በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጉዞህ አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጉዞህ አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጉዞህ አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?

ፊሊፒንስ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አውሮፕላን ስትሄድ ‘አብራሪው መንገዱን የሚያውቀው እንዴት ነው?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ምናልባት በርካታ የሆኑ አልፎ ተርፎም በመቶዎች የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች ያለህበት አውሮፕላን የሚጓዝበትን መንገድ አቋርጠው ወደተለያየ አቅጣጫ እንደሚበሩ ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልህ ይሆናል። አውሮፕላኖቹን እርስ በርስ ከመጋጨት የሚጠብቃቸው ምንድን ነው?

መንገደኞች እንዲህ ስላሉት ጥያቄዎች ማሰባቸው ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ፣ በአውሮፕላኖች መጓዝ በሞተር ብስክሌት ወይም በመኪና ከመሄድ የበለጠ አስተማማኝ መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። * በአውሮፕላን መጓዝ ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎት ነው።

ጉዞህ አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ

ካፒቴኑ ወይም አውሮፕላኑን የሚቆጣጠረው አብራሪ የአውሮፕላኑን ደህንነት የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይሁን እንጂ ሌሎች አውሮፕላኖች በዙሪያው ሲበሩ ማየት የማይችልባቸውና መኖራቸውንም እንኳ የማያውቅባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ አገሮች የአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎት አላቸው። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መሬት ላይ ሆነው በበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች አማካኝነት እያንዳንዱን የበረራ እንቅስቃሴ ይከታተላሉ።

በካሊፎርኒያ ለ13 ዓመታት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሆኖ የሠራው ሳሙኤል እንዲህ ብሏል:- “የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች በበረራ ወቅት አደጋ እንዳይከሰት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። የእነዚህ ባለሙያዎች ተቀዳሚ ተግባር አውሮፕላኖች ተራርቀው እንዲበሩ ማድረግ ነው” ብሏል። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ የሆነችው ሜልባ እንደሚከተለው በማለት ተጨማሪ አስተያየት ሰጥታለች:- “ከሁሉ ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አደጋ እንዳይደርስ ማድረግ ቢሆንም የተቀላጠፈና ሥርዓቱን የጠበቀ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖርም እናደርጋለን።” በመሆኑም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ግጭቶች እንዳይከሰቱ ብቻ ሳይሆን የአውሮፕላኖች በረራ እንዳይስተጓጎልም እርዳታ ያበረክታሉ።

ይህም ሲባል አውሮፕላን አብራሪው በበረራ መቆጣጠሪያ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ሥራውን ሲያከናውን በመሬት ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች ደግሞ የበረራውን ሂደት በትኩረት ይከታተላሉ ማለት ነው። አብራሪው በመነሻና በመድረሻ ጣቢያዎቹ ካሉት ተቆጣጣሪዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በመንገዱ ላይ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ ተቆጣጣሪዎች ጋርም በሬዲዮ ይነጋገራል።

በከፍተኛ ፍጥነት የሚበሩ አውሮፕላኖች ባሉበት በዚህ ዘመን አብራሪው ገና ያላያቸውን ከፊቱ የሚጠብቁትን ነገሮች እንዲያውቅ መርዳት በጣም አስፈላጊ ነው። እስቲ ለአንድ አፍታ በዓይነ ሕሊናህ ሁለት አውሮፕላኖች አንዳቸው በሌላኛው ትይዩ ሆነው በአንድ መሥመር ሲበሩ ይታይህ። አብራሪዎቹ ከፊታቸው አውሮፕላን እየመጣ እንዳለ የሚያዩት አውሮፕላኖቹ ሊጋጩ ጥቂት ሴኮንዶች ብቻ ሲቀራቸው ሊሆን ይችላል! እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይከሰት መከላከል የአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ ኃላፊነት ነው። አብራሪዎቹ ከፊት ለፊታቸው የሚመጣውን አውሮፕላን ከማየታቸው አስቀድሞ በመካከላቸው ሰፊ ክፍተት እንዲኖር ትእዛዝ ይሰጣቸዋል።

የአውሮፕላኑን የበረራ ሁኔታ መከታተል

በመሬት ላይ ያሉት በሬዲዮ ሞገድ የሚሠሩ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያዎች አውሮፕላኑን ለመምራት የሚያስችል መልእክት ለማስተላለፍ ያገለግላሉ። አብራሪው፣ የተላለፈውን መልእክት ተቀብለው አውሮፕላኑ ያለበትን ቦታ በትክክል የሚነግሩ መሣሪያዎች አሉት። እነዚህ የመልእክት ማስተላለፊያዎች የሚገኙት በተወሰኑ አካባቢዎች በመሆኑ አውሮፕላኖቹ ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ድረስ የሚጓዙት ከአንዱ የመልእክት ማስተላለፊያ ጣቢያ ወደሌላው እየተሸጋገሩ ነው። እነዚህ የመልእክት ማስተላለፊያ መሣሪያዎች ራሳቸውን የቻሉ የአየር ላይ መንገዶችን ፈጥረዋል ማለት ይቻላል።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ አውሮፕላኖቹ በአየር መንገዶቹ ላይ የት እንደደረሱ ይከታተላሉ። አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት አብራሪዎቹ ሊሄዱ ያሰቡበትን የበረራ መሥመር ካርታ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው የአውሮፕላኑ ዓይነት፣ የሚበርበት መሥመር፣ ሰዓት፣ ከፍታና ሌሎች መረጃዎች የተጻፉበት መዝገብ ወይም ፍላይት ፕሮግረስ ስትሪፕ ቅጅ ይኖረዋል። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ኃላፊ የሆኑት ሳልቫዶር ራፋኤል ይህ መዝገብ ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “በአየር መንገዱ ላይ የተወሰኑ መገናኛ ጣቢያዎች አሉ። አብራሪው እነዚህ ጣቢያዎች ላይ ሲደርስ መረጃውን ለተቆጣጣሪው ሪፖርት ያደርጋል። ከዚያም ተቆጣጣሪው ያገኘውን መረጃ በእጁ ላይ በሚገኘው ፍላይት ፕሮግረስ ስትሪፕ ቅጅ ላይ ይመዘግበዋል።” በመሆኑም ተቆጣጣሪው አውሮፕላኑ እየተጓዘበት ያለውን መሥመር በአእምሮው መሳል ይችላል።

ተቆጣጣሪው ይህን የጉዞ ሪፖርት ለማግኘት የሚጠቀምበት ሌላው መሣሪያ ደግሞ ሬዲዮ ነው። ይህም አውሮፕላኑ ያለበትን ስፍራ ለማወቅ የሚረዳው ከመሆኑም ሌላ ከሌላ አውሮፕላን ጋር እንዳይጋጭና ርቀቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ለአብራሪው ትእዛዝ ለመስጠት ያስችለዋል። የአየር ተቆጣጣሪዎችና የአውሮፕላን አብራሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በርካታ ሬዲዮዎች የሚይዙ ሲሆን የተለያዩ የአየር ሞገዶችንም መጠቀም ይችላሉ። ስለሆነም ድንገት አንዱ አልሠራም ቢል ሌላውን ይጠቀማሉ።

የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ አብራሪው መልእክት የሚቀበለው እንዴት ነው? በቋንቋ አለመግባባት ምክንያት አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግ ሲባል ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከበረራ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የጋራ መግባቢያ እንዲሆን ወስኗል። በተጨማሪም በሬዲዮ ሲነገሩ ተመሳሳይ የሚመስሉ አንዳንድ ቃላት፣ ፊደሎችና ቁጥሮች ስላሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለአብራሪዎች ትእዛዝ በሚሰጡበት ጊዜ አንድ ዓይነት ሐረጎችንና የቃላት አነባበቦችን እንዲጠቀሙ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በረራው ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ አብራሪዎች ተቆጣጣሪዎቹ የሰጧቸውን አንዳንድ ትእዛዞች ደግመው እንዲናገሩ ይጠየቃሉ።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ የሚጠቀሙበት ሌላ መሣሪያ ደግሞ ራዳር ነው። የሬዲዮ ሞገዶች ከአውሮፕላኑ ጋር ተጋጭተው ነጥረው ሲመለሱ የራዳሩ አንቴና ይቀልባቸዋል። በዚህ ጊዜ በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ኮምፒውተር ላይ ምልክት መታየት ይጀምራል። አብዛኞቹ አውሮፕላኖች መለያ ምልክታቸውን ለራዳሩ የሚያስተላልፍ መሣሪያ ተገጥሞላቸዋል። የተላለፈው መልእክት በኮምፒውተሩ ውስጥ ካለው መረጃ ጋር ተዳምሮ ለተቆጣጣሪው የአውሮፕላኑን ዓይነት፣ የበረራ ቁጥሩን፣ የሚጓዝበትን ፍጥነትና ከፍታ የሚገልጽ የተሟላ መረጃ ይሰጠዋል።

