በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሴቶች አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋል?

ሴቶች አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሴቶች አገልጋዮች መሆን ይገባቸዋል?

“ለሴቶች የቅስና ማዕረግ በመስጠት ረገድ ምንም ለውጥ ባለመደረጉ ሲገርመኝና ስናደድ ኖሬያለሁ” በማለት አንዲት የካቶሊክ እምነት ተከታይ ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ ለተሰኘ ጋዜጣ ጽፋ ነበር። ብዙ ሰዎችም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። ደግሞም እኮ በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ሴቶች አገልጋዮች፣ ቄሶች፣ ጳጳሳትና ረቢዎች በመሆን ያገለግላሉ።

በሁለት ተቃራኒ ጎራ የተሰለፉት ማለትም ሴቶችን አገልጋዮች ሆነው መሾማቸውን የሚያወግዙም ሆኑ መድረክ ላይ ቆመው እንዲሰብኩ የሚፈቅዱላቸው ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥብቅ እንደሚከተሉ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሁለቱንም አመለካከት አይደግፍም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ “አገልጋይ” የሚለውን ቃል እንዴት እንደሚጠቀምበት መመልከት ይኖርብናል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አገልጋዮች

“አገልጋይ” የሚለው ቃል ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ብዙ ሰዎች ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ወንድም ይሁን ሴት ለአምልኮ የሚሰበሰብ ጉባኤን የሚያስተዳድር የሃይማኖት መሪ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን ሰፋ ባለ መንገድ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “በክንክራኦስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነችው እኅታችን” በማለት የጠራትን ፌበን የተባለችውን ክርስቲያን እንመልከት።—ሮሜ 16:1 አ.መ.ት

ስለ ፌበን ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው በክንክራኦስ ጉባኤ ፊት ቆማ ሃይማኖታዊ አገልግሎት ስታከናውን ነው? ፌበን ታከናውን የነበረው አገልግሎት ምን ነበር? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘[“ወንጌልን በማሰራጨት ረገድ፣” አ.መ.ት] ከጎኔ የተሰለፉት የሥራ ባልደረቦቼ’ በማለት ስለ አንዳንድ ሴቶች ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:2, 3

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በዋነኝነት ወንጌልን ያሠራጩ የነበረው “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” በማገልገል ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) በዚያ ሥራ የተካፈሉት ሁሉ አገልጋዮች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ጵርስቅላ ትገኝበታለች፤ ጵርስቅላና ባሏ ክርስቲያን ሆኖ ላልተጠመቀ አንድ ፈሪሃ አምላክ ላለው ሰው ‘የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራርተውለታል።’ (የሐዋርያት ሥራ 18:25, 26) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እንደ ፌበን ሁሉ ጵርስቅላና ሌሎች በርካታ ሴቶችም ውጤታማ አገልጋዮች ነበሩ።

የተከበረ የሥራ ድርሻ

ወንዶች ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ጉባኤውን የማስተዳደር ሥራ ስለሚያከናውኑ ሕዝባዊ አገልግሎት ለሴቶች የተሰጠ ዝቅተኛ ሥራ ነበር? በፍጹም! እንዲህ የምንልበት ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከባድ የጉባኤ ኃላፊነቶች ያሉባቸውን ወንዶችን ጨምሮ ሁሉም ክርስቲያኖች በሕዝባዊ አገልግሎት መካፈል እንዳለባቸው በግልጽ ይናገራል። (ሉቃስ 9:1, 2) ሁለተኛ፣ ሕዝባዊ አገልግሎት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ኢየሱስ ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ አስተምሯቸውም’ በማለት የሰጠውን ትእዛዝ የሚፈጽሙበት ዋነኛ መንገድ ነበር፤ ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20

