በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኤች አይ ቪ ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ደም አስተማማኝ ነው ሊባል ይችላል?

በኤች አይ ቪ ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ደም አስተማማኝ ነው ሊባል ይችላል?

በኤች አይ ቪ ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ደም አስተማማኝ ነው ሊባል ይችላል?

በናይጄሪያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

▪ ይህ አወዛጋቢ ጥያቄ የተነሳው ከናይጄሪያ ታዋቂ ሆስፒታሎች በአንዱ ውስጥ ደም የተሰጣት አንዲት ሕፃን በኤች አይ ቪ ተይዛ በመገኘቷ ነበር።

የሆስፒታሉ የሕክምና ዳይሬክተር እንደተናገሩት ከሆነ ኤኒዮላ የተባለችው ይህች ሕፃን ከተወለደች ብዙም ሳይቆይ በወፍ በሽታ መያዟን ማወቅ ተችሎ ነበር። ከዚያም ሐኪሟ ደሟ መለወጥ እንዳለበት ስለወሰነ አባቷ የተወሰነ ደም ለገሰ። ይሁን እንጂ የአባቷ ደም ከእሷ ደም ጋር የማይስማማ ሆኖ በመገኘቱ ከሆስፒታሉ የደም ባንክ በመውሰድ ደም ተሰጣት። ምንም እንኳ ሁለቱም ወላጆቿ ሲመረመሩ ኤች አይ ቪ እንደሌለባቸው ቢረጋገጥም ሕፃኗ ግን ደም ከተሰጣት በኋላ ብዙም ሳይቆይ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተገኘባት። ሆስፒታሉ እንደሚለው ከሆነ “ደሙ ለሕፃኗ ከመሰጠቱ በፊት ተመርምሮ ከኤች አይ ቪ ነፃ እንደሆነ ተረጋግጦ ነበር።”

ታዲያ ሕፃኗ እንዴት በበሽታው ልትያዝ ቻለች? የናይጄሪያ መንግሥት አወዛጋቢ የሆነውን ይህን ጉዳይ ከመረመረ በኋላ ሕፃኗ በበሽታው የተያዘችው በተሰጣት ደም ምክንያት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ። ናይጄሪያን ትሪቢዩን የተሰኘው ጋዜጣ የቫይረስ ተመራማሪ የሆኑ አንድ ሰው ያሉትን በመጥቀስ እንደዘገበው “ለጋሹ ደም የሰጠው በሰውነቱ ውስጥ ያሉት በኤች አይ ቪ መያዙን የሚያመለክቱት በሽታን የሚከላከሉ ፀረ እንግዳ አካላት [አንቲቦዲስ] በምርመራ ሊገኙ በማይችሉበት ጊዜ [ዊንዶው ፔሬድ] ላይ ነበር።”

ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ተከስቶ የማያውቅ ቢሆንም ደም መውሰድ አደጋ ያለው ለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል፣ ኤች አይ ቪ በደም ውስጥ መኖሩ የማይታወቅበትን ይህን ጊዜ አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል:- “በሽታን የመከላከል አቅማችን በምርመራው ወቅት ሊታዩ የሚችሉ በቂ ፀረ እንግዳ አካላትን እስኪያመርት ድረስ የተወሰነ ጊዜ ሊፈጅ የሚችል ሲሆን የጊዜው ርዝማኔ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ይህ ወቅት በእንግሊዝኛው በተለምዶ “ዊንዶው ፔሬድ” እየተባለ ይጠራል። አብዛኞቹ ሰዎች ሰውነታቸው በምርመራ ሊገኙ የሚችሉ በቂ ፀረ እንግዳ አካላትን ሊሠራ የሚችለው ቫይረሱ ወደ ሰውነታቸው ከገባ ከ2 እስከ 8 ሳምንታት ባሉት ጊዜያት (በአማካይ በ25 ቀናት) ውስጥ ነው። እንደዚያም ሆኖ አንዳንድ ግለሰቦች ሰውነታቸው በምርመራ ወቅት ሊገኙ የሚችሉ ፀረ እንግዳ አካላትን እስኪሠራ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ሊፈጅ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። . . . እምብዛም ያልተለመደ ቢሆንም አንዳንዴ እስከ 6 ወራት ሊፈጅ ይችላል።”

ስለዚህ የአንድ ሰው ደም የኤች አይ ቪ ምርመራ ተደርጎለት ከቫይረሱ ነፃ ነው ቢባል በኤድስ ላለመያዝ ዋስትና ይሆናል ማለት አይደለም። በሳን ፍራንሲስኮ የተቋቋመው ኤድስ ፋውንዴሽን እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል:- “በዊንዶው ፔሬድ ጊዜ ኤች አይ ቪ በምርመራ ሊገኝ ባይችልም እንኳ ቫይረሱ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል። እንዲያውም ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሽታውን ለሌሎች የሚያስተላልፉት በዚህ ወቅት ላይ (በኤች አይ ቪ ከተያዙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ) ነው።”

የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም ራቁ’ በማለት የሚሰጠውን መመሪያ ሲከተሉ ኖረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) ይህ መመሪያ ያስገኘላቸው ጥበቃ የአምላክን ትእዛዛት ማክበር የጥበብ እርምጃ እንደሆነ በጥብቅ አስገንዝቧቸዋል። በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? * የተሰኘውን ብሮሹር ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።