በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የመንግሥት ዜና ቁጥር 35

ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የጎረቤት ፍቅር ቀዝቅዟል

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት ወዴት ዞር ማለት እንደሚችሉ ግራ በመጋባታቸው በጣም ተጨንቀዋል። ጡረታ የወጣች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- ‘አንድ ቀን ማታ እኔ ባለሁበት ፎቅ ላይ የምትኖር ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት የቤቴን በር አንኳኩታ ገባችና ብቸኝነት እንደተሰማት ነገረችኝ። ሥራ የበዛብኝ መሆኑን በትህትናና በግልጽ ነገርኳት። ስለረበሽኩሽ ይቅርታ ብላኝ ተመልሳ ሄደች።’

የሚያሳዝነው ይህች መበለት በዚያው ቀን ማታ የራሷን ሕይወት አጠፋች። ይህ ከሆነ በኋላ ጡረታ የወጣችው ሴት ከፈጸመችው አሳዛኝ ስህተት “ትልቅ ትምህርት” እንዳገኘች ተናግራለች።

ለጎረቤት ፍቅር አለማሳየት ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ ውጤቶች ያስከትላል። የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ግዛቶች በነበሩት በቦስኒያና ሄርዞጎቪና የጎሣ ግጭት በተፈጠረበት ወቅት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ከመደረጉም በላይ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ይህን ያደረጉት እነማን ናቸው? “የገዛ ጎረቤቶቻችን ናቸው” ስትል አንዲት ከመንደሯ የተፈናቀለች ልጅ በምሬት ተናግራለች። “በደንብ እናውቃቸዋለን” ብላለች።

በሩዋንዳ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያላንዳች ርኅራኄ ተጨፍጭፈዋል፤ ብዙዎቹ የተገደሉት በገዛ ጎረቤቶቻቸው ነው። “ሁቱዎችና ቱትሲዎች ወገን ሳይለዩና የትኛው ሁቱ የትኛው ደግሞ ቱትሲ እንደሆነ እንኳን ሳያውቁ አንድ ላይ [ከመኖርም] አልፈው እርስ በርሳቸው ይጋቡ ነበር” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። “ከዚያም ድንገት ሁኔታው ተለወጠ” እና “ጭፍጨፋው ተጀመረ።”

በተመሳሳይም እስራኤል ውስጥ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ብዙዎቹ አይሁዶችና አረቦች በጥላቻ ዓይን የሚተያዩ ናቸው። በአየርላንድ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች እንዲሁም በሌሎች አገሮች የሚገኙ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ በርካታ ሰዎች በመካከላቸው ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ዓለም የአሁኑን ጊዜ ያህል ፍቅር ያጣበት ዘመን በታሪክ ውስጥ ታይቶ አያውቅም።

የጎረቤት ፍቅር የቀዘቀዘው ለምንድን ነው?

ፈጣሪያችን መልሱን ይሰጠናል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የምንኖርበትን ዘመን የ“መጨረሻው ቀን” ብሎ ይጠራዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ይህ ያለንበት ጊዜ “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው ” ሰዎች የሚኖሩበት ዘመን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን “የሚያስጨንቅ ዘመን” አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር “የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል። ይህ ዘመን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ተብሎም ተጠርቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 NWማቴዎስ 24:3, 12 NW

ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ፍቅር መጥፋቱ በዚህ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እየኖርን እንዳለን ከሚያመለክቱት ማስረጃዎች አንዱ ነው። በተጨማሪም ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩበት ይህ ዓለም በቅርቡ ጠፍቶ ጽድቅ በሚሰፍንበትና በፍቅር በሚተዳደር አዲስ ዓለም እንደሚተካ የሚያመለክት በመሆኑ ልንደሰት ይገባል።—ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:7, 13

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ለውጥ መጥቶ ሰዎች ሁሉ እርስ በርስ መዋደድና በሰላም አብሮ መኖር ወደሚችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለንን?

የጎረቤት ፍቅር​—እውን የሆነ ነገር ነው

በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ ሕግ አዋቂ “ጎረቤቴ ማን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። ‘እንዳንተው ያሉ አይሁዶች’ የሚል መልስ ይሰጠኛል ብሎ እንደጠበቀ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ታሪክ ላይ የሌሎች አገር ሰዎችንም እንደ ጎረቤቶቻችን አድርገን መመልከት እንዳለብን አመልክቷል።—ሉቃስ 10:29-37 NWዮሐንስ 4:7-9

ኢየሱስ ለአምላክ ካለን ፍቅር ቀጥሎ ሕይወታችንን ሊገዛው የሚገባው ነገር ለጎረቤቶቻችን የምናሳየው ፍቅር መሆን እንዳለበት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 22:34-40) ይሁን እንጂ ሌሎችን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎችን ያቀፈ ማኅበር ከዚህ በፊት ኖሮ ያውቃልን? የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን አድርገዋል! ለሌሎች በነበራቸው ፍቅር ተለይተው ይታወቁ ነበር።—ዮሐንስ 13:34, 35

