በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ገነት ትሆናለች?

ምድር ገነት ትሆናለች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ምድር ገነት ትሆናለች?

ሰው ፍጹም ሆኖ፣ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርቶ እንዲሁም ከበሽታና ከሞት ነፃ ሆኖ የኖረበት ወርቃማ ዘመን እንደነበረ የሚናገሩ አፈ ታሪኮች ያሏቸው በርካታ ሕዝቦች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል በግብፅ፣ በሜክሲኮ፣ በፔሩና በቲቤት የሚኖሩት ሕዝቦች ይገኙበታል። እነዚህ አፈ ታሪኮች ሰው እንዴት ኃጢአት ውስጥ እንደወደቀ የሚናገር ሐሳብም አካተው ይዘዋል።

ምንም እንኳ አፈ ታሪኮቹ የተዛቡና የተጨማመረባቸው ቢሆኑም ይህን ያህል መመሳሰላቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ሊባል አይችልም። ይህም ብዙ ሰዎች አፈ ታሪኮቹ ቀደም ሲል ከተፈጸሙ ታሪካዊ ክንውኖች የተወሰዱ መሆን አለባቸው ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። በእርግጥም በአፈ ታሪኮቹ ውስጥ የሚነገሩት አንዳንድ ተመሳሳይ መግለጫዎች በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ውስጥ ከተገለጹት ሐሳቦች ጋር አስደናቂ ተመሳሳይነት አላቸው። ሆኖም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች እንደ አፈ ታሪኮቹ የተድበሰበሰ መረጃ ሳይሆን አንድ እውነተኛ ታሪክ ሊይዝ የሚገባውን ሐቅ በዝርዝር የያዙ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ፍጹም የሆነ ጅምር

አምላክ የመጀመሪያዎቹን የሰው ልጆች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ኤደን ገነት ተብሎ በሚጠራ ለምለም ቦታ እንዳኖራቸው የዘፍጥረት መጽሐፍ ይነግረናል። ፍጹም ጤንነት የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋም ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር። የሚሞቱት ኃጢአት ከሠሩ ብቻ ነበር። (ዘፍጥረት 2:8-17፤ ሮሜ 5:12) አዳምና ሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ተብለው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በመጨረሻም የአምላክ ዓላማ መላዋ ምድር እሱን በደስታ የሚታዘዙ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች የሞላባት ገነት እንድትሆን ማድረግ ነበር።

የሚያሳዝነው አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው የፈጣሪያቸውን ዓላማ ከግቡ የማድረስ አጋጣሚያቸውንና ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጡ። ይሁንና ይሖዋ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ከፍጻሜ ያደርሳል። ይሖዋ፣ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 55:11) በእርግጥም ይሖዋ ምድር የእሱን ባሕርይ የሚያንጸባርቁ የሰው ልጆች የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን የማድረግ ዓላማው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ጭብጦች መካከል አንዱ ነው።—ሮሜ 8:19-21

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሠሩ ወዲያውኑ አምላክ ‘የጥንቱን እባብ’ ሰይጣን ዲያብሎስን የሚያጠፋና ክፉ ሥራውን የሚያፈርስ አንድ ‘ዘር’ ወይም ልጅ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገባ። (ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 12:9፤ 1 ዮሐንስ 3:8) የዚህ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ከጊዜ በኋላ ተረጋግጧል። (ገላትያ 3:16) ከዚህም በላይ አምላክ ኢየሱስን፣ ምድርን የሚገዛው የሰማያዊው መንግሥት ወይም መስተዳድር ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ራእይ 11:15

ክርስቶስ፣ አዳም ማድረግ ሳይችል የቀረውን ነገር በሙሉ ይፈጽማል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ኋለኛው አዳም” በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ከዚህ በተጨማሪም ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት በተናገረ ጊዜ የምድር የወደፊት ተስፋ በአምላክ መንግሥት ላይ የተመካ መሆኑን አሳይቷል።—ማቴዎስ 6:10

ኢየሱስ የወደፊቱ የምድር ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” የማለት መብት ነበረው። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ በአእምሮው ይዞት የነበረው ገነት የሚቋቋመው በምድር ላይ ነው፤ ምክንያቱም ይህ የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሐቅ በሚገባ ይደግፋል። ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ተመልከት።

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።” (መዝሙር 72:16) “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።” (ምሳሌ 2:21) “[ነቀፋ የሌለባቸውም] በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:9

ከላይ ከተጠቀሱት አባባሎች ጋር በሚስማማ መንገድ ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5) ቆየት ብሎም ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ . . . እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚናገሩት በሰማይ ስላለች “ገነት” ሳይሆን በምድር ላይ ስለምትቋቋመው ገነት እንደሆነ ግልጽ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ምን ይላሉ?

በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በክርስቶስ መንግሥት ሥር ምድር ገነት እንደምትሆን ያምናሉ። ጆሴፍ ሳይስ የተባሉ የሃይማኖት ምሑር ‘በመሲሑ አገዛዝ ሥር የምትተዳደረው መላዋ ምድር በስተ መጨረሻ፣ አዳም ኃጢአት ባይሠራ ኖሮ ልትኖር የምትችለውን ዓይነት ምድር መሆኗ አይቀርም’ በማለት ተናግረዋል። ሄነሪ ኦልፈርድ፣ ዘ ኒው ቴስታመንት ፎር ኢንግሊሽ ሪደርስ በሚል ርዕስ በጻፉት ሐተታ ላይ ‘ይህ የአምላክ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ ራሱን የቻለ መንግሥት እስኪሆንና ተገዢዎቹ ምድርን እስኪወርሱ ድረስ መሥራቱን ይቀጥላል። በመጨረሻም ተገዢዎቹ በታደሰችና በተባረከች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ’ ብለዋል።—በሰያፍ የጻፉት እሳቸው ናቸው።

በተመሳሳይም፣ ታዋቂ የሳይንስ ሊቅና ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የነበረው አይዛክ ኒውተን “ከፍርድ ቀን በኋላ ምድር ለ1,000 ዓመት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች” በማለት ጽፏል።

ምድር በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለምትሆን ከዚያ በኋላ ክፋት ጨርሶ አይኖርም። (ኢሳይያስ 11:1-5, 9) አዎን፣ ምድር ሙሉ በሙሉ ገነት በመሆን ለፈጣሪዋ ለዘላለም ውዳሴ ታመጣለች።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር?—ዘፍጥረት 1:28

▪ የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?—ማቴዎስ 6:10

▪ ወደፊት ክፋት ጨርሶ የማይኖረው ለምንድን ነው?—ኢሳይያስ 11:1-5, 9

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።” —ማቴዎስ 5:5