ተቆጣጣሪው አውሮፕላኖች እንዳይጋጩ ለማድረግ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ አማራጮች አሉት። አብራሪው (1) አቅጣጫውን እንዲቀይር ትእዛዝ ሊሰጠው ይችላል። ወይም ደግሞ አንዱ አውሮፕላን ሌላውን ለመቅደም ከተቃረበ (2) ፍጥነቱን እንዲያስተካክል ሊነግረው ይችላል። አውሮፕላኖች እንዳይቀራረቡ ለማድረግ የሚጠቀምበት ሌላው በጣም የተለመደ መንገድ ደግሞ (3) ከፍታቸውን እንዲቀይሩ መንገር ነው።

አደገኛ ሁኔታ ሲኖር ራዳሩ ለተቆጣጣሪው የተለያዩ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን እንዲያሳይ መደረጉም የአውሮፕላን ጉዞን ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ለማስቻል የሚደረገው ጥረት ክፍል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት አውሮፕላኖች እርስ በርስ በጣም ከተቀራረቡ የራዳር መሣሪያው የማስጠንቀቂያ ምልክት ማሳየትና ድምጽ ማሰማት ይጀምራል። አንዱ አውሮፕላን ወደ ምድር በጣም እየቀረበ ከሄደ ደግሞ ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል ሊሰማ ይችላል።

ዓላማው የአንተን ደህንነት መጠበቅ ነው

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል ጥረት በመደረግ ላይ ነው። በመሬት ላይ ያሉት የበረራ መቆጣጠሪያዎች ብዙውን ጊዜ አንድ አውሮፕላን የሚጓዝበትን መንገድና ከፍታ ሳይቀያይር እንዲበር ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ አቋራጭ መንገዶችን ትቶ ረዥም ጉዞ የሚጠይቁ መንገዶችን መከተል ማለት ይሆናል። ለወደፊቱ የሚደረጉት የአውሮፕላን በረራዎች፣ ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም የተባለውን አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ በመሳሰሉ በሳተላይት በሚታገዙ መሣሪያዎች ላይ የተመኩ ይሆናሉ፤ ይህም አውሮፕላኖች የሚጓዙበትን መንገድ እንደ አስፈላጊነቱ ለመቀያየር የሚያስችላቸው ከመሆኑም ሌላ ውቅያኖስ አቋራጭ በረራዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ይረዳል።

የአየር ትራፊክ ቁጥጥርን በሚዳስሰው በዚህ አጭር ዘገባ ላይ እንደተመለከትከው የምትጓዝበት አውሮፕላን የት እንደደረሰ የሚያውቀው አብራሪው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በመሬት ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች በረራውን ይቆጣጠሩታል። ይህ የቁጥጥር አገልግሎት አደጋን ለመቀነስና ደህንነትህን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም በአውሮፕላን ላይ የሚደርሰው አደጋ መጠን በጣም አነስተኛ መሆኑ ምንም አያስገርምም!

ስለዚህ በአውሮፕላን ስትጓዝ እምብዛም መጨነቅ የለብህም። ለሚቀጥለው ጊዜ፣ ረዥም በረራ ስታደርግ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች የአንተን ደህንነት ለመጠበቅ በንቃት እንደሚሠሩ አስታውስ። ስለሆነም ዘና ብለህ ተጓዝ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ፣ የመንገደኛ አውሮፕላኖች በአንድ ዓመት ውስጥ 11,000,000,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን በረራ አድርገዋል፤ ይሁን እንጂ በዓመቱ ውስጥ በእያንዳንዱ 334,448 ሰዓት በረራ ውስጥ የደረሰው አደጋ በአማካይ አንድ ብቻ ነበር።

[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የአውሮፕላኑን የበረራ ሁኔታ መከታተል

ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት

በመሬት ላይ ያሉ አቅጣጫ ጠቋሚ የሬዲዮ መልእክት ማስተላለፊያ መሣሪያዎች

ሬዲዮ

የራዳር አንቴና

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ማዕከል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ማማና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች:- NASA Ames Research Center; የቁጥጥር ማዕከል:- U. S. Federal Aviation Administration