በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

“ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” በማለት ኢዮብ የተባለ ሰው ከብዙ ዘመናት በፊት ጠይቆ ነበር። (ኢዮብ 14:14) ምናልባት እርስዎም ይህን የመሰለ ጥያቄ ጠይቀው ይሆናል። በዚችው ምድር ላይ አሁን ያለው ሁኔታ ሁሉ ተሻሽሎ በሞት ከተለዩአቸው ዘመዶችዎ ጋር እንደገና አብራችሁ መኖር እንደምትችሉ ቢያውቁ ምን ይሰማዎት ነበር?

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እኮ “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ። . . . ይነሣሉ” የሚል ተስፋ ሰጥቷል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—ኢሳይያስ 26:19፤ መዝሙር 37:29

እንዲህ ባለው ተስፋ ላይ የጸና እምነት እንዲኖረን አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልገናል:- ሰዎች ለምን ይሞታሉ? ሙታን የት ናቸው? እንደገና በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ እንዴት እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን?

ሞት እና ስንሞት ምን እንደምንሆን

ሰዎች እንዲሞቱ በመጀመሪያ የአምላክ ዓላማ እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ ዔደን ተብላ በምትጠራ በምድራዊት ገነት ውስጥ አስቀመጣቸው። ልጆችን እንዲወልዱና መኖሪያቸው የሆነችውን ገነትን በምድር ሁሉ እንዲያስፋፉ አዘዛቸው። የሚሞቱት ትእዛዙን ከጣሱ ብቻ ነበር።ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15-17

አዳምና ሔዋን አምላክ ላሳያቸው ደግነት አመስጋኝነት ጐደላቸውና ሳይታዘዙ ቀሩ። በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል የተነገራቸውን ቅጣት እንዲቀበሉ ተደረጉ። አምላክ አዳምን “ወደ መሬት ትመለሳለህ” “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 3:19) አዳም ከመፈጠሩ በፊት ፈጽሞ ኅልውና አልነበረውም፤ አፈር ነበር። ሳይታዘዝ ቀርቶ ኃጢአት በሠራ ጊዜም ቢሆን ወደ አፈር ማለትም ወደ አለመኖር ሁኔታ እንዲመለስ ተፈረደበት።

ስለዚህ ሞት አለመኖር ወይም ሕይወት አልባነት ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትና ሞት ተቃራኒ ነገሮች መሆናቸውን ሲያመለክት “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው፣ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል። (ሮሜ 6:23) ሞት ስሜትና አሳብ የሌለበት ሙሉ በድንነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያመለክት:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉ፣ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” ይላል። (መክብብ 9:5) አንድ ሰው ሲሞት “መንፈሱ ይወጣል፣ ወደ መሬትም ይመለሳል፣ በዚያን ጊዜ ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።መዝሙር 146:3, 4 አዓት

ይሁን እንጂ በኤደን ውስጥ ያንን ትዕዛዝ ያፈረሱት አዳምና ሔዋን ብቻ ሆነው ሳለ እኛ ሁላችን የምንሞተው ለምንድነው? ሁላችን የተወለድነው አዳም ካመጸ በኋላ ስለሆነና ከሱም ኃጢአትንና ሞትን ስለወረስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “በአንድ ሰው [በአዳም] ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ ስለዚህ ኃጢአት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” — ሮሜ 5:12፤ ኢዮብ 14:4

ሆኖም ‘ሰው ሲሞት እኮ ሕያው ሆና የምትቀጥል ነፍስ አለችው፤ አይደለም እንዴ?’ ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል። እንደዚያ ብለው የሚያስተምሩ ብዙ ሰዎች አሉ። እንዲያውም ሞት ወደ ሌላ ሕይወት የሚያስገባ መተላለፊያ በር ነው ይላሉ። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነቱ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። የእግዚአብሔር ቃል እርስዎ ራስዎ ነፍስ እንደሆኑ ማለትም አካላዊና አእምሮአዊ ባሕሪዎ ተጠቃሎ ነፍስዎ ራስዎ እንደሆኑ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 2:7፤ ኤርምያስ 2:34፤ [የ1879 እትም] ምሳሌ 2:10) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ይላል። (ሕዝቅኤል 18:4) ሰው ሥጋው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ፈጽሞ የማትሞት ነፍስ አለችው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ በየትም ቦታ አያስተምርም።

ሰዎች እንደገና ሕያዋን መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

ኃጢአትና ሞት ወደ ዓለም ከገቡ በኋላ ሙታን በትንሣኤ አማካኝነት ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ ዓላማው እንደሆነ አምላክ ገልጿል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “አብርሃም . . . እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ [ልጁን ይስሐቅን] ሊያስነሳው እንዲችል አስቧልና” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 11:17-19) መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን ስለሚችለው አምላክ ሲናገር “ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” ስለሚል የአብርሃም እምነት ከንቱ አልነበረም።ሉቃስ 20:37, 38

