በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ የኦፔራ ዘፋኝ መሆን የሚቻልበት መንገድ

ጥሩ የኦፔራ ዘፋኝ መሆን የሚቻልበት መንገድ

ጥሩ የኦፔራ ዘፋኝ መሆን የሚቻልበት መንገድ

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዘፋኙ ራሱን ቀና፣ ደረቱን ነፋ፣ ግንባሩን ፈታ አድርጎ፣ አፉን እንደገጠመ ዘና ባለ ሁኔታ ቀጥ ብሎ ቆሟል። ኦርኬስትራው የመግቢያውን ሙዚቃ ባጭሩ ከተጫወተ በኋላ ዘፋኙ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየውን ዜማውን ማሰማት ይጀምራል። ድምፁ ከእሱ አፍ የሚወጣ እስከማይመስል ድረስ ዜማውን ያላንዳች ችግር ያንቆረቁረዋል። ዘፈኑን ሲጨርስ አዳራሹን የሞላው ሕዝብ ጭብጨባውን ያቀልጠዋል።

ኦፔራ፣ ዘፋኝ የሆኑ ተዋንያን በኦርኬስትራ እየታጀቡ የሚያቀርቡት ድራማ ነው። ኦፔራ ትወዳለህ? ኦፔራ በሚቀርብበት አዳራሽ ተገኝተህ የማየት አጋጣሚ አግኝተህ ታውቃለህ? አንድ የኦፔራ አቀንቃኝ ለጆሮ የሚጥም ድምፅ እንዲያወጣ የሚረዳው ቁልፍ ነገር ምን ይመስልሃል?

ድምፅ የሙዚቃ መሣሪያ ነው

ድምፅ ከአምላክ የተገኘ ድንቅ ስጦታ ሲሆን የሙዚቃ መሣሪያ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። እንደ አንድ የኦፔራ ዘፋኝ መዝፈን የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም ለብዙዎች መዝፈን ልክ እንደ መብላት ወይም መተኛት ያለችግር የሚያደርጉት የሕይወታቸው ክፍል ነው። ድምፅህ ጥሩ ይሁንም አይሁን ይህ “የሙዚቃ መሣሪያ” ማለትም ድምፅ እንዴት እንደሚሠራ ይበልጥ ለማወቅ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም።

ድምፅ እንዲፈጠር የሚያደርገው የአካል ክፍል በጉሮሮህ መሃል የሚገኘው ማንቁርት ነው። ማንቁርት፣ ዙሪያውን በለስላሳ አጥንት (cartilage) የተሸፈነ እንደ ቀፎ ያለ ክፍት ቦታ ሲሆን በውስጡ የድምፅ አውታር የሚባሉ ሁለት ትንንሽ ጡንቻዎች አሉት። ታዲያ ድምፅ የሚፈጠረው እንዴት ነው? በምትተነፍስበት ወቅት የድምፅ አውታሮችህ ዘና ስለሚሉ በአየር መተላለፊያ ቧንቧው ውስጥ ግሎቲስ ተብሎ የሚጠራ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ክፍተት ይፈጥራሉ። በምትዘፍንበት ጊዜ ደግሞ በማንቁርትህ ውስጥ ተገፍቶ የሚያልፈው አየር ስለሚጨምር፣ ግሎቲስ ይጠባል፤ እንዲሁም የድምፅ አውታሮችህ በመርገብገብ ድምፅ ይፈጥራሉ። የድምፅ አውታሮቹ በተወጠሩ መጠን የሚፈጠረው እርግብግቢትም ስለሚጨምር ቀጭን ድምፅ ይፈጠራል። በሌላ በኩል ደግሞ በማንቁርት ውስጥ የሚያልፈው የአየር ግፊት ሲቀንስና የድምፅ አውታሮቹ ዘና ሲሉ የግሎቲስ ክፍተት ይሰፋል፤ እንዲሁም የሚፈጠረው እርግብግቢት ይቀንሳል፤ ይህም ወፍራም ድምፅ እንዲፈጠር ያደርጋል።

ጥሩ የኦፔራ ዘፋኝ ለመሆን የሚያስፈልገው ስልትና ቁመና

ኤንሪኮ ካሩሶ ወጣት ሳለ ልዩ ድምፅ ነበረው፤ ይሁን እንጂ ድምፁ ኃይል ያንሰው ነበር። ሥልጠና መውሰዱ ግን ድምፁ ኃይል እንዲኖረው ረድቶታል። ውብ የሆነ ድምፅ በተፈጥሮ የሚገኝ ስጦታ ነው፤ ይሁን እንጂ ጥሩ የኦፔራ ዘፋኝ ለመሆን ዘዴውን መማርም አስፈላጊ ነው። ዘፋኙ በቂ ትንፋሽ እንዲኖረው እንዴት አየር መሳብ እንዳለበት መማር ያስፈልገዋል። ከዚያም ያስገባውን አየር እንዴት እንደሚቆጣጠር ማወቅ አለበት። ፋሪኔሊ በመባል የሚታወቀው እውቁ የ18ኛው መቶ ዘመን አቀንቃኝ ካርሎ ብሮስኪ በአንድ ትንፋሽ 150 ኖታዎችን መዝፈን ይችል እንደነበር ይነገራል።

