መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ነው ተብሎ ትምክሕት ሊጣልበት አይችልም ይላሉ። አመለካከታቸውም ሰፊ ተቀባይነት አገኝቷል። ይህም በመሆኑ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሁሉ እውነት አይደለም በማለት ገሸሽ ያደርጉታል።
በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ሲል የተናገረው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ማመንን የሚያበረታታ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በአምላክ መንፈስ መሪነትና አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ይናገራል።—ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ ለመተማመን ጠንካራ መሠረት ይኖራልን? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ላለመሆኑ ይኸውም እርስ በርሱ የሚጋጭና አንድ ወጥ ሐሳብ የሌለው ለመሆኑ ማስረጃ ይገኛልን?
እርስ በርሱ የሚጋጭ ነውን?
ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል ቢሉም ለዚህ አንድ ምሳሌ ያሳየዎት ሰው ይኖራልን? የሚቀርቡበትን የምርመራ ጥያቄዎች መቋቋም የሚችል አንድም ምሳሌ አይተን አናውቅም። እርግጥ በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ እርስ በርስ የሚቃረኑ የሚመስሉ ሐሳቦች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ያላቸው ችግር አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችንና በዚያን ጊዜ የነበሩትን ሁኔታዎች አለማወቃቸው ነው።
ለምሳሌ አንዳንዶች ‘ቃየን ሚስት ከየት አገኘ?’ ብለው በመጠየቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት ለመጠቆም ይሞክራሉ። አዳምና ሔዋን የነበሯቸው ልጆች ቃየንና አቤል ብቻ ናቸው ብለው ያስባሉ። አስተሳሰባቸው ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ካለመረዳት የተነሳ የተፈጠረ ነው። አዳም “ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 5:4) ስለዚህ ቃየን ከእህቶቹ አንዷን አግብቶ ነበር ማለት ነው። ወይም ደግሞ የወንድሙን ወይም የእህቱን ልጅ አግብቶ ሊሆን ይችላል።
ለመተቸት የሚፈልጉ ሰዎች እርስ በርስ የሚቃረን ሐሳብ ለማግኘት ይጥራሉ። ስለዚህ ‘መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት አንዱ የሆነው ማቴዎስ አንድ የጦር መኰንን ኢየሱስ እንዲረዳው ወደ እርሱ መጣ ይላል፤ ሉቃስ ግን ወደ ኢየሱስ የመጡት መኰንኑ የላካቸው ሰዎች ናቸው ይላል። ታዲያ ትክክለኛው ሐሳብ የትኛው ነው?’ ይላሉ። (ማቴዎስ 8:5, 6፤ ሉቃስ 7:2, 3) ይሁንና ይህ በእርግጥ እርስ በርሱ የሚቃረን ነውን?
ሰዎች ያከናወኑት አንድ ሥራ የበላይ ኃላፊያቸው እንደሠራው ተደርጎ ቢወራ ምክንያታዊ የሆነ ሰው ነገሩ ሐሰት ነው ብሎ አይናገርም። ለምሳሌ ያህል በአንድ ከተማ አንድን መንገድ የከተማው ከንቲባ እንደሠሩት ተደርጎ ዘገባ ቢቀርብ ነገር ግን መንገዱን የሠሩት መሐንዲሶችና ሌሎች ሠራተኞች ቢሆኑ እርስዎ ዘገባው ስሕተት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታልን? እንደዚያ አድርገው እንደማይመለከቱት የተረጋገጠ ነው። በተመሳሳይም ማቴዎስ የጦር መኰንኑ ኢየሱስን እንዲረዳው ጠየቀው ቢልና ሉቃስ ይህ ጥያቄ የቀረበው በልዑካን አማካኝነት ነው ብሎ ቢዘግብ ዘገባው እርስ በርስ የሚቃረን አይሆንም።
ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫዎች በተገኙ ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ስሕተት የሚመስሉ ሐሳቦች ትክክል ሆነው ይገኛሉ።
ታሪክና ሳይንስ
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትክክለኛነት በአንድ ወቅት በሰፊው በጥርጣሬ የሚታይ ነበር። ለምሳሌ ተቺዎች ሳርጎን እንደተባለው የአሦር ንጉሥ፣ እንደ ባቢሎኑ ብልጣሶርና የሮሙ ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸው ሰዎች በእርግጥ በሕይወት የነበሩ ሰዎች ስለመሆናቸው ተጠራጥረውት ነበር። ይሁን እንጂ የቅርብ ጊዜ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትክክል መሆኑን አንድ በአንድ አረጋግጠዋል። ታሪክ ተመራማሪው ሞሼ ፐርልማን “በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተዘገቡት ታሪኮችም ሳይቀር ትክክለኛ ስለመሆናቸው ይጠራጠሩ የነበሩ ተቺዎች አመለካከታቸውን በድንገት መለወጥ ጀምረዋል” ሲሉ ጽፈዋል።
መጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ ነው ብለን እንድናምንበት ከተፈለገ ከሳይንስም አንፃር ሲታይ ትክክለኛ መሆን አለበት። ታዲያ እንደዚያ ነውን? ሳይንቲስቶች መጽሐፍ ቅዱስን በመቃረን ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ የለውም ብለው ሲከራከሩ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ሆኖም የከዋክብት ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮ በቅርብ ጊዜ ይህን መግለጫ የሚያፈርስ አዲስ አሳብ ጠቅሰዋል:- “በከዋክብት ጥናት የተገኘው ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም አፈጣጠር ወደሚገልጸው አሳብ እንደሚመራን እያየን ነው። ዝርዝር ሁኔታው ይለያይ እንጂ በከዋክብት ምርምርና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹት ዋና ዋና ነገሮች አንድ ናቸው።”—ሰዎች ስለ መሬት ቅርጽ የነበራቸውንም አስተሳሰብ ቀይረዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ “ጠፈርን ለመመራመር የተደረጉ ጉዞዎች የመሬት ቅርጽ ብዙ ሰዎች ያምኑት እንደነበረው ጠፍጣፋ ሳይሆን ክብ እንደሆነ አሳይተዋል” በማለት ገልጿል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ ትክክለኛ ነበር! እነዚህ የጠፈር ጉዞዎች ከመደረጋቸው ከ2,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 40:22 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በምድር ክበብ ላይ” ወይም ሌሎች ትርጉሞች እንደሚሉት “በሉል ምድር” (ዱዌይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) “ድቡልቡል በሆነችው ምድር ዙሪያ” (ሞፋት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ይቀመጣል።”
