በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሻንጉሊቶች ኦፔራ የሚያቀርቡበት ቦታ

አሻንጉሊቶች ኦፔራ የሚያቀርቡበት ቦታ

አሻንጉሊቶች ኦፔራ የሚያቀርቡበት ቦታ

ኦስትሪያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“አዎን፣ ሙዚቃው በጣም ደስ ይል ነበር፤ ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ግን በአሻንጉሊቶች በመጠቀም ትርዒት የማሳየቱ ጥበብ ነበር። በተለያዩ የሰውነታቸው ክፍሎች ላይ የታሰሩ ሲባጎዎችን በመሳብ እንዲንቀሳቀሱ የሚደረጉት አሻንጉሊቶች፣ ከዚህ ቀደም ካየሁት እንዲህ ዓይነት ትርዒት ሁሉ ይበልጥ የተወሳሰቡ እንቅስቃሴዎችን ያሳዩ ነበር!”

ይህን የተናገረችው ሴት የገለጸችው ለትንንሽ ልጆች ስለተዘጋጀ የአሻንጉሊቶች ትርዒት ነው? አይደለም። ለማመን ሊከብድህ ቢችልም፣ በአድናቆት እንደዚያ ብላ የተናገረችው ኦፔራ ለማየት የሄደች ትልቅ ሴት ናት። ይህ አስደናቂ ኦፔራ የቀረበው የት ነው? የዝነኛው የሙዚቃ ደራሲ የሞዛርት የትውልድ ከተማ በሆነችው በሳልዝበርግ፣ ኦስትሪያ በሚገኝ በጣም ለየት ያለ ኦፔራ ማሳያ ውስጥ ነበር።

ለመሆኑ ከግማሽ ሜትር እስከ አንድ ሜትር የሚደርስ ርዝማኔ ያላቸው ከእንጨት የተሠሩ አሻንጉሊቶች ኦፔራ እንደሚያቀርቡ ሰምተህ ታውቃለህ? በሳልዝበርግ ከተማ በሚገኘው የአሻንጉሊቶች ቲያትር ቤት እንዲህ ዓይነት ትርዒት ይቀርባል። አሻንጉሊቶቹ በመድረክ ላይ መጨፈር ሲጀምሩና ማራኪ የሆነው ሙዚቃ ሲደመጥ፣ ተመልካቹ በደስታ ተውጦ ያለበትን ዓለም በመርሳት ወደ ምናባዊው ዓለም መጓዙ አይቀርም።

የገሐዱና የምናባዊው ዓለም መቀላቀል

ኦርኬስትራው የሙዚቃ ተውኔቱን መክፈቻ መጫወት ሲጀምርና የመጀመሪያውን ትርዒት ለማቅረብ መጋረጃው ሲገለጥ አንዳንድ ጊዜ ተመልካቹ በሚያየው ነገር በጣም ይገረማል። እነዚያ በመድረኩ ላይ የሚውረገረጉትና ኦፔራ የሚጫወቱ ይመስል ሰውነታቸውን የሚያንቀሳቅሱት በእርግጥ ከእንጨት የተሠሩ አሻንጉሊቶች ናቸው? ከአሻንጉሊቶቹ አናት በላይ የሚታዩት እነዚያ ሁሉ ቀጫጭን ሲባጎዎችስ ምንድን ናቸው? አንዳንድ ተመልካቾች ሁኔታው እንደጠበቁት ሳይሆን በመቅረቱ ተበሳጭተው ‘ምነው ሁሉንም ነገር ወለል ብሎ እንዲታይ አደረጉት!’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ከዚህም በላይ ሙዚቀኞቹና ኦርኬስትራው አይታዩም። ቀደም ብሎ የተቀዳ የኦፔራ ሙዚቃ ማዳመጥ የሚለው ነገር ለተመልካቹ ላይጥመው ይችላል። አዘውትሮ ኦፔራ የሚመለከት ሰው በንዴት በግኖ ‘እንዴት ያበሳጫል!’ ብሎ ያስብ ይሆናል። ቆይ እስቲ አንዴ! ተመልካቹ፣ ቀስ በቀስ እንዲያውም ሳይታወቀው አመለካከቱ እየተለወጠ ነው።