ዛሬስ? ክርስቶስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች አሉን? ኢንሳይክሎፔድያ ካናዲያና እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉት ነገር በጥንት ዘመን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ይከተሉት የነበረው ክርስትና ማንሠራራቱንና እንደገና መቋቋሙን የሚያሳይ ነው . . . ሁሉም ወንድማማቾች ናቸው።”

ይህ ምን ማለት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ዘር፣ ብሔር፣ የትውልድ ሐረግም ሆነ ማንኛውም ነገር ሌሎች ሰዎችን እንዲጠሉ አያደርጋቸውም ማለት ነው። በተጨማሪም ሰይፋቸውንና ጦራቸውን በምሳሌያዊ መንገድ ቀጥቅጠው ወደ ማረሻና ማጭድ የለወጡ በመሆናቸው ማንንም አይገድሉም። (ኢሳይያስ 2:4) እንዲያውም ምሥክሮቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት የታወቁ ናቸው።—ገላትያ 6:10

በካሊፎርኒያው ሳክራሜንቶ ዩኒየን ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ “ዓለም በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት በሥራ ቢተረጉም ደም መፋሰስና ጥላቻ ተወግዶ በምትኩ ፍቅር ሊነግሥ ይችል እንደነበር መጥቀሱ ብቻ ይበቃል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም። በሀንጋሪ እየታተመ በሚወጣው ሪንግ የተባለ መጽሔት ላይ የአንድ ዓምድ አዘጋጅ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “በምድር ላይ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ቢሆኑ ኖሮ ጦርነት ይቀር ነበር ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፤ የፖሊሶች ሥራ የትራፊክ እንቅስቃሴን መቆጣጠርና ፓስፖርት መስጠት ብቻ ይሆን ነበር።”

ይሁን እንጂ ሰዎች በሙሉ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ከተፈለገ ዓለም አቀፍ የሆነ ትልቅ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ምንም አያጠያይቅም። ይህ ለውጥ የሚመጣው እንዴት ነው? (እባክዎ ከጀርባ ያለውን ገጽ ይመልከቱ።)

ሰዎች ሁሉ እርስ በርስ የሚዋደዱበት ጊዜ

ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ጸሎት በቅርቡ አንድ ድንገተኛ ለውጥ እንደሚከሰት ያመለክታል። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል።—ማቴዎስ 6:10

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ከሰማይ ሆኖ የሚገዛ እውን መስተዳድር ነው። “መንግሥተ ሰማያት” ተብሎ የተጠራው ለዚህ ነው። ‘የሰላም መስፍን’ የሆነው ኢየሱስ የዚህ መንግሥት ገዥ እንዲሆን አባቱ ሾሞታል።—ማቴዎስ 10:7፤ ኢሳይያስ 9:6, 7፤ መዝሙር 72:1-8

የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ይህ በጥላቻ የተሞላ ዓለም ምን ይደርስበት ይሆን? ይህ “መንግሥት” የዚህን ዓለም ብልሹ መንግሥታት በሙሉ ‘ይፈጫቸዋል፤ ያጠፋቸውማል።’ (ዳንኤል 2:44) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለሙም . . . ያልፋል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል’ ሲል ይገልጻል።—1 ዮሐንስ 2:17

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚያመጣውን አዲስ ዓለም አስመልክቶ ሲናገር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:9-11, 29፤ ምሳሌ 2:21, 22) ያ ጊዜ እንዴት ያለ አስደሳች ዘመን ይሆናል! “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” (ራእይ 21:4) የሞቱ ሰዎች እንኳን እንደገና ሕያው ይሆናሉ፤ መላዋ ምድር ቃል በቃል ወደ ገነትነት ትለወጣለች።—ኢሳይያስ 11:6-9፤ 35:1, 2፤ ሉቃስ 23:43፤ ሥራ 24:15

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር እንድንችል አምላክ ባስተማረን መሠረት እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባል። (1 ተሰሎንቄ 4:9) በሩቅ ምሥራቅ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ “መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ መሠረት ሁሉም ሰው እርስ በርስ መዋደድን የሚማርበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ” ብሏል። አምላክ የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን! “ተናግሬአለሁ . . . አደርግማለሁ” ብሏል።—ኢሳይያስ 46:11

ሆኖም የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ማግኘት እንዲችሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት እርስዎም የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት መቅሰም ይኖርብዎታል። (ዮሐንስ 17:3) አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚል ርዕስ ያለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር ለዚህ ይረዳዎታል። ከዚህ በፊት ባለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ቅጽ ሞልተው በአቅራቢያዎ ወደሚገኘው አድራሻ በመላክ አንድ ቅጂ ማግኘት ይችላሉ።

አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ማግኘት እፈልጋለሁ።

□ ያለ ክፍያ የሚደረገውን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተመለከተ እንድታነጋግሩኝ እፈልጋለሁ።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ደፈጣ ተዋጊና የቀብር ሥነ ሥርዓት በቦስኒያ:- Reuters/Corbis-Bettmann