በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል?

ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል?

ወጣቶች​—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል?

“አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት “ሕይወቴን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልጠቀምበት እፈልጋለሁ” በማለት ተናግራለች። አንተም የእርሷ ዓይነት ፍላጎት እንደሚኖርህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከሕይወትህ ‘ከሁሉ የተሻለውን’ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? መገናኛ ብዙኃንና እኩዮችህ፣ ምናልባትም አስተማሪዎችህ ጭምር ከሕይወትህ የበለጠ ጥቅም ማግኘት የምትችለው ብዙ ገንዘብ በማከማቸትና ስመ ጥር ሰው በመሆን ነው ይሉ ይሆናል!

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶችን ሲያስጠነቅቅ ቁሳዊ ሃብት ማሳደድ “ነፋስን እንደ መከተል ነው” ይላል። (መክብብ 4:4) ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ቁሳዊ ሃብት የማግኘትና ስመ ጥር የመሆን ሕልማቸውን ሊያሳኩ የሚችሉት በጣም ጥቂት ወጣቶች ብቻ መሆናቸው ነው። እነርሱም ቢሆኑ ሁሉም ነገር እንዳሰቡት ሆኖ አላገኙትም። “ከባዶ ሣጥን በምንም አይለይም” በማለት ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ይጣጣር የነበረ አንድ እንግሊዛዊ ወጣት ተናግሯል። “ስትከፍተው ውስጡ ባዶ ነው።” እርግጥ ነው፣ ሥራ አንዳንድ ጊዜ ብልጽግናም ሆነ እውቅና እንደሚያስገኝ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ “መንፈሳዊ ፍላጎትህን” አያሟላልህም። (ማቴዎስ 5:3 NW) ከዚህም በላይ 1 ዮሐንስ 2:17 “ዓለሙም . . . ያልፋ[ል]” በማለት ያስጠነቅቃል። በዚህ ዓለም የተሳካልህ ብትሆንም እንኳ ይህ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው።

በዚህም የተነሳ መክብብ 12:1 [አ.መ.ት] “በወጣትነትህ ጊዜ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ወጣቶችን ያሳስባል። አዎን፣ ሕይወትህን ይሖዋን ከማገልገል ሌላ በተሻለ መንገድ ልትጠቀምበት አትችልም። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ አምላክን ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? በአምላክ አገልግሎት መካፈል ምን ማድረግን ይጠይቃል?

የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ብቁ መሆን

በመጀመሪያ አምላክን የማገልገል ምኞት ማዳበር ይገባሃል። ይሁን እንጂ ይህ ምኞትና ፍላጎት እንዲሁ፣ ምናልባትም ወላጆችህ ክርስቲያን ስለሆኑ ብቻ በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም። ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት ይኖርብሃል። “ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት ጸሎት ሊረዳህ ይችላል” በማለት አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት ተናግራለች።​—መዝሙር 62:8፤ ያዕቆብ 4:8

ሮሜ 12:2 ልትወስድ የሚገባህን ሌላ እርምጃ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- ‘የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ እወቁ።’ ስለ ተማርካቸው አንዳንድ ነገሮች የተጠራጠርክበት ጊዜ አለ? ካለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በመከተል እነዚህ ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ‘ለራስህ ፈትነህ’ አረጋግጥ! በግልህ ምርምር አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አንብብ። ስለ አምላክ መማር የጭንቅላት እውቀት መሰብሰብ ብቻ ማለት አይደለም። ያነበብከው ነገር በምሳሌያዊው ልብህ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። ይህም ለአምላክ ያለህን ፍቅር ያሳድግልሃል።​—መዝሙር 1:2, 3

ከዚያም የተማርከውን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምናልባትም ትምህርት ቤት አብረውህ ለሚማሩ ለማካፈል ጥረት አድርግ። ቀጣዩ እርምጃ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ ይሆናል። በምትሰብክበት ጊዜ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ይህም መጀመሪያ ላይ ፍርሃት እንዲሰማህ ያደርግ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ‘በወንጌል እንዳናፍር’ ያሳስበናል። (ሮሜ 1:16) ይዘህ የምትሄደው ሕይወትና ተስፋ ሰጪ መልእክት ነው! ታዲያ ምን የሚያሳፍርህ ነገር አለ?

ወላጆችህ ክርስቲያኖች ከሆኑ በዚህ ሥራ አብረሃቸው መሰማራት ጀምረህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ምንም ሳትናገር በር ላይ ከመቆም ወይም መጽሔቶችንና ትራክቶችን ከማበርከት የበለጠ ነገር ማድረግ ትችላለህ? ከመጽሐፍ ቅዱስህ እየጠቀስክ የቤቱን ባለቤት ማስረዳት ትችላለህ? የማትችል ከሆነ ወላጆችህ ወይም በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ የጎለመሰ አንድ ወንድም እንዲረዱህ አድርግ። ያልተጠመቅህ የምሥራቹ አስፋፊ ለመሆን የሚያስችልህን ብቃት ለማሟላት ግብ አውጣ!