ተመልካቹ መጀመሪያ ላይ የተሰማውን ጥርጣሬ ካሸነፈ በኋላ በሲባጎ የሚንቀሳቀሱት አሻንጉሊቶች በሚያሳዩት ማራኪ ትርዒት መመሰጥ ይጀምራል። ከዚያም የገሐዱና የምናባዊው ዓለም አስደናቂ በሆነ መንገድ መቀላቀል ይጀምራሉ። ለአሻንጉሊቶቹ ሕይወት የሰጧቸው የሐር ሲባጎዎች መኖራቸውም እንኳ ይረሳል። ተመልካቹ አሻንጉሊቶቹ በሚያቀርቡት ትርዒት በጣም ከመደሰቱም በላይ አሻንጉሊቶች በአነስተኛ ኦፔራ መድረክ ላይ ትርዒት እንዲያቀርቡ ለማድረግ መታሰቡ ራሱ ያስገርመዋል። ብዙም ሳይቆይ ትርዒቱ እንደ እንግዳ ነገር መታየቱ ይቀራል፤ ተመልካቹም ሕይወት የሌላቸው አሻንጉሊቶች እያየ መሆኑን ይረሳዋል። በእርግጥም፣ አሻንጉሊቶቹ ተጠራጣሪ የሆኑ ተመልካቾችን እንኳ ሳይቀር ወደራሳቸው ትንሽ ዓለም በማስገባት የማዝናናት አስገራሚ ችሎታ አላቸው።

በመድረክ ላይና ከመድረክ በስተጀርባ

ከመድረክ በስተጀርባ ያለው እንቅስቃሴም በመድረኩ ላይ የሚታየውን ያህል አስገራሚ ነው ማለት ይቻላል። እውነተኛዎቹ ተዋናዮች ከመድረኩ በስተጀርባ ወይም ይበልጥ በትክክል ለመግለጽ፣ ከመድረኩ አናት ላይ በተሠራ ድልድይ ላይ ሆነው አሻንጉሊቶቹን የሚያንቀሳቅሷቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የምልክት ቋንቋ የሚናገሩ ይመስል እጆቻቸውን ወዲያ ወዲህ እያወናጨፉ አሻንጉሊቶቹን ሰውነታቸው ላይ በታሰረው ሲባጎ አማካኝነት በማንቀሳቀስ፣ ልክ እንደ እውነተኛ የኦፔራ ተጫዋቾች እንዲዘፍኑ፣ እንዲያለቅሱ፣ የጦር መሣሪያ ይዘው እንዲዋጉ ወይም እጅ እንዲነሱ ያደርጓቸዋል።

በአንድ ወቅት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ይህን የኪነ ጥበብ ዘርፍ በጣም አስደናቂ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሲያብራራ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከመድረኩ በስተጀርባ የሚሆኑት ሰዎች ዕድሜም ሆነ ጾታ ሳይገድባቸው የፈለጉትን ክፍል መጫወት ይችላሉ፤ የሚጠበቅባቸው ብቃት ከፍተኛ ችሎታ ብቻ ነው።” በሳልዝበርግ፣ አሻንጉሊቶችን በሲባጎ እያንቀሳቀሱ የሚያጫውቱት ሰዎች በአሻንጉሊቶቹ ላይ ሕይወት ለመዝራት የሚጠቀሙበት ጥበብ በእርግጥም በጣም አስገራሚ ነው።

በድን የሆኑ ምስሎችን በሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች መተካት

የሳልዝበርጉ በሲባጎ የሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች ቲያትር ቤት፣ በ1913 ከሞዛርት ኦፔራዎች አንዱን ለመጀመሪያ ጊዜ ካቀረበበት ወቅት አንስቶ ከ90 ለሚበልጡ ዓመታት ስኬታማ ሆኖ ቆይቷል። የቲያትር ቤቱ መሥራች የቅርጻ ቅርጽ ባለሞያ የነበረው አንቶን አይከር ነው። አይከር የሞያ ሥልጠና ጊዜውን በሙኒክ የሠራ ሲሆን ከዚያም በገሐዱ ዓለም ያሉ ሰዎች የሚያደርጉትን የሚመስል አስደናቂ እንቅስቃሴ ማሳየት የሚችሉ በሲባጎ የሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶችን ሠራ። አይከር መንቀሳቀስ የማይችሉ ምስሎችን ከመቅረጽ ይልቅ በሲባጎ በሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች መሥራት ይበልጥ አስደሳች እንደሆነ አስተዋለ።

