የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች
የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች
ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ስለመንግሥቱ እንዲጸልዩ ነግሮአቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ስለ “መንግሥቱ ምሥራች” አዘውትሮ ይናገር ነበር። (ማቴዎስ 4:23) እንዲያውም ከማንኛውም ነገር ይልቅ ደጋግሞ የተናገረው ስለመንግሥቲቱ ነው። ለምን? ምክንያቱም አምላክ ዛሬ የሰውን ሕይወት በጣም አስጨናቂ ያደረጉትን ችግሮች ለመፍታት መሣሪያ አድርጐ የሚጠቀምባት ይህች መንግሥት ስለሆነች ነው። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጦርነትን፣ ረሀብን፣ በሽታንና ዐመጽን ያቆማቸዋል። አንድነትንና ሰላምንም ያመጣል።
ይህን በመሰለ ዓለም ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ ይህንን ጽሑፍ ማንበብ አለብህ። የአምላክ መንግሥት ሲባል በበላይነት የሚያስተዳድር አካል ማለት መሆኑን ከምንባቡ ትማራለህ። ይህች መንግሥት ግን የሰውን ዘር ካስተዳደሩት መንግሥታት ሁሉ የበለጠች ናት። ከዚህም ሌላ አምላክ ስለራሱ መንግሥት የነበሩትን ዓላማዎች እንዴት አስደሳች በሆነ መንገድ ለአገልጋዮቹ ቀስ በቀስ እንደገለጸላቸው ትረዳለህ። በተጨማሪም መንግሥቲቱ ዛሬም ቢሆን እንዴት ልትረዳህ እንደምትችል ትገነዘባለህ።
እንዲያውም አሁኑኑ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ትችላለህ። ሆኖም የእርሷ ዜጋ ለመሆን ከመምረጥህ በፊት ስለ መንግሥቲቱ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ያስፈልግሃል። ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ እንድታነብ እናበረታታሃለን። ጽሑፉ ስለ አምላክ መንግሥት የሚነግርህ ነገር ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው።
እንግዲህ በመጀመሪያ የአምላክ መንግሥት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነችበትን ምክንያት እንመልከት።
በሰው ታሪክ መጀመሪያ ላይ አምላክ ሰውን ፍጹም አድርጐ ሠራው፤ በአንዲት ገነትም አኖረው። በዚያን ጊዜ መንግሥቲቱ አታስፈልግም ነበር።
ይሁንና አዳምና ሔዋን የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ ላይ ያመጸውን የሰይጣንን ቃል ሰሙ። ሰይጣን ስለአምላክ ውሸት ነገራቸውና እንደ እርሱ በአምላክ ላይ እንዲያምጹ አደረጋቸው። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ስለሆነ” መሞት የሚገባቸው ሆኑ።—ሮሜ 6:23
ፍጽምና የሌለው ኃጢአተኛ ሰው ፍጹማን ልጆች መውለድ አይችልም። ይህም በመሆኑ የአዳም ልጆች በሙሉ ፍጽምና የጐደላቸው፣ ኃጢአተኞችና ሟች ሆነው ተወለዱ።—ሮሜ 5:12
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ለመላቀቅ የአምላክ መንግሥት ዕርዳታ አስፈለጋቸው። የአምላክ መንግሥት ሰይጣን በአምላክ ስም ላይ የከመረውንም ስድብ ሁሉ ታስወግዳለች።
ይሖዋ አምላክ የሰውን ልጆች ከኃጢአት ለማዳን አንድ ልዩ “ዘር” ለመላክ ቃል ገባ። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ “ዘር” በአምላክ መንግሥት ውስጥ ንጉሥ እንዲሆን የአምላክ ዓላማ ነበር። ታዲያ ይህ ዘር ማን ይሆን?
