በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለተጨነቁ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

ለተጨነቁ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

ለተጨነቁ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ

“ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ” ይኖራል። (ሮሜ 8:22) ይህ ቃል ከ1,900 ዓመታት በፊት በተጻፈበት ጊዜ የሰው ልጅ ሥቃይ ከፍተኛ ነበር። ብዙ ሰዎች ተጨንቀው ነበር። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 5:14 NW

ዛሬ፣ የሰው ልጅ ጭንቀት ከዚያ የበለጠ ሆኗል፤ ከምን ጊዜውም በበለጠ ብዙ ሰዎች ተጨንቀዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሊያስደንቀን ይገባልን? አይገባም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻው ቀን” በማለት ያለንበትን ዘመን ለይቶ ያመለክታል። “የሚያስጨንቅ ዘመን” ብሎም ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚያስፈራም ነገር” እንደሚኖር ተንብዮአል።—ሉቃስ 21:7-11፤ ማቴዎስ 24:3-14

ሰዎች ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ሐሳብ፣ ፍርሃት፣ ሐዘን ወይም ሌሎች አፍራሽ ስሜቶች ሲያጋጥሟቸው ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ይይዛቸዋል። የመንፈስ ጭንቀት ወይም የመረረ ሐዘን መንስዔው የሚወዱት ሰው መሞት፣ ፍቺ፣ ከሥራ መፈናቀል፣ ወይም ስር የሰደደና የማይሽር በሽታ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ሰዎች የከንቱነት ስሜት ሲሰማቸው፣ ምንም የማይቀናቸውና ማንኛውንም ሰው የማይጠቅሙ እንደሆኑ በሚሰማቸው ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ይመጣባቸዋል። ማንኛውም ሰው የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞት ሊበሳጭ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አንድ ሰው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማውና መጥፎ ከሆነ ሁኔታ መላቀቅ የሚችልበት መንገድ አልታይ ሲለው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊያድርበት ይችላል።

በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ስሜት አጋጥሟቸዋል። ኢዮብ በበሽታና በደረሰበት መጥፎ አጋጣሚ ተሠቃይቷል። አምላክ እንደተወው ተሰምቶት ስለነበር ሕይወት እንዳንገሸገሸው ገልጾ ነበር። (ኢዮብ 10:1፤ 29:2, 4, 5) ያዕቆብ ልጁ የሞተ መስሎት ተጨንቆ ነበር። ማጽናኛን አልቀበልም ብሎ ነበር፤ ሞትንም ተመኝቷል። (ዘፍጥረት 37:33-35) ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት በመፈጸሙ የተነሣ መንፈሱ ስለተሰበረ የተሰማውን ሐዘን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ቀኑን ሙሉ በሐዘንና በትካዜ አሳለፍሁ። ደክሜያለሁ።”—መዝሙር 38:6, 8 የ1980 ትርጉም፤ 2 ቆሮንቶስ 7:5, 6

ዛሬ ብዙዎች ከአእምሮአቸው፣ ከስሜታቸውና ከሰውነታቸው አቅም በላይ የሆነ የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመግፋት ከሚገባው በላይ በሥራ በመወጠራቸው በመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ተዘፍቀዋል። በውጥረት ላይ አፍራሽ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ሲታከሉበት ሰውነትን ሊጎዱና በአእምሮ ውስጥ የኬሚካል አለመመጣጠን እንዲኖር አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። በዚህም ሳቢያ የመንፈስ ጭንቀት ይከሰታል።—ከምሳሌ 14:30 ጋር አወዳድር።

የሚያስፈልጋቸው እርዳታ

በፊልጵስዩስ ይኖር የነበረ አንድ አፍሮዲጡ የተባለ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ‘እንደ ታመመ [ጓደኞቹ] ስለሰሙ ተጨንቆ ነበር።’ ጓደኞቹ ለሐዋርያው ጳውሎስ ስንቅ አስይዘው ወደ ሮም ከላኩት በኋላ የታመመው አፍሮዲጡ ጓደኞቼ ያሰቡትን አልፈጸምኩላቸውም፤ ምንም የማይቀናው ሰው ነው ይላሉ የሚል ስሜት ሳይሰማው አይቀርም። (ፊልጵስዩስ 2:25-27፤ 4:18) ሐዋርያው ጳውሎስ የረዳው እንዴት ነበር?

በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ጓደኞቹ የጻፈውን እንዲህ የሚል ደብዳቤ አስይዞ አፍሮዲጡን ወደ ቀዬው ላከው:- “[አፍሮዲጡን] በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፣ እርሱን የሚመስሉትን አክብሯቸው።” (ፊልጵስዩስ 2:28-30) ጳውሎስ እሱን በማሞገስ መናገሩና የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እርሱን በጋለ መንፈስና የመውደድ ስሜት መቀበላቸው አፍሮዲጡን አጽናንቶትና ጭንቀቱንም ለማቃለል ረድቶት መሆን አለበት።

“የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የተጨነቁ ሰዎችን ለመርዳት ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንደሆነ አያጠራጥርም። “ሌላው ሰው እንደሚያስብልህ ማወቅ በጣም ይረዳል” በማለት አንዲት በመንፈስ ጭንቀት ትሠቃይ የነበረች ሴት ተናግራለች። “አንድ ሰው ‘ችግርህ ገብቶኛል፤ ደህና ትሆናለህ’ ብሎ ሲናገር መስማቱ በጣም አስፈላጊ ነው።”

የተጨነቀው ሰው ብዙውን ጊዜ በእሱ ቦታ ሆኖ ችግሩን የሚረዳለትና ምሥጢሩን የሚካፈለው ሰው ፈልጎ ለማግኘት ራሱ መነሳሳት ይኖርበታል። እርዳታ የሚሰጠው ሰው በጥሞና የሚያዳምጥና ትዕግሥተኛ መሆን ይኖርበታል። እሱ ወይም እሷ የተጨነቀውን ሰው ከመውቀስ ወይም ‘እንዲህ ሊሰማህ አይገባም’ ወይም ‘ልክ አይደለህም’ የሚሉትን የመሰሉ ትችቶችን ከማቅረብ መታቀብ ያስፈልጋቸዋል። የተጨነቀው ሰው በቀላሉ ሆድ ይብሰዋል፤ እንዲህ ያሉ ሂሶች ደግሞ ስለራሱ ከበፊቱ የባሰ መጥፎ ስሜት እንዲሰማው ከማድረግ በስተቀር የሚፈይዱት ነገር አይኖርም።

አንድ የተጨነቀ ሰው የማይረባ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። (ዮናስ 4:3) ይሁን እንጂ ዋናው ነገር አምላክ አንድን ሰው እንዴት ይመለከተዋል የሚለው ጥያቄ መሆኑን ማስታወስ ይኖርበታል። ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ‘ንቀውት’ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ በአምላክ ፊት የነበረውን ቦታ አልለወጠበትም። (ኢሳይያስ 53:3) አምላክ ውድ ልጁን የሚወደውን ያህል እርስዎንም እንደሚወድዎት እርግጠኛ ይሁኑ።—ዮሐንስ 3:16

ኢየሱስ ተጨንቀው ለነበሩት ሰዎች አዝኖላቸዋል፤ በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ዋጋማነት እንዲገነዘቡም ለመርዳት ሞክሯል። (ማቴዎስ 9:36፤ 11:28-30፤ 14:14) ሌላው ቀርቶ አነስተኛ የሆኑትና ከቁብ የማይቆጠሩት ድንቢጦች በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳላቸው ገልጿል። “ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም” ብሏል። የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚጥሩትን የሰው ልጆችማ ምንኛ የላቀ ዋጋ ይሰጣቸው! ኢየሱስ ስለዚህ ሲናገር “የእናንተ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው” ብሏል።—ሉቃስ 12:6, 7

እውነት ነው፣ ከባድ ጭንቀት ውስጥ የተዘፈቀና በድክመቱና በሚሠራቸው ስህተቶች ትልቅ ሐዘን የተሰማው ሰው በአምላክ ፊት ከፍተኛ ዋጋ አለኝ ብሎ ማመን ሊያስቸግረው ይችላል። የአምላክ ፍቅርና እንክብካቤ ፈጽሞ እንደማይገባው ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ‘ልባችን በእኛ ላይ ይፈርዳል’ ሲል የአምላክ ቃል ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ ወሳኙ ነገር ይህ ነውን? በፍጹም አይደለም። ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች አፍራሽ አስተሳሰብ ሊያድርባቸው እንደሚችልና አልፎ ተርፎም በራሳቸው ላይ ሊፈርዱ እንደሚችሉ አምላክ ያውቃል። ስለዚህ ቃሉ “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል” በማለት ማጽናኛ ይሰጣቸዋል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20

አዎን፣ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ከምንሠራቸው ኃጢአቶችና ስህተቶች አሻግሮ ሌሎች ሁኔታዎችንም ይመለከታል። ስህተት እንድንፈጽም የሚያደርጉንን አስጨናቂ ሁኔታዎች፣ የምንከተለውን የአኗኗር መንገድ በጠቅላላ እንዲሁም ዝንባሌያችንንና አስተሳሰባችንን ያውቃል። ኃጢአትን፣ በሽታንና ሞትን ከወላጆቻችን እንደወረስንና በዚህም የተነሣ አቅማችን ውስን መሆኑን ያውቃል። በራሳችን ማዘናችንና መበሳጨታችን ራሱ ኃጢአት መሥራት እንደማንፈልግና ከአምላክ ብዙ ርቀን እንዳልሄድን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ከፈቃዳችን ውጪ ‘ለከንቱነት እንደተገዛን’ ይናገራል። ስለዚህ አምላክ በሚደርስብን መጥፎ ሁኔታ ያዝንልናል፤ ድክመቶቻችንንም በርኅራኄ ግምት ውስጥ ያስገባልናል።—ሮሜ 5:12፤ 8:20

“እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። “ምሥራቅም ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ።” (መዝሙር 103:8, 12, 14) እውነትም ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው። “እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

የተጨነቁ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው እርዳታ በአብዛኛው የሚገኘው ወደ መሐሪው አምላካቸው በመቅረብና ‘ትካዜያቸውን በእርሱ ላይ እንዲጥሉ’ ያቀረበላቸውን ግብዣ በመቀበል ነው። በእርግጥም “የተቀጠቀጠውን ልብ ሕያው” ማድረግ ይችላል። (መዝሙር 55:22፤ ኢሳይያስ 57:15) ስለዚህ የአምላክ ቃል “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ [በይሖዋ] ላይ ጣሉት” በማለት እንድንጸልይ ያበረታታናል። (1 ጴጥሮስ 5:7) አዎን፣ በጸሎትና በምልጃ አማካኝነት ሰዎች ወደ አምላክ መቅረብ ይችላሉ። በዚህ መንገድ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” በማግኘት መደሰት ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ መዝሙር 16:8, 9

በኑሮ ዘይቤም ላይ ተግባራዊ ለውጦችን ማድረግ አንድ ሰው አንድን የመንፈስ ጭንቀት እንዲቋቋም ሊረዳው ይችላል። የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ገንቢ ምግብ መብላት ንጹሕ አየርና በቂ ዕረፍት ማግኘት እንዲሁም ከሚገባው በላይ ቴሌቪዥን ከመመልከት መቆጠብ ሁሉም ጠቃሚ ናቸው። አንዲት ሴት ከበድ ያለ የእግር ጉዞ እንዲያደርጉ በመቀስቀስ የተጨነቁ ሰዎችን መርዳት ችላለች። አንዲት የመንፈስ ጭንቀት ያደረባት ሴት “በእግሬ ወዲያና ወዲህ መንሸራሸር አልፈልግም” ባለቻት ጊዜ ሴትየዋ በእርጋታ “አዎን፣ ትሄጃለሽ” በማለት ጠበቅ አድርጋ መለሰችላት። ሴትየዋ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- ‘ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ ተጓዝን። ወደ ቤት ስንመለስ ድክም ብሏት የነበረ ቢሆንም ተሽሏት ነበር። ሞክረህ እስክታየው ድረስ ከበድ ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ምን ያህል እንደሚጠቅም ማመን አትችልም።”

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሕክምናዎችን ጨምሮ ማንኛውም ነገር ቢሞከር እንኳን የመንፈስ ጭንቀትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ አይቻልም። “ሁሉንም ነገር ሞክሬያለሁ” በማለት አንዲት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ተናግራለች። “ጭንቀቱ ግን እንዳለ ነው።” ልክ እንደዚሁም ብዙውን ጊዜ ዕውሮችን፣ ደንቆሮዎችን ወይም ሽባዎችን መፈወስ አይቻልም። ሆኖም የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው ሰዎች የሰው ልጅ በሽታዎች በሙሉ ተወግደው ዘላቂ እፎይታ የሚገኝበትን አስተማማኝ ተስፋ የሚገልጸውን የአምላክ ቃል ዘወትር በማንበብ መጽናኛና ተስፋ ማግኘት ይችላሉ።—ሮሜ 12:12፤ 15:4

ማንም ሰው ዳግመኛ የማይጨነቅበት ጊዜ

ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች በምድር ላይ የሚከሰቱትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በዘረዘረ ጊዜ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ [መዳናችሁ] ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።” (ሉቃስ 21:28) ኢየሱስ ከጥፋት ተርፎ ጽድቅ ወደሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ስለመግባት መናገሩ ነበር። በዚያ ዓለም “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት” ይደርሳል።—ሮሜ 8:21

ቀደም ሲል ከነበሩት ጫናዎች መላቀቅና በየቀኑ ፍጹም ብሩህ የሆነ አእምሮ ይዞ የዕለቱን የሥራ እንቅስቃሴ በሚገባ ለማከናወን በመጓጓት መነሣት ለሰው ዘር እንዴት ያለ እፎይታ ይሆን! የጭንቀት ደመና በማንም ሰው ላይ ማንዣበቡ ያበቃለት ነገር ይሆናል። ለሰው ዘር የተሰጠው አስተማማኝ ተስፋ እግዚአብሔር “እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ይላል።—ራእይ 21:3, 4

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።