አንዳንድ ሴቶች በጉባኤ ውስጥ የሚያከናውኑት አንድ ሌላ አስፈላጊ የሥራ ድርሻም አለ። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አረጋውያን ሴቶች . . . ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ ይህም ወጣት ሴቶችን ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ በመርዳት ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ . . . እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላቸዋል።” (ቲቶ 2:3, 4) በመሆኑም በክርስቲያናዊ ሕይወት ተሞክሮ ያካበቱ የጎለመሱ ሴቶች እምብዛም ተሞክሮ የሌላቸውን ወጣት ሴቶች ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ የመርዳት መብት አላቸው። ይህም ቢሆን የተከበረና ክብደት የሚሰጠው የሥራ ድርሻ ነው።

በጉባኤ ውስጥ ማስተማር

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሴቶች በጉባኤ ፊት ቆመው እንዲያስተምሩ የተነገረበት አንድም ቦታ የለም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶች “በጉባኤ ውስጥ ዝም ይበሉ” በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል። ለምን? አንዱ ምክንያት “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት” መከናወን እንዲችል እንደሆነ ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 14:34, 40) ጉባኤው ተግባሩን በጥሩ ሁኔታ እንዲያከናውን አምላክ የማስተማርን ሥራ የሰጠው ለአንድ ቡድን ነው። ይሁንና አንድ ሰው ወንድ ስለሆነ ብቻ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንደማይሰጠው ልብ በል፤ ይህ ኃላፊነት የሚሰጠው ብቃቱን በሚገባ ለሚያሟሉ ወንዶች ነው። *1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9

ታዲያ አምላክ ለሴቶች የሰጣቸው የሥራ ድርሻ ዝቅ የሚያደርጋቸው ነው? በጭራሽ። ይሖዋ አምላክ ሴቶች ስለ እሱ በሕዝብ ፊት ምሥክርነት እንዲሰጡ ከፍ ያለ የሥራ ድርሻ እንደሰጣቸው አስታውስ። (መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም) በዛሬው ጊዜ ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያከናውኑ ወንድና ሴት የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለንስሐ እንዲበቁና መዳንን እንዲያገኙ ረድተዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:21፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) ይህ ደግሞ ቀላል ግምት የሚሰጠው ሥራ አይደለም!

ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የተሰጠው የሥራ ድርሻ ለሁለቱም ክብር የሚሰጥ ሲሆን ሰላምን ያሰፍናል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ሰው የትራፊክ መጨናነቅ በበዛበት መንገድ ለመሻገር ዓይኖቹና ጆሮዎቹ ተቀናጅተው ይሠራሉ። በተመሳሳይም ወንዶችና ሴቶች እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው የሥራ ድርሻ መሠረት የአምላክን ፈቃድ ሲፈጽሙ አምላክ ጉባኤውን ሰላም በመስጠት ይባርከዋል።—1 ቆሮንቶስ 14:33፤ ፊልጵስዩስ 4:9 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 አንድ ወንድ በጉባኤ ውስጥ ያለው ሥልጣን ውስን መሆኑንም ልብ በል። ለክርስቶስ የሚገዛ ሲሆን ሥራውን ማከናወን ያለበት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በተጨማሪም የጉባኤ ኃላፊነት ያለባቸው ወንዶች ትሕትናና የትብብር መንፈስ በማሳየት ‘አንዳቸው ለሌላው መገዛት’ አለባቸው።—ኤፌሶን 5:21

^ አን.15 ክርስቲያን ሴቶች፣ አምላክ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ እንዲያከናውኑት የሰጣቸውን የሥራ ድርሻ ሲያከብሩ በሰማይ ላሉ መላእክት አርዓያ ይሆናሉ።—1 ቆሮንቶስ 11:10

ይህን አስተውለኸዋል?

● በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሴቶች ያስተምሩ የነበረው እንዴት ነው?—የሐዋርያት ሥራ 18:26

● በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች እንዲሆኑ የሚሾሙት እነማን ናቸው?—1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

● አምላክ ክርስቲያን ሴቶች በዛሬ ጊዜ የሚያከናውኑትን አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል?—መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ።” —መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም