ዘኁልቁ 12:1-16

  • ሚርያምና አሮን ሙሴን ነቀፉት (1-3)

    • ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገር ነበር (3)

  • ይሖዋ ለሙሴ ተሟገተለት (4-8)

  • ሚርያም በሥጋ ደዌ ተመታች (9-16)

12  ሙሴ ኩሻዊት ሴት አግብቶ ስለነበር ባገባት ኩሻዊት ሴት+ የተነሳ ሚርያምና አሮን ይነቅፉት ጀመር።  እነሱም “ለመሆኑ ይሖዋ የሚናገረው በሙሴ አማካኝነት ብቻ ነው? በእኛስ በኩል አልተናገረም?”+ ይሉ ነበር። ይሖዋም ይህን ይሰማ ነበር።+  ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር።*+  ይሖዋም ድንገት ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን “ሦስታችሁም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ውጡ” አላቸው። በመሆኑም ሦስቱም ወጡ።  ይሖዋም በደመና ዓምድ ወርዶ+ በድንኳኑ መግቢያ ላይ በመቆም አሮንንና ሚርያምን ጠራቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ።  እሱም እንዲህ አለ፦ “እባካችሁ ቃሌን ስሙ። አንድ የይሖዋ ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር በራእይ አማካኝነት+ ራሴን አሳውቀው በሕልምም+ አነጋግረው ነበር።  አገልጋዬን ሙሴን በተመለከተ ግን እንዲህ አይደለም! እሱ በቤቴ ሁሉ ላይ አደራ የተጣለበት* ሰው ነው።+  እኔ እሱን የማነጋግረው ፊት ለፊት*+ በግልጽ እንጂ በእንቆቅልሽ አይደለም፤ እሱም የይሖዋን አምሳል ያያል። ታዲያ አገልጋዬን ሙሴን ስትነቅፉት ምነው አልፈራችሁም?”  በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በእነሱ ላይ ነደደ፤ ትቷቸውም ሄደ። 10  ከዚያም ደመናው ከድንኳኑ ላይ ተነሳ፤ በዚህ ጊዜ ሚርያም በሥጋ ደዌ ተመታ እንደ በረዶ ነጭ ሆና ነበር።+ አሮንም ወደ ሚርያም ዞር ሲል በሥጋ ደዌ ተመታ አየ።+ 11  አሮንም ወዲያውኑ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይቅርታ አድርግልኝ ጌታዬ! እባክህ ይህን ኃጢአት አትቁጠርብን! የፈጸምነው የሞኝነት ድርጊት ነው። 12  እባክህ፣ ግማሽ አካሉ ተበልቶ የተወለደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ!” 13  ሙሴም “አምላክ ሆይ፣ እባክህ ፈውሳት! እባክህ!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ።+ 14  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አባቷ ፊቷ ላይ ቢተፋባት ለሰባት ቀን ተዋርዳ ትቆይ አልነበረም? አሁንም ከሰፈር ውጭ ለሰባት ቀን ተገልላ እንድትቆይ ይደረግ፤+ ከዚያ በኋላ እንድትመለስ ማድረግ ይቻላል።” 15  ስለዚህ ሚርያም ለሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጭ ተገልላ እንድትቆይ ተደረገ፤+ ሕዝቡም ሚርያም ተመልሳ እንድትቀላቀል እስኪደረግ ድረስ ጉዞውን አልቀጠለም። 16  ከዚያም ሕዝቡ ከሃጼሮት+ ተነስቶ በፋራን ምድረ በዳ+ ሰፈረ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሙሴ ከማንኛውም ሰው ይልቅ በጣም ትሑት (ገር) ነበር።”
ቃል በቃል “ታማኝ መሆኑን ያስመሠከረ።”
ቃል በቃል “አፍ ለአፍ።”