በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቋጥኝ ላይ የሚኖሩት ጦጣዎች ምስጢር

በቋጥኝ ላይ የሚኖሩት ጦጣዎች ምስጢር

በቋጥኝ ላይ የሚኖሩት ጦጣዎች ምስጢር

ስለ ጦጣዎች ስታስብ፣ ለኑሮ የሚስማማቸው ሞቃታማ አካባቢ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በወይና ደጋ አካባቢም ጥቂት የጦጣ ዝርያዎች ይገኛሉ። ሆኖም ከተለመደው ለየት ባለ አካባቢ የሚኖሩ አንድ ወይም ሁለት ዝርያዎች አሉ።

በሰሜን አፍሪካ በሚገኘው በረጅሙ የአትላስ ተራራ አናት ላይ በረዶ መጣሉ የተለመደ ነው፤ በዚያ አካባቢ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ባርበሪ ዝንጀሮዎች በተራራው ላይ በሚገኙት የጥድና የባሉጥ ዛፎች መካከል ሲዘዋወሩ ይታያሉ። * ከዚህ ቦታ በስተ ሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቆ በአውሮፓ ደቡባዊ ጫፍ ላይ በሚገኘው የጅብራልተር ቋጥኝ ላይ ደግሞ የእነዚሁ ጦጣዎች ዝርያ ይገኛል።

‘እነዚህ የጦጣ ዝርያዎች በጅብራልተር ቋጥኝ ላይ እንዴት ሊገኙ ቻሉ?’ ለሚለው ጥያቄ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች ምን ምላሽ ይሰጣሉ? አንዳንዶች ጥንት እነዚህ ጦጣዎች በተለያዩ የአውሮፓ ግዛቶች ይኖሩ እንደነበርና በጅብራልተር የሚኖሩት ጦጣዎች ብቻ እንደተረፉ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ቅኝ ግዛታቸውን ያስፋፉ የነበሩ አረቦች ወይም እንግሊዞች ወደ ጅብራልተር ቋጥኝ እንዳመጧቸው ያስባሉ። በአፈ ታሪክ ደግሞ ጦጣዎቹ አውሮፓን ከአፍሪካ የሚለያትን ጠባብ የባሕር ወሽመጥ የተሻገሩት ከረጅም ጊዜ በፊት በነበረና አሁን በቦታው በማይገኝ የመሬት ውስጥ መሿለኪያ እንደሆነ ይነገራል። የመጡት ከየትም ይሁን ከየት፣ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ የሚገኙት ብቸኞቹ የጫካ ጦጣዎች እነሱ ናቸው።

እነዚህ ጦጣዎች የጅብራልተርን ቋጥኝ ላይኛ ክፍል የሸፈነውን የጥድ ጫካ መኖሪያቸው አድርገውታል። ምንም እንኳ የጦጣዎቹ ቁጥር ወደ መቶ ገደማ ብቻ ቢሆንም እንደ ዓለም አቀፉ የዝንጀሮ ጥበቃ ማኅበር አባባል ከሆነ “ባሕረ ገብ በሆነው በዚህ ቦታ የታወቁ ነዋሪዎች” ናቸው። *

ጅብራልተር በየዓመቱ በሰባት ሚሊዮን ቱሪስቶች የሚጎበኝ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ተጫዋች ጦጣዎች በቂ ምግብ የማግኘት አጋጣሚ አላቸው። ምንም እንኳ የሚመገቧቸውን ዕፅዋት ለማግኘት ጫካውን የሚያስሱ ቢሆንም አካባቢውን ሊጎበኙ ከመጡ ሰዎች ምግብ መለመንን አልፎ አልፎም መስረቅን ለምደዋል። የአካባቢው ባለ ሥልጣናትም ለጦጣዎቹ ፍራፍሬና አትክልት ያቀርቡላቸዋል።

ጦጣዎቹ ራሳቸውን ከመመገብ በተጨማሪ የቀኑን አንድ አምስተኛ የሚሆነውን ጊዜ የሚያሳልፉት እርስ በርስ በመቆነጃጀት ነው። ወንድም ሆኑ ሴት ጦጣዎች ለልጆቻቸው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሲሆን አብረዋቸውም ይጫወታሉ። ጦጣዎቹ ተቀራርበው በመንጋ የሚኖሩ እንደመሆናቸው መጠን እርስ በርስ የሚጣሉበትም ጊዜ አለ። ትላልቆቹ ጦጣዎች ትንንሾቹን ለማባረር ሲፈልጉ ያስፍራሯቸዋል ወይም በቁጣ ይጮኹባቸዋል። ከዚህም በላይ ጥርሳቸውን የማንቀጭቀጭ ለየት ያለ ልማድ ያላቸው ሲሆን ይህ ደግሞ የሚያረጋጋቸው ይመስላል።

እነዚህ ጦጣዎች ወደ ጅብራልተር እንዴት እንደመጡ አሁንም ድረስ ምስጢር ቢሆንም ተግባቢ የሆኑት እነዚህ የጦጣ ዝርያዎች የሜዲትራንያን ባሕር መግቢያ ላይ ለሚገኘው ለጅብራልተር ቋጥኝ ልዩ ውበት ጨምረውለታል። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ጅብራልተር አሁን ያለው ዓይነት መስህብ አይኖረውም ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 እንደ እውነቱ ከሆነ ባርበሪ የሚባሉት ዝንጀሮዎች ጅራት አልባ ጦጣዎች እንጂ ዝንጀሮዎች አይደሉም።

^ አን.5 የባርበሪ ዝንጀሮዎች ዝርያ የሆኑትና በጃፓን የሚገኙት መካክ የተባሉ ጦጣዎችም በጃፓን ፍል ውኃ በሚገኝባቸው ቦታዎች የታወቁ የጎብኚዎች መስህብ ናቸው። እነዚህ ጦጣዎች በቀዝቃዛው ወቅት በፍል ውኃዎቹ አካባቢ ይሰባሰባሉ።