እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ?
‘የምኑን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በሰዎች አእምሮ ውስጥ ስለሚጉላሉት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች። ምናልባት ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎች አንተንም ያሳስቡህ ይሆናል:-
-
አምላክ በእርግጥ ያስብልናል?
-
ጦርነትና መከራ ማብቂያ ይኖራቸው ይሆን?
-
ስንሞት ምን እንሆናለን?
-
ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
-
አምላክ እንዲሰማኝ እንዴት መጸለይ ይኖርብኛል?
-
በሕይወቴ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? የተለያዩ ሰዎች ብትጠይቅ የተለያዩ መልሶች ይሰጡሃል። የሃይማኖት መሪዎች የሚሰጧቸው መልሶችም ቢሆኑ እርስ በርስ የሚጋጩ ናቸው። ወደ ቤተ መጻሕፍት ወይም ወደ መጻሕፍት መደብሮች ብትሄድ ደግሞ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ታገኝ ይሆናል። ይሁንና አንዱ መጽሐፍ የሚሰጠው መልስ ከሌላው ጋር ይጋጫል። ሌሎቹ ደግሞ ለጊዜው ጠቃሚ ይመስላሉ፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ ጊዜ ያለፈባቸው ይሆኑና እንደገና መሻሻል ወይም በሌላ መተካት ያስፈልጋቸዋል።
ይሁን እንጂ፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች አስተማማኝ መልስ የሚገኝበት አንድ መጽሐፍ አለ። እሱም እውነትን የያዘ መጽሐፍ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) ይህ “ቃል” በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በመባል ይታወቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች የሚሰጠውን ግልጽና እውነተኛ መልስ በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ታገኛለህ።
አምላክ በእርግጥ ያስብልናል?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? የምንኖረው ጭካኔና የፍትሕ መዛባት በሞላበት ዓለም ነው። ብዙ ሃይማኖቶች በዛሬው ጊዜ እየደረሰብን ያለውን መከራ ያመጣው አምላክ ነው ብለው ያስተምራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? አምላክ በፍጹም ክፋትን አያመጣም። ኢዮብ 34:10 “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” ይላል። አምላክ ለሰዎች በጎ ዓላማ አለው። ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ . . . መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) አምላክ በጥልቅ የሚያስብልን ከመሆኑ የተነሳ ለእኛ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ሲል ውድ ዋጋ ከፍሏል።—ዮሐንስ 3:16
በተጨማሪም ዘፍጥረት 1:26-28፤ ያዕቆብ 1:13 እና 1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን ተመልከት።
ጦርነትና መከራ ማብቂያ ይኖራቸው ይሆን?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሏል። ሁላችንም መከራ ይደርስብናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? አምላክ፣ በመላው ምድር ላይ ሰላም የሚያሰፍንበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ምድርን ሲገዛ ሰዎች “ጦርነት አይማሩም።” ከዚህ ይልቅ “ሰይፋቸውን ማረሻ . . . ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።” (ኢሳይያስ 2:4) እንዲሁም አምላክ ለማንኛውም ዓይነት የፍትሕ መዛባትና መከራ መቋጫ ያበጅለታል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—ራእይ 21:3, 4
በተጨማሪም መዝሙር 37:10, 11፤ 46:9 እና ሚክያስ 4:1-4ን ተመልከት።
ስንሞት ምን እንሆናለን?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች፣ አንድ ሰው ሲሞት ከውስጡ ወጥታ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር አለች ብለው ያስተምራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የሞቱ ሰዎች ሕያዋንን ሊጎዱ ይችላሉ ወይም አምላክ ክፉዎችን በሲኦል እሳት ውስጥ ለዘላለም ይቀጣቸዋል ብለው ያምናሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ሰው ሲሞት ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ይሆናል። መክብብ 9:5 ‘ሙታን ምንም አያውቁም’ በማለት ይናገራል። ሙታን ምንም ስለማያውቁና ስሜት ስለሌላቸው፣ ወይም ምንም ነገር ማድረግ ስለማይችሉ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊጎዱ ወይም ሊጠቅሙ አይችሉም።—መዝሙር 146:3, 4
በተጨማሪም ዘፍጥረት 3:19 እና መክብብ 9:6, 10ን ተመልከት።
ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? ሁላችንም መኖር የምንፈልግ ከመሆኑም በላይ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ሕይወትን ማጣጣም እንፈልጋለን። ስለዚህ በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና ለማየት መመኘታችን ተፈጥሯዊ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ትንሣኤ ያገኛሉ። ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከሞት የሚነሱ ሰዎች፣ ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ገነት በሆነች ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። (ኢሳይያስ 65:21-25) በዚህ ተስፋ መሠረት ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ፍጹም ጤናና ዘላለማዊ ሕይወት አግኝተው ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 37:29
