በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት

ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት

ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት

በሰው በተጨናነቀ የመጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ አንዲት እናት “መደርደሪያዎቹ በመጻሕፍት ተሞልተዋል፤ ልጄን የሚረዳ ግን አንድም መጽሐፍ የላችሁም!” በማለት መጽሐፍ የምትሸጠው ሴት ላይ ጮኸችባት። ይህች እናት የቅርብ የቤተሰባቸው አባል በድንገት በመሞቱ ምክንያት ልጇ ያጋጠመውን ሐዘን እንዲቋቋም ለመርዳት የሚያስችላትን ምክር ለማግኘት ፈልጋ ነበር።

ይህች እናት መጨነቋ ተገቢ ነው። አንድ ልጅ የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ ከፍተኛ ሐዘን ይሰማዋል። እርግጥ ነው፣ ልጆች የቤተሰባቸውን እንክብካቤ እያገኙ ያድጋሉ፤ ሆኖም ከቤተሰባቸው መካከል በጣም የሚቀርቡትንና የሚወዱትን ሰው ሞት ሊነጥቃቸው ይችላል። ታዲያ ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን እንዲህ ያለው ሁኔታ መከሰቱ የማይቀር በሚሆንበት ጊዜ ወይም ሲከሰት ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

እውነት ነው፣ የምትወዱትን ሰው በሞት ስታጡ በሐዘን ከመዋጣችሁ የተነሳ ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ላትሰጡ ትችላላችሁ። ያም ሆኖ ልጃችሁ የእናንተ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አትዘንጉ። በሚኒሶታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ በማይድን በሽታ ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ የሚያደርግ ተቋም ያዘጋጀው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “አብዛኛውን ጊዜ ልጆች፣ ሌሎች ሰዎች የሚያወሩትን ነገር በጨረፍታ በመስማት የተዛባ አሊያም የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም ልጆች እውነቱ ሊነገራቸው ይገባል።” በዚህም የተነሳ የልጆቻችሁን የመረዳት ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሁኔታውን በግልጽ መንገራችሁ ጥበብ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ልጆች የተከሰተውን ነገር የመረዳት ችሎታቸው በእጅጉ ስለሚለያይ ይህን ማድረጉ ቀላል አይደለም።—1 ቆሮንቶስ 13:11

የሞትን ምንነት ማስረዳት

ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ስለ ሞት ሲያስረዱ “ተኝቷል፣” “ጠፍቷል” ወይም “ሄዷል” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን ከመጠቀም መቆጠብ እንዳለባቸው አንዳንድ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። ስለ ሁኔታው በደንብ ሳያስረዱ በእነዚህ አባባሎች መጠቀም ልጆችን ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ስለ ሞት ሲናገር እንቅልፍን እንደ ምሳሌ የተጠቀመ ሲሆን እንዲህ ማድረጉም ተገቢ ነበር። ይሁንና ይህን የተናገረው ለልጆች እንዳልነበር አስታውሱ። ከዚህም በተጨማሪ ስለተናገረው ነገር ማብራሪያ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል” ብሏቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ትልልቅ ሰዎች ቢሆኑም ኢየሱስ “እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ [መስሏቸው]” ነበር። በመሆኑም “አልዓዛር ሞቶአል” በማለት በግልጽ ነገራቸው። (ዮሐንስ 11:11-14) ትልልቅ ሰዎች እንዲህ ያለ ግልጽ ማብራሪያ ካስፈለጋቸው ልጆች ደግሞ የበለጠ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው።

ሜሪ አን ኤምስዊለር እና ጄምስ ኤምስዊለር የተባሉ ጸሐፊዎች እንዲህ ብለዋል:- “አንዲት ወላጅ ለልጇ ስለ ሞት ስታስረዳ ለስለስ ያሉ ቃላትን ለመጠቀም ትሞክር ይሆናል። እንዲህ ማድረጓ ግን ከዚህ በፊት አስቦት የማያውቀው እንዲሁም አስፈሪና ጎጂ የሆነ ሐሳብ በልጇ አእምሮ ