በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?

አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?

የመንግስት ዜና ቁጥር 36

አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?

አዲሱ ሺህ ዓመት-የአዲስ ዘመን መባቻ ነው?

ታኅሣሥ 31, 1999 እኩለ ሌሊት ላይ 20ኛውን መቶ ዘመን ተሰናብተነዋል። * ሁከት የነገሠበት ምዕተ ዓመት ነበር። ይሁን እንጂ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አስደናቂ የሕክምና ሳይንስ ምጥቀት፣ ከፍተኛ የኢንፎርሜሽን ልውውጥና ዓለም አቀፋዊ የሆነ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የታየበት ምዕተ ዓመትም ነበር። በመሆኑም አዲሱ ሺህ ዓመት በብዙዎች ዘንድ የተስፋና የለውጥ ተምሳሌት ተደርጎ ታይቷል። ጦርነት፣ ድህነት፣ የአካባቢ ብክለትና በሽታ የሚወገድበት ዘመን ይሆን?

ብዙዎች እንደዚያ ብለው ይጠብቃሉ። ይሁን እንጂ አዲሱ ሺህ ዓመት አንተን የሚጠቅሙ ማለትም የአንተም ሆነ የቤተሰብህ ሕይወት አስተማማኝና ዋስትና ያለው እንዲሆን የሚያደርጉ ለውጦች የማምጣቱ አጋጣሚ ምን ያህል ነው? ከፊታችን ከተጋረጡት ችግሮች መካከል የጥቂቶቹን ስፋት ተመልከት።

ብክለት

በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች “በዓለም አቀፍ ደረጃ በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ከመሆኑም በላይ መጠነ ሰፊ ብክለትና የስርአተ ምህዳር መዛባት እያስከተሉ ነው።” በአሁኑ ጊዜ ያሉት አዝማሚያዎች በዚህ መልኩ ከቀጠሉ “በተፈጥሯዊው ሁኔታ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እያየለ ይሄዳል።”—“ግሎባል ኢንቫይሮመንት አውትሉክ—2000፣” የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም

በሽታ

“በ2020 በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከአሥር ሰዎች መካከል ሰባቱን እንደሚገድሉ የሚገመት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ያለው አኃዝ ግን ከግማሽ ያነሰ ነው።”—“ዘ ግሎባል በርደን ኦቭ ዲዚዝ፣” ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 1996

አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ “በ2010 [የኤድስ] ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባቸው 23 አገሮች ውስጥ [የሚኖሩት] ሰዎች ቁጥር ከ66 ሚልዮን ያነሰ ይሆናል።”—“ከንፍረንቲንግ ኤድስ:- ኤቪደንስ ፍሮም ዘ ዴቨሎፒንግ ዎርልድ፣” በአውሮፓ ኮሚሽን እና በዎርልድ ባንክ የቀረበ ሪፖርት

ድህነት

“ወደ 1.3 ቢልዮን የሚጠጋው የዓለማችን ሕዝብ እያንዳንዱን ቀን የሚገፋው ከአንድ ዶላር ባነሰ ገንዘብ ሲሆን ወደ 1 ቢልዮን የሚጠጋው ደግሞ መሠረታዊ የምግብ ፍላጎቱን ማሟላት አይችልም።”—“ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት 1999፣” የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም

ጦርነት

“[በተለያዩ አገሮች] ውስጥ የሚነሱ ብጥብጦች ታይቶ ወደማያውቅ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ። በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖታዊ [ልዩነቶች] የሚቀሰቀሰው . . . እንዲህ ዓይነቱ ብጥብጥ . . . በሚቀጥለው ሩብ ምዕተ ዓመት . . . በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያልቁበትን የተለመደ ዓይነት ግጭት ያስከትላል።”—“ኒው ዎርልድ ካሚንግ:- አሜሪካን ሴክዩሪቲ ኢን ዘ ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸሪ፣” በብሔራዊ ደህንነት የዩ ኤስ ኮሚሽን/21ኛው መቶ ዘመን

እንግዲያው አዲሱ ሺህ ዓመት በመጥባቱ የታየው ፈንጠዝያና ደስታ ብክለት፣ በሽታ፣ ድህነትና ጦርነት ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ የሚንሠራፉበት ዘመን መቃረቡን የሚያሳየውን እውነታ ሸፍኖታል። ለእነዚህ ችግሮች ዋና መንስኤ የሆኑት ነገሮች በሳይንሳዊ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ወይም በፖለቲካ ሊወገዱ የማይችሉት እንደ ስግብግብነት፣ እርስ በርስ አለመተማመንና ራስ ወዳድነት ያሉት ባሕርያት ናቸው።

