ይሖዋ ማን ነው?
ይሖዋ ማን ነው?
ኤንሪ ሙኦ የተባለው የ19ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ አሳሽ የካምቦዲያን ጥቅጥቅ ያለ ደን እየጣሰ ካቋረጠ በኋላ በአንድ ቤተ መቅደስ ዙሪያ ወደተሠራ ሰፊ የውኃ ጉድጓድ ደረሰ። ይህ ቤተ መቅደስ አንግኮር ዋት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በምድር ላይ ከሚገኙት ሃይማኖታዊ ቅርሶች ሁሉ ትልቁ ነው። ሙኦ ይህን በድንጋይ ሽበት የተሸፈነ መዋቅር ገና ሲመለከት የሰው እጅ ሥራ ውጤት መሆኑን እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም። “የማይክልአንጄሎ ዓይነት ችሎታ ባለው አንድ ጥንታዊ ሰው የተሠራው ይህ ቤተ መቅደስ ግሪክ ወይም ሮም ትተውልን ካለፉት ቅርስ ሁሉ የላቀ ነው” ሲል ጽፏል። ለብዙ ምዕተ ዓመታት ተትቶና ተረስቶ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ውስብስብ መዋቅር በስተጀርባ አንድ ንድፍ አውጪ መኖሩን በፍጹም አልተጠራጠረም።
ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የተጻፈ ጥበብ ያለበት አንድ መጽሐፍ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” በማለት ተመሳሳይ የሆነ አሳማኝ ነጥብ ማቅረቡ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዕብራውያን 3:4) ሆኖም አንዳንዶች ‘የተፈጥሮና የሰው ሥራ የተለያየ ነው’ በማለት ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ አባባል የሚስማሙት ሁሉም ሳይንቲስቶች አይደሉም።
በዩ ኤስ ኤ ፔንሲልቬንያ ውስጥ በሚገኘው በሊሃይ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቢሂ “ባዮኬሚካላዊ ቅንባሮዎች ግዑዝ ነገሮች አለመሆናቸውን” አምነው ከተቀበሉ በኋላ “ሕያው የሆኑ ባዮኬሚካላዊ ቅንባሮዎች የማሰብ ችሎታ ባለው አካል ሊነደፉ ይችላሉ?” ብለው ጠይቀዋል። ቀጥለውም ሳይንቲስቶች እንደ ጀነቲካዊ ምህንድስና የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም በሕያዋን ዘአካሎች ላይ መሠረታዊ ለውጦች የሚያስከትል ንድፍ እያወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ግዑዝም ሆኑ ሕይወት ያላቸው ነገሮች “ሊሠሩ” ይችላሉ! ቢሂ በማጉያ መነጽር አማካኝነት ብቻ ሊታዩ በሚችሉት ሕይወት ያላቸው ሕዋሳት ላይ ምርምር ሲያደርጉ በጣም ውስብስብ የሆነ አስገራሚ ቅንባሮ መኖሩን አስተውለዋል።
ይህ ቅንባሮ ተግባራቸውን ለማከናወን አንዳቸው በሌላው ላይ ጥገኛ ከሆኑ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። ታዲያ የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው? “ሕዋስን ማለትም በሞሊኪውል ደረጃ የሚገኘውን ሕይወት ለማጥናት የተደረጉት የእነዚህ ተከታታይ ጥረቶች ውጤት ሕዋስ በ‘ንድፍ!’ የተገኘ መሆኑን ጥርት ባለ ድምፅ ይናገራል።”ከእነዚህ ውስብስብ ቅንባሮዎች በስተጀርባ ያለው ንድፍ አውጪ ማን ነው?
ንድፍ አውጪው ማን ነው?
መልሱ ቀደም ሲል በተጠቀሰውና ጥንታዊ የጥበብ መጽሐፍ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ በመክፈቻ ቃላቱ ላይ በጣም ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ሁሉን የነደፈው ማን ስለመሆኑ ለተነሣው ጥያቄ መልስ ይሰጣል:- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1
ሆኖም አምላክ ናቸው ተብሎ ከሚነገርላቸው ሌሎች አካላት ራሱን ለመለየት ፈጣሪ ልዩ በሆነ ስም ራሱን ለይቶ ይገልጻል:- “ሰማያትን የፈጠረ . . . ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፣ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን . . . የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላል።” (ኢሳይያስ 42:5, 8) የአጽናፈ ዓለምን ንድፍ ያወጣውና ወንድንና ሴትን በምድር ላይ የሠራው አምላክ ስሙ ይሖዋ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ማን ነው? ምን ዓይነት አምላክ ነው? እርሱን ማዳመጥ የሚኖርብህስ ለምንድን ነው?
የስሙ ትርጉም
በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ የሚለው የፈጣሪ ስም ትርጉሙ ምንድን ነው? መለኮታዊው ስም በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה) የተጻፈ ሲሆን በዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ሰፍሮ ይገኛል። ይህ ስም ሃዋሕ (“መሆን”) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አስደራጊ ግስ ሲሆን “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማሳካት ሲል ራሱን መሆን የሚያስፈልገውን እንዲሆን ያደርጋል። የገባቸውን ተስፋዎች ለመፈጸም ፈጣሪ፣ ፈራጅ፣ አዳኝ፣ ሕይወት ጠባቂና የመሳሰሉትን ይሆናል። ከዚህም በላይ የዕብራይስጡ ግስ በሂደት ላይ ያለን አንድ ድርጊት በሚያመለክት መንገድም ተሠርቶበታል።
ይህ ደግሞ ይሖዋ አሁንም ድረስ ራሱን የተስፋዎች ፈጻሚ እያደረገ እንዳለ ያመለክታል። አዎን፣ ይሖዋ ሕያው አምላክ ነው!የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪና የገባቸውን ተስፋዎች ፈጻሚ የሆነውን ይህን አካል በጣም የሚስብ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ይሖዋ ራሱን ልዩ የሚያደርጉትን ባሕርያቱን ሲገልጥ “እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” በማለት ይናገራል። (ዘጸአት 34:6, 7) ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ታማኝ ፍቅር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይሖዋ ያወጣው ዘላለማዊ ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ለፍጥረቶቹ በታማኝነት ፍቅር ማሳየቱን ይቀጥላል። እንዲህ ያለውን ፍቅር በአድናቆት አትመለከተውም?
ይሖዋ ለቁጣ የዘገየና ስህተቶቻችንን ይቅር ለማለት የፈጠነ ነው። ስህተት ከሚፈላልግ ሰው ጋር ሳይሆን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ከሆነ ሰው ጋር መቀራረብ ያስደስታል። ያ ማለት ግን ይሖዋ ጥፋትን ችላ ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። “እኔ እግዚአብሔር ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 61:8) የፍትሕ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በክፋታቸው የሚቀጥሉ እምቢተኛ ኃጢአተኞችን ለዘላለም አይታገሥም። ስለዚህ ይሖዋ በራሱ ጊዜ በዓለማችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እንደሚያስወግድ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
ፍቅርንና ፍትሕን ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማንጸባረቅ ጥበብ ሮሜ 11:33-36) የፈጣሪን ጥበብ በማንኛውም ቦታ ለማየት ይቻላል። ዕጹብ ድንቅ የሆነው ተፈጥሮ ለዚህ ምሥክር ነው።—መዝሙር 104:24፤ ምሳሌ 3:19
ይጠይቃል። ይሖዋ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እነዚህን ሁለት ባሕርያት ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምባቸዋል። (ይሁን እንጂ ጥበብ ያለው መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም። ፈጣሪ በአእምሮው ውስጥ ያለውን ነገር ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ የተሟላ ኃይልም ሊኖረው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ እንዲህ ያለ ኃይል ያለው አምላክ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ፣ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ . . . በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።” (ኢሳይያስ 40:26) አዎን፣ ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስችል ‘ከፍተኛ ኃይል’ አለው። እንደነዚህ ያሉት ባሕርያት ወደ ይሖዋ እንድትሳብ አያደርጉህም?
ይሖዋን ማወቅ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
ይሖዋ ‘ምድርን የፈጠረው’ ከእርሱ ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና ላላቸው ሰዎች ‘መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ’ አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18፤ ዘፍጥረት 1:28) ለምድራዊ ፍጥረታቱ ያስባል። የሰው ዘር አትክልት በሞላበት ገነት ውስጥ ፍጹም በሆነ መንገድ መኖር እንዲጀምር አደረገ። ሆኖም ሰዎች ምድርን በማበላሸት ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ ይሖዋን ያሳዝነዋል። ቢሆንም ይሖዋ ከስሙ ጋር በሚስማማ መንገድ ለሰውና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር ያደርሳል። (መዝሙር 115:16፤ ራእይ 11:18) ልጆቹ በመሆን እርሱን ለመታዘዝ ለሚፈልጉ ሁሉ ምድርን መልሶ ገነት ያደርጋታል።—ምሳሌ 8:17፤ ማቴዎስ 5:5
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በዚህ ገነት ውስጥ ልታገኝ የምትችለውን ሕይወት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) ይሖዋ እንድታገኝ የሚፈልገው እውነተኛ ሕይወት እንዲህ ያለውን ነው። እንዴት ያለ ደግ አባት ነው! ስለ እርሱ ይበልጥ ለማወቅና በገነት ውስጥ ለመኖር ምን ነገር ማድረግ እንደሚጠበቅብህ ለመማር ፈቃደኛ ነህ?
ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች በሙሉ ከ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም የተወሰዱ ናቸው። ከጥቅስ ቀጥሎ “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።