አዳም ኃጢአት ከሠራ 2, 000 ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ በጣም ታማኝ የሆነ አብርሃም የሚባል ሰው ይኖር ነበር። ይሖዋ አብርሃም የገዛ ከተማውን ለቅቆ እንዲወጣና በጳለስጢና ምድር በድንኳን ውስጥ እንዲኖር ነገረው።
አብርሃም ይሖዋ የነገረውን ሁሉ ይፈጽም ነበር። አንድ ጊዜ ይሖዋ አንድ በጣም አስቸጋሪ ነገር እንዲያደርግ ቢነግረውም አብርሃም ታዝዟል። ይስሐቅ የተባለውን ልጁን በመሰዊያ ላይ እንዲሰዋለት ይሖዋ ነገረው።
ይሖዋ ሰብዓዊ መስዋዕት መፈለጉ አልነበረም። ለማወቅ የፈለገው አብርሃም ምን ያህል እንደሚወድደው ነው። አብርሃም ይስሐቅን ለመግደል እጁን ሲዘረጋ ይሖዋ አስቆመው።
አብርሃም ባሳየው ታላቅ እምነት የተነሳ ይሖዋ የጳለስጢናን ምድር ለዘሮቹ እንደሚሰጥና ተስፋ የተደረገበት ዘር በእርሱና በይስሐቅ በኩል እንደሚመጣ ቃል ገባለት።—ዘፍጥረት 22:17, 18፤ 26:4, 5
ይስሐቅ ኤሳውና ያዕቆብ የተባሉ መንትያ ልጆች ነበሩት። ይሖዋም ተስፋ የተደረገበት ዘር በያዕቆብ በኩል እንደሚመጣ ተናገረ።—ይሖዋ እሥራኤል የሚል ስም ያወጣለት ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆችን ወለደ። ውሎ አድሮ እነርሱም በሙሉ ልጆች ወለዱ። ስለዚህ የአብርሃም ልጆች መብዛት ጀመሩ።—ዘፍጥረት 46:8–27
ያ አካባቢ በከባድ ረሀብ በተመታ ጊዜ ያዕቆብና ቤተሰቡ ፈርዖን የተባለው የግብጽ ንጉሥ ባደረገላቸው ግብዣ ስፍራውን ለቅቀው በግብጽ መኖር ጀመሩ።—ዘፍጥረት 45:16–20
በግብጽ በመኖር ላይ ሳሉ ተስፋ የተሰጠበት ዘር የያዕቆብ ልጅ የይሁዳ ዘር እንደሚሆን ተገለጠ።—ዘፍጥረት 49:10
ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ ሞተ፣ ዘሮቹም በቁጥር እየበዙ ሄዱና ታላቅ ሕዝብ ሆኑ። በዚህ ጊዜ ግብጻውያን ፈሩአቸውና ባሪያ አድርገው ገዙአቸው።—ዘፀአት 1:7–14
በመጨረሻም በዚያን ጊዜ ወደ ነበረው ፈርዖን ሄዶ የእስራኤልን ልጆች ነፃ መልቀቅ አለብህ የሚል ጥያቄ አንዲያቀርብ ይሖዋ ሙሴ የተባለውን በጣም ታማኝ ሰው ላከ።—ፈርዖን አሻፈረኝ አለ። ስለዚህ ይሖዋ በግብጻውያን ላይ አሥር መቅሰፍቶችን አመጣ። በመጨረሻው መቅሰፍት ላይ ይሖዋ መልአኩን ልኰ የግብጻውያንን የበኩር ልጆች ገደለ። ዘፀአት ምዕራፍ 7 እስከ 12
አምላክ እሥራኤላውያን ለራታቸው ጠቦት እንዲያርዱና ደሙን በበሮቻቸው መቃን ላይ እንዲቀቡ ነገራቸው። በዚህ መንገድ ገዳዩ መልአክ ቤታቸውን አልፎ ይሄዳል። ስለዚህ የእስራኤላውያን በኩራት ልጆች ከግድያው ዳኑ።—ዘፀአት 12:1–35
በዚህ ሳቢያ ፈርዖን እሥራኤላውያን ግብጽን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። በኋላ ግን ሃሳቡን ለወጠና እነርሱን ለመመለስ ማሳደድ ጀመረ።
እሥራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተሻግረው እንዲያመልጡ ይሖዋ መንገድ ከፈተላቸው። ፈርዖንና ሠራዊቱም እነርሱን ተከትለው ለመሻገር ሲሞክሩ በውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ።—ዘፀአት 15:5–21