የሰው ልጅ የሚባረክበት ሺህ ዓመት

በአንድ ወቅት አንድ ጥንታዊ ጸሐፊ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጅ ምድርን ለመግዛት ችሎታው ብቻ ሳይሆን መብቱም የለውም። የሰው ልጆችን ችግሮች ለመፍታት መብቱና ችሎታው ያለው ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።—ሮሜ 11:33-36፤ ራእይ 4:11

ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው መቼና እንዴት ነው? ወደ “መጨረሻው ቀን” እንደተቃረብን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስህን ግለጥና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ። ሰዎች በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” የሚያሳዩአቸውን ባሕርያት በግልጽ ይዘረዝራል። በተጨማሪም ማቴዎስ 24:3-14 እና ሉቃስ 21:10, 11 ስለ “መጨረሻው ቀን” ይናገራሉ። እነዚህ ጥቅሶች የሚያተኩሩት ከ1914 ጀምሮ ሲከናወኑ በቆዩት እንደ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት፣ ቸነፈርና መጠነ ሰፊ የምግብ እጥረት ባሉ ክስተቶች ላይ ነው።

በቅርቡ የ“መጨረሻው ቀን” ይደመደማል። ዳንኤል 2:44 እንዲህ ይላል:- “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ . . . እነዚያንም [ምድራዊ] መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” ስለዚህ አምላክ ምድርን የሚገዛ መንግሥት ወይም መስተዳድር እንደሚያቋቁም አስቀድሞ ተተንብዮአል። ራእይ 20:4 እንደሚለው ከሆነ ይህ መስተዳድር ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛል! በዚህ ክብራማ ሺህ ዓመት የኑሮ ሁኔታዎች ለመላው የሰው ዘር የሚሻሻሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት:-

ኢኮኖሚ። “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

ጤና። “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6

አካባቢያዊ ሁኔታ። አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን ያጠፋል።’—ራእይ 11:18

በሰዎች መካከል የሚኖረው ግንኙነት። “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:9

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች የሚያምኑ በመሆኑ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት ሊኖራቸው ችሏል። ከዚህም የተነሳ የኑሮን ጫናዎችና ችግሮች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወትህ መመሪያ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

ወደ ሕይወት የሚመራ እውቀት!

አንዳንድ ጊዜ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሱበት ደረጃ በጣም የሚያስደንቅ ሊሆን ይችላል! ያም ሆኖ ግን ሰብዓዊ እውቀት የአብዛኞቹን ሰዎች ሕይወት የተረጋጋና አስደሳች ሊያደርገው አልቻለም። ይህን ማድረግ የሚችለው ብቸኛው እውቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዮሐንስ 17:3 ላይ ተገልጿል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”

እንዲህ ዓይነቱ እውቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ ይገኛል። ምንም እንኳ ብዙዎች ስለዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ጠንከር ያሉ አስተያየቶች የሚሰነዝሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ይህን መጽሐፍ ራሳቸው ለመመርመር ሞክረው አያውቁም። አንተስ? እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትልቅ ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ሆኖም ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር ሲታይ ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትና ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር የሚጠቅም’ ብቸኛ መጽሐፍ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

እንግዲያው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቅ መጀመር የምትችለው እንዴት ነው? ለምን የይሖዋ ምሥክሮች እንዲረዱህ አታደርግም? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በየቤታቸው ያላንዳች ክፍያ ያስተምራሉ። በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? እንደተባለው ብሮሹር ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ ጽሑፎች ይጠቀማሉ። ይህ ብሮሹር አምላክ ማን ነው? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብህን ሕይወት ሊያሻሽልልህ የሚችለው እንዴት ነው? እንደሚሉት ላሉ መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ለሚኖሩህ በርካታ ጥያቄዎች እጥር ምጥን ያሉ መልሶች ይሰጣል።

ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ቤትህ መጥቶ እንዲያነጋግርህ የምትፈልግ ከሆነ እባክህ ከታች ያለውን ቅጽ ሙላ። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ክብራማው የአምላክ መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው!

አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ማግኘት እፈልጋለሁ። በየትኛው ቋንቋ እንደሚፈልጉ ይግለጹ․

□ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 እዚህ ላይ የተጠቀምነው አዲሱን ሺህ ዓመት በተመለከተ በምዕራቡ ዓለም በስፋት ተቀባይነት ያገኘውን አመለካከት ነው። እንደ ደንቡ ከሆነ አዲሱ ሺህ ዓመት የሚጀምረው ጥር 1, 2001 ላይ ነው።