ብዙም ሳይቆይ የአይከር ቤተሰብም እንዲህ ያለው መዝናኛ በጣም አስደሰታቸው። ቤተሰቡ በሲባጎ ለሚንቀሳቀሱት አሻንጉሊቶች ልብስ በመስፋት የረዱት ከመሆኑም ሌላ በሙዚቃና በንግግር የሚቀርቡ ክፍሎችን በመጫወትም በደስታ እገዛ አድርገውለታል። በጣም ስኬታማ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙም ሳይቆይ አዳዲስ የሙዚቃ ትርዒቶችን ማዘጋጀት ጀመሩ። ከ1927 ጀምሮ በሌሎች አገሮችም ትርዒታቸውን እንዲያቀርቡ በክብር እንግድነት ይጋበዙ ጀመር። ዛሬም ቢሆን እነዚህ አሻንጉሊቶች እንደ ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉት በርካታ አገሮች አዘውትረው ትርዒት ያሳያሉ። በየትኛውም ባሕል ቢሆን ሕዝቡ በሲባጎ በሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች የሚቀርበውን መዝናኛ ይወደዋል።

እንዲህ ዓይነቱን መዝናኛ ትወደዋለህ?

ኦፔራ የሚለው ቃል “ብዙውን ጊዜ የተውኔት አልባሳት የለበሱ ዘፋኞች በመሣሪያ በመታጀብ የሚያቀርቡት የሙዚቃ ድራማ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በኦፔራ ላይ የሚዘፈኑት ዘፈኖች ሐሳብ ወይም ጽሑፉ በአፈ ታሪክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ በታሪክና በልብ ወለድ ላይ የተመሠረተ ነው። የጽሑፉ ይዘት አሳዛኝ፣ አስቂኝ ወይም የፍቅር ታሪክ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ከላይ በተጠቀሰው የአሻንጉሊቶች ቲያትር ቤት ውስጥ ትርዒቶቹ የሚቀርቡት በጀርመንኛ ወይም በጣሊያንኛ ነው። ስለዚህ በዝግጅቱ እንደምትደሰት ለማወቅ ተተርጉሞ የቀረበውን መግለጫ አስቀድሞ መመልከቱ ጥበብ ነው።

ታዲያ አንድ ክርስቲያን አንድ ኦፔራ ሊያየው የሚገባ መሆን አለመሆኑን ሊወስን የሚችለው እንዴት ነው? በዘፋኞቹ ዝና ወይም ደግሞ በሙዚቃው ውበት ላይ ብቻ ተመሥርቶ መወሰን ይኖርበታል? ወይስ የኦፔራውን ጭብጥ ከግምት ማስገባት አለበት?

አንድ ክርስቲያን በሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች ረገድ እንደሚያደርገው ሁሉ አንድን ኦፔራ ማዳመጥ ያለበት መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ የኦፔራውን መግለጫ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰጠው መመዘኛ ጋር ማስተያየት ነው:- “በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኦስትሪያ

ቪየና

ሳልዝበርግ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሻንጉሊቶቹ ተዋናዮች በተለያዩ ኦፔራዎች ላይ ለመቅረብ ዝግጁ ናቸው

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሳልዝበርጉ በሲባጎ የሚንቀሳቀሱ አሻንጉሊቶች ቲያትር ቤት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሥራቹ፣ አንቶን አይከር

[ምንጭ]

By courtesy of the Salzburg Marionette Theatre

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኙት ሁሉም ፎቶዎች:- By courtesy of the Salzburg Marionette Theatre