ይሖዋ የእሥራኤልን ልጆች በበረሃ ወደሚገኘው የሲና ተራራ እየመራ አመጣቸው። እዚያም ሕጉን ሰጣቸውና ይህንን ሕግ ቢጠብቁ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ እንደሚሆኑ ነገራቸው። በዚህ መሠረት እሥራኤላውያን ወደፊት በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የመያዝ አጋጣሚ ተዘርግቶላቸው ነበር።—እሥራኤላውያን በሲና ተራራ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ይሖዋ ለቅድመ አያታቸው ለአብርሃም ቃል ወደገባለት የጳለስጢና ምድር እየመራ ወሰዳቸው። እሥራኤላውያን በጳለስጢና ምድር መኖር ከጀመሩ በኋላ በነገሥታት እንዲገዙ አምላክ ፈቀደ። በዚያን ጊዜ አምላክ በምድር ላይ መንግሥት ነበረው።
በእሥራኤል ላይ የነገሠው ሁለተኛው ንጉሥ የይሁዳ ዘር የሆነው ዳዊት ነበር። ዳዊት በእሥራኤል ጠላቶች ላይ እየዘመተ ድል ካደረገ በኋላ ኢየሩሳሌምን የአገሩ ርዕሰ ከተማ አደረገ።
አንድን ንጉሥ ይሖዋ ከደገፈው ማንም ምድራዊ ገዥ ወግቶ ሊያሸንፈው እንደማይችል በዳዊት ዘመነ መንግሥት የተከሰቱት ሁኔታዎች ያሳያሉ።
ተስፋ የተሰጠበት ዘር ከዳዊት ዘሮች አንዱ እንደሚሆን ይሖዋ ገለጸ።—1 ዜና 17:7, 11, 14
ከዳዊት በኋላ ልጁ ሰለሞን ገዛ እርሱም ጥበበኛ ንጉሥ ነበረ። እሥራኤል በእርሱ በሚገዛበት ጊዜ በልጽጐ ነበር።
ሰሎሞን ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ አንድ ጥሩ ቤተመቅደስ አሠራ። በሰለሞን ዘመነ መንግሥት በእሥራኤል ምድር የነበሩት ሁኔታዎች ወደፊት የምትመጣው የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች የምታመጣላቸውን አንዳንድ በረከቶች ያሳያሉ።—1 ነገሥት 4:24, 25
ይሁንና ከሰለሞን በኋላ የተነሱት ብዙዎቹ ነገሥታት በጣም ከዳተኞች ነበሩ።
ቢሆንም የዳዊት ዘሮች በኢየሩሳሌም ገና በመግዛት ላይ እያሉ ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ ተጠቅሞ ወደፊት አንድ የዳዊት ልጅ መላዋን ምድር በታማኝነት እንደሚገዛ ትንቢት አስነገረ። እርሱም ያ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ነው።—ኢሳይያስ 9:6, 7
የዚህኛው መንግሥት ክብር ከሰለሞን መንግሥት ክብር እጅግ የላቀ እንደሚሆን ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ተናግሯል።—ኢሳይያስ ምዕራፍ 11 እና 65
በዚህ ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ተስፋ የተሰጠበት ይህ ዘር ማን ይሆን የሚለው ጥያቄ በይበልጥ ያስጨንቃቸው ጀመር።
ይሁን እንጂ የእስራኤል ነገሥታት በክፋት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ስለደረሱ በ607 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ባቢሎናውያን አገሪቱን ወርረው እንዲይዙ ይሖዋ ፈቀደላቸው። አብዛኛው ሕዝብ ግዞተኛ ሆኖ ወደ ባቢሎን ተወሰደ። ይሖዋ ግን ቀደም ሲል የገባውን ቃል አልረሳውም። አሁንም ቢሆን ያ ዘር በዳዊት የትውልድ መሥመር መምጣት ነበረበት።—በእሥራኤል ላይ የደረሰው ነገር አንድ ጥበበኛና ታማኝ ሰብዓዊ ንጉሥ ብዙ ጥቅሞችን ማምጣት ቢችልም እነዚህ ጥቅሞች ውስን መሆናቸውን አሳየ። ታማኝ ሰዎች ይሞታሉ፤ ተከታዮቻቸው ግን ታማኝ ላይሆኑ ይችላሉ። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? መፍትሔው ተስፋ የተደረገበት ዘር ነው።
በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ያ ዘር በመጨረሻው ብቅ አለ። እሱ ማን ነው?
