በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ኢኳዶር

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ኢኳዶር

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ኢኳዶር

ብሩኖ የተባለ በጣሊያን የሚኖር አንድ ወጣት ወንድም ከተለያየ አቅጣጫ ጫና ይደረግበት ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት ሲያጠናቅቅ ዘመዶቹና አስተማሪዎቹ ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተል ተጽዕኖ አድርገውበት ነበር። ይሁን እንጂ ብሩኖ ከጥቂት ዓመታት በፊት ራሱን ለይሖዋ ሲወስን በሕይወቱ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የአምላክን ፈቃድ ለማስቀደም ቃል ገብቷል። ታዲያ ምን ምርጫ አደረገ? እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል እንደምጠብቅና በሕይወቴ ውስጥ አንደኛውን ቦታ ለእሱ እንደምሰጠው ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት። ነገር ግን አሰልቺ የሆነ ሕይወት መምራት እንደማልፈልግ፣ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ የማቀርበው አገልግሎት አስደሳችና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያቀፈ ቢሆን ደስ እንደሚለኝ በጸሎቴ ውስጥ በሐቀኝነት ገለጽኩ።”

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ብሩኖ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ በምትገኘው በኢኳዶር ማገልገል ጀመረ። ብሩኖ “ይሖዋ ከጠበቅሁት በላይ ለጸሎቴ መልስ ሰጥቶኛል” በማለት ተናግሯል። ኢኳዶር ሲደርስ ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ ወደዚህ አገር የተዛወሩ ብዙ ወጣቶችን በማግኘቱ በጣም ተገረመ።

‘ይሖዋን የፈተኑ’ ወጣቶች

ብሩኖን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ይሖዋ ያቀረበውን የሚከተለውን ግብዣ ተቀብለዋል፦ “በዚህ [ፈትኑኝ]፤ . . . የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።” (ሚል. 3:10) እነዚህ ወጣቶች ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር የተነሳ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር በመሄድ የእሱን ፈቃድ ለማራመድ ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን በፈቃደኝነት ሰጥተዋል፤ በዚህም መንገድ ይሖዋን ፈትነዋል።

እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ አዲሱ ምድባቸው ሲደርሱ “አዝመራው ብዙ . . . ሠራተኞቹ ግን ጥቂት” መሆናቸውን በገዛ ዓይናቸው መመልከት ችለዋል። (ማቴ. 9:37) ለምሳሌ ያህል፣ ከጀርመን የመጣችው ዣክሊን በኢኳዶር ላለው ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው በማለት የተሰማትን ደስታ ገልጻለች፦ “በኢኳዶር ሳገለግል ገና ሁለት ዓመቴ ነው፤ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ያሉኝ ሲሆን 4ቱ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። ደስ አይልም?” ከካናዳ የመጣችው ሾንታል እንደሚከተለው በማለት ትናገራለች፦ “በ2008፣ በኢኳዶር የባሕር ጠረፍ ላይ ወደሚገኝና አንድ ጉባኤ ብቻ ወዳለበት አካባቢ ተዛውሬ ማገልገል ጀመርኩ። በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ ሦስት ጉባኤዎችና ከ30 የሚበልጡ አቅኚዎች አሉ። ብዙ አዳዲስ ሰዎች እድገት ሲያደርጉ ከማየት የበለጠ ነገር የለም!” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በቅርቡ በአንዴስ ተራሮች ላይ ወደምትገኝና 2,743 ሜትር ከፍታ ወዳላት አንዲት ከተማ ተዛውሬያለሁ። የከተማዋ ነዋሪዎች ከ75,000 በላይ ቢሆኑም በዚያ ያለው ጉባኤ ግን አንድ ብቻ ነው። በጣም ፍሬያማ ክልል ነው! በአገልግሎቴም በጣም ደስተኛ ነኝ!”

