በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት—ዓለም አቀፍ ችግር

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት—ዓለም አቀፍ ችግር

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት—ዓለም አቀፍ ችግር

በዓለም ዙሪያ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስወገድ ኅዳር 25 ቀን ተከብሮ ይውላል። ሴቶች መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ ሲባል ይህ ቀን እንዲከበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀው በ1999 ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰድ ለምን አስፈለገ?

በብዙ ባሕሎች ሴቶች ዝቅ ተደርገው ይታያሉ፤ እንዲሁም የወንዶች የበታች እንደሆኑ ይቆጠራሉ። የሚደርስባቸው በደልም ሥር የሰደደ ነው። የበለጸጉ በሚባሉት አገሮችም እንኳ ሳይቀር በሴቶች ላይ በማንኛውም መልኩ የሚደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን እንደተናገሩት “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ችግር ከመሆኑም በላይ በሁሉም ማኅበረሰቦችና ባሕሎች ውስጥ ያለ ነገር ነው። ሴቶች ዘራቸው፣ ጎሣቸውና ትውልዳቸው ምንም ይሁን ምን አሊያም ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ይምጡ ወይም ምንም ዓይነት ቦታ ይኑራቸው ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።”

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባልደረባና በሴቶች ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት የቀድሞ ሪፖርተር የሆኑት ራዲካ ኩማራስዋሚ እንደገለጹት አብዛኞቹ ሴቶች የሚፈጸምባቸውን ጥቃት “ሊነገር የማይገባው ነውርና በኅብረተሰቡ ውስጥ የተደበቀ አሳፋሪ የሕይወት ገጽታ” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በሆላንድ የሚገኝ አንድ ድርጅት ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በአንድ የደቡብ አሜሪካ አገር 23 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ወይም ከአራት ሴቶች አንዷ በቤት ውስጥ በሆነ መልኩ ጥቃት ይፈጸምባታል። በተመሳሳይም የአውሮፓ ምክር ቤት፣ ከአራት የአውሮፓ ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ በቤት ውስጥ ጥቃት እንደሚደርስባት ገምቷል። የብሪታንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ አስተዳደር እንደገለጸው በእንግሊዝና በዌልስ በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ በየሳምንቱ በአማካይ ሁለት ሴቶች አሁን አብሯቸው በሚኖረው ወይም በቀድሞው የትዳር አጋራቸው ተገድለዋል። ኢንዲያ ቱዴይ ኢንተርናሽናል የተሰኘ መጽሔት እንደገለጸው “በመላው ሕንድ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ፍርሃት የዘወትር ጓደኛቸው ሲሆን ተገድዶ መደፈር ደግሞ በማንኛውም ጎዳና ላይ፣ በየትኛውም የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ፣ በማንኛውም ሰዓት ወይም የትም ቦታ ሊያጋጥማቸው የሚችል ነገር ነው።” አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት “በስፋት የተዛመተ [የዘመናችን] የሰብዓዊ መብት ፈተና” በማለት ገልጾታል።

ከላይ የተጠቀሱት አኃዛዊ መረጃዎች አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃሉ? ይህን ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንወያይበታለን።