ሁለተኛ ዜና መዋዕል 11:1-23

  • የሮብዓም አገዛዝ (1-12)

  • ታማኝ የሆኑ ሌዋውያን ወደ ይሁዳ መጡ (13-17)

  • የሮብዓም ቤተሰብ (18-23)

11  ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ተዋግተው መንግሥቱን ለሮብዓም እንዲያስመልሱ ከይሁዳ ቤትና ከቢንያም ነገድ+ የተውጣጡ 180,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎች* ወዲያውኑ ሰበሰበ።+  ከዚያም የይሖዋ ቃል የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደሆነው ወደ ሸማያህ+ እንዲህ ሲል መጣ፦  “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲሁም በይሁዳና በቢንያም ላሉት እስራኤላውያን ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦  ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከወንድሞቻችሁ ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”’”+ ስለዚህ የይሖዋን ቃል ሰምተው ተመለሱ፤ በኢዮርብዓምም ላይ አልዘመቱም።  ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ገነባ።  ቤተልሔምን፣+ ኤጣምን፣ ተቆአን፣+  ቤትጹርን፣ ሶኮን፣+ አዱላምን፣+  ጌትን፣+ ማሬሻህን፣ ዚፍን፣+  አዶራይምን፣ ለኪሶን፣+ አዜቃን፣+ 10  ጾራን፣ አይሎንንና+ ኬብሮንን+ ገነባ፤* እነዚህ በይሁዳና በቢንያም የነበሩ የተመሸጉ ከተሞች ናቸው። 11  በተጨማሪም የተመሸጉትን ከተሞች አጠናከረ፤ በከተሞቹም ላይ አዛዦችን ሾመ፤ በእነዚህ ከተሞች ምግብ፣ ዘይትና የወይን ጠጅ አከማቸ፤ 12  በከተሞቹም ሁሉ ትላልቅ ጋሻዎችና ጦር አስቀመጠ፤ ከተሞቹንም እጅግ አጠናከራቸው። ይሁዳንና ቢንያምንም መግዛቱን ቀጠለ። 13  በመላው እስራኤል ያሉት ካህናትና ሌዋውያንም የነበሩበትን ክልል በሙሉ ለቀው በመሄድ ከእሱ ጎን ቆሙ። 14  ሌዋውያኑ የይሖዋ ካህናት ሆነው እንዳያገለግሉ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አባረዋቸው ስለነበር+ የግጦሽ መሬታቸውንና ርስታቸውን+ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። 15  በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች፣ ፍየል ለሚመስሉት አጋንንትና*+ ለሠራቸው የጥጃ ምስሎች+ የራሱን ካህናት ሾመ።+ 16  የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለመፈለግ ከልባቸው ቆርጠው የተነሱ ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች ለአባቶቻቸው አምላክ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+ 17  ለሦስት ዓመት በዳዊትና በሰለሞን መንገድ ይመላለሱ ስለነበር በእነዚህ ሦስት ዓመታት የይሁዳን መንግሥት አጠናከሩ፤ ደግሞም ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም ድጋፍ ሰጡ። 18  ከዚያም ሮብዓም የዳዊት ልጅ የሆነውን የየሪሞትን ሴት ልጅ ማሃላትን አገባ። ማሃላት የእሴይ ልጅ፣ የኤልያብ+ ሴት ልጅ የሆነችው የአቢሃይል ልጅ ነበረች። 19  ከጊዜ በኋላም የኡሽ፣ ሸማርያህ እና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20  ከእሷ በኋላ የአቢሴሎም+ የልጅ ልጅ የሆነችውን ማአካን አገባ። እሷም አቢያህን፣+ አታይን፣ ዚዛን እና ሸሎሚትን ወለደችለት። 21  ሮብዓም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ የሆነችውን ማአካን ከሌሎቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ሁሉ+ አስበልጦ ይወዳት ነበር፤ እሱም 18 ሚስቶችና 60 ቁባቶች ነበሩት፤ ደግሞም 28 ወንዶች ልጆችና 60 ሴቶች ልጆች ወለደ። 22  ሮብዓምም የማአካን ልጅ አቢያህን ሊያነግሠው ስለፈለገ በወንድሞቹ ላይ ራስና መሪ አድርጎ ሾመው። 23  ይሁን እንጂ ማስተዋል የታከለበት እርምጃ በመውሰድ ከወንዶች ልጆቹ መካከል አንዳንዶቹን በይሁዳና በቢንያም ምድር ሁሉ ወደሚገኙት ወደተመሸጉት ከተሞች+ ሁሉ ላካቸው፤* የሚያስፈልጓቸውንም ነገሮች በብዛት ሰጣቸው፤ ብዙ ሚስቶችም አጋባቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የተመረጡ ተዋጊዎች።”
ወይም “አጠናከረ።”
ቃል በቃል “ለፍየሎችና።”
ወይም “ወደተመሸጉት ከተሞች ሁሉ በተናቸው።”