረው የባዶነት ስሜትም ጠፋ።

ያገኘሁት ጥቅም

 ሕይወቴ በአስገራሚ መንገድ መለወጥ ጀመረ! ማጨስ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት እንዲሁም የብልግና ቃላት መጠቀም አቆምኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ውስጤ የነበረው ምሬት ጠፋ፤ ያሠቃየኝ የነበረው ቅዠትም ቆመ። በተጨማሪም በልጅነቴ በደረሰብኝ በደልና በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃዬ ምክንያት ይሰማኝ የነበረውን ሥር የሰደደ የበታችነት ስሜት ማሸነፍ ቻልኩ።

 ይሖዋን የምትወድና በሚገባ የምትደግፈኝ ሚስት አግኝቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነኝ፤ ወንድሞቼንና እህቶቼን ለማበረታታትና ለማስተማር የተለያዩ ጉባኤዎችን እጎበኛለሁ። ፈዋሽ በሆነው የአምላክ ቃል እንዲሁም አምላክ በሚሰጠን ግሩም ሥልጠና የተነሳ አሁን በራሴ አላፍርም።

እኔ እርዳታ እንዳገኘሁ ሁሉ ከባለቤቴ ጋር ሆኜ ሌሎችን መርዳት ያስደስተኛል