ከአምላክ የተላከ አንድ መልአክ ማርያም ተብላ ለምትጠራ ገና ያላገባች እሥራኤላዊት ልጃገረድ መልሱን ሰጣት። ወንድ ልጅ እንደምትወልድና ስሙ ኢየሱስ እንደሚባል ነገራት። መልአኩ የተናገረው ቃል የሚከተለው ነው:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ [ይሖዋ (አዓት)] አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ስለዚህ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት ዘር እንዲሆን በመጨረሻም በአምላክ መንግሥት ውስጥ ንጉሥ ሆኖ እንዲያስተዳድር የአምላክ ሃሳብ ነበር ማለት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ታማኝ ሰዎች ልዩ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ የተወለደው በተአምር ነበር። እናቱ ድንግል ስትሆን ሰብዓዊ አባት አልነበረውም። ቀደም ሲል ኢየሱስ በሰማይ ይኖር ነበር። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል የኢየሱስን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማሕፀን አዛወረው። ስለዚህ የአዳምን ኃጢአት አልወረሰም። ኢየሱስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ኃጢአት አልሠራም።—1 ጴጥሮስ 2:22
ኢየሱስ ሰላሳ ዓመት ሲሞላው ተጠመቀ።
ለሰዎች ስለአምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር። ከጊዜ በኋላም የዚያ መንግሥት ንጉሥ ራሱ መሆኑን አስታወቀ።—ማቴዎስ 4:23፤ 21:4–11
ከዚህም ሌላ ብዙ ተዓምራትን አድርጐአል።
የታመሙትን ፈውሷል።—ማቴዎስ 9:35
የተራቡትን በተአምር መግቦአል።—ማቴዎስ 14:14–22
ሌላው ቀርቶ ሙታንን አስነስቷል።—ዮሐንስ 11:38–44
እነዚህ ተአምራት ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግላቸው ያሳያሉ።
ዮሐንስ 18:36) የአምላክ መንግሥት “ሰማያዊት ኢየሩሳሌም” በሚል ስም የምትታወቀውም በዚህ ምክንያት ነው።—ዕብራውያን 12:22, 28
ንጉሥ ዳዊት ኢየሩሳሌምን እንዴት የመንግሥቱ ርዕሰ ከተማ እንዳደረገ ታስታውሳለህን? የአምላክ መንግሥት በምድር ሳይሆን በሰማይ እንደምትሆን ኢየሱስ አስረድቷል። (የአምላክ መንግሥት ዜጐች ሊያከብሩአቸው የሚገቡአቸውን ሕጐች ኢየሱስ በዝርዝር ገልጾአል። እነዚህ ሕጐች በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ከሁሉ የሚበልጡት ሕጐች ሰዎች አምላክን መውደድ፤ እርስ በርሳቸውም መዋደድ አለባቸው የሚሉት ናቸው።—ማቴዎስ 22:37–39
በተጨማሪም ኢየሱስ በመንግሥቱ ውስጥ የሚገዛው እርሱ ብቻ እንዳልሆነ ገልጾአል። የተመረጡ ሰዎች ወደ ሰማይ ሄደው እዚያ ከእርሱ ጋር እንዲገዙ የአምላክ ዓላማ ነበር። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 14:3) ወደዚያ የሚሄዱት ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? ራእይ 14:1 144, 000 ናቸው በማለት ይመልስልናል።
ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት ወደ ሰማይ የሚሄዱት 144, 000 ብቻ ከሆኑ የቀሩት የሰው ዘሮች ምን ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩት ሰዎች “ሌሎች በጐች” ተብለው ተጠርተዋል።—ዮሐንስ 10:16
ስለዚህ ሁለት ተስፋዎች አሉ ማለት ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመግዛት ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ይሖዋ አምላክ የጠራቸው 144, 000 ሰዎች አሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ግን የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በመሆን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር እርግጠኛ ተስፋ አላቸው።—ራእይ 5:10
ሰይጣን ኢየሱስን በኃይል ይጠላውና ይቃወመው ነበር። ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ከሰበከ በኋላ ሰይጣን እንዲታሰርና በእንጨት ላይ ተቸንክሮ እንዲገደል አድርጐአል። አምላክ ይህንን ለምን ፈቀደ?
ከአዳም የመጣን እንደመሆናችን ሁላችንም ኃጢአተኞች እንደሆንና መሞት እንደሚገባን አስታውስ።—ሮሜ 6:23
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ስለተወለደ ፍጹም ሰው እንደነበረና ሞት እንደማይገባው አስታውስ። ሰይጣን ኢየሱስን በመግደል ‘ሰኰናውን እንዲቀጠቅጥ’ አምላክ ፈቅዶለት ነበር። አምላክ ግን መሞት የማይችል መንፈሳዊ አካል አድርጐ እንደገና ሕይወት ሰጠው። ኢየሱስ ግን አሁንም ቢሆን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የማግኘት መብት ስለነበረው ይህንን መብቱን የሰውን ልጆች ከኃጢአት ለመዋጀት ሊጠቀምበት ይችላል።—ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 5:12, 21፤ ማቴዎስ 20:28
የኢየሱስ መስዋዕት ምን ትርጉም እንዳለው ሙሉ በሙሉ እንዲገባን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚሁ ጉዳይ ትንቢታዊ ትርጉም ባላቸው ምሳሌያዊ ነገሮች ተጠቅሞአል።
ለምሳሌ ያህል ፍቅሩን ለመፈተን ይሖዋ አብርሃም ወንድ ልጁን እንዲሰዋለት መጠየቁ ትዝ ይልሃልን?
