ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:1-22
א [አሌፍ]
2 ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ በቁጣው ደመና እንዴት ሸፈናት!
የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጥሏል።+
በቁጣው ቀን የእግሩን ማሳረፊያ አላስታወሰም።+
ב [ቤት]
2 ይሖዋ የያዕቆብን መኖሪያዎች በሙሉ ያላንዳች ርኅራኄ ውጧል።
የይሁዳን ሴት ልጅ የተመሸጉ ቦታዎች በቁጣው አፈራርሷል።+
መንግሥቱንና መኳንንቷን ወደ መሬት ጥሏል፤ ደግሞም አርክሷል።+
ג [ጊሜል]
3 የእስራኤልን ብርታት* ሁሉ በታላቅ ቁጣ ቆረጠ።
ጠላት በቀረበ ጊዜ እሱ ቀኝ እጁን መለሰ፤+በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳትም ቁጣው በያዕቆብ ላይ ነደደ።+
ד [ዳሌት]
4 እንደ ጠላት ደጋኑን ወጠረ፤* ቀኝ እጁም እንደ ባላጋራ ተዘጋጀች፤+ለዓይን የሚማርኩትን ሁሉ ገደለ።+
በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳንም ላይ+ ቁጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።+
ה [ሄ]
5 ይሖዋ እንደ ጠላት ሆነ፤+እስራኤልን ዋጠ።
ማማዎቿን ሁሉ ዋጠ፤የተመሸጉ ስፍራዎቿን ሁሉ አወደመ።
በይሁዳ ሴት ልጅ ዘንድ ለቅሶንና ዋይታን አበዛ።
ו [ዋው]
6 የራሱን ዳስ በአትክልት ቦታ እንዳለች ጎጆ አፈረሰ።+
በዓሉ እንዲያከትም* አደረገ።+
ይሖዋ በጽዮን፣ በዓልና ሰንበት እንዲረሳ አድርጓል፤በኃይለኛ ቁጣውም ንጉሡንና ካህኑን አቃሏል።+
ז [ዛየን]
7 ይሖዋ መሠዊያውን ናቀ፤መቅደሱን ተወ።+
የማይደፈሩ ማማዎቿን ግንቦች ለጠላት አሳልፎ ሰጠ።+
በበዓል ቀን እንደሚደረገው ሁሉ በይሖዋ ቤት በታላቅ ድምፅ ጮኹ።+
ח [ኼት]
8 ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ለማፍረስ ቆርጧል።+
የመለኪያ ገመዱን ዘርግቷል።+
ከማጥፋትም እጁን አልመለሰም።
የመከላከያ ግንቡና ቅጥሩ እንዲያዝኑ አደረገ።
በአንድነትም ደከሙ።
ט [ቴት]
9 በሮቿ ወደ መሬት ሰጠሙ።+
መቀርቀሪያዎቿን አስወገደ፤ ደግሞም ሰባበረ።
ንጉሥዋና መኳንንቷ በብሔራት መካከል ናቸው።+
ሕግ* የለም፤ ነቢያቷም እንኳ ከይሖዋ የተገለጠላቸው ራእይ የለም።+
י [ዮድ]
10 የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው መሬት ላይ ይቀመጣሉ።+
በራሳቸው ላይ አቧራ ይነሰንሳሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ።+
የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ መሬት ደፍተዋል።
כ [ካፍ]
11 ከማልቀሴ ብዛት ዓይኖቼ ፈዘዙ።+
አንጀቴ ተላወሰ።
በሕዝቤ ሴት ልጅ* ላይ ከደረሰው ውድቀት+እንዲሁም በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ከወደቁት ልጆችና ሕፃናት+ የተነሳ ጉበቴ መሬት ላይ ፈሰሰ።
ל [ላሜድ]
12 ልክ እንደቆሰለ ሰው በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ሲወድቁና
በእናቶቻቸው ጉያ ሆነው ለመሞት ሲያጣጥሩ፣*እናቶቻቸውን “እህልና የወይን ጠጅ የት አለ?” ብለው ይጠይቃሉ።+
מ [ሜም]
13 የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ ምሥክር የሚሆን ምን ነገር ላቀርብልሽ እችላለሁ?ከምንስ ጋር ላመሳስልሽ እችላለሁ?