በተመሳሳይም የኦፔራ ዘፋኞች ሰውነታቸውን በመጠቀም ድምፃቸውን እንዴት ማጉላት እንደሚችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል። በሙያው የሠለጠኑ አንዳንድ ሰዎች እንደሚናገሩት ወፍራም ድምፅ እንዲፈጠር የሚረዱት በደረት ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ሲሆኑ እነዚህ ቦታዎች ድምፁን እንደ ከበሮ በማስተጋባት እንዲጎላ ያደርጉታል። በመንገጭላና በፊት አጥንቶች ውስጥ ያሉ ክፍተቶች ደግሞ ቀጭን ድምፅ ጎልቶ እንዲወጣ ይረዳሉ።

ብዙዎች አንድ ሰው የሚዘፍነው በጉሮሮው ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አንድ ዘፋኝ በሚዘፍንበት ጊዜ ሙሉ ኃይሉን ስለሚጠቀም የሚዘፍነው መላው አካሉ ነው መባሉ የተገባ ነው። በመላው ሰውነታችን ላይ ያሉትን ጡንቻዎች አቀናጅቶ ለመጠቀም በሚገባ ሚዛንን መጠበቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም ኦፔራ መዝፈን ብዙ ኃይል ይጠይቃል፤ ምናልባትም አንዳንድ የኦፔራ ዘፋኞች ደልዳላ ሰውነት ያላቸው ለዚህ ሊሆን ይችላል። በ20ኛው መቶ ዘመን ከነበሩት በጣም ታዋቂ የኦፔራ አቀንቃኞች መካከል አንዷ ማሪያ ካላስ ነች። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ድምፅዋ እየተበላሸ መጣ፤ ይህ የሆነው ከልክ በላይ ምግብ መቀነሷ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጣም እንድትከሳ ስላደረጋት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

በኦፔራ ዘፈን ታሪክ የታዩ ለውጦች

ኦፔራ በአዘፋፈን ስልትና በሌሎች መንገዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ለውጥ አድርጓል። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት። ኦፔራ የሚዘፈነው በጸሎት ቤት ወይም በሌሎች ጠባብ ቦታዎች መሆኑ ቀርቶ ትላልቅ የኦፔራ ቤቶች ሲከፈቱ፣ ለስለስ ባለ ድምፅ ይዘፈን የነበረው ኦፔራ በወፍራምና በኃይለኛ ድምፅ ለሚዘፈን የኦፔራ ዓይነት ቦታውን ለቀቀ። የሰውነትን ተፈጥሯዊ የማስተጋባት ኃይል መጠቀም እየተዘወተረ የመጣው በዚህ ጊዜ ነበር። ይህ ለውጥ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው፣ ሞዛርት ይጠቀምባቸው የነበሩት አነስ ያሉ ኦርኬስትራዎች፣ ቨርዲ እና ዋግነር እንደተጠቀሙባቸው ባሉ ትልልቅ ኦርኬስትራዎች መተካታቸው ነው። ከ17ኛው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ የኦፔራ ሙዚቃ ሙሉ በሙሉ የተመካው በዘፋኙ ችሎታ ላይ ነበር። ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ የነበረው አቀራረብ ግን ከበፊቱ በጣም የተለየ ነበር። በዚህ ወቅት፣ የዘፋኙ ድምፅ በኦፔራ ውስጥ ያለው አስፈላጊነት ባይቀንስም ሌሎች የኦፔራ ገጽታዎችም ከዘፋኙ ድምፅ ባልተናነሰ ሁኔታ ትልቅ ቦታ እየተሰጣቸው መጣ።

ኦፔራ የማደግ ተስፋ የነበረው መሆኑ ብዙዎች አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎችን እንዲሠሩ አነሳስቷቸዋል። ጥልቅ ስሜት የሚቀሰቅሱና የማይረሱ ሙዚቃዎችን ከደረሱ በጣም ዝነኛ የሙዚቃ ደራሲዎች መካከል ፓይሲየሎ፣ ሲማሮሳ፣ ግሉክ፣ ሞዛርት፣ ዶኒዜቲ፣ ሮዚኒ፣ ቤሊኒ፣ ዋግነር፣ ቨርዲ፣ ፑቺኒ፣ ቢዜት፣ ሜየርቢርና ማስካኚ ይገኙበታል።

በሙዚቃ ስም የተፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች

በኦፔራ ዘፈን ታሪክ ውስጥ አሳዛኝ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት የጣሊያኑን ኦፔራ ተቆጣጥረውት ስለነበሩት ካስትራቲ ተብለው ስለሚጠሩት ዘፋኞች አስብ። * ወንዶች ልጆች ለአቅመ አዳም ከመድረሳቸው በፊት የማኮላሸት ተግባር ይፈጸምባቸው ነበር። ይህ የሚደረገው ልዩ ቃና እና ኃይል ያለውን ቀጠን ያለ ድምፃቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ሲባል ነው። ይህ ልማድ እንዲስፋፋ ያደረገችው “ሴቶች በጸሎት ቤት እንዳይዘምሩ የከለከለችው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ናት” በማለት ግዊዶ ታርቶኒ ተናግሯል።

