በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትልቁ ደሴት የተባለው ለምንድን ነው?

ትልቁ ደሴት የተባለው ለምንድን ነው?

ትልቁ ደሴት የተባለው ለምንድን ነው?

ሃዋይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ብዙዎች ስለ ሃዋይ ደሴቶች ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት በነጭ አሸዋ የተሸፈኑትን የባሕር ዳርቻዎች፣ ጥርት ብሎ የሚታየውን ውኃ፣ ነፋስ የሚያወዛውዛቸውን የዘንባባ ዛፎች እንዲሁም በረጅም ምሰሶ ላይ በተሰቀሉ ቲኪ ተብለው የሚጠሩ ችቦዎች በሚፈነጥቁት ብርሃን በረንዳ ላይ ሆነው የሚያሳልፏቸውን ሞቃታማ ምሽቶች ያስታውሱ ይሆናል። በዚህ ላይ ደግሞ የበሰለ አናናስ በብዛት የገባበት ሉዋው የተባለ ባሕላዊ ምግብ፣ ታሮ ከሚባለው ተክል ሥር የሚዘጋጀው ፖይ የተባለ የሃዋይ ምግብ፣ ከጥሬ የሳልሞን ዓሣ የሚዘጋጅ ሎሚሎሚ የሚባል ሰላጣ እንዲሁም ካሉዋ አሳማ (በሙዝ ቅጠል ተጠቅልሎ መሬት ውስጥ የሚበስል ሙሉ አሳማ) ሲጨመሩ ስለ ሃዋይ የሚሰጠው መግለጫ የተሟላ ይሆናል። ከዚህ በላይ የሚፈልግ ማን አለ?

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ብዙ ሰዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ብዙ አስደሳች ነገሮችን በሃዋይ ማግኘት ይችላሉ! መጀመሪያ ነገር፣ የሃዋይ ደሴት ትልቁ ደሴት ተብሎ የተጠራው በሃዋይ ደሴቶች ውስጥ የሚካተቱን ሌሎቹን ዋና ዋና ደሴቶች ማለትም ኦዋሁን፣ ማዊንና ካዋይን አንድ ላይ ጠቅልሎ መያዝ ስለሚችል ነው! ይህ አስገራሚ ደሴት 10,432 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው መሬት የሚሸፍን ሲሆን አሁንም ገና እየሰፋ ነው። ለማንኛውም ይህን በኋላ ላይ እንመለስበታለን።

አቀማመጡና የአየር ንብረቱ

ትልቁ ደሴት ከሌሎቹ ይልቅ ወደ ደቡብ የሚያደላ በመሆኑ ተስማሚ የአየር ጠባይ አለው። በባሕር ዳርቻዎቹ ላይ ባሉት የእንግዶች ማረፊያ ቦታዎች ላይ በሞቃት ወቅቶች (ከግንቦት እስከ ጥቅምት) ቀን ላይ አማካይ የሙቀት መጠኑ 26 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ አካባቢ ሲሆን በቀዝቃዛ ወቅቶች (ከኅዳር እስከ ሚያዝያ) ደግሞ 21 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ አካባቢ ይደርሳል፤ ሌሊት ላይ በአብዛኛው ከ15-18 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ከነፋስ የተከለለው ኮና የሚባለው አውራጃ ይበልጥ ፀሐያማ ሲሆን ሂሎ የሚባለው ለነፋስ የተጋለጠው አካባቢ ደግሞ በአመዛኙ ዝናባማ ነው።

ሞቃታማው የአየር ንብረትና በእሳተ ገሞራ የሚፈጠረው ለም አፈር ብዙ ዓይነት ፍራፍሬዎችና አትክልቶች እንዲበቅሉ ያስችላል። የሚያማምሩ ደማቅ አበባዎች ያሏቸው ዕፅዋትና አንቱሪም የሚባሉ ለጌጥ የሚሆኑ ተክሎችን ጨምሮ ጣፋጭ ማንጎዎች፣ ፓፓያዎች፣ ሊቺ የሚባሉ የቻይና ፍሬዎች እንዲሁም ሌሎች አስገራሚ ፍራፍሬዎች ሞልተዋል። የለውዝ ዝርያ የሆነ ማካዴሚያ የሚባል ዛፍና የቡና ተክሎች በብዛት ይገኛሉ። የኮና ቡና በዓለም የታወቀ ነው። ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ የቡና አከፋፋዮች የኮናን ቡና ለመቅመስና የሚፈልጉትን ያህል ለማዘዝ በየዓመቱ ወደሚከበረው የኮና ቡና በዓል ይጎርፋሉ።

ትልቁ ደሴት የተለያየ የአየር ንብረት ያላቸው ክልሎች ሲኖሩት ከእነዚህም መካከል ዝናብ በብዛት የሚያገኙ ደኖች፣ በረሃ የሆኑ ቦታዎች እንዲሁም አፈሩ በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ ዕፅዋት የማይበቅሉባቸው አካባቢዎች ይገኙበታል። ሞቃት የአየር ንብረት ባለበትና ዝናብ በማይለየው አካባቢ ያሉት ደኖች የሚገኙት በምሥራቃዊው የደሴቱ ክፍል ነው። በዚህ አካባቢ መልካቸው ለትንግርት የሆኑ ብዙ ዓይነት ወፎች እንዲሁም ላባ የሚመስል ቅጠል ያላቸው ፈርን የተባሉ ተክሎችና የተለያዩ ባለ አበባ የዱር ዛፎች ይገኛሉ። በኮና ኮሃላ አውራጃ፣ የዓመቱ አማካይ የዝናብ መጠን 25 ሴንቲ ሜትር ሲሆን በሂሎ አካባቢ ደግሞ ከ250 ሴንቲ ሜትር በላይ ነው።

ኪላዌ—ንቅ ሆኖም ጋብ ያለ እሳተ ገሞራ

በደሴቱ ላይ ተለይተው የታወቁ አምስት እሳተ ገሞራዎች ያሉ ሲሆን እነሱም ማውና ሎኣ፣ ማውና ኬኣ፣ ኪላዌ፣ ኮሃላ እና ሁዋላላይ ናቸው። ኪላዌ የሚለው ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “ብዙ መትፋት” ማለት ነው። በ1979 ኪላዌ አስደናቂ በሆነ መንገድ በመፈንዳት እንደገና ንቅ እሳተ ገሞራ ሆኗል። እየቀለጠ የሚፈሰው ከፍተኛ ግለት ያለው ዐለት ከ1983 ወዲህ ያለማቋረጥ እየፈሰሰ ነው። ይህ ፈሳሽ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የሚገኙ ሦስት ከተሞችን ያጠፋ ቢሆንም ብዙ ሄክታር መሬት እንዲፈጠር አድርጓል።

የቀለጠው ዐለት በኃይል እያስገመገመ ውቅያኖሱ ውስጥ ሲገባ ከፍተኛ የሆነ እንፋሎትና ጭስ እንዲሁም ደመና እና በጥቁር አሸዋ የተሸፈኑ አዳዲስ የባሕር ዳርቻዎችን ይፈጥራል። ኪላዌን አብዛኛውን ጊዜ ከቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ማየት ይቻላል።

ማውና ኬኣ የሚባለው በ4,205 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውና ረዘም ላለ ጊዜ ፈንድቶ የማያውቀው እሳተ ገሞራ በደሴቲቱ ላይ ከሚገኙት ሁሉ ረጅሙ ተራራ ነው። ይህ ተራራ 4,169 ሜትር ከፍታ ካለው ማውና ሎኣ የሚበልጠው በትንሹ ነው። ሆኖም ማውና ኬኣ በውቅያኖሱ ወለል ከሚገኘው የተራራው ግርጌ ጀምሮ ከተለካ ርዝመቱ 9,000 ሜትር ስለሚሆን በዓለም ላይ ካሉት ተራሮች በሙሉ በርዝመቱ አንደኛ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ማውና ሎኣ የያዘው ቦታ 40,000  ኪሎ ሜትር ኩብ በመሆኑ በዓለም ላይ ካሉት ተራሮች በሙሉ እጅግ ግዙፍ በመሆን ተለይቶ ይታወቃል!

የተለያዩ መስህቦች

በክረምት ወራት ብዙውን ጊዜ በማውና ኬኣ ተራራ ላይ በረዶ ስለሚጥል፣ ነጭ ተራራ የሚለው ቅጽል ስሙ ተስማሚ መጠሪያ ነው። ምንም እንኳ ቁልቁለቱ ቋጥኝ የበዛበት በመሆኑ በበረዶው ላይ መንሸራተት አደገኛ ቢሆንም አንዳንድ የደሴቲቱ ነዋሪዎች በዚህ ተራራ ላይ ይንሸራተታሉ። በአሁኑ ጊዜ 11 አገሮች የተከሏቸው በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ በጣም ኃይለኛ የሆኑት 13 ቴሌስኮፖች ተኮልኩለው የሚገኙት በተራራው አናት ላይ ባለው የማውና ኬኣ የሳይንስ ምርምር ጣቢያ ነው።

በትልቁ ደሴት የባሕር ዳርቻዎች ላይ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች ሞልተዋል። አየሩም ሆነ ውቅያኖሱ ምንጊዜም ሞቅ ያለ በመሆኑ ዓመቱን ሙሉ የውኃ ላይ ስፖርቶችን ማካሄድ ይቻላል። በነጭ አሸዋ በተሸፈኑት ዝነኛ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ሆቴሎች ይገኛሉ፤ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ በእግር አሊያም አስቸጋሪ ለሆኑ መንገዶች በተሠሩ መኪኖች ብቻ ሊደረስባቸው የሚችል ርቀው የሚገኙ የባሕር ዳርቻዎችም አሉ።

በእውነትም ትልቁ ደሴት ከተለያዩ ነገሮች ማለትም ከትልቅነቱ፣ ከሚገኝበት ቦታ፣ ከአየር ንብረቱና ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ አንጻር ብዙ ጥቅሞች አሉት። የደሴቱ ነዋሪዎች የወዳጅነት መንፈስ ያላቸውና ለሰዎች አሳቢ ከመሆናቸውም በላይ ሞቅ ያለውን የሃዋይን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት የሚደሰቱ ሆነው ታገኟቸዋላችሁ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒሃው

ካዋይ

ኦዋሁ

ሆኖሉሉ

ሞሎካይ

ማዊ

ላናይ

ካሆኦላዌ

ሃዋይ

ሂሎ

ኮሃላ

ማውና ኬኣ

ሁዋላላይ

ማውና ሎኣ

ኪላዌ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማውና ኬኣ፣ በስተ ጀርባ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. Geological Survey/ Photo by T.J. Takahashi