ተፈታታኝ ሁኔታዎች

እርግጥ ነው፣ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ማገልገል የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳሉት አይካድም። እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ወዳሰቡት ቦታ ከመሄዳቸው በፊትም ጭምር እንቅፋቶች ያጋጥሟቸዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣችው ኬይላ እንዲህ ብላለች፦ “በአገሬ ሳለሁ አንዳንድ ወንድሞች በቅንነት የሰነዘሯቸው አሉታዊ አስተያየቶች ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ። ወደ ሌላ አገር ሄጄ በአቅኚነት ማገልገል የፈለግኩት ለምን እንደሆነ አልገባቸውም። በዚህም የተነሳ ‘ያደረግኩት ውሳኔ ትክክል ነው?’ የሚል ሐሳብ አንዳንድ ጊዜ ይመጣብኝ ነበር።” ያም ሆኖ ኬይላ ለመሄድ ወሰነች። እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች፦ “በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ መጸለዬና ከጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ጋር በደንብ መወያየቴ ይሖዋ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎችን የሚባርክ መሆኑን እንዳስተውል ረድቶኛል።”

ለብዙዎች እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ አዲስ ቋንቋ መማር ነው። ከአየርላንድ የመጣችው ሻቦን እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦ “ሐሳቤን መግለጽ አለመቻሌ ለእኔ ከባድ ነበር። በትዕግሥት የመጠበቅን ዝንባሌ ማዳበር፣ ቋንቋውን በትጋት ማጥናት እንዲሁም ስሳሳት በራሴ መሳቅ ነበረብኝ።” ከኢስቶኒያ የመጣችው አና ደግሞ እንደሚከተለው ብላለች፦ “ከሙቀቱ፣ ከአቧራውና ሙቅ ሻወር ከማጣት በላይ የከበደኝ ስፓንኛ መማር ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይሰማኝ ነበር። በስህተቶቼ ላይ ሳይሆን በማደርገው መሻሻል ላይ ማተኮር ነበረብኝ።”

ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ ናፍቆት ነው። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣው ጆናታን እንደሚከተለው በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “የተመደብኩበት ቦታ እንደደረስኩ ከጓደኞቼና ከቤተሰቤ በመለየቴ ሆድ ባሰኝ። ይሁን እንጂ በግል ጥናቴና በአገልግሎቴ ላይ በማተኮር ይህን ስሜት ማሸነፍ ችያለሁ። ብዙም ሳይቆይ ከአገልግሎት ያገኘኋቸው አስደሳች ተሞክሮዎችና በጉባኤ ያፈራኋቸው አዳዲስ ጓደኞች ደስታዬን መልሼ እንዳገኝ ረድተውኛል።”

ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ የኑሮው ሁኔታ ነው። በምትሄዱበት አካባቢ ያለው ሕይወት የለመዳችሁት ዓይነት ላይሆን ይችላል። ከካናዳ የመጣው እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “በአገራችሁ ሳላችሁ እንደ ኤሌክትሪክና የቧንቧ ውኃ ያሉትን መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደ ቀላል ነገር ትመለከቷቸዋላችሁ። እዚህ ግን እንደልብ አይገኙም።” ከዚህም ሌላ በማደግ ላይ ባሉ ብዙ አገሮች ውስጥ ድህነት፣ ምቹ ያልሆነ መጓጓዣ እንዲሁም ብዙ ሰዎች ማንበብና መጻፍ አለመቻላቸው በጣም የተለመዱ ነገሮች ናቸው። ከኦስትሪያ የመጣችው ኤንስ የአካባቢው ሕዝብ ባሉት መልካም ባሕርያት ላይ በማተኮሯ እንዲህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ፣ ደግ፣ ተባባሪ እንዲሁም ትሑት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ስለ አምላክ ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አለው።”

‘ማስቀመጫ እስኪጠፋ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት’ ማግኘት

ከላይ የተጠቀሱት ወጣቶች በሙሉ፣ በኢኳዶር ለማገልገል ሲሉ መሥዋዕትነት ቢከፍሉም ይሖዋ ከጠበቁት “በላይ እጅግ አብልጦ” እንደሚሰጥ ተገንዝበዋል። (ኤፌ. 3:20) በእርግጥም ‘ማስቀመጫ እስኪያጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት’ እንዳገኙ ይሰማቸዋል። (ሚል. 3:10) እነዚህ ወጣቶች ስለ አገልግሎታቸው የተሰማቸውን ነገር ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦

ብሩኖ፦ “ኢኳዶር ውስጥ ማገልገል የጀመርኩት አስገራሚ በሆነው የአማዞን ክልል ነበር። ከጊዜ በኋላም የኢኳዶርን ቅርንጫፍ ቢሮ የማስፋፋቱ ሥራ ሲከናወን ተሳትፎ አድርጌያለሁ። አሁን በቤቴል እያገለገልኩ ነው። በጣሊያን ሳለሁ በሕይወቴ ውስጥ ይሖዋን ለማስቀደም ወስኜ ነበር፤ ይሖዋም ቢሆን ለእሱ የማቀርበው አገልግሎት አስደሳችና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያቀፈ እንዲሆን በማድረግ ምኞቴን ፈጽሞልኛል።”

