በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!

የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!

የመንግሥት ዜና ቁ. 37

ለመላው ዓለም የቀረበ መልእክት

የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!

የሐሰት ሃይማኖት ምንድን ነው?

የሚጠፋውስ እንዴት ነው?

አንተስ ከጥፋቱ ትተርፍ ይሆን?

የሐሰት ሃይማኖት ምንድን ነው?

በሃይማኖት ስም ወንጀል ሲፈጸም ስታይ በጉዳዩ ታዝናለህ? የአምላክ አገልጋዮች ነን የሚሉ ሰዎች የሚያካሂዱት ጦርነት እንዲሁም የሚፈጽሙት የሽብር ጥቃትና ሙስና ያበሳጭሃል? ሃይማኖት ለብዙ ችግሮች መንስኤ የሆነው ለምንድን ነው? ለዚህ ተጠያቂው ሃይማኖት በአጠቃላይ ሳይሆን የሐሰት ሃይማኖት ብቻ ነው። ብዙ የሃይማኖት ሰዎች በታላቅ አክብሮት የሚያዩት ኢየሱስ ክርስቶስ ‘መጥፎ ዛፍ መጥፎ ፍሬ እንደሚያፈራ’ ሁሉ የሐሰት ሃይማኖትም መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ አባላትን እንደሚያፈራ ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:15-17) የሐሰት ሃይማኖት የሚያፈራው ፍሬ ምንድን ነው?

የሐሰት ሃይማኖት . . .

ጦርነትና ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ይገባል:- ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት “በመላው እስያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ መሪዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ ሲሉ ሰዎች ለሃይማኖት ያላቸውን አመለካከት መጠቀሚያ ያደርጋሉ” ብሏል። ከዚህም የተነሳ መጽሔቱ “የዓለም ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆንበት ጊዜ የቀረበ ይመስላል” ሲል አስጠንቅቋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንድ የታወቁ የሃይማኖት መሪ “ግድያው እንዲቆም በመጀመሪያ አሸባሪዎችን መግደል ይኖርባችኋል” ሲሉ ተናግረዋል። ታዲያ ያቀረቡት መፍትሔ ምንድን ነው? “በጌታ ስም ሁሉንም ፍጅዋቸው” የሚል ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:20) እንዲያውም ኢየሱስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:44) አባሎቻቸው ጦርነት ውስጥ የሚገቡ ስንት ሃይማኖቶች ታውቃለህ?

የውሸት ሃይማኖታዊ ትምህርት ያስተምራል:- አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ነፍስ ወይም መንፈስ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከአካሉ ተለይታ መኖር የምትቀጥል የማትታይ ነገር ነች ብለው ያስተምራሉ። ይህን ትምህርት መሠረት በማድረግ ብዙ ሃይማኖቶች ለሟቹ ነፍስ ለመጸለይ ገንዘብ በማስከፈል ምዕመናኑን ይበዘብዛሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከዚህ የተለየ ነው። “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4) “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።” (መክብብ 9:5) ኢየሱስ ሙታን ትንሣኤ እንደሚያገኙ አስተምሯል፤ ሰዎች የማትሞት ነፍስ ብትኖራቸው ኖሮ ትንሣኤ ባላስፈለገ ነበር። (ዮሐንስ 11:11-25) የአንተ ሃይማኖት ነፍስ አትሞትም ብሎ ያስተምራል?

የፆታ ብልግናን በቸልታ ያልፋል:- በምዕራባውያን አገሮች፣ አንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች ወንድ ከወንድና ሴት ከሴት ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎችን ቄስ አድርገው የሚሾሙ ከመሆኑም ሌላ መንግሥት በተመሳሳይ ፆታ መካከል ለሚፈጸም ጋብቻ እውቅና እንዲሰጥ ግፊት ያሳድራሉ። የፆታ ብልግናን የሚያወግዙ አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ልጆችን በፆታ ያስነወሩ የሃይማኖት መሪዎችን በቸልታ አልፈዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን ብሎ ያስተምራል? “በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የፆታ ብልግናን በቸልታ የሚያልፉ ሃይማኖቶች ታውቃለህ?

መጥፎ ፍሬ የሚያፈሩ ሃይማኖቶች የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? ኢየሱስ “ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 7:19) አዎን፣ የሐሰት ሃይማኖት ይቆረጣል፤ ከዚያም ይጠፋል! ይሁንና ይህ የሚፈጸመው እንዴትና መቼ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 እና 18 ላይ የሚገኝ አንድ ትንቢታዊ ራእይ መልሱን ይዟል።

የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋው እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። በአንድ የሚያስፈራ አውሬ ላይ አንዲት አመንዝራ ሴት ተቀምጣለች። ይህ አውሬ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች አሉት። (ራእይ 17:1-4) ይህች አመንዝራ የምትወክለው ማንን ነው? ሴቲቱ “በምድር ነገሥታት ላይ” ተጽዕኖ የምታሳድር ናት። ሐምራዊ ልብስ ለብሳለች፣ ዕጣን ታጨሳለች እንዲሁም እጅግ ባለጠጋ ነች። ከዚህ በተጨማሪ በአስማቷ “ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል።” (ራእይ 17:18፤ 18:12, 13, 23) መጽሐፍ ቅዱስ ይህች አመንዝራ በዓለም ዙሪያ ያለች ሃይማኖታዊ ድርጅት መሆኗን እንድንረዳ ያስችለናል። የምትወክለውም አንድን ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን መጥፎ ፍሬ የሚያፈሩትን ሃይማኖቶች በሙሉ ነው።

