ሁለተኛ ዜና መዋዕል 8:1-18

  • ሰለሞን ያከናወናቸው ሌሎች የግንባታ ሥራዎች (1-11)

  • በሥርዓቱ መሠረት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚከናወነው አምልኮ (12-16)

  • የሰለሞን መርከቦች (17, 18)

8  ሰለሞን የይሖዋን ቤትና የራሱን ቤት* ገንብቶ በጨረሰበት በ20ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ+  ኪራም+ የሰጠውን ከተሞች መልሶ ገነባቸው፤ እስራኤላውያንንም በዚያ አሰፈረ።  በተጨማሪም ሰለሞን በሃማትጾባ ላይ ዘምቶ ያዛት።  ከዚያም በምድረ በዳ የምትገኘውን ታድሞርንና በሃማት+ የሠራቸውን የማከማቻ ከተሞች ሁሉ ገነባ።*+  ደግሞም ቅጥሮች፣ በሮችና መቀርቀሪያዎች ያሏቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ይኸውም ላይኛውን ቤትሆሮንንና+ ታችኛውን ቤትሆሮንን+ ገነባ፤  በተጨማሪም ባዓላትን፣+ የሰለሞንን የእህልና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች በሙሉ፣ የሠረገላ ከተሞቹን በሙሉ፣+ የፈረሰኞቹን ከተሞች እንዲሁም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በእሱ ግዛት ውስጥ ባለው ምድር ሁሉ መገንባት የፈለጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሠራ።  ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን+ ከሂታውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከሂዋውያንና ከኢያቡሳውያን+ የተረፉትን ሕዝቦች በሙሉ፣  ይኸውም እስራኤላውያን ፈጽመው ያላጠፏቸውን+ በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ዘሮቻቸውን ሰለሞን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ መለመላቸው፤+ እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ።  ሆኖም ሰለሞን ለሚያከናውነው ሥራ ከእስራኤላውያን መካከል አንዳቸውንም ባሪያ አላደረገም፤+ ምክንያቱም እነሱ ተዋጊዎቹ፣ የጦር መኮንኖቹ፣ የሠረገለኞቹና የፈረሰኞቹ አለቆች ነበሩ።+ 10  በሠራተኞቹ ላይ የተሾሙት ይኸውም የንጉሥ ሰለሞን የበታች ተቆጣጣሪዎቹ አለቆች+ 250 ነበሩ። 11  በተጨማሪም ሰለሞን የፈርዖንን ሴት ልጅ+ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ ወደሠራላት ቤት አመጣት፤+ ይህን ያደረገው “እሷ ሚስቴ ብትሆንም የይሖዋ ታቦት የገባባቸው ቦታዎች ቅዱስ ስለሆኑ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት ልትኖር አይገባም” በማለት ነበር።+ 12  ከዚያም ሰለሞን ከበረንዳው+ ፊት ለፊት በሠራው የይሖዋ መሠዊያ+ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለይሖዋ አቀረበ።+ 13  ለሙሴ ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በሥርዓቱ መሠረት በየዕለቱ ሊቀርቡ የሚገባቸውን መባዎች ማለትም የየሰንበቱን፣+ የየወሩን መባቻና+ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚደረጉትን የተወሰኑትን በዓላት+ ይኸውም የቂጣን* በዓል፣+ የሳምንታትን በዓልና+ የዳስን* በዓል+ መባዎች አቀረበ። 14  በተጨማሪም አባቱ ዳዊት ባወጣው ደንብ መሠረት ካህናቱን በየአገልግሎት ምድባቸው፣+ ሌዋውያኑንም በየዕለቱ ሊከናወን በሚገባው ሥርዓት መሠረት ካህናቱ ባሉበት አምላክን እንዲያወድሱና+ እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ስፍራ ላይ ሾማቸው፤ በር ጠባቂዎቹንም በተለያዩ በሮች ላይ በየቡድናቸው መደባቸው፤+ የእውነተኛው አምላክ ሰው ዳዊት ይህን ትእዛዝ አስተላልፎ ነበርና። 15  እነሱም ንጉሡ ማንኛውንም ጉዳይ ወይም ግምጃ ቤቶቹን በተመለከተ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ከሰጠው ትእዛዝ ፈቀቅ አላሉም። 16  በመሆኑም የይሖዋ ቤት መሠረቱ ከተጣለበት ጊዜ+ አንስቶ ሥራው እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ሰለሞን የሠራው ሥራ ሁሉ በሚገባ የተደራጀ* ነበር። የይሖዋም ቤት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ።+ 17  ከዚያም ሰለሞን በኤዶም ምድር+ በባሕሩ ዳርቻ ወደሚገኙት ወደ ዔጽዮንጋብርና+ ወደ ኤሎት+ ሄደ። 18  ኪራም+ በአገልጋዮቹ አማካኝነት መርከቦችንና ልምድ ያላቸው ባሕረኞችን ላከለት። እነሱም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር ወደ ኦፊር+ በመሄድ 450 ታላንት* ወርቅ+ አምጥተው ለንጉሥ ሰለሞን ሰጡት።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “መልሶ ገነባ።”
ወይም “የጊዜያዊ መጠለያን።”
ወይም “ሥርዓታማ፤ የተሟላ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።