የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?
የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?
“ይህን አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን፤ ስለዚህ የአንተ አሳብ ምን እንደሆነ መስማት እንፈልጋለን።” (ሥራ 28:22 የ1980 ትርጉም) እነዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮም ይኖሩ የነበሩ የማኅበረሰብ መሪዎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። በውጭ ያሉት ተቺዎች የሚሉትን ብቻ ሳይሆን ከምንጩ ለመስማት ፈልገው ነበር።
ዛሬም በተመሳሳይ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ የተቃውሞ ቃል ይነገራል፤ ስለዚህ አለምክንያት ከሩቁ ከሚጠሏቸው ምንጮች ስለ እነርሱ እውነቱን ለማወቅ መጠበቁ ስህተት ይሆናል። በዚህ ምክንያት ከዋና ዋናዎቹ እምነቶቻችን አንዳንዶቹን ስንገልጽልዎ ደስ ይለናል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና እግዚአብሔር
‘ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈና ጠቃሚ እንደሆነ’ እናምናለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ምንም እንኳ አንዳንዶች ክርስቲያኖች አይደሉም እያሉ ቢናገሩም ይህ አባባል ፈጽሞ እውነት አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለም” በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረውን ቃል ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን።—ሥራ 4:12
ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነና “የላከኝ አባቴ ነው” ብሎ ስለተናገረ የይሖዋ ምሥክሮች እግዚአብሔር ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ያምናሉ። (ዮሐንስ 10:36፤ 6:57) ኢየሱስ ራሱ:- “ከእኔ አብ ይበልጣል” በማለት አረጋግጧል። (ዮሐንስ 14:28፤ 8:28) በዚህ ምክንያት የሥላሴ እምነት እንደሚለው ኢየሱስ ከአብ ጋር እኩል ነው ብለን አናምንም። ከዚህ ይልቅ በእግዚአብሔር እንደተፈጠረና የሱም የበታች እንደሆነ እናምናለን።—ቆላስይስ 1:15፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የአምላክ ስም ጅሆቫ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ ደግሞ ይሖዋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ:- “በስሜም ይሖዋ አልተገለጥሁላቸውም” ይላል። (ዘጸአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ከዚህ ጋር በመስማማት ኢየሱስ ተከታዮቹን “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ በማስተማር ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ ሰጥቷል። ራሱም ለአምላክ ሲጸልይ “ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6
የይሖዋ ምሥክሮችም ኢየሱስን በመምሰል የአምላክን ስምና ዓላማዎቹን ለሌሎች መግለጽ እንዳለባቸው ያምናሉ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም ለመጠራት የመረጥነው “የታመነው ምሥክር” የተባለውን የኢየሱስን ምሳሌ ስለምንከተል ነው። (ራእይ 1:5፤ 3:14) ኢሳይያስ 43:10 አምላክን ለሚወክሉት ሕዝብ “እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምሥክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነው።
የአምላክ መንግሥት
ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። መንግሥቱንም የትምህርቱ ዋና መልዕክት አድርጎ ሰብኳል። (ማቴዎስ 6:10፤ ሉቃስ 4:43) መንግሥቲቱ ከሰማይ ሆና ምድርን የምትገዛ እውን መስተዳደር መሆኗንና ኢየሱስ ክርስቶስም ለዓይን በማይታይ ሁኔታ እንዲገዛ የተሾመላት ንጉሥ እንደሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “አለቅነት በጫንቃው ላይ ይሆናል . . . በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 9:6, 7
ይሁን እንጂ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይሆንም። በሰማይ ከእርሱ ጋር 2 ጢሞቴዎስ 2:12) በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ለመንገሥ ከሞት የሚነሡት ሰዎች ቁጥር ‘ከምድር የተዋጁ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ’ ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል።—ራእይ 14:1, 3
ሆነው የሚገዙ ተባባሪ ነገሥታት ይኖሩታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ብንጸና ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን” ብሎ ጽፎአል። (እርግጥ ማንኛውም መንግሥት ተገዥዎች ይኖሩታል። የይሖዋ ምሥክሮችም ከእነዚህ ሰማያዊ ነገሥታት በተጨማሪ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች እንደሚኖሩ ያምናሉ። ውብ ገነት የምትሆነዋ ምድር ውሎ አድሮ በእነዚህ የአምላክ መንግሥት ተገዥዎች ትሞላለች። ሁሉም ለክርስቶስና ለተባባሪዎቹ ነገሥታት ይገዛሉ። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ምድር በጭራሽ እንደማትጠፋና “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚፈጸም በጥብቅ ያምናሉ።—መዝሙር 37:29፤ 104:5
ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት የምትመጣው እንዴት ነው? የምትመጣው ሁሉም ሰዎች የአምላክን መንግሥት በፈቃደኝነት ሲቀበሉ ነውን? መንግሥቲቱ እንድትመጣ አምላክ በምድር ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ይገልጻል። “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል። እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች፤ ታጠፋቸውማለች፤ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው መቼ ነው? አሁን እየተፈጸሙ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ቅርብ በሆነ ጊዜ እንደምትመጣ ያምናሉ። በማቴዎስ 24:3-14፤ በሉቃስ 21:7-13, 25-31 እና በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ።
አሁን ያለው ክፉ የነገሮች ሥርዓት ‘መጨረሻ ቀኖቹ’ እንደደረሱበት የሚያሳዩትን አስቀድሞ የተነገሩትን ትንቢቶች እንዲመረምሩ ግብዣችንን እናቀርባለን። እነርሱም‘አምላካችንን ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ ሐሳባችንና ኃይላችን ስለምንወድ፤ እንዲሁም ጐረቤቶቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን ስለምንወድ’ በብሔር፣ በዘር ወይም በጐሣ የተከፋፈልን አይደለንም። (ማርቆስ 12:30, 31) በሁሉም አገሮች በሚገኙት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ዘንድ በሚታየው ፍቅር በሰፊው እንታወቃለን። (ዮሐንስ 13:35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) በዚህ ምክንያት በእነዚህ አገሮች የፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋም እንይዛለን። ኢየሱስ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ሲል እንደተናገረላቸው እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን እንጥራለን። (ዮሐንስ 17:16) ከዓለም መለየት ማለት በዛሬው ጊዜ በጣም የተስፋፋውን ብልሹ ምግባር ይኸውም ውሸት፣ ስርቆት፣ ዝሙት፣ ምንዝር፣ ግብረ ሰዶም፣ ደምን አለአግባብ መጠቀም፣ የጣዖት አምልኰ እና እነዚህን የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን ሌሎች ነገሮች አለማድረግ ማለት መሆኑን እናምናለን።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ኤፌሶን 5:3-5፤ ሥራ 15:28, 29
የወደፊቱን ተስፋ በተመለከተ
የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ማለት በዚህ ዓለም የምንኖረው የአሁኑ ሕይወት ብቻ እንዳልሆነ እናምናለን። ሰዎች በአምላክ ዘንድ የጽድቅ አቋም አግኝተው በአዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል ኢየሱስ ደመ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲያፈስ ይሖዋ ወደ ምድር እንደላከው እናምናለን። አንዱ የኢየሱስ ሐዋርያ እንዳለው “በደሙ ጸድቀናል።” (ሮሜ 5:9፤ ማቴዎስ 20:28) የወደፊቱን የዘላለም ሕይወት በር ከፋች ለሆነው ለዚህ የቤዛ ዝግጅት የይሖዋ ምሥክሮች አምላክንና ልጁን በጥልቅ ያመሰግናሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ መንግሥት ውስጥ በትንሣኤ መዝሙር 146:3, 4፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ መክብብ 9:5) አዎ፣ ሙታን ወደፊት በሕይወት መኖር የሚችሉት አምላክ በትንሣኤ ሲያስባቸው ብቻ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
ሙታን አማካይነት ሕይወት እንደሚገኝ ሙሉ እምነት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት “በዚያን ጊዜ ሐሳቡ ይጠፋል” ስለሚል ሰው ከሞተ ሕልውናው አቁሟል ብለን እናምናለን። (ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት በዛሬው ጊዜ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ስታጠፋቸው አሁን በሕይወት የሚገኙ ብዙ ሰዎች ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ያምናሉ። በተጨማሪም ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውሃ እንደተረፉ ሁሉ አሁንም የጥፋቱ ተራፊዎች በፀዳችው ምድር ላይ ሕያዋን ሆነው እንደሚኖሩ እናምናለን። (ማቴዎስ 24:36-39፤ 2 ጴጥሮስ 3:5-7, 13) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ስለሚል ከመጪው የጥፋት ፍርድ መዳን የይሖዋን ብቃቶች በማሟላት ላይ የተመካ እንደሆነ እናምናለን።—1 ዮሐንስ 2:17፤ መዝሙር 37:11፤ ራእይ 7:9, 13-15፤ 21:1-5
የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት በሙሉ በዚህች ትንሽ ጽሑፍ ላይ መዘርዘር እንደማይቻል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እንዲጥሩ እንጋብዝዎታለን።
ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም ለመጠራት የመረጥነው የኢየሱስን ምሳሌ ስለምንከተል ነው