በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥንታዊ ባሕሎች በዘመናዊቷ ሜክሲኮ

ጥንታዊ ባሕሎች በዘመናዊቷ ሜክሲኮ

ጥንታዊ ባሕሎች በዘመናዊቷ ሜክሲኮ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዛሬዋ ሜክሲኮ ውስጥ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ባሕሎችና እምነቶች እንዲሁም እንደ ሞባይል ስልኮችና ኢንተርኔት ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች ይታያሉ። ባለፉት ዘመናት፣ የአገሪቱ የቀድሞ ነዋሪዎች የሆኑት ሕንዶች የነበሯቸው አንዳንድ ባሕሎች ከሮም ካቶሊክ ሃይማኖት እምነቶች ጋር ተቀላቅለዋል። እንዲያውም እነዚህ ባሕሎች አሁንም በሜክሲኮ ካቶሊኮች የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ይንጸባረቃሉ።

ለአብነት ያህል፣ በየዓመቱ ኅዳር 2 ቀን በሜክሲኮ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የነፍሳት ሁሉ ቀን (የሙታን ቀን ተብሎም ይጠራል) የሚባለውን በዓል ለማክበር ወደ መካነ መቃብሮች ይሄዳሉ። እዚያም ለሞቱ ዘመዶቻቸው አበቦች፣ ምግብ እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ያስቀምጣሉ። እንዲያውም አንዳንዶች፣ ሟቾቹ ይወዷቸው የነበሩ ዘፈኖችን የሚጫወቱ የሙዚቃ ቡድኖችን ያዘጋጃሉ። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ካቶሊኮች በቤታቸው ውስጥ አምልኮ የሚያከናውኑበት ቦታ የሚያዘጋጁ ሲሆን እዚያም የሟቹን ፎቶግራፍ ያስቀምጡ ይሆናል።

ኢንሲክሎፔድያ ደ ሜሂኮ እንደገለጸው፣ የሙታንን ቀን ከማክበር ጋር የተያያዙ አንዳንድ ልማዶች “የአገሪቱ የቀድሞ ነዋሪዎች የነበሩት ሕንዶች ኦችፓኒዝትሊ እና ቴኦትሌኮ በተባሉት ወራት የሚያከብሯቸውን በዓላት ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ ይመስላል። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ኬምፓሱቺል የተባሉ አበቦችና ከበቆሎ የተዘጋጀ ተማሌ የተባለ ምግብ ለማኔስ [ለሙታን ነፍሳት] የሚቀርብ ሲሆን ይህም የሚደረገው ልክ ሰብል እንደተሰበሰበ ማለትም በጥቅምት መጨረሻና በኅዳር መጀመሪያ ላይ ነበር።” ኢንሳይክሎፒዲያው እንዳመለከተው አንዳንዶቹ ባሕሎች፣ የላቲን አሜሪካ የቀድሞ ነዋሪዎች ያከብሯቸው በነበሩት በዓላት ላይ የነበረውን ዓይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ።

ሃይማኖታዊ አምልኮ

ታኅሣሥ 12 በሜክሲኮ ለሚገኙ ካቶሊኮች የበዓል ቀን ነው። በዚህ ዕለት ከተለያዩ የሜክሲኮ ግዛቶች የሚመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በሜክሲኮ ሲቲ፣ በቴፔያክ ሂል አጠገብ ወደሚገኘው የግዋዳሉፕ ድንግል ቤተ ክርስቲያን ይጎርፋሉ። በርካታ ሰዎች ለዚህች ድንግል እየጸለዩ በእግራቸው ለብዙ ቀናት ይጓዛሉ። ወደ ቦታው ሲደርሱም በእንብርክክ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ በመግባት (ከላይ) ጽጌረዳዎችን የማቅረብ ልማድ አላቸው።

በዛሬው ጊዜ በመኖሪያ ቤቶችና በአፓርታማዎች እንዲሁም በአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታዎችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ሌሎች አካባቢዎች የግዋዳሉፕ ድንግል ምስሎች ይታያሉ። የግዋዳሉፕ ድንግል፣ “የአምላክ እናት” እንዲሁም ‘ጥቁሯ ትንሽ የቴፔያክ ድንግል’ የሚሉ ስያሜዎችም ተሰጥተዋታል። ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ፣ አማኞች ፈውስና ተአምራትን እንደምትፈጽም ሲናገሩ ብዙውን ጊዜ ይሰማሉ።

