በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?

የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?

የመንግሥት ዜና ቁጥር 34

የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?

ችግር የሌለበት ገነት ሊመጣ ይችል ይሆን?

አሳሳቢ ችግሮች እየተባባሱ የመጡት ለምንድን ነው?

ሰዎች ምን ጊዜም ችግር አልተለያቸውም። ብዙዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እነዚህን ችግሮች ይፈታቸዋል ብለው ቢያስቡም አሳሳቢ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ነው።

ወንጀል:- በመንገድ ላይ ሲጓዙ አልፎ ተርፎም በራሳቸው ቤት ውስጥ ተቀምጠው እያሉ ስጋት የማይሰማቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በአንድ የአውሮፓ አገር በቅርብ ዓመት ውስጥ ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ የወንጀል ሰለባ እንደሆነ ተዘግቧል።

የአካባቢ ሁኔታ:- የአየር፣ የምድርና የውኃ ብክለት ይበልጥ እየተስፋፋ ሄዷል። በታዳጊ አገሮች ውስጥ አንድ አራተኛው ሕዝብ ንጹሕ ውኃ አያገኝም።

ድህነት:- በአሁኑ ጊዜ ከምን ጊዜውም በበለጠ ብዙ ድሃና ረሃብተኛ ሰዎች አሉ። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በድህነት ተቆራምደው ይኖራሉ፤ በዓለም ላይ ከሚገኘው የሠራተኛ ኃይል 30 በመቶ ማለትም ወደ 800 ሚልዮን የሚጠጉት ሥራ የላቸውም ወይም አጥጋቢ የሆነ ሥራ አላገኙም። ይህ ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው።

ረሃብ:- እርስዎ የሚመገቡት በቂ ምግብ ቢኖርዎትም እንኳ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ የላቸውም። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በየዓመቱ ቢያንስ ቢያንስ 13 ሚልዮን ሰዎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ይሞታሉ፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው።

ጦርነት:- በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ በተካሄደ የጎሳ ብጥብጥ አልቀዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን ጦርነቶች ከአንድ መቶ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል።

ሌሎች ችግሮች:- ከላይ ከተዘረዘሩት ችግሮች ሌላ እየተባባሰ የሄደው የቤተሰብ መፈራረስ፣ ባል አልባ የሆኑ ብዙ እናቶች፣ እየጨመረ የሚሄደው የቤት እጦት፣ በጣም የተስፋፋው በአደንዛዥ ዕፅ ሰውነትን መጉዳትና በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሄደው የሥነ ምግባር ብልግናም አለ። አንድ የቀድሞው የአሜሪካ ካቢኔ አባል “ሥልጣኔ እንደተበላሸ የሚያሳዩ . . . ብዙ ምልክቶች አሉ” በማለት በትክክል ተናግረዋል። ባለፉት 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ ሕዝብ ቁጥር 41 በመቶ አድጓል፤ ሆኖም ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች 560 በመቶ፣ ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ሕፃናት 400 በመቶ፣ ፍቺዎች 300 በመቶ፣ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 200 በመቶ አድጓል። በሌሎች አገሮችም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም።

ችግሮች እየተባባሱ የሄዱት ለምንድን ነው?

ፈጣሪያችን መልሱን ይሰጠናል። የአምላክ ቃል ይህን በችግር የተሞላ ጊዜ ‘አስጨናቂ ዘመን’ የሚሆንበት ‘የመጨረሻ ቀን’ ሲል ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህ የመጨረሻ ቀን የምን መጨረሻ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የዓለም መጨረሻ” እንዳለ ይናገራል።—ማቴዎስ 24:3

በዛሬው ጊዜ እየጨመሩ የመጡት ችግሮች የክፋትንና ለክፋት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን መጨረሻ ጨምሮ የዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ እንደቀረበ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃ ናቸው። (ማቴዎስ 24:3–14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ራእይ 12:7–12) አምላክ በቅርቡ እጁን ጣልቃ በማስገባት በዛሬው ጊዜ ያሉት ችግሮች ሙሉ በሙሉ መፍትሔ እንዲያገኙ ያደርጋል።—ኤርምያስ 25:31–33፤ ራእይ 19:11–21

የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች አልበጁም

የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በዛሬው ጊዜ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከማገዝ ይልቅ በችግሮቹ ላይ ሌላ ችግር የሚጨምሩ ናቸው። በጦርነቶች ወቅት ካቶሊኮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ካቶሊኮችን፣ ፕሮቴስታንቶችም በሚልዮን የሚቆጠሩ ፕሮቴስታንቶችን ገድለዋል። አብዛኞቹ ሰዎች ካቶሊኮች በሆኑባት በሩዋንዳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እርስ በእርስ መጨፋጨፋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው! (በስተግራ ያለውን ሥዕል ይመልከቱ።)