ከጊዜ በኋላ ራስህን ለአምላክ ለመወሰን ትገፋፋለህ። አምላክን ለማገልገል ትሳላለህ ማለት ነው። (ሮሜ 12:1) ይሁን እንጂ ራስን ለአምላክ መወሰን በአንተና በአምላክ መካከል ብቻ ተወስኖ የሚቀር ነገር አይደለም። አምላክ ራሳቸውን ለእርሱ የወሰኑ ሁሉ “ለመዳን የሚያበቃ የሕዝብ ምሥክርነት እንዲሰጡ” ይጠብቅባቸዋል። (ሮሜ 10:10 NW) በምትጠመቅበት ጊዜ በመጀመሪያ ስለእምነትህ የቃል ምሥክርነት ትሰጣለህ። ከዚያም በውኃ ትጠመቃለህ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ጥምቀት እንደቀላል ነገር የሚታይ እርምጃ አይደለም። ይሁን እንጂ ሳይሆንልኝ ቢቀርስ ብለህ በማሰብ ወደኋላ ማለት አይገባህም። ብርታት እንዲሰጥህ በአምላክ ላይ ከተማመንክ “ከወትሮው የተለየ ኃይል” በመስጠት ጸንተህ እንድትቆም ይረዳሃል።​—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW፤ 1 ጴጥሮስ 5:10

በምትጠመቅበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክር ትሆናለህ። (ኢሳይያስ 43:10) ይህም በሕይወትህ ልታደርግ ባሰብከው ነገር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ይኖርበታል። ራስን ለአምላክ መወሰን ‘ራስን መካድን’ ይጠይቃል። (ማቴዎስ 16:24) አንዳንድ የግል ግቦችህንና ምኞቶችህን ትተህ ‘የአምላክን መንግሥት ማስቀደም’ ሊያስፈልግህ ይችላል። (ማቴዎስ 6:33) ስለሆነም ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ይከፍታል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን እንመልከት።

አምላክን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል የሚያስችሉ አጋጣሚዎች

● አቅኚነት አንደኛው አጋጣሚ ነው። አንድ አቅኚ አስፋፊ በየወሩ ቢያንስ 70 ሰዓት ምሥራቹን በመስበክ የሚያሳልፍ የተጠመቀና ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን ነው። በመስኩ ረዥም ሰዓት ለማሳለፍ መቻልህ የመስበክና የማስተማር ችሎታህን እንድታሳድግ ይረዳሃል። በርካታ አቅኚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው ተጠምቀው ምሥክሮች እንዲሆኑ በመርዳት ደስታ አግኝተዋል። ይህን የመሰለ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ ምን ዓለማዊ ሥራ አለ?

ብዙዎቹ አቅኚዎች ወጪያቸውን ለመሸፈን የትርፍ ጊዜ ሥራ ይሠራሉ። ብዙዎቹ ከትምህርት ቤት ወይም ከወላጆቻቸው የእጅ ሙያ በመማር ለዚህ ኃላፊነት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን ካጠናቀቅክ በኋላ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል እንደሚጠቅምህ አንተም ሆንክ ወላጆችህ የሚሰማችሁ ከሆነ ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል የገፋፋህ ውስጣዊ ምኞት ብዙ ገንዘብ የማግኘት ፍላጎት ሳይሆን አገልግሎትህን ምናልባትም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትህን ስኬታማ ለማድረግ መሆን አለበት።

የአንድ አቅኚ ትኩረት ማረፍ የሚኖርበት በዓለማዊ ሥራው ላይ ሳይሆን በአገልግሎቱ ማለትም ሌሎች ሕይወት እንዲያገኙ በመርዳቱ ሥራ ላይ ነው! ለምን አቅኚ የመሆን ግብ አታወጣም? ብዙውን ጊዜ አቅኚነት ወደ ሌሎች መብቶች የሚያሸጋግር ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ አቅኚዎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረዋል። ሌሎች የውጭ አገር ቋንቋ ተምረው በገዛ አገራቸው ውስጥ በውጭ አገር ቋንቋ በሚገለገል ጉባኤ ወይም በባዕድ አገር ያገለግላሉ። አዎን፣ አቅኚነት ብዙ ወሮታ ያለው የሕይወት መንገድ ነው!

● የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት የሚያስችል ሌላው መስክ ነው። ሁለት ወር የሚፈጀው ይህ ትምህርት ቤት፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ትተው ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑ ተሞክሮ ያላቸው አቅኚዎችን ለማሠልጠን የተዘጋጀ ነው። እነዚህ አቅኚዎች በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀውን ወንጌላዊ ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚሉ ያህል ነው። (ኢሳይያስ 6:8፤ ዮሐንስ 7:29) ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው መሄዳቸው አኗኗራቸውን ቀላል ማድረግ ይጠይቅባቸው ይሆናል። የሚሄዱበት አካባቢ ባሕል፣ የአየር ጠባይ እንዲሁም ምግብ ከለመዱት ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አዲስ ቋንቋ መማር ያስፈልጋቸው ይሆናል። ትምህርት ቤቱ፣ ከ23 እስከ 65  ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነጠላ ወንድሞችና እህቶችም ሆኑ ባለትዳሮች በተመደቡበት ቦታ የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት እንዲሁም ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ እንዲጠቀሙባቸው የሚያስችሏቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

● የቤቴል አገልግሎት በአንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በፈቃደኝነት ማገልገልን የሚጠይቅ ነው። አንዳንድ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ሥራ ላይ በቀጥታ ይሠራሉ። ሌሎች ደግሞ ሕንፃዎችንና መሣሪያዎችን እንደመጠገን ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ለማሟላት በሚያስችሉ የጉልበት ሥራዎች በመመደብ ድጋፍ ሰጪ አገልግሎት ያከናውናሉ። ሁሉም የሥራ ምድቦች ለይሖዋ አገልግሎት የሚቀርብባቸው ቅዱስ መብቶች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በቤቴል የሚያገለግሉ ሁሉ የሚያከናውኑት ማንኛውም ሥራ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትንና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወንድሞቻቸውን የሚጠቅም እንደሆነ ያውቃሉ።

አንዳንድ ጊዜ ልዩ ሙያ ያላቸው ወንድሞች ቤቴል ገብተው እንዲያገለግሉ ይጋበዛሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ለሥራቸው የሚያስፈልገውን ሥልጠና የሚያገኙት ቤቴል ከገቡ በኋላ ነው። በቤቴል የሚያገለግሉ ሁሉ በዚያ የሚሠሩት ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ብለው አይደለም። ከዚያ ይልቅ በሚዘጋጅላቸው ምግብ፣ መኖሪያና የግል ወጪያቸውን ለመሸፈን በሚሰጣቸው አነስተኛ የወጪ መተኪያ ረክተው ይኖራሉ። አንድ ወጣት የቤቴል ቤተሰብ አባል የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “በጣም አስደናቂ ነው! የየዕለቱን ተግባር ማከናወን ቀላል አይደለም። ሆኖም እዚህ በማገልገሌ እርካታና በረከቶችን አግኝቻለሁ።”

● የግንባታ አገልግሎት በቅርንጫፍ ሕንፃና በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የመካፈል አጋጣሚ ያስገኛል። የግንባታ አገልጋዮች (ይህ መጠሪያቸው ነው) እንዲህ ባሉት የግንባታ ሥራዎች ላይ እገዛ ያደርጋሉ። ይህ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ የገነቡት ሠራተኞች ካከናወኑት አገልግሎት ጋር የሚመሳሰል የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ነው። (1 ነገሥት 8:13-18) ለግንባታ አገልጋዮች የሚደረገው የእንክብካቤ ዝግጅት ከቤቴል ቤተሰብ አባላት ጋር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ መካፈላቸው ምንኛ ታላቅ መብት ነው!

ይሖዋን በሙሉ ነፍስ አገልግል

ሕይወትህን ይሖዋን ከማገልገል ሌላ በተሻለ መንገድ ልትጠቀምበት አትችልም። ለምን ከአሁኑ ጀምረህ አምላክን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል የሚያስችል ግብ አታወጣም? የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን በተመለከተ ከወላጆችህ፣ ከጉባኤህ ሽማግሌዎችና ከወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር ተነጋገር። በቤቴል ለማገልገል ወይም በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመሠልጠን የምትፈልግ ከሆነ በክልል ስብሰባዎች ላይ ከአመልካቾች ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝ።

እርግጥ ነው ሁሉም ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችል ብቃት ወይም ሁኔታ አይኖራቸውም። በጤና እክል፣ በገንዘብ ችግርና በቤተሰብ ኃላፊነቶች ምክንያት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል የማይችሉ ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መከተል አለባቸው። (ማቴዎስ 22:37) ይሖዋ ሁኔታህ በሚፈቅድልህ መጠን የቻልከውን ሁሉ እንድታደርግ ይጠብቅብሃል። ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋን ማገልገል ዋነኛው የሕይወትህ ግብ እንዲሆን አድርግ። ልትደርስባቸው የምትችላቸው ቲኦክራሲያዊ ግቦች አውጣ። አዎን፣ “በወጣትነትህ ጊዜ ፈጣሪህን አስብ።” እንዲህ ማድረግህም ዘላለማዊ በረከት ያስገኝልሃል!

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በቀር በመጽሔቱ ላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ከ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም የተወሰዱ ናቸው። ከጥቅስ ቀጥሎ “አ.መ.ት” ሲባል ጥቅሱ “በ1993 ዓ.ም ከታተመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርናሽናል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማኅበር ፈቃድ ተቀድቶ የታተመ” መሆኑን ያመለክታል። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።