የግዋዳሉፕ ድንግል አምልኮ አመጣጥ

ሴት አምላክን ማምለክም ሆነ ከላይ የተጠቀሰው በዓል ሌሎች ገጽታዎች፣ አዝቴኮች ለሚያመልኳት ኪሁዋግዋተል የተባለች እናት አምላክ በሚቀርበው አምልኮ ውስጥ ይገኙ ነበር፤ ይህች አምላክ ቶናንትሲን ተብላም የምትጠራ ሲሆን ትርጉሙም “ትንሿ እናታችን” ማለት ነው። ሜሂኮ ኣ ትራቬስ ደ ሎስ ሲግሎስ (ሜክሲኮ ባለፉት ዘመናት) የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ይህችን አምላክም ሆነ ዊትሲሎፖችትሊ የተባለውን ልጇን፣ ቀደም ሲል የአዝቴኮች ዋና ከተማ ወደነበረችው ወደ ቴኖችቲትላን (የአሁኗ ሜክሲኮ ሲቲ) ያመጧቸው የጥንቶቹ አዝቴኮች ናቸው።

በቴፔያክ ሂል የሚገኘውን የኪሁዋግዋተል ቤተ መቅደስ ስፔናውያን ደምስሰውት ነበር። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ከሆነ ኮሎምበስ ወደዚህ አህጉር ከሄደ 40 ዓመታት ሊሆነው አካባቢ፣ የግዋዳሉፕ ድንግል የአገሩ ተወላጅ ለሆነ ህዋን ዲዬጎ የተባለ ሰው ከተገለጠችለት በኋላ በዚያ ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ እንዲሠራላት ጠየቀችው።

አዝቴኮች፣ ለኪሁዋግዋተል ትልቅ ክብር ይሰጧት ነበር። ኪሁዋግዋተል፣ ያልተጎነጎነ ረጅም ፀጉር እንደነበራትና ከላይ እስከታች ነጭ ቀሚስ ትለብስ እንደነበር ይነገራል። የቤተ መቅደሷ መግቢያ በጣም ዝቅ ያለ በመሆኑ መግባት የሚቻለው በእንብርክክ ብቻ ነበር። ምዕመናኑ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ምስሏን ማየት የሚችሉ ሲሆን በምስሏ ዙሪያ የሚገኙት ጣዖታት “የአማልክት እናት” ያስመስሏታል።

በኪሁዋግዋተል በዓል ላይ ከሚከናወኑት ነገሮች መካከል የሰው መሥዋዕት ማቅረብ፣ ጭፈራ እንዲሁም “በእጃቸው፣ በአንገታቸውና በጭንቅላታቸው ላይ ጽጌረዳ” የተደረገላቸው ጦረኞች የሚያሳዩት ሰልፍ ይገኙበታል። እነዚህን ስጦታዎች ለዊትሲሎፖችትሊ መሥዋዕት እንዲሆኑ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ ያስቀምጧቸዋል። ከጓቲማላ የሚመጡትን ጨምሮ የአገሪቱ የቀድሞ ነዋሪዎች የሆኑ አንዳንድ ሕንዶች በኪሁዋግዋተል በዓል ላይ ለመገኘት ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው ይጓዙ ነበር።

የአንድ የአምልኮ ሥርዓት አመጣጥ ለውጥ ያመጣል?

ካቶሊኮች የሚያመልኳት የግዋዳሉፕ ድንግል የአምልኮ ሥርዓት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነተኛ አምላክ ከማያመልኩ ሰዎች የመጣ እንደሆነ ግልጽ ነው። (መዝሙር 83:18) ታዲያ ይህን ማወቃችን ስለዚህ የአምልኮ ሥርዓት ባለን አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል? የአንድ አምልኮ አመጣጥ፣ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ወይም እንዳይኖረው ሊያደርግ ይችላል?

በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል:- “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ . . . ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ኅብረት አለው?” ከዚህም በላይ ጳውሎስ “ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 6:14, 15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:21

በዛሬው ጊዜም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ማበረታቻ አስፈላጊ ነው። እኛም ለአምላክ ስለምናቀርበው አምልኮ ልናስብ እንዲሁም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል:- ‘የማቀርበው አምልኮ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነው? ወይስ የአምልኮዬ አንዳንድ ገጽታዎች የሐሰት አማልክትን ከሚያመልኩ ሰዎች የተወሰዱ ናቸው?’ እውነተኛውን አምላክ፣ ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልግ ሰው ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት በማድረግ የጥበብ እርምጃ ይወስዳል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ግዋዳሉፕ ድንግል ቤተ ክርስቲያን የሚጎርፉ ምዕመናን

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኅዳር 2 ቀን በሚከበረው በዓል ላይ በመካነ መቃብሮች አጠገብ የሚጫወቱ ሙዚቀኞች