አዎ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ እሱ የመረጣቸውን ለማስነሣት የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ:- “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምጹን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል . . . በዚህ አታድንቁ” ብሏል።ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ ናይን ከምትባል የእሥራኤላውያን ከተማ የሚመጡ ሬሳ ያጀቡ ሰዎች አጋጠሙት። የሞተው ወጣት የአንዲት መበለት ብቸኛ ልጅ ነበር። ኢየሱስ የደረሰባትን ከባድ ሐዘን ሲመለከት አዘነላት። ስለዚህ የሞተውን ሰው “አንተ ጐበዝ እልሃለሁ፤ ተነሣ!” ብሎ አዘዘው። ሞቶ የነበረው ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት።ሉቃስ 7:11-17

ኢየሱስ የአይሁድ ምኩራብ አለቃ የሆነውን የኢያኢሮስን ቤት በጐበኘ ጊዜም ይህች መበለት አጋጥሟት የነበረው ዓይነት ታላቅ ደስታ ሆኖ ነበር። የ12 ዓመት ልጁ ሞታ ነበር። ኢየሱስ ኢያኢሮስ ቤት እንደደረሰ ወደ ሞተችው ልጅ ቀረበና:- “አንቺ ብላቴና ተነሽ!” አለ። “እርስዋም ተነሣች።”ሉቃስ 8:40-56

ከዚህ በኋላ ደግሞ የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር ሞተ። ኢየሱስ አልዓዛር ቤት በደረሰ ጊዜ አልአዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። እህቱ ማርታ በጥልቅ ያዘነች ብትሆንም “በመጨረሻ ቀን እንደሚነሳ አውቃለሁ” በማለት ተስፋዋን ገለጸች። ኢየሱስ ግን ወደ መቃብሩ ሄደና ድንጋዩን እንዲያነሱት አዝዞ “አልዓዛር ሆይ፤ ወደ ውጭ ና” ብሎ ተጣራ! እሱም ወጣ።ዮሐንስ 11:11-44

እስቲ ቆም ይበሉና ስለዚህ ጉዳይ ያስቡ:- አልዓዛር ሞቶ በነበረባቸው አራት ቀናት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር? አልዓዛር ደስታ ባለበት ሰማያዊ ስፍራ ወይም በመሰቃያ ቦታ እንደነበረ የተናገረው ነገር አልነበረም። እንደዚህ ባለ ቦታ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ግን ይናገር ነበር። አልዓዛር ሙሉ በሙሉ የማይሰማ በድን ሆኖ ነበር። ኢየሱስ ወደ ሕይወት ባይመልሰው ኖሮ ‘እስከ መጨረሻው ቀን ትንሣኤ ድረስ’ እንደሞተ ይቆይ ነበር።

ኢየሱስ ያስነሣቸው ሰዎች እንደገና ስለሞቱ እርሱ ያደረጋቸው ተዓምራት የሰጡት ጥቅም ጊዜያዊ ብቻ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሙታን በአምላክ ኃይል ተነሥተው እንደገና በሕይወት ለመኖር የሚችሉ ስለመሆናቸው ከ1,900 ዓመታት በፊት ኢየሱስ ያደረገው ነገር ማረጋገጫ ሰጥቷል! ስለዚህ ኢየሱስ በተዓምራቱ አማካኝነት በአምላክ መንግሥት ሥር የሚከናወነውን ሁኔታ በአነስተኛ መንገድ አሳይቷል።

የምናፈቅረው ሰው ሲሞት

በትንሣኤ ተስፋ የሚያምኑ ቢሆኑም እንኳ ጠላት የሆነው ሞት አደጋ ከጣለ በጣም ሊያዝኑ ይችላሉ። አብርሃም ሚስቱ ሣራ እንደገና በሕይወት እንደምትኖር እምነት ነበረው፤ ይሁን እንጂ “አብርሃም ለሣራ ሊያለቅስላትና ሊያዝንላት ተነሣ” የሚል ቃል እናነባለን። (ዘፍጥረት 23:2) ኢየሱስም አልአዛር በሞተ ጊዜ “በመንፈሱ አዘነ፤ በራሱም ታወከ።” ከዚያም “እምባውን አፈሰሰ።” (ዮሐንስ 11:33, 35) ስለዚህ የሚያፈቅሩት ሰው ሲሞት ማልቀስ ደካማነትን አያሳይም።

ልጅ ሲሞት በተለይ ለእናትየዋ ኀዘኑ ከባድ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት እናት ሊሰማት ስለሚችለው መሪር ሐዘን ይገልጻል። (2 ነገሥት 4:27) ልጁን ላጣው አባትም ቢሆን ሁኔታው ከባድ ነው። ንጉሥ ዳዊት ልጁ አቤሰሎም በሞተ ጊዜ “በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን” ብሎ አልቅሷል።2 ሳሙኤል 18:33

ይሁን እንጂ በትንሣኤ ጽኑ እምነት ስላለዎት ፈጽሞ መጽናናት እስከማይችሉ ድረስ አያዝኑም። ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አንቀላፍተው ስላሉት” አያዝኑም። (1 ተሰሎንቄ 4:13) ከዚህ ይልቅ በጸሎት ወደ አምላክ ይቀርባሉ። መጽሐፍ ቅዱስም “እርሱ ራሱ ይደግፍሃል” በማለት ተስፋ ይሰጣል።መዝሙር 55:22

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።