በተጨማሪም ኢዮብ 14:14, 15፤ ሉቃስ 7:11-17 እና የሐዋርያት ሥራ 24:15ን ተመልከት።
አምላክ እንዲሰማኝ እንዴት መጸለይ ይኖርብኛል?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች ይጸልያሉ ለማለት ይቻላል። ሆኖም ብዙዎቹ ጸሎታቸው እንዳልተሰማላቸው ይሰማቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ኢየሱስ፣ ስንጸልይ አንድ ዓይነት ነገር በመደጋገም ከማነብነብ እንድንቆጠብ አስተምሮናል። “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:7) አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን የምንፈልግ ከሆነ እሱ በሚፈልገው መንገድ መጸለይ አለብን። ይህን ለማድረግ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ማወቅና ባወቅነው መሠረት መጸለይ ያስፈልገናል። አንደኛ ዮሐንስ 5:14 “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” በማለት ይገልጻል።
በተጨማሪም መዝሙር 65:2፤ ዮሐንስ 14:6፤ 16:23, 24 እና 1 ዮሐንስ 3:22ን ተመልከት።
በሕይወቴ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ገንዘብ፣ ዝና ወይም ውበት ቢኖራቸው ደስተኛ እንደሚሆኑ ይሰማቸዋል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ጥረት ባደረጉ መጠን ደስታ እየራቃቸው ይሄዳል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” በማለት ለደስታ ቁልፉ ምን እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3) እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው፣ ስለ አምላክና አምላክ ለእኛ ስላለው ዓላማ የሚገልጸውን መንፈሳዊ እውነት የማወቅ ፍላጎታችንን ለማርካት ጥረት ካደረግን ብቻ ነው። ይህ እውነት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ይህንን እውነት ማወቃችን በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነውና ያልሆነው ነገር ምን እንደሆነ ለመለየት ይረዳናል። የምናደርገው ውሳኔም ሆነ ድርጊታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚስማማ ከሆነ ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆናል።—ሉቃስ 11:28
በተጨማሪም ምሳሌ 3:5, 6, 13-18 እና 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን ተመልከት።
ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የተሻለ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህም ሆነ ለሌሎች በርካታ ጥያቄዎች የተሟላና አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።
መጽሐፍ ቅዱስ ለስድስት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ በአጭሩ ተመልክተናል። ከዚህ የበለጠ እውቀት ማግኘት ትፈልጋለህ? ‘መንፈሳዊ ነገሮችን ከተጠሙ’ ሰዎች አንዱ ከሆንክ ከዚህ የበለጠ ለማወቅ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ሌሎች የሚያሳስቡህ ርዕሰ ጉዳዮችም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ያህል፣ ‘አምላክ የሚያስብልን ከሆነ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይህን ያህልይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ያቅማማሉ። እንዲህ የሚሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ትልቅ መጽሐፍ አድርገው ስለሚመለከቱት ነው። ታዲያ ለጥያቄዎችህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ማግኘት እንድትችል እርዳታ ብታገኝ ደስ ይልሃል? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ ሁለት ዝግጅቶች አድርገውልሃል።
አንደኛው፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ሥራ የሚበዛባቸው ሰዎች አንገብጋቢ ለሆኑ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ግልጽ መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በነፃ የሚሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ነው። በአቅራቢያህ ከሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ብቃት ያለው አንድ ሰው ቤትህ ድረስ ወይም ለአንተ አመቺ የሆነ ሌላ ቦታ በየሳምንቱ እየመጣ ያላንዳች ክፍያ ለጥቂት ደቂቃዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሊያወያይህ ይችላል። በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል። ብዙዎቹ በቀሰሙት ትምህርት በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ “እውነትን አገኘሁ!” ብለዋል።
ማንም ሰው ቢሆን ከዚህ የበለጠ ሀብት ሊያገኝ አይችልም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከአጉል እምነት፣ ግራ ከመጋባትና ከፍርሃት ነፃ ያወጣናል። ከዚህም በላይ ተስፋ፣ ዓላማና ደስታ እንዲኖረን ያደርጋል። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል።—ዮሐንስ 8:32