በጣም የታወቁ የኦፔራ ዘፋኞች ኮከቦች ለመሆን የበቁ ሲሆን አንዳንድ አድናቂዎቻቸው አምልከዋቸዋል። በሉቺያኖ ፓቫሮቲ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የታየው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ማሪያ ካላስ ላ ዲቪና (መለኮታዊ) ተብላ የተጠራች ሲሆን ጆአን ሰዘርላንድ ደግሞ ላ ስቱፔንዳ (ዕጹብ ድንቅ) ተብላለች። ያም ሆነ ይህ የኦፔራ ዘፈን ይህን ያህል ተወዳጅነት ያተረፈው፣ የአድማጮችን ስሜት የመቀስቀስ ኃይል ያለው የሙዚቃ ዓይነት በመሆኑ ነው።

ወደፊት አንተም አንዲት የኦፔራ ዘፋኝ ለስለስ ያለ ታዋቂ ዘፈን ስታዜም የማየት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። ይህን የመሰለ አጋጣሚ ካገኘህ፣ እንዲህ ያለውን ማራኪ ድምፅ ለማውጣት ምን ያህል ሥልጠና እንደጠየቀባት ቆም ብለህ አስብ። እንዲህ ማድረግህ ስለ ኦፔራ አንድ ጸሐፊ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ እንድታስተጋባ ያነሳሳህ ይሆናል:- ኦፔራ “ቃላትን ከሙዚቃ ጋር የሚያዋህድና ለግጥም . . . የዜማ ክንፍ የሚያወጣለት” የሙዚቃ ዓይነት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 ካስትራቲ ተብለው ይጠሩ ስለነበሩት የኦፔራ ዘፋኞች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የየካቲት 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 11-14ን ተመልከት።

[ገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዳንድ የድምፅ ዓይነቶች

ኮለረቱረ ሶፕራኖ:- ፈጣንና ቀጭን ዜማዎችን በቀላሉ መዝፈን የሚያስችል የሴት ድምፅ። ዘፋኟ ብዙውን ጊዜ የምትጫወተው ደስተኛና አስቂኝ ገጸ ባሕርይ በመወከል ነው።

ሊሪክ ሶፕራኖ:- መረዋ የሴት ድምፅ። ዘፋኟ የምትጫወተው አዛኝ የሆነችን ወይም ፍቅር የያዛትን ገጸ ባሕርይ ወክላ ነው።

ድራማቲክ ሶፕራኖ:- ወፈር ያለ የሴት ድምፅ። ባጠቃላይ ሲታይ ዘፋኟ ልብ አንጠልጣይ የሆነ ገጸ ባሕርይ ወክላ እንድትጫወት ትመደባለች።

ሜዞ ሶፕራኖ:- ከድራማቲክ ሶፕራኖ ይበልጥ ውብና ወፈር ያለ የሴት ድምፅ። ዘፋኟ ብዙውን ጊዜ የምትጫወተው ባልቴት ወይም የዋናዋ ገጸ ባሕርይ ባላንጣ ሆና ነው።

ኮንትራልቶ:- ጥቂቶች ብቻ የታደሉት የሴት ድምፅ። ዘፋኟ ከሜዞ ሶፕራኖ ጋር የሚመሳሰል ገጸ ባሕርይ ወክላ ትጫወታለች።

ቴነር:- ከሶፕራኖ ጋር ተመሳሳይ ባሕርይ ያለው የወንድ ድምፅ፤ ማለትም ለስለስ ያለ፣ አስደሳችና ልብ አንጠልጣይ። ዘፋኙ ብዙውን ጊዜ የሚጫወተው የዋናዋ ገጸ ባሕርይ ፍቅረኛ ወይም ዋና ባለታሪክ በመሆን ነው።

ባሪቶን:- ይህ ድምፅ በቴነርና በባሶ መካከል የሚመደብ ነው። ዘፋኙ የወንድምን፣ የአባትን ወይም የተቀናቃኝን ቦታ ወክሎ ይጫወታል።

ባሶ:- ከወንዶች ድምፅ በጣም ወፍራሙ ሲሆን በሦስት ይከፈላል። እነሱም ብሪሊያንት፣ ካንታንቴ እና ፕሮፉንዶ ናቸው። የመጀመሪያው ደስተኛና አስቂኝ ለሆኑ ገጸ ባሕርያት የሚስማማ ሲሆን ሁለተኛው አዛኝ ለሆነ ገጸ ባሕርይ፣ እንዲሁም ሦስተኛው ጥልቅ ስሜትን ለሚገልጹ ገጸ ባሕርያት የሚሆን ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦፔራ መድረክ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦፔራ ቤት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

መድረክ:- Philip Groshong for The Cincinnati Opera; አዳራሽ:- Courtesy of Tourism Office of Budapest