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ዜግነታቸው የተለየ ስለሆነ ጠመንጃ ወይም ቆንጨራ ይዞ ወደ ጦር ሜዳ በመሄድ ይገድላቸው ነበርን? በፍጹም አያደርገውም! “እግዚአብሔርንም የሚወድ” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወንድሙንም መውደድ አለበት።’ (1 ዮሐንስ 4:20, 21) የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች በዚህ በኩል የሚበጁ ሆነው አልተገኙም። “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን . . . በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16

በተጨማሪም የዓለም ሃይማኖቶች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ባለማሟላት በምድር ዙሪያ ላለው አሳዛኝ የሥነ ምግባር ውድቀት አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖትን ከእውነተኛው ሃይማኖት ‘በፍሬው’ ማለትም አባላቱ በሚሠሩት ሥራ መለየት ትችላላችሁ ብሎ ተናግሯል። በተጨማሪም “መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል” ብሏል። (ማቴዎስ 7:15–20) የአምላክ ቃል መጥፎ ፍሬ ከሚያፈራና ጥፋት ከሚደርስበት ሃይማኖት እንድንወጣ አጥብቆ ይመክረናል።—ራእይ 18:4

እውነተኛ ሃይማኖት የሚጠበቅበትን አድርጓል

እውነተኛ ሃይማኖት “መልካም ፍሬ” በተለይም ፍቅርን ያፈራል። (ማቴዎስ 7:17፤ ዮሐንስ 13:34, 35) ይህን የመሰለ ፍቅር እያሳየ ያለ አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች ወንድማማች ማኅበር የትኛው ነው? የራሳቸውን ሃይማኖት የሚከተሉትንም ሆነ ማንኛውንም ሌላ ሰው ለመግደል እጃቸውን የማያነሱት እነማን ናቸው?—1 ዮሐንስ 3:10–12

ይህን “መልካም ፍሬ” በማፍራት ረገድ ጥሩ ስም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። በምድር ዙርያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ‘ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ አድርገዋል።’ (ኢሳይያስ 2:4) የአምላክን መንግሥት “ወንጌል” በዓለም ዙርያ እንዲሰብኩ ክርስቶስ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመፈጸምም ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። (ማቴዎስ 24:14) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ይጠብቃሉ እንዲሁም ያራምዳሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:9–11

እውነተኛ ሃይማኖት የሚጠበቅበትን አድርጓል። የሰውን ዘር ችግሮች የመፍታት ችሎታ ወዳለው ብቸኛ አካል ሰዎችን እየመራ ነው። በቅርቡ ይህ አካል ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ዓለም ያመጣል። ይህ አካል ማን ነው? (እባክዎን በጀርባ በኩል ያለውን ገጽ ይመልከቱ።)

ችግር የሌለበት ገነት ያላንዳች ጥርጥር ይመጣል

ቢችሉ ኖሮ የሰውን ዘር እያንገላቱ ያሉትን ችግሮች በሙሉ አያስወግዷቸውም ነበርን? በእርግጥ ይህን ያደርጉ ነበር! የሰውን ዘር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ኃይልና ጥበብ ያለው ብቸኛው አፍቃሪ ፈጣሪያችን ከዚህ ያነሰ ነገር ያደርጋል ብለን ማሰብ ይኖርብናልን?

አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በምትመራው ሰማያዊት መንግሥቱ አማካኝነት በሰው ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህች መንግሥት በምድር ላይ የሚገኙትን ብልሹ መንግሥታት “ትፈጫቸዋለች።” (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ይህን የምታደርገው ለምንድን ነው? መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ለአምላክ በመናገር መልሱን ይሰጠናል:- “በምድር ሁሉ ላይ ጌታና ሁሉን ቻይ አምላክ አንተ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደሆንህ ይወቁ።”—መዝሙር 83:18 የ1980 ትርጉም

ይህ ዓለም ሲጠፋ ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም ያልፋል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል’ ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) እነዚህ ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች ለዘላለም የሚኖሩት የት ነው? “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ መልስ ይሰጣል።—መዝሙር 37:9–11, 29፤ ምሳሌ 2:21, 22

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ሞት አይኖርም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ አይኖርም።’ (ራእይ 21:4) ወንጀል፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ኀዘን ወይም ሞት አይኖሩም! እንዲያውም የሞቱ ሰዎች እንኳ እንደገና ሕያዋን ይሆናሉ! ‘ትንሣኤ ይኖራል።’ (ሥራ 24:15) ምድር ራሷ ደግሞ ቃል በቃል ወደ ገነትነት ትለወጣለች።—ኢሳይያስ 35:1, 2፤ ሉቃስ 23:43

አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ አስደሳቹን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የዘላለም ሕይወትም፣ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም) በዓለም ዙርያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልበ ቅን ሰዎች ይህን እውቀት እየቀሰሙ ነው። ይህን እውቀት ማግኘታቸው በአሁኑ ጊዜ ያሉባቸውን ብዙ የግል ችግሮች እንዲቋቋሙ ከማስቻሉም በላይ መፍትሔ ሊያገኙላቸው ያልቻሏቸው ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮች አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ እንደሚያገኙ ሙሉ ትምክህት እንዲያድርባቸው አድርጓል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

WHO photo by P. Almasy

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Jerden Bouman/Sipa Press