ይህ ትንቢታዊ ትርጉም ያለው ምሳሌ ነበር። የሚያመለክተውም የኢየሱስን መስዋዕት ነው። ያ ሁኔታ ይሖዋ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ ልጁ ኢየሱስ እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ እንዲሞት እንዴት እንደፈቀደለት ያሳያል።—ዮሐንስ 3:16
ይሖዋ እሥራኤላውያንን ከግብጽ እንዴት እንደታደጋቸውና መልአኩ ቤታቸውን እንዲያልፍ በማድረግ የበኩር ልጆቻቸውን እንዳዳነላቸው ታስታውሳለህን?—ዘፀአት 12:12, 13
ይህም ትንቢታዊ ትርጉም ያለው ምሳሌ ነበር። የጠቦቱ ደም ለእሥራኤላውያን የበኩር ልጆች ሕይወት ማለት እንደነበረ ሁሉ የፈሰሰው የኢየሱስ ደምም ለሚያምኑበት ሁሉ ሕይወት ማለት ነው። በዚያ ምሽት የተከናወኑት ነገሮች ለእሥራኤላውያን ነፃነት እንዳመጡላቸው ሁሉ የኢየሱስም ሞት ለሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚሆንበትን ጥርጊያ ከፍቶላቸዋል።
ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 1:29
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀመዛሙርትን ሰብስቦ የመንግሥቱን ምሥራች እርሱ ከሞተ በኋላም ቢሆን እንዲሰብኩ አሰለጠናቸው።—አምላክ በመንግሥቱ ውስጥ ከኢየሱስ ጋር እንዲነግሡ የመረጣቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እነርሱ ነበሩ።—ሉቃስ 12:32
አይሁዳውያን ሕጉን ቢጠብቁ ‘የካህናት መንግሥት’ ትሆናላችሁ ብሎ አምላክ ቃል እንደገባላቸው ታስታውሳለህን? አሁን ኢየሱስን ከተቀበሉ የዚያ መንግሥት ክፍል የመሆንና ሰማያዊ ካህናት ሆኖ የማገልገል ዕድል ተከፈተላቸው። አብዛኞቹ ግን ኢየሱስን ለመቀበል አሻፈረን አሉ።
ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ አይሁዶች የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች መሆናቸው አከተመ። የጳለስጢና ምድር ተስፋ የተደረገበት ምድር መሆኑ ቀረ።—ማቴዎስ 21:43፤ 23:37, 38
ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን ሰዎች ሲሰበስብ ቆይቷል። ከእነርሱ መካከል በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ዛሬ በምድር ላይ ይገኛሉ። ቅቡዓን ቀሪዎች ብለን እንጠራቸዋለን።—ራእይ 12:17
አሁን የአምላክ መንግሥት ምን ማለት እንደሆነች መረዳት ጀምረሃል። ሰማይ ውስጥ ሆና ሰዎችን የምትገዛ አስተዳደር ናት። ንጉሥዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ከምድር የተመረጡ 144, 000 ሰዎችም አብረውት ይገዛሉ። መንግሥቲቱ በምድር ላይ የሚገኙ ታማኝ የሰው ዘሮችን ትገዛለች። ለምድር ሰላም የማምጣት ኃይልም ይኖራታል።
ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተነሳ ከዚያም ወደ ሰማይ ሄደ። እዚያ ሆኖ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን መግዛት እንዲጀምር አምላክ እስኪነግረው ድረስ ቆየ። (መዝሙር 110:1) ታዲያ አምላክ እንደዚያ ብሎ የነገረው መቼ ነው?
አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ለሰዎች ስለ መንግሥቱ አንዳንድ ነገሮችን በሕልም ገልጾላቸዋል።
በዳንኤል ዘመን ይሖዋ እንደዚህ ያለ አንድ ሕልም ለባቢሎኑ ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳይቷል። ሕልሙ ስለአንድ ትልቅ ዛፍ የሚገልጽ ነበር።—ዳንኤል 4:10–37
ዛፉ ተቆረጠ፤ ጉቶውም ለሰባት ዓመታት ታስሮ ቆየ።
ዛፉ ናቡከደነፆርን ያመለክት ነበር። ጉቶው ለሰባት ዓመታት እንደታሠረ ሁሉ ናቡከደነፆርም ለሰባት ዓመታት አእምሮውን ስቶ ቆየ። ከዚያም የአእምሮው ጤንነት ተመለሰለት።
ይህ ሁሉ ትንቢታዊ ምሳሌ ነበር። ናቡከደነፆር የይሖዋን ዓለም አቀፋዊ ገዥነት ያመለክት ነበር። በመጀመሪያ ላይ ለዚህ የይሖዋ ገዥነት መግለጫ ሆኖ ያገለገለው በኢየሩሳሌም የነበረው የንጉሥ ዳዊት ዘሮች መንግሥት ነው። በ607 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ባቢሎን ኢየሩሳሌምን ወግታ ከያዘች በኋላ ያ የነገሥታት መሥመር ተቋረጠ። “ሕጋዊ መብት ያለው እስኪመጣ ድረስ” ከንጉሥ ዳዊት መሥመር ሌላ ንጉሥ አይነሳም። (ሕዝቅኤል 21:27) ያ “ሕጋዊ መብት ያለው” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።
ኢየሱስ መግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ ከ607 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በመነሣት ምን ያህል ዓመታት ማለፍ ነበረባቸው? ሰባት ትንቢታዊ ዓመታት። ይህም 2, 520 ዓመታት ማለት ነው። (ራእይ 12:6, 14) ከ607 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ተነሥተን ብንቆጥር 2, 520 ዓመታት ወደ 1914 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ያደርሰናል።
ስለዚህ ኢየሱስ በሰማይ ውስጥ ሆኖ በ1914 መግዛት ጀመረ። ይህ ምን ትርጉም ነበረው?
ትርጉሙ ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው ራእይ አማካኝነት ይገልጽልናል።
ዮሐንስ በሰማይ አንዲት ሴት ወንድ ልጅ ስትወልድ ተመለከተ።—ራእይ 12:1–12
ሴቲቱ በሰማይ አምላክን የሚያገለግሉትን መላእክት በሙሉ የሚያጠቃልለውን የአምላክን ሰማያዊ ድርጅት ታመለክታለች። ወንዱ ልጅዋ የአምላክ መንግሥት ምሳሌ ነው። ይህ መንግሥት ‘የተወለደው’ በ1914 ነው።
ከዚያ ቀጥሎ ምን ሆነ? ኢየሱስ ንጉሥ ከሆነ በኋላ የወሰደው የመጀመሪያው እርምጃ ሰይጣንንና ከእርሱ ጋር ሆነው ያመጹትን መላእክት ከሰማይ ወደ ምድር መጣል ነበር።—ራእይ 12:9
የዚህ ውጤት ምን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባህር ወዮላችሁ፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዷልና።”—ራእይ 12:12
ስለዚህ ኢየሱስ ከሰማይ መግዛት ሲጀምር በምድር ላይ ጠላቶቹ በኃይል መሯሯጥ ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሱስ በጠላቶቹ መካከል መግዛት ጀመረ።—መዝሙር 110:1, 2
ይህ ሁኔታ ለሰው ልጆች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ኢየሱስ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረት፣ በሽታና የምድር መንቀጥቀጥ እንደሚበዛ ነግሮናል።—ማቴዎስ 24:7, 8፤ ሉቃስ 21:10, 11
ከ1914 ጀምሮ እነዚህ ነገሮች በመፈጸም ላይ እንዳሉ ተመልክተናል። ይህም መንግሥቲቱ መግዛት እንደጀመረች የምናውቅበት ሌላው ምክንያት ነው።
“ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሳ ይደክማሉ” ተብሎ ተነግሮ ነበር። (ሉቃስ 21:25, 26) ይህም ከ1914 ጀምሮ ሲፈጸም ተመልክተናል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ላይ ሲጨምር ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ . . . እርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞችና ራሳቸውን የማይገዙ” እንደሚሆኑ ተናገረ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
ስለዚህ በዛሬው ጊዜ መኖር ለምን በጣም አስጨናቂ እንደሆነ ታውቃለህ። ሰይጣን በመሯሯጥ ላይ ነው። ይሁን እንጂ የአምላክም መንግሥት ጭምር ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት።