አመንዝራይቱ የምትጋልበው አውሬ የዓለምን የፖለቲካ ኃይሎች ይወክላል። * (ራእይ 17:10-13) የሐሰት ሃይማኖት በዚህ ፖለቲካዊ አውሬ ላይ ተቀምጣ በሚያደርገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና አቅጣጫውን ለመቆጣጠር ጥረት ታደርጋለች።

ይሁንና በቅርቡ አንድ አስገራሚ ሁኔታ ይከሰታል። “አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቊቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል።” (ራእይ 17:16) የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች፣ ፈጽሞ ባልተጠበቀና አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሙሉ በሙሉ ያጠፏታል! ይህን እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ “ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነው” የሚል መልስ ይሰጣል። (ራእይ 17:17) አዎን፣ አምላክ የሐሰት ሃይማኖት በእርሱ ስም ለፈጸመቻቸው አስጸያፊ ድርጊቶች በሙሉ ተጠያቂ ያደርጋታል። የፖለቲካ ውሽሞቿን እንደ ፍርድ አስፈጻሚ አካል አድርጎ በመጠቀም ፍጹም የሆነ የፍትሕ እርምጃ ይወስድባታል።

ከሐሰት ሃይማኖት ዕጣ ፈንታ ተካፋይ ላለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል? አንድ የአምላክ መልእክተኛ “ሕዝቤ ሆይ፤ . . . ከእርሷ ውጡ” በማለት ያሳስባል። (ራእይ 18:4) በእርግጥም፣ ከሐሰት ሃይማኖት ሸሽቶ ለመውጣት ጊዜው አሁን ነው! ይሁንና ሸሽተህ የምትሄደው ወዴት ነው? አምላክ የለም ወደሚሉ ሰዎች ጎራ መሄድ የለብህም፤ ምክንያቱም እነርሱም ቢሆኑ የሚጠብቃቸው ጥፋት ነው። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ከአደጋ ማምለጥ የምትችለው ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ከመጣህ ብቻ ነው። ታዲያ እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

እውነተኛው ሃይማኖት ምን ዓይነት ጥሩ ፍሬ ማፍራት ይኖርበታል?—ማቴዎስ 7:17

እውነተኛ ሃይማኖት . . .

በፍቅር ይታወቃል:- እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች “ከዓለም አይደሉም።” በዘር ወይም በባሕል የተከፋፈሉ አይደሉም፤ እንዲሁም ‘እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ።’ (ዮሐንስ 13:35፤ 17:16፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) አንዳቸው ሌላውን ከመግደል ይልቅ አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ፈቃደኞች ናቸው።—1 ዮሐንስ 3:16

በአምላክ ቃል ላይ እምነት አለው:- እውነተኛ ሃይማኖት ‘ወግ’ እና “የሰው ሥርዓት” ከማስተማር ይልቅ ሃይማኖታዊ ትምህርቶቹ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። (ማቴዎስ 15:6-9) ለምን? ምክንያቱም “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ [ስላለባቸውና] ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት” ስለሚጠቅሙ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የቤተሰብን አንድነት ያጠናክራል፤ ሰዎች ንጹሕ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ያበረታታል:- እውነተኛ ሃይማኖት ባሎች ‘ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው እንዲወዱ’ ያሠለጥናል፣ ሚስቶች ‘ባሎቻቸውን እንዲያከብሩ’ ያበረታታል እንዲሁም ልጆች ‘ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ’ ያስተምራል። (ኤፌሶን 5:28, 33፤ 6:1) ከዚህ በተጨማሪ፣ የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች ሁሉ በአርዓያነት የሚታይ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው ይጠበቅባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-10

እነዚህን መሥፈርቶች የሚያሟላ ሃይማኖት ይገኛል? በ2001 የታተመው ሆሎኮስት ፖለቲክስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ትምህርትና አኗኗር ቢከተሉ ኖሮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደረሰው እልቂት ባልተከሰተ እንዲሁም ዓለማችንን እያስጨነቀ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል በተወገደ ነበር።”

በእርግጥም በ235 አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማስተማር ብቻ ሳይሆን ተግባራዊም ያደርጋሉ። አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ ትችል ዘንድ ብቃቶቹን እንዲያስተምሩህ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድትጠይቃቸው እናበረታታሃለን። እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ አሁን ነው፤ ዛሬ ነገ አትበል። የሐሰት ሃይማኖት መጥፊያ ቀርቧል!—ሶፎንያስ 2:2, 3

የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚሰብኩት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልእክት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ከታች ባለው አድራሻ እንድትጽፍ እናበረታታሃለን።

□ ነቅተህ ጠብቅ! የተባለውን ብሮሹር ማግኘት እፈልጋለሁ።

□ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሐሰት ሃይማኖት “በምድር ነገሥታት ላይ” ተጽዕኖ ታሳድራለች

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨ ሐሳብ]

“ሕዝቤ ሆይ፤ . . . ከእርሷ ውጡ”