በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተዓምራቱ በእርግጥ ተፈጽመዋልን?

ተዓምራቱ በእርግጥ ተፈጽመዋልን?

ምዕራፍ 6

ተዓምራቱ በእርግጥ ተፈጽመዋልን?

በ31 እዘአ አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በሰሜናዊ ጳለስጢና ወደምትገኘው ናይን ከተማ እየተጓዙ ነበር። ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረቡ አስከሬን አጅበው ወደ ቀብር የሚሄዱ ሰዎች አገኙ። የሞተው አንድ ወጣት ነበር። የዚህ ወጣት እናት ባሏ የሞተባት ሴት ስትሆን የነበራት ልጅ አንድ እርሱ ብቻ ስለነበር አሁን ብቻዋን መቅረቷ ነው። ዘገባው እንደሚገልጽልን ኢየሱስ “አዘነላትና:- አታልቅሽ አላት። ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፣ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም:- አንተ ጎበዝ እልሃለሁ፣ ተነሣ። የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ።”—⁠ሉቃስ 7:​11-15

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ኢየሱስ በናይን ከተማ አቅራቢያ የሠራው ተዓምር ምንድን ነው? (ለ) ተዓምራት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያህል ቦታ አላቸው? ይሁንና እነዚህ ተዓምራት እንደተፈጸሙ ሁሉም ሰዎች ያምናሉን?

ይህ ልብ የሚነካ ታሪክ ነው። ይሁን እንጂ እውነት ነውን? ብዙ ሰዎች እንደነዚህ ዓይነት ነገሮች በእርግጥ ተፈጽመዋል ብለው ማመን ይከብዳቸዋል። የሆነ ሆኖ ተዓምራት ከመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ ተነጥለው የሚታዩ ነገሮች አይደሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን ማለት ተዓምራት እንደተፈጸሙ ማመን ማለት ነው። እንዲያውም ጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተመሠረተው ትልቅ ግምት በሚሰጠው አንድ ተዓምር ላይ ሲሆን ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።

አንዳንዶች የማያምኑበት ምክንያት

2, 3. ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሃም ተዓምራት ሊፈጸሙ አይችሉም የሚለውን ሐሳቡን ለማሳመን የተጠቀመበት አንደኛው የመከራከሪያ ነጥብ ምንድን ነው?

2 በተዓምራት ታምናለህ? ወይስ በዚህ በሳይንስ በተራቀቀ ዘመን ተዓምራት ወይም በሌላ አባባል ከሰው በላይ በሆነ ኃይል ጣልቃ ገብነት አስገራሚ ክንውኖች ተፈጽመዋል ብሎ ማመን ምክንያታዊ እንደማይሆን ይሰማሃል? በተዓምራት አላምንም የምትልም ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከሁለት መቶ ዘመናት በፊት የነበረው ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሃም ተመሳሳይ ችግር ነበረበት። ምናልባትም አንተ በተዓምራት የማታምንበት ምክንያት ከእርሱ ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል።

3 ሃም ተዓምራት ይከናወናሉ የሚለውን ሐሳብ የተቃወመው ከሦስት ዋና ዋና ነጥቦች በመነሣት ነበር።1 የመጀመሪያውን ምክንያት ሲገልጽ “ተዓምር የተፈጥሮን ሕግ የሚጻረር ነገር ነው” በማለት ጽፏል። የሰው ልጅ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ዘመናት አንስቶ በተፈጥሮ ሕግ ላይ ሲመካ ኖሯል። አንድን ዕቃ በቁሙ ከእጁ ቢለቅቀው እንደሚወድቅ፣ ፀሐይ ሁልጊዜ ጠዋት ወጥታ ማታ እንደምትጠልቅና የመሳሰሉትን ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል። ማንም ባይነግረውም ሁሉም ነገሮች ተመሳሳይ ሥርዓት ተከትለው እንደሚሄዱ ያውቃል። ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ የሆነ ምንም ነገር ሊፈጸም አይችልም። ሃም ተዓምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ለሚለው ክርክሩ ይኸኛው ‘ማስረጃ’ “ምንም እንከን የማይወጣለት” እንደሆነ ተሰምቶታል።

4, 5. ዴቪድ ሃም ተዓምራት ሊፈጸሙ እንደማይችሉ ለማሳመን ያቀረባቸው ሌሎች ሁለት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

4 ሁለተኛው ምክንያቱ ሰዎች በቀላሉ ይሞኛሉ የሚል ነበር። አንዳንድ ሰዎች በተለይ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ከሆነ በድንቆችና በተዓምራት ማመን ይፈልጋሉ። ተዓምር የሚባሉት ብዙዎቹ ነገሮች ደግሞ ሐሰት ሆነው ተገኝተዋል። ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ባብዛኛው ተዓምራት ተፈጽመዋል ተብሎ የሚነገረው ሥልጣኔ ባልነበረበት ዘመን ነው። የተማሩ ሰዎች እየተበራከቱ ሲመጡ ተዓምራት ተፈጸሙ እያሉ ማውራት እየቀረ መጥቷል። እንደ ሃም አገላለጽ ከሆነ “እንዲህ ዓይነት እንግዳ ክስተቶች በእኛ ዘመን ፈጽሞ አይታዩም።” በመሆኑም ከዚህ ቀደምም ቢሆን ተዓምራት አልተፈጸሙም ለማለት እንደሚቻል ተሰምቶታል።

5 እስከ ዛሬም ድረስ ተዓምራትን በመቃወም የሚቀርቡት የመከራከሪያ ነጥቦች እነዚህኑ አጠቃላይ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተመረኮዙ ስለሆኑ ሃም ያቀረባቸውን የተቃውሞ ሐሳቦች አንድ በአንድ እንመርምር።

የተፈጥሮን ሕግ ይጻረራሉን?

6. ተዓምራት ‘የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረኑ’ ናቸው በሚል ምክንያት ሊፈጸሙ አይችሉም ብሎ መከራከር ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው?

6 ተዓምራት ‘የተፈጥሮን ሕግ ስለሚቃረኑ’ እውነት ሊሆኑ አይችሉም የሚለውን የተቃውሞ ሐሳብ በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል? እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ለተመለከተው ሰው ይህ አሳማኝ ምክንያት ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ በእርግጥ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው። አብዛኛውን ጊዜ ተዓምር ከተለመዱት የተፈጥሮ ሕጎች ውጭ የሚፈጸም ነገር ነው ለማለት ይቻላል። * ያልተጠበቀ ነገር ከመሆኑ የተነሣ ተመልካቾች ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እጁን ያስገባበት ነገር ሲፈጸም ማየታቸውን እንዲያምኑ የሚያደርግ ነገር ነው። በመሆኑም ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ‘ተዓምራት ተዓምራዊ በመሆናቸው ብቻ ሊፈጸሙ አይችሉም!’ የሚል ነው። ተቻኩለህ ወደዚህ መደምደሚያ ከመድረስህ በፊት ማስረጃዎቹን ለምን አትመረምርም?

7, 8. (ሀ) ሳይንቲስቶች ከምናውቃቸው የተፈጥሮ ሕጎች አንጻር ምን ነገር ሊሆን ይችላል ምን ነገር ሊሆን አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይ አመለካከታቸውን ያሰፉት እንዴት ነው? (ለ) በአምላክ የምናምን ከሆነ እንግዳ የሆኑ ነገሮችን ለማከናወን ያለውን ኃይል በተመለከተ ምን ነገር ልናምን ይገባል?

7 ሐቁ ግን ዛሬ ያሉት የተማሩ ሰዎች የተለመዱት የተፈጥሮ ሕጎች በማንኛውም ቦታና አጋጣሚ ተግባራዊ ይሆናሉ ለማለት የዴቪድ ሃምን ያህል አይደፍሩም። ሳይንቲስቶች ከተለመዱት ሦስትዮሽ ስፍረቶች (three dimensions) ማለትም ከርዝመት፣ ከስፋትና ከቁመት በተጨማሪ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ብዙ ስፍረቶች ይኖሩ ይሆናል የሚለውን ሐሳብ ለማስተናገድ ፈቃደኞች ናቸው።2 ሳይንቲስቶች፣ ግዙፍ ከዋክብት የዴንሲቲያቸውን መጨረሻ መገመት እስከማይቻል ድረስ እየተኮማተሩ ሄደው ብላክ ሆል የሚባል ነገር ይፈጠራል የሚል ቲዮሪ አላቸው። በእነዚህ ከዋክብት አካባቢ የሕዋው አሠራር ራሱ ስለሚዛባ ጊዜ ባለበት ይቆማል እየተባለም ይነገራል።3 አልፎ ተርፎም ሳይንቲስቶች አንዳንድ ሁኔታዎች ጊዜን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ሊያስኬዱት ይችላሉ ሲሉ ተከራክረዋል!4

8 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቴፈን ደብልዩ ሃውኪንግ ሉካሴያን አጽናፈ ዓለሙ እንዴት እንደጀመረ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “በነባሩ አጠቃላይ የንጽጽራዊ ቲዮሪ መሠረት . . . አጽናፈ ዓለሙ የተገኘው ማብቂያ የሌለው ዴንሲቲና የህዋ⁠-⁠ጊዜ ኩርበት [space-time curvature] በስበት ኃይል ሲዛቡ መሆን አለበት። እንዲህ ባለው ሁኔታ ሥር ደግሞ የሚታወቁት የፊዚክስ ሕጎች በሙሉ አይሠሩም።”5 በመሆኑም ዛሬ ያሉት ሳይንቲስቶች አንድ ነገር ከተለመዱት የተፈጥሮ ሕጎች ጋር የሚቃረን ስለሆነ ብቻ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም የሚል እምነት የላቸውም። እንግዳ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንግዳ የሆኑ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ እንዳለ የምናምን ከሆነ ከዓላማው ጋር የሚስማማ ሆኖ ሲያገኘው እንግዳ የሆነ ማለትም ተዓምራዊ ነገር እንዲፈጸም ማድረግ እንደሚችል አምነን መቀበል ይኖርብናል።​—⁠ዘጸአት 15:​6-10፤ ኢሳይያስ 40:​13, 15

የሐሰት ተዓምራትን በሚመለከት ምን ማለት ይቻላል?

9. አንዳንድ የሐሰት ተዓምራት መኖራቸው እውነት ነውን? ለምን እንደዚያ ብለህ እንደመለስክ አብራራ።

9 ምክንያታዊ የሆነ ማንም ሰው የሐሰት ተዓምራት እንዳሉ አይክድም። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች የታመሙ ሰዎችን በእምነት ፈውስ ለማዳን የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው ይናገራሉ። የሕክምና ዶክተር የሆኑት ዊሊያም ኤ ኖላን ሥራዬ ብለው እንዲህ ባሉት ፈውሶች ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የእምነት ፈዋሾችም ሆኑ በእስያ ያሉ መንፈሳዊ ኃይል ተሰጥቷቸዋል የሚባልላቸው ሰዎች ፈውሰዋቸዋል የተባሉትን ብዙ ግለሰቦች ሁኔታ በቅርብ ተከታትለዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ያገኟቸው ሰዎች በሙሉ ያሰቡት ባለመፈጸሙ ያዘኑና የተታለሉ ነበሩ።6

10. አንዳንድ ተዓምራት ሐሰት ሆነው መገኘታቸው ሁሉም ተዓምራት የሐሰት ናቸው ለማለት የሚያስችል እንደሆነ ይሰማሃልን?

10 እንዲህ ዓይነት ማታለል ተፈጽሟል ማለት እውነተኛ ተዓምራት ፈጽሞ አልተከናወኑም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የሐሰት የገንዘብ ኖቶች እንደተሠራጩ እንሰማለን። ይህ ማለት ግን ሁሉም የገንዘብ ኖት የሐሰት ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ የታመሙ ሰዎች መድኃኒት አዋቂ ነን በሚሉ ሰዎችና አታላይ ሐኪሞች ላይ ትልቅ እምነት በመጣል ገንዘባቸውን ይከሰክሳሉ። ይህ ማለት ግን ሁሉም ሐኪሞች አጭበርባሪዎች ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንድ ሰዓሊያን “የጥንቱን [የሥዕል] ሥራ” አስመስለው በመሥራት በኩል የተካኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ሁሉም ሥዕሎች በዚህ መንገድ የተሠሩ ናቸው ማለት አይደለም። እንደዚህም ሁሉ አንዳንዶች ተዓምራት እንሠራለን ማለታቸው ሐሰት ሆኖ ስለተገኘ ብቻ እውነተኛ ተዓምር በፍጹም ሊከናወን አይችልም ማለት አይደለም።

‘ዛሬ ተዓምራት አይፈጸሙም’

11. ዴቪድ ሃም ተዓምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ያለበት ሦስተኛ ምክንያት ምንድን ነው?

11 ሦስተኛው የተቃውሞ ሐሳብ “እንዲህ ዓይነት እንግዳ ክስተቶች በእኛ ዘመን ፈጽሞ አይታዩም” የሚል ነው። ሃም ተዓምር ሲፈጸም አይቶ ስለማያውቅ ተዓምራት ይፈጸማሉ ብሎ ማመን ከብዶታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሁልጊዜ አያዋጣም። ማንኛውም አስተዋይ የሆነ ሰው ከስኮትላንዳዊው ፈላስፋ በፊት በነበረው ዘመን የተፈጸሙ በእርሱ ዘመን ግን ያልተደገሙ “እንግዳ ክስተቶች” መኖራቸውን አምኖ መቀበል ይኖርበታል። እነዚህ ክስተቶች ምንድን ናቸው?

12. ዛሬ በሥራ ላይ ያሉትን የተፈጥሮ ሕጎች ተጠቅመን ልናብራራቸው የማንችል ነገር ግን በጥንት ዘመን የተፈጸሙ ምን ድንቅ ነገሮች አሉ?

12 አንዱ ሕይወት በምድር ላይ መጀመሩ ነው። ከዚያም አንዳንድ ሕያዋን ሆነው የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት ተገኙ። በመጨረሻም የሰው ልጅ ጥበብን፣ የማሰብና የማፍቀር ችሎታን እንዲሁም ሕሊናን ተላብሶ ወደ ሕልውና መጣ። ዛሬ ያሉትን የተፈጥሮ ሕጎች መሠረት በማድረግ እነዚህ አስገራሚ ነገሮች እንዴት እንደተከናወኑ ማስረዳት የሚችል አንድም ሳይንቲስት አይገኝም። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች እንደተከናወኑ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ አለን።

13, 14. ዛሬ እንደ ተራ ነገር የሚታዩት ለዴቪድ ሃም ግን እንደ ተዓምር ሊሆኑበት የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

13 ከዴቪድ ሃም ዘመን ወዲህ ስለተፈጸሙት ‘እንግዳ ነገሮችስ’ ምን ማለት ይቻላል? የጊዜ ሂደት ወደኋላ ተመልሶ ዛሬ ባለንበት ዓለም ውስጥ ያለው ነገር ምን እንደሚመስል ለሃም የምንነግርበት አጋጣሚ አገኘን እንበል። በሃምበርግ የሚገኝ አንድ ነጋዴ ከእርሱ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በቶኪዮ ከሚገኝ ሌላ ሰው ጋር ድምፁን በኃይል ከፍ ማድረግ ሳያስፈልገው መነጋገር ስለመቻሉ፣ በስፔይን የሚካሄድ የእግር ኳስ ጨዋታ ቀጥታ ጨዋታው እየተካሄደ እንኳ ሳይቀር በዓለም ዙሪያ ሊታይ እንደሚችል፣ በሃም ዘመን በውቂያኖስ ይንሳፈፉ ከነበሩት መርከቦች እጅግ የሚበልጥ ግዝፈት ያለው ነገር 500 የሚያክሉ ሰዎችን ጭኖ ከምድር ሊነሣና በአየር ላይ እየበረረ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ሊጓዝ እንደሚችል ለማስረዳት ሞከርን እንበል። ምን ምላሽ የሚሰጥ ይመስልሃል? ‘በፍጹም ሊሆን አይችልም! እንዲህ ያሉ እንግዳ ክስተቶች በእኛ ዘመን ሊፈጸሙ አይችሉም!’

14 ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ‘እንግዳ’ ነገሮች በእኛ ዘመን ተፈጽመዋል። ለምን? የሰው ልጅ፣ ሃም ፈጽሞ ሊገምታቸው የማይችላቸውን ሳይንሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም እንደ ስልክ፣ ቴሌቪዥንና አውሮፕላን ያሉትን ነገሮች ለመሥራት በመቻሉ ነው። ታዲያ አምላክ ቀደም ባሉት ዘመናት እኛ እስከ ዛሬም ድረስ ልንረዳው በማንችለው መንገድ እንደ ተዓምር የሚቆጠሩ ነገሮችን ያከናወነባቸው ወቅቶች አሉ ብሎ ማመን ይህን ያህል አስቸጋሪ ይሆናል?

እንዴት ማወቅ እንችላለን?

15, 16. ተዓምራት በእርግጥ ተፈጽመው ከነበረ ስለ እነርሱ ማወቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ምን ይሆናል? በምሳሌ አስረዳ።

15 እርግጥ ተዓምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ ማለት ተፈጽመዋል ማለት አይደለም። ጥንት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ በምድራዊ አገልጋዮቹ አማካኝነት እውነተኛ ተዓምራትን አከናውኖ እንደሆነና እንዳልሆነ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የምንገኘው ሰዎች እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዲህ ያሉትን ነገሮች ለማረጋገጥ ምን ዓይነት ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ትጠብቃለህ? እልም ያለ ገጠር ውስጥ የሚኖርን አንድ የባላገር ሰው ወደ አንድ ትልቅ ከተማ አምጥተው አስጎበኙት እንበል። ወደ አገሩ ሲመለስ የሥልጣኔውን ትንግርት በእርሱ አካባቢ ላሉ ሰዎች እንዴት ሊያስረዳቸው ይችላል? መኪና እንዴት እንደሚሽከረከር ወይም በእጅ ከሚያዝ ራዲዮ ውስጥ ሙዚቃ የሚወጣው ለምን እንደሆነ ሊያስረዳቸው አይችልም። ኮምፒዩተር የሚባል ነገር መኖሩን እንዲያምኑ ለማድረግ ኮምፒዩተር ሠርቶ ሊያሳያቸው አይችልም። ማድረግ የሚችለው ያየውን መናገር ብቻ ነው።

16 እኛ ያለንበት ሁኔታ ከዚህ የገጠር ሰው ጎረቤቶች ጋር የሚመሳሰል ነው። አምላክ ተዓምራትን አከናውኖ ከነበር ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የዓይን ምሥክሮችን መግለጫ መስማት ይሆናል። የዓይን ምሥክሮቹ ያዩትን ነገር ከመናገር ሌላ ተዓምራቱ እንዴት እንደተፈጸሙ ማስረዳትም ሆነ ያን የመሰለ ነገር ሠርተው ማሳየት አይችሉም። የዓይን ምሥክሮች ሊታለሉ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። እንዲሁም በቀላሉ ነገሮችን አጋንነው ሊገልጹ ወይም የተሳሳተ ነገር ሊያስተላልፉ ይችላሉ። እንግዲያው እነዚህ የዓይን ምሥክሮች የሚሰጡትን ምሥክርነት ለማመን እንድንችል እውነተኞች፣ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና በትክክለኛ ውስጣዊ ዝንባሌ የሚሠሩ መሆናቸውን እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል።

ከሁሉ ይበልጥ ማስረጃ ያለው ተዓምር

17. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ተዓምራት ሁሉ ይበልጥ ብዙ ማስረጃ ያለው የትኛው ተዓምር ነው? (ለ) ኢየሱስ ሊሞት አካባቢ የተከናወኑት ሁኔታዎች ምን ይመስሉ ነበር?

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ተዓምራት ሁሉ ይበልጥ ጠንካራ ማረጋገጫ የሚገኝለት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው። ታዲያ ይህን ተዓምር ለምን እንደ ናሙና አድርገን አንመለከተውም። በመጀመሪያ የቀረበውን ዘገባ ተመልከት:- ኢየሱስ ኒሳን 14 ማለትም እንደዛሬው የሳምንት አቆጣጠር ሐሙስ ዕለት ምሽት ተያዘ። * በአይሁድ መሪዎች ፊት በቀረበ ጊዜ አምላክን ተሳድቧል የሚል ውንጀላ በማቅረብ እንዲገደል ወሰኑበት። የአይሁድ መሪዎቹ ኢየሱስን የሮማ ገዥ ወደነበረው ወደ ጴንጤናዊው ጲላጦስ አቀረቡት። ጲላጦስም ለእነርሱ ተጽእኖ በመንበርከክ እንዲገደል አሳልፎ ሰጠው። ዓርብ ጠዋት ረፋዱ ላይ (በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት በዚያው ኒሳን 14 ዕለት) በመከራው እንጨት ላይ ተቸንክሮ ከቆየ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሞተ።​—⁠ማርቆስ 14:​43-65፤ 15:​1-39

18. እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን የሚገልጸው ወሬ መሠራጨት የጀመረው እንዴት ነው?

18 አንድ የሮማ ወታደር ኢየሱስ በእርግጥ መሞቱን ለማረጋገጥ ጎኑን በጦር ከወጋው በኋላ አስከሬኑ በአዲስ መቃብር ውስጥ እንዲያርፍ ተደረገ። የሚቀጥለው ቀን ኒሳን 15 (ዓርብ/ቅዳሜ) ሰንበት ነበር። ይሁን እንጂ ኒሳን 16 ዕለት ማለትም እሁድ ጠዋት አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ወደ መቃብሩ ሲሄዱ ምንም ነገር አልነበረም። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ እንደታየ የሚገልጹ ወሬዎች መሰማት ጀመሩ። መጀመሪያ አካባቢ እነዚህ ወሬዎች ያገኙት ምላሽ ዛሬ ሊኖር የሚችለው ዓይነት ምላሽ ነበር። አልታመኑም። ሐዋርያቱ ሳይቀሩ አናምንም አሉ። ይሁን እንጂ ሕያው የሆነውን ኢየሱስን በዓይናቸው ካዩ በኋላ በእርግጥም ከሙታን መነሣቱን አምነው ከመቀበል ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም።​—⁠ዮሐንስ 19:​31–20:​29፤ ሉቃስ 24:​11

ባዶው መቃብር

19-21. (ሀ) ሰማዕቱ ጀስቲን እንደገለጸው ከሆነ ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ መስበካቸውን አይሁዳውያን የተቃወሙት እንዴት ነበር? (ለ) ኒሳን 16 ዕለት ከኢየሱስ መቃብር ጋር በተያያዘ ምን ነገር እንደተፈጸመ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

19 ኢየሱስ በእርግጥ ትንሣኤ አግኝቷል ወይስ ይህ ሁሉ ነገር እንዲሁ ፈጠራ ነው? በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች ሊያነሡት ከሚችሉት ጥያቄ አንዱ የኢየሱስ አስከሬን አሁንም በመቃብሩ ውስጥ አለ? የሚል ነው። ተቃዋሚዎቻቸው አስከሬኑን በተቀበረበት ቦታ ማግኘት ቢችሉና እንዳልተነሣ ማስረጃ ቢያቀርቡ ኖሮ የኢየሱስ ተከታዮች ትልቅ እንቅፋት በገጠማቸው ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚያ እንዳደረጉ የሚገልጽ አንድም መዝገብ የለም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከሆነ መቃብሩን እንዲጠብቁ ለተመደቡት ወታደሮች ገንዘብ ሰጥተው “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት” እንዲሉ አድርገዋል። (ማቴዎስ 28:​11-13) የአይሁድ መሪዎች ይህን ስለማድረጋቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭም ማስረጃ እናገኛለን።

20 ኢየሱስ ከሞተ ከአንድ መቶ ዘመን በኋላ ሰማዕቱ ጀስቲን ዳያሎግ ዊዝ ትራይፎ (ከትራይፎ ጋር የተደረገው ውይይት) የተባለ የጽሑፍ ሥራ አዘጋጅቶ ነበር። በዚያም ውስጥ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ [አይሁዳውያን] ኢየሱስ የሚባል አንድ የገሊላ አታላይ አምላክ የለሽ የሆነና ዓመፅ የሞላበት የመናፍቅነት እንቅስቃሴ በማፍለቁ ሰቅላችሁ እንደገደላችሁት ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት ከተቀበረበት መቃብር ውስጥ ሰርቀው እንደወሰዱት የሚገልጽ ወሬ በምድር ሁሉ እንዲያናፍሱላችሁ የተመረጡና የተሾሙ ወንዶችን ልካችኋል።”7

21 ትራይፎ አይሁዳዊ ስለነበር ዳያሎግ ዊዝ ትራይፎ የተጻፈው ክርስትናን ከአይሁድ እምነት ለመከላከል ነበር። በመሆኑም አይሁዳውያኑ የኢየሱስን አስከሬን ክርስቲያኖች ከመቃብሩ ውስጥ ሰርቀውታል የሚል ክስ አቅርበው ባይሆን ኖሮ ሰማዕቱ ጀስቲን ከላይ እንዳለው ብሎ ባልተናገረ ነበር። አለዚያ ግን በቀላሉ ማስረጃ ቀርቦበት ዋሽተሃል በሚል ክስ ሊመሠረትበት ይችል ነበር። ሰማዕቱ ጀስቲን እንደዚያ ለማለት የቻለው በእርግጥም አይሁዳውያኑ መልእክተኞችን በመላካቸው ነው። እነርሱም ይህን ያደረጉት መቃብሩ በእርግጥም በ33 እዘአ ኒሳን 16 ዕለት ባዶ ስለተገኘና ኢየሱስ አልተነሣም ለማለት አስከሬኑን በማስረጃነት ማቅረብ ስላልቻሉ ነው። ታዲያ መቃብሩ ባዶ ከሆነ የተፈጸመው ነገር ምን ነበር? አስከሬኑን ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀውታልን? ወይስ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን ለማረጋገጥ በተዓምራዊ ሁኔታ ተወግዶ ነበር?

ሐኪሙ ሉቃስ የደረሰበት መደምደሚያ

22, 23. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስን ትንሣኤ በጥልቀት የመረመረው የተማረ ሰው ማን ነው? ምን የመረጃ ምንጮችንስ ማግኘት ችሏል?

22 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከፍተኛ ትምህርት የነበረው ጉዳዩን በጥንቃቄ የመረመረ ሰው ሐኪሙ ሉቃስ ነበር። (ቆላስይስ 4:​14) ሉቃስ ዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ ሁለት መጻሕፍት የጻፈ ሲሆን አንዱ ወንጌል ወይም የኢየሱስን አገልግሎት የሚተርክ መጽሐፍ ነው። ሌላው ደግሞ የሐዋርያት ሥራ ተብሎ የሚጠራና ከኢየሱስ ሞት በኋላ በነበሩት ዓመታት ክርስትና እንዴት እንደተስፋፋ የሚገልጽ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ነው።

23 ሉቃስ በወንጌሉ መግቢያ ላይ እርሱ በቅርብ ያገኛቸውን ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ብዙ ማስረጃዎች ጠቅሷል። የኢየሱስን ታሪክ በሚመለከት ስላገላበጣቸው የጽሑፍ መዛግብት ተናግሯል። እንዲሁም ለኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የዓይን ምሥክር የሆኑ ሰዎችን እንዳነጋገረ ገልጿል። ከዚያም ‘ሁሉን ከመጀመሪያ ጀምሮ በትክክል ተከትሎ’ እንደ ጻፈ ተናግሯል። (ሉቃስ 1:​1-3) ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ሉቃስ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርጓል። ሉቃስ ጥሩ ታሪክ ጸሐፊ ነበርን?

24, 25. የሉቃስን የታሪክ ጸሐፊነት ብቃት ብዙዎች እንዴት ይመለከቱታል?

24 ጥሩ ታሪክ ጸሐፊ መሆኑን ብዙዎች መስክረውለታል። በ1913 ሰር ዊሊያም ራምሴይ ትምህርት ሲሰጡ የሉቃስ የጽሑፍ ሥራ ያለውን ታሪካዊ ይዘት በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። የደረሱበት መደምደሚያ ምን ነበር? “ሉቃስ ድንቅ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። እውነተኛና እምነት የሚጣልበት ነገር በማስፈሩ ብቻ ሳይሆን ሥራዎቹ በትክክል ታሪካዊነትን የተላበሱ ናቸው።”8 በቅርብ ዓመታት የነበሩ ተመራማሪዎችም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ዘ ሊቪንግ ዎርድ ኮሜንታሪ የተባለው መጽሐፍ ስለ ሉቃስ ወንጌል በሚገልጸው ጥራዝ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ሉቃስ ታሪክ ጸሐፊም (ትክክለኛ) የሃይማኖት ምሁርም ነበር።”

25 በሰሜን አየርላንድ የብሉይ ኪዳን ግሪክኛ ፕሮፌሰር የነበሩት ዶክተር ዴቪድ ጉዲንግ ስለ ሉቃስ እንደተናገሩት ከሆነ “የብሉይ ኪዳን ታሪክ ጸሐፊዎችንና የቱሳይዳይደስን [በጥንቱ ዓለም ከነበሩት ታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ታሪክ ጸሐፊ] ስልት የተከተለ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊ ነው። ልክ እንደ እነርሱ የመረጃዎቹን ምንጮች ለማግኘት፣ ተፈላጊውን ነጥብ ለመምረጥና በሥርዓት ለማስቀመጥ ያላደረገው ጥረት የለም። . . . ቱሳይዳይደስ ከዚህ ዘዴ በተጨማሪ ትክክለኛ ታሪክ የማቅረብ ከፍተኛ ምኞት ነበረው። ሉቃስ የሠራው ከዚህ ያነሰ ነገር ነው ብለን የምናስብበት ምንም ምክንያት አይኖርም።”9

26. (ሀ) የኢየሱስን ትንሣኤ በሚመለከት ሉቃስ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? (ለ) እዚህ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ማጠናከሪያ የሆነው ነገር ምን ሊሆን ይችላል?

26 ይህ ከፍተኛ ብቃት የነበረው ሰው የኢየሱስ መቃብር ኒሳን 16 ዕለት ባዶ ሆኖ መገኘቱን አስመልክቶ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? ሉቃስ በወንጌሉም ሆነ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱ የማይታበል ሐቅ መሆኑን ዘግቧል። (ሉቃስ 24:​1-52፤ ሥራ 1:​3) ይህን ጉዳይ በሚመለከት አንዳችም ጥርጣሬ አልነበረውም። ምናልባትም በትንሣኤው ተዓምር ላይ የነበረውን እምነት ያጠናከረለት ነገር ራሱ ያጋጠመው ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ለትንሣኤው የዓይን ምሥክር ባይሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ ተዓምራት ሲሠራ እንደተመለከተ ዘግቧል።​—⁠ሥራ 20:​7-12፤ 28:​8, 9

ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን ተመለከቱ

27. ኢየሱስን ከትንሣኤው በኋላ እንዳዩት ከተናገሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው?

27 ሁለቱን ወንጌሎች የጻፏቸው ኢየሱስን የሚያውቁት፣ ሲሞት ያዩትና ከትንሣኤውም በኋላ በዓይናቸው እንደተመለከቱት የሚናገሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህም የቀድሞው ቀረጥ ሰብሳቢ ሐዋርያው ማቴዎስና የተወደደው የኢየሱስ ሐዋርያ ዮሐንስ ናቸው። ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስም ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን እንዳየው ተናግሯል። ከዚህ በተጨማሪ ጳውሎስ ኢየሱስን ከሞቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ያዩትን ሰዎች ስም ከመዘርዘሩም ሌላ “ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች” እንደተገለጠ ገልጿል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​3-8

28. የኢየሱስ ከሞት መነሣት በጴጥሮስ ላይ ምን ውጤት ነበረው?

28 ጳውሎስ የዓይን ምሥክር እንደነበሩ ከሚጠቅሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ የኢየሱስ ሥጋዊ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ ነው። ያዕቆብ ኢየሱስን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቅ ግልጽ ነው። ሌላው ደግሞ ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው። ታሪክ ጸሐፊው ሉቃስ እንደዘገበው ጴጥሮስ ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ኢየሱስ ትንሣኤ ስለ ማግኘቱ በድፍረት መሥክሯል። (ሥራ 2:​23, 24) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጴጥሮስ እንደጻፋቸው የሚታወቁ ሁለት መልእክቶች ሲኖሩ በመጀመሪያው መልእክት ውስጥ በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ ያለው እምነት ብዙ ዓመታት ካለፉም በኋላ ቢሆን ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ብርቱ ኃይል እንደሆነለት ገልጿል። እንዲህ ብሏል:- “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።”​—⁠1 ጴጥሮስ 1:​3

29. ለትንሣኤው የዓይን ምሥክር የነበሩትን ሰዎች ማነጋገር ባንችልም ምን አስገራሚ ማስረጃ ማግኘት እንችላለን?