ከ1914 በኋላ ምንም ያህል ጊዜ ሳይቆዩ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ ያላቸው ቀሪዎች መንግሥቲቱ የተቋቋመች መሆኗን የሚገልጸውን ምሥራች መናገር ጀመሩ። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ይህ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በመላዋ ምድ ላይ ተስፋፍቷል።—የዚህ የስብከት ሥራ ዓላማ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ለመንገር ነው።
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጐች ለመሆን እንዲመርጡ ለመርዳት ነው።
የሰው ልጆች በግ መሰልና እና ፍየል መሰል ሕዝቦች በመሆን በሁለት ወገን እንደሚከፈሉ ኢየሱስ ተናግሮ ነበር።—ማቴዎስ 25:31–46
“በጎች የተባሉት እርሱንና ወንድሞቹን የሚያፈቅሩት ሰዎች ናቸው። “ፍየሎች” የተባሉት ደግሞ እንደዚያ የማያደርጉ ሰዎች ናቸው።
“በጎቹ” የዘላለም ሕይወት ሲያገኙ “ፍየሎቹ” ግን አያገኙም።
ይህ የመከፋፈል ሥራ የሚከናወነው ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በሚደረገው ስብከት አማካኝነት ነው
ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ከዚህ ቀጥሎ እነሆ:- “በዘመኑ ፍጻሜ [የይሖዋ (አዓት)] ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።”—የሰው ዘር በአሁኑ ጊዜ የሚኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ ነው።
የይሖዋ የአምልኰ “ቤት” ከሐስት ሃይማኖቶች በላይ “ከፍ ከፍ” ብሎአል።
“ብዙ አሕዛብ ሄደው ኑ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ተራራ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፣ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል። በጐዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።”—ኢሳይያስ 2:3
ስለዚህ ከሁሉም አሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ይመጣሉ። ሌሎችም አብረዋቸው እንዲያመልኩት ግብዣ ያቀርቡላቸዋል። ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ እንዴት መመላለስ እንደሚቻል ይማራሉ።
“ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሠይፍ አያነሳም፣ ሠልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4
ይሖዋን የሚያመልኩት ሰዎች አንድነት አላቸው ሰላማውያንም ናቸው።
በአምላክ መንግሥት ሥር በሚካሄደው በዚህ የሥራ እንቅስቃሴ የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከሦስት ሚልዮን ተኩል የሚበልጡ የመንግሥቱ ተገዢዎች አሉ።
እነርሱም ከቀሪዎቹ ዙሪያ ተሰብስበዋል። እነዚህ ቀሪዎች ወደ ሰማይ ለመሄድና ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ተስፋ ያላቸው የ144, 000 ቀሪዎች ናቸው።
በአምላክ ድርጅት በኩል መንፈሳዊ ምግብ ያገኛሉ።—ማቴዎስ 24:45–47
እርስ በርሳቸው ከልብ የሚፋቀሩ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ናቸው።—ዮሐንስ 13:35
የአእምሮ ሰላምና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ በማግኘት በደስታ ይኖራሉ።—ፊልጵስዩስ 4:7
ስለዚህ ምሥራቹ መሰበክ ይኖርበታል። “በጐቹ” ተሰብስበው ማለቅ አለባቸው። ከዚያስ በኋላ መንግሥቲቱ ምን ታደርጋለች?
ታማኙ ንጉሥ ዳዊት በአምላክ ጠላቶች ላይ ዘምቶ ድል እንዳደረጋቸው ታስታውሳለህን? ንጉሡ ኢየሱስም ልክ እንደዚሁ ያደርጋል።
አንድ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልም አንድ ትልቅ ምስል አይቶ ነበር። ምስሉ እስከ ዘመናችን ድረስ የቀጠሉትን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያመለክታል።
ከዚያ ቀጥሎ ከአንድ ተራራ የተፈነቀለ አንድ ድንጋይ ተመለከተ። ድንጋዩ ያንን ምስል ፈጨው። ድንጋዩ የአምላክን መንግሥት ይወክላል።
ይህ ማለት አሁን ያለው ክፉ የሆነ የነገሮች ሥርዓት ይደመሰሳል ማለት ነው።—ዳንኤል 2:44
መንግሥቲቱ ቀጥሎ ያሉትን ነገሮች እንዳልነበሩ ታደርጋቸዋለች።