ድንግሊቱ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አጽናናሽ ዘንድ ከማን ጋር ላወዳድርሽ እችላለሁ?
የደረሰብሽ ጥፋት እንደ ባሕር ሰፊ ነውና።+ ማን ሊፈውስሽ ይችላል?+
נ [ኑን]
14 ነቢያትሽ ያዩልሽ ራእይ ሐሰትና ከንቱ ነው፤+ተማርከሽ እንዳትወሰጂ ለማድረግ በደልሽን አላጋለጡም፤+ይልቁንም ራእይ ተገለጠልን እያሉ ሐሰትና አሳሳች ቃል ይነግሩሻል።+
ס [ሳሜኽ]
15 በመንገድ የሚያልፉ ሁሉ በማሾፍ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል።+
“‘ፍጹም ውበት የተላበሰችና የምድር ሁሉ ደስታ’+ በማለት ይጠሯት የነበረችው ከተማ ይህች ናት?” እያሉ በመገረም
በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፏጫሉ፤+ ራሳቸውንም ይነቀንቃሉ።
פ [ፔ]
16 ጠላቶችሽ ሁሉ በአንቺ ላይ አፋቸውን ከፍተዋል።
እነሱ ያፏጫሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ፤
ደግሞም “ዋጥናት።+ ስንጠብቀው የነበረው ቀን ይህ ነው!+ ጊዜው ደርሶ ለማየት በቃን!”+ ይላሉ።
ע [አይን]
17 ይሖዋ ያሰበውን አድርጓል፤+የተናገረውን፣ ከጥንትም ጀምሮ ያዘዘውን+ ፈጽሟል።+
ያላንዳች ርኅራኄ አፍርሷል።+
ጠላት በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ደስ እንዲሰኝ፣ የባላጋራዎችሽም ብርታት* ከፍ ከፍ እንዲል አድርጓል።
צ [ጻዴ]
18 የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፣ ልባቸው ወደ ይሖዋ ይጮኻል።
እንባሽ እንደ ጅረት ቀን ከሌት ይፍሰስ።
ለራስሽ ፋታ አትስጪ፤ ዓይንሽ እንባ ማፍሰሱን አያቋርጥ።*
ק [ኮፍ]
19 ተነሺ! ሌሊት፣ ክፍለ ሌሊቶቹ ሲጀምሩ ጩኺ።
በይሖዋ ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ።
በረሃብ ምክንያት በየመንገዱ ማዕዘን* ተዝለፍልፈው ለወደቁት+ ልጆችሽ ሕይወት* ስትዪ፣እጆችሽን ወደ እሱ ዘርጊ።
ר [ረሽ]
20 ይሖዋ ሆይ፣ ክፉኛ የቀጣኸውን እይ፤ ደግሞም ተመልከት።
ሴቶች የሆዳቸውን ፍሬ፣ የገዛ ራሳቸውን ልጆች* ይብሉ?+ደግሞስ ካህናቱና ነቢያቱ በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ይገደሉ?+
ש [ሺን]
21 ወንድ ልጅና ሽማግሌ ሞተው በየመንገዱ ተዘርረዋል።+
ደናግሌና* ወጣት ወንዶቼ በሰይፍ ወድቀዋል።+
በቁጣህ ቀን ገደልክ፤ ያላንዳች ርኅራኄ አረድክ።+
ת [ታው]
22 በበዓል ቀን እንደሚደረገው ሁሉ+ ሽብርን ከየአቅጣጫው ጠራህ።
በይሖዋ የቁጣ ቀን ያመለጠም ሆነ በሕይወት የተረፈ የለም፤+የወለድኳቸውንና* ያሳደግኳቸውን ልጆች ጠላቴ ፈጃቸው።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ቀንድ።”
^ ቃል በቃል “ረገጠ።”
^ ወይም “እንዲጠፋ።”
^ ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
^ በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ነፍሳቸው ስታጣጥር።”
^ ቃል በቃል “ቀንድ።”
^ ቃል በቃል “የዓይንሽ ሴት ልጅ እንባ ማፍሰሷን አታቋርጥ።”
^ ቃል በቃል “በጎዳና ሁሉ ራስ ላይ።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “የገዛ ራሳቸውን ጤናማ ልጆች።”
^ ወይም “ወጣት ሴቶቼና።”
^ ወይም “ጤናማ ሆነው የወለድኳቸውንና።”