ስለዚህ ሰዎች በምርምር ብዙ እያወቁ በሄዱ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ሊታመንበት እንደሚችል የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ ይገኛል። የብሪቲሽ ሙዚየም የቀድሞ ዲሬክተር የነበሩት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “እስከ ዛሬ ድረስ የተገኙት የምርምር
ውጤቶች መጽሐፍ ቅዱስን ዋጋ አላሳጡትም፤ እንዲያውም እያደገ የሄደው ዕውቀት ለመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እየሰጠ ነው።”ወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ መናገር
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ይሆናሉ የሚላቸው ነገሮች፣ ለምሳሌ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይመጣል ሲል የሚሰጠው ተስፋ ጭምር ልንተማመንባቸው እንችላለንን? (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ባለፉት ዘመናት ተመዝግቦ የሚገኘው ማስረጃ ምን ያሳያል? ከመቶ ዓመታት እንኳን ቀደም ብሎ የተነገሩ ትንቢቶች በትክክል በዝርዝር ተፈጽመዋል! ይህ ተደጋግሞ ታይቷል።
ለምሳሌ ያህል ኃያል የነበረችው ባቢሎን እንደምትወድቅ 200 ዓመታት ቀደም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። እንዲያውም ከፋርሳውያን ጋር ግንባር የፈጠሩት ሜዶናውያን ድል አድራጊዎች እንደሚሆኑ በስም ተጠቅሰዋል። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ገና ሳይወለድ ስመጥር ድል አድራጊ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። የባቢሎን መከላከያ የሆነው ውኃ ይኸውም የኤፍራጥስ ወንዝ እንደሚደርቅና ‘የባቢሎን በሮችም እንደሚዘጉ’ መጽሐፍ ቅዱስ ተናግሮ ነበር።—ኤርምያስ 50:38፤ ኢሳይያስ 13:17–19፤ 44:27 እስከ 45:1
ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዱተስ እንደዘገበው እነዚህ በዝርዝር የተገለጹ ሁኔታዎች ተፈጽመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ባቢሎን በመጨረሻ ለመኖሪያነት የማትሆን የፍርስራሽ ቦታ ሆና እንደምትቀር መጽሐፍ ቅዱስ በቅድሚያ ተናግሮ ነበር። ልክ እንደዚያው ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ባቢሎን የፍርስራሽ ቁልል ያለባት ባዶ መሬት ናት። (ኢሳይያስ 13:20–22፤ ኤርምያስ 51:37, 41–43) መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ ፍጻሜ ባገኙ በሌሎች ትንቢቶችም የተሞላ ነው።
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በዓለም ላይ ያለውን የነገሮች ሥርዓት በሚመለከት ምን ትንቢት ይናገራል? እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ። 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
የአምልኮት መልክ አላቸው፣ ኃይሉን ግን ክደዋል።”—በእርግጥም አሁን የዚህን ፍጻሜ እየተመለከትን ነው! ነገር ግን ስለዚህ ዓለም ‘መጨረሻ ዘመንም’ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ ራብም ይሆናል’ በማለት ትንቢት ተናግሯል። በተጨማሪም “ታላቅ የመሬት መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” እንደሚሆን ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:11
በእርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ነው! ይሁንና “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” እንዲሁም “ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ ይለውጣሉ . . . ከዚያም በኋላ የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም” ስለሚሉትና ስለመሳሰሉት ገና ወደፊት ስለሚፈጸሙ ትንቢቶች ምን ለማለት ይቻላል?—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 2:4፤ የ1980 ትርጉም
አንዳንዶች ‘እንደዚያ ቢሆን በጣም ጥሩ ነበር፤ ግን ሊሆን አይችልም’ ይላሉ። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን የገባልንን ተስፋ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለንም። የእርሱ ቃል ሊታመን የሚችል ነው! (ቲቶ 1:2) እርስዎ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ቢመረምሩ ይህ አባባል በጣም እውነተኛ ሆኖ ያገኙታል።
ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እስከ ዛሬ ድረስ የተገኙት የምርምር ውጤቶች መጽሐፍ ቅዱስን ዋጋ አላሳጡትም፤ እንዲያውም እያደገ የሄደው ዕውቀት ለመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እየሰጠ ነው።”