የሐሰት ሃይማኖት ወደ ባህር እንደተጣለ የወፍጮ ድንጋይ ዳግመኛ እንደማይታይ ሆኖ ይደመሰሳል።—ራእይ 18:21
አምላክን የሚያፈቅሩ ሁሉ አሁኑኑ የሐሰት ሃይማኖትን ለቅቀው እንዲወጡ የምናበረታታው በዚህ ምክንያት ነው።—ራእይ 18:4
ቀጥሎ ንጉሡ ኢየሱስ ‘አሕዛብን ይመታል . . . በብረት በትርም ይገዛቸዋል።’—ራእይ 19:15
በዚህ የተነሳ ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥትን ግብር ቢከፍሉና የአገሩን ሕጐች ቢታዘዙም በፖለቲካ ውስጥ አይገቡም።
በመጨረሻው ሰይጣን ራሱ “ታላቁ ዘንዶ” ወደ ጥልቁ ይጣላል።—ራእይ 20:2, 3
ከዚህ መከራ የሚተርፉት ኢየሱስን እንደ ንጉሣቸው አድርገው በመቀበል የሚገዙለት “በጐቹ” ብቻ ናቸው።—ማቴዎስ 25:31–34, 41, 46
ሐዋርያው ዮሐንስ ከመከራው የሚተርፉትን “በጎች” በራእይ ተመልክቷል።
“ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ።”—ራእይ 7:9
የምሥራቹን ስብከት እሺ ብለው የሚቀበሉት ሁሉ ተሰባስበው “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሆነዋል።
እነርሱ “ከታላቁ መከራ” ይወጣሉ።—ራእይ 7:14
“የዘንባባ ዝንጣፊዎች” መያዛቸው ኢየሱስን እንደ ንጉሣቸው አድርገው መቀበላቸውን ያሳያል።
“ነጭ ልብስ” መልበሳቸው በኢየሱስ መስዋዕት ላይ እምነት ያላቸው መሆኑን ያመለክታል።
“በጉ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ከዚያ በኋላ ምን ምን በረከቶችን አግኝተው ይደሰታሉ? ታማኙ ንጉሥ ሰለሞን በሚገዛበት ጊዜ በእሥራኤል እንዴት ያለ ደስታ እንደነበረ ታስታውሳለህን? ይህ ሁኔታ በንጉሡ በኢየሱስ ሥር በምድር ላይ የሚኖረውን ደስታ በትንሹ የሚያመለክት ሥዕል ነው።
ልክ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው በሰዎችና በእንስሳት መካከል ቃል በቃል ሰላም ይሰፍናል።—መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 11:6–9
ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በሽተኞችን ይፈውስ እንደነበረ ሁሉ ወደፊትም በሽታን ከሰው ልጆች ሁሉ ያርቃል።—ኢሳይያስ 33:24
ኢየሱስ ብዙ ሕዝብን በተአምር ይመግብ እንደነበረ ሁሉ ወደፊትም የምግብ እጥረት የተባለውን ነገር ሁሉ ለሰው ልጆች ያስወግድላቸዋል።—መዝሙር 72:16
ሙታንን እንዳስነሳ ሁሉ ወደፊትም ራሳቸውን ለአምላክ መንግሥት ለማስገዛት ሙሉ አጋጣሚ ያላገኙትን ሙታን በሙሉ ያስነሳል።—ዮሐንስ 5:28, 29
የሰውን ልጆች አዳም ወዳሳጣቸው የፍጽምና ደረጃ ቀስ በቀስ ያደርሳቸዋል።
ታዲያ ወደፊት የሚመጣው ጊዜ አስደናቂ አይደለምን? አንተ በዓይንህ ልታየው ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ አሁን ራስህን ለአምላክ መንግሥት ለማስገዛት ጥረት አድርገህ ከበጎቹ አንዱ ሁን።
መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተህ ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን እወቅ።—ዮሐንስ 17:3
ከመንግሥቱ ዜጐች ጋር የቅርብ ግንኙነት መሥርት።—ዕብራውያን 10:25
የመንግሥቲቱን ሕጐች ተማራቸው ታዘዛቸውም።—ኢሳይያስ 2:3, 4
ይሖዋን ለማገልገል ሕይወትህን ለእርሱ ወስን፣ ከዚያም ተጠመቅ።—ማቴዎስ 28:19, 20
እንደ ስርቆት፣ ውሸት፣ ብልግናና ስካር የመሳሰሉትን ይሖዋ አምላክን የሚያስከፉ ነገሮች አስወግድ። 1 ቆሮንቶስ 6:9–11
የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ በሚደረገው ጥረት ተሳተፍ።—ማቴዎስ 24:14
ከዚያ በኋላ አዳም ያጠፋት ገነት በአምላክ እርዳታ ለዘሮቹ ተመልሳ ስትቋቋም ለማየት ትችላለህ። በተጨማሪም የሚቀጥለው ተስፋ ሲፈጸም ትመለከታለህ:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፣ ከእነርሱም ጋር ያድራል። እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፣ እምባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
607 ከዘአበ 1914 እዘአ
ከዘአበ እዘአ
500 1,000 1,500 2,000 2,520
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም
ይስሐቅ
ያዕቆብ
ይሁዳ
ዳዊት
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
144,000
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳም
ኢየሱስ