ቦ፦ “በኢኳዶር ጊዜዬን በሙሉ የማሳልፈው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በመሆኑ ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ችያለሁ። እግረ መንገዴንም ውብ የሆኑ ቦታዎችን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቻለሁ፤ ይህ ደግሞ ሁልጊዜ የምመኘው ነገር ነበር።”

አና፦ “እንደ እኔ ያለች ነጠላ እህት የሚስዮናዊ ዓይነት ሕይወት መምራት ትችላለች ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። አሁን ግን የሚቻል ነገር እንደሆነ ተረድቻለሁ። ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና ደቀ መዛሙርት በማድረጉና የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባቱ ሥራ በመካፈሌ እንዲሁም አዳዲስ ጓደኞችን በማፍራቴ በጣም ተደስቻለሁ።”

ኤልክ፦ “በትውልድ አገሬ በኦስትሪያ ሳለሁ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንኳ እንዲሰጠኝ ብዙ ጊዜ ይሖዋን በጸሎት እጠይቀው ነበር። እዚህ ከመጣሁ በኋላ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አግኝቻለሁ! የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ በሚማሩት ነገር ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ማየቴ ትልቅ እርካታ ሰጥቶኛል።”

ጆል፦ “ይሖዋን ለማገልገል ሲባል ወደማያውቁት ቦታ መሄድ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ከምንጊዜውም የበለጠ በእሱ መመካት እንዳለባችሁ ትማራላችሁ፤ ይሖዋ ጥረታችሁን ሲባርከው ማየት በጣም ያስደስታል! ከዩናይትድ ስቴትስ ወደዚህ አገር በመጣሁ በዓመቴ በማገለግልበት ቡድን ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች ቁጥር ከ6 ወደ 21 አድጓል። የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ያከበርነው 110 ሆነን ነው።”

አንተስ?

እናንት ወጣቶች፣ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ወይም አገር ሄዳችሁ ለማገልገል ሁኔታችሁ ይፈቅድላችኋል? እርግጥ ነው፣ እንዲህ የመሰለ ትልቅ ውሳኔ ማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ ማውጣት ይጠይቃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ለይሖዋና ለሰዎች ጠንካራ ፍቅር ማዳበር አስፈላጊ ነው። ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር ካላችሁና ብቃቱን የምታሟሉ ከሆነ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቃችሁ ጸልዩ። በተጨማሪም ይህን ፍላጎታችሁን አስመልክታችሁ ክርስቲያን ከሆኑ ወላጆቻችሁና ከጉባኤያችሁ ሽማግሌዎች ጋር ተወያዩ። እናንተም አስደሳችና አርኪ በሆነው በዚህ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ትወስኑ ይሆናል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ መጸለዬና ከጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ጋር በደንብ መወያየቴ ይሖዋ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎችን የሚባርክ መሆኑን እንዳስተውል ረድቶኛል።”​—ኬይላ ከዩናይትድ ስቴትስ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ለማገልገል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

• ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር

በነሐሴ 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ከገጽ 4-6 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች መከለስ

• በሌላ አካባቢ ካገለገሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር መወያየት

• ልትሄዱበት ያሰባችሁትን አካባቢ ባሕልና ታሪክ ማጥናት

• በአካባቢው ስለሚነገረው ቋንቋ መሠረታዊ እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በሌላ አካባቢ የሚያገለግሉ አንዳንዶች ራሳቸውን በገንዘብ ለመደገፍ . . .

• በየዓመቱ ወደ ትውልድ አገራቸው በመሄድ ለጥቂት ወራት ይሠራሉ

• ቤታቸውን ወይም ንግዳቸውን ያከራያሉ

• በኢንተርኔት አማካኝነት ሥራቸውን ያከናውናሉ

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1 ዣክሊን ከጀርመን

2 ብሩኖ ከጣሊያን

3 ቦ ከካናዳ

4 ሻቦን ከአየርላንድ

5 ጆል ከዩናይትድ ስቴትስ

6 ጆናታን ከዩናይትድ ስቴትስ

7 አና ከኢስቶኒያ

8 ኤልክ ከኦስትሪያ

9 ሾንታል ከካናዳ

10 ኤንስ ከኦስትሪያ