29 ሉቃስ፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ አይተነዋል፣ አነጋግረነውማል ያሉትን ሰዎች ማነጋገር እንደቻለ ሁሉ እኛም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የጻፉትን ነገር ማንበብ እንችላለን። ከዚያ በኋላ እነዚህ ሰዎች ተታልለው ይሁን ወይም እኛን ለማታለል እየሞከሩ ወይም ደግሞ በእርግጥ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ተመልክተውት እንደሆነ ማረጋገጥ እንችላለን። እውነቱን ለመናገር ከሆነ ሊታለሉ የሚችሉበት መንገድ የለም። በርከት ያሉት ኢየሱስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የእርሱ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። አንዳንዶቹም በመከራው እንጨት ላይ ተሰቃይቶ ሲሞት በዓይናቸው ተመልክተዋል። ወታደሩ ጎኑን በጦር ሲወጋውና ደምና ውኃ ሲፈስስ ተመልክተዋል። ወታደሩም ኢየሱስ ስለ መሞቱ እርግጠኛ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም እርግጠኞች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ እንዳዩትና እንዳነጋገሩትም ተርከዋል። እነዚህ ሰዎች በፍጹም ተታልለው ሊሆን አይችልም። ታዲያ ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቷል በማለት ሊያታልሉን እየሞከሩ ነውን?​—⁠ዮሐንስ 19:​32-35፤ 21:​4, 15-24

30. የጥንቶቹ የኢየሱስ ትንሣኤ የዓይን ምሥክሮች ዋሽተዋል ማለት የማይቻለው ለምንድን ነው?

30 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያስፈልገን ‘የሚሉትን ነገር እነሱ ራሳቸው ያምኑበታል ወይ?’ ብለን መጠየቅ ነው። እንደሚያምኑበት ምንም ጥርጥር የለውም። የዓይን ምሥክሮች እንደነበሩ የሚናገሩትን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም ክርስቲያኖች የኢየሱስ ትንሣኤ የእምነታቸው ሁሉ መሠረት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ክርስቶስ . . . ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት።” (1 ቆሮንቶስ 15:​14, 17) እነዚህ ቃላት ክርስቶስ ከሞት ተነሥቶ አይቼዋለሁ የሚል ሰው የተናገራቸው ከመሆናቸው አንፃር ስናየው ውሸት ይመስላሉን?

31, 32. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምን መሥዋዕትነቶችን ከፍለዋል? ይህስ እነዚያ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቷል ብለው መናገራቸው ውሸት ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ የሚሆነው እንዴት ነው?

31 በዚያ ዘመን ክርስቲያን መሆን ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው። ክርስቲያን መሆን ክብር፣ ሥልጣን ወይም ሀብት የሚያስገኝ ነገር አልነበረም። እንዲያውም ሁኔታው ፍጹም ተቃራኒ ነበር። ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መካከልም ብዙዎቹ ለእምነታቸው ሲሉ ‘ገንዘባቸውን መነጠቃቸውን በደስታ ተቀብለውታል።’ (ዕብራውያን 10:​34) ክርስትና ብዙውን ጊዜ በውርደትና በስቃይ ሞት የሚደመደም የመሥዋዕትነትና የስደት ሕይወት መምራት የሚጠይቅ ነበር።

32 አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ከሃብታም ቤተሰብ የወጡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሐዋርያው ዮሐንስ አባት በገሊላ ከፍተኛ የዓሣ ንግድ የነበረው ሰው ነበር። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉት ብዙዎች ጥሩ አጋጣሚ ነበራቸው። ለምሳሌ ጳውሎስ ክርስትናን በተቀበለበት ጊዜ የታወቀው ረቢ የገማልያል ተማሪ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በአይሁድ ገዥዎች ዓይን ውስጥ ገብቶ ነበር። (ሥራ 9:​1, 2፤ 22:​3፤ ገላትያ 1:​14) ይሁን እንጂ ሁሉም ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን የሚገልጸውን ተጨባጭ መልእክት ለማዳረስ ሲሉ ዓለም ላቀረበላቸው ነገር ጀርባቸውን ሰጥተዋል። (ቆላስይስ 1:​23, 28) በውሸት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ለሚያውቁት ነገር ይህን ያህል መሥዋዕትነት ይከፍሉ ነበርን? መልሱ አይከፍሉም ነው። ነገር ግን በእውነት ላይ እንደተመሠረተ የሚያውቁት ነገር ስለነበር ያን ያህል ለመሰቃየትም ሆነ ለመሞት ፈቃደኞች ሆነዋል።

ተዓምራት በእርግጥ ተፈጽመዋል

33, 34. ይህ ትንሣኤ በእርግጥ የተፈጸመ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙት ሌሎች ተዓምራት ምን ማለት እንችላለን?

33 በእርግጥም ማስረጃው ፍጹም አሳማኝ ነው። ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 16 ዕለት በእርግጥ ከሞት ተነሥቷል። ይህ ትንሣኤ ደግሞ እውነት ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የምናገኛቸው ሌሎቹም ተዓምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ። ለእነዚህ ተዓምራትም ቢሆን የዓይን ምሥክሮች የሚሰጡት ጠንካራ ማስረጃ አለን። ኢየሱስ በናይን የነበረችውን መበለት ወንድ ልጅ ከሞት እንዲያስነሣ ያስቻለው እርሱን ከሞት ያስነሣው ኃይል ነው። እንደዚሁም ኢየሱስ ሌሎች ቀለል ያሉ ነገር ግን ድንቅ የፈውስ ተዓምራት እንዲያደርግ አስችሎታል። ኢየሱስ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በተዓምር እንዲመግብም ሆነ በውኃ ላይ እንዲራመድ የረዳው እርሱ ነው።​—⁠ሉቃስ 7:​11-15፤ ማቴዎስ 11:​4-6፤ 14:​14-21, 22-31

34 እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተዓምራት መናገሩ መጽሐፉን እንድንጠራጠር የሚያደርግ ምክንያት አይሆንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ዘመናት ተዓምራት መከናወን መቻላቸው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘር ሌላም ውንጀላ አለ። ብዙ ሰዎች እርስ በርሱ ስለሚጋጭ የአምላክ ቃል ሊሆን አይችልም ይላሉ። ይህ ነገር እውነት ነውን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 “አብዛኛውን ጊዜ” ያልነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አንዳንዶቹ ተዓምራት እንደ ምድር መንቀጥቀጥ ወይም ናዳ ያሉትን ተፈጥሮአዊ ክስተቶች የሚጨምሩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው። ይሁን እንጂ ልክ በተፈለጉበት ትክክለኛ ሰዓት በመፈጸማቸውና ይህም በአምላክ ትእዛዝ የተደረጉ ነገሮች መሆናቸውን ስለሚያሳይ እንደ ተዓምር ይታያሉ።​—⁠ኢያሱ 3:​15, 16፤ 6:​20

^ አን.17 የአይሁዳውያኑ ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት 12 ሰዓት ድረስ ይዘልቃል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 81 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የክርስትና ጠላቶች ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን አስከሬን እንደሰረቁት ተናግረዋል። ይህ ነገር እውነት ከሆነ ክርስቲያኖች በእርሱ ትንሣኤ ላይ ለተመሠረተው እምነታቸው ለመሞት ሳይቀር እንዴት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ?

[በገጽ 85 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዛሬ ተዓምራት የማይፈጸሙት ለምንድን ነው?

አንዳንድ ጊዜ:- ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ዓይነት ተዓምራት ዛሬ የማይፈጸሙት ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይነሣል። መልሱ በወቅቱ ተዓምራት የታቀደላቸውን ዓላማ አከናውነዋል፤ ዛሬ ግን አምላክ የሚጠብቅብን በእምነት እንድንኖር ስለሆነ ነው።​—⁠ዕንባቆም 2:​2-4፤ ዕብራውያን 10:​37-39

በሙሴ ዘመን የተከናወኑት ተዓምራት ሙሴ መሾሙን የሚያረጋግጡ ነበሩ። ይሖዋ ሙሴን እየተጠቀመበት እንዳለና የሕጉ ቃል ኪዳን መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው እንዲሁም እስራኤላውያን የአምላክ የተመረጠ ብሔር መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ነበሩ።​—⁠ዘጸአት 4:​1-9, 30, 31፤ ዘዳግም 4:​33, 34

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከናወኑት ተዓምራት ኢየሱስና ከእርሱም በኋላ ደግሞ ገና ጨቅላ የነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ከአምላክ ተልእኮ እንደተሰጣቸው የሚያረጋግጡ ሆነው አገልግለዋል። ሲጠበቅ የነበረው መሲህ ኢየሱስ መሆኑን፣ እርሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን የአምላክ ልዩ ሕዝብ መሆናቸው ቀርቶ በክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደተተኩና ከዚህ የተነሣ በሙሴ ሕግ ሥር መሆናቸው እንዳበቃ በግልጽ አሳይተዋል።​—⁠ሥራ 19:​11-20፤ ዕብራውያን 2:​3, 4

ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ተዓምራት መፈጸማቸው አብቅቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፣ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​8-10

ዛሬ ሁሉንም የአምላክ ራእይዎችና ምክሮች የያዘው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። ትንቢቶች ሲፈጸሙ ተመልክተናል እንዲሁም ስለ አምላክ ዓላማ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተናል። በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ተዓምራት ማየት አያስፈልገንም። የሆነ ሆኖ ግን እነዚህ ተዓምራት እንዲከናወኑ ያስቻለው የአምላክ መንፈስ ዛሬም ከተዓምር በማይተናነስ መንገድ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫ የሆኑ ነገሮች እንዲከናወኑ ያደርጋል። ወደፊት በምናየው ምዕራፍ ውስጥ ይህን ጉዳይ በሰፊው እንዳስሳለን።

[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፀሐይን በየማለዳው መውጣት የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሕጎች አስተማማኝ መሆናቸው ተዓምራት እንደማይፈጸሙ ማረጋገጫ ይሆናል የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ

[በገጽ 77 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምድር ለሕያዋን ነገሮች መኖሪያ ሆና መፈጠሯ ሊደገም የማይችል ‘ድንቅ ክስተት’ ነው

[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዛሬ ያሉትን ድንቅ የዘመናዊ ሳይንስ ውጤቶች ከዛሬ 200 ዓመታት በፊት ይኖር ለነበረ ሰው እንዴት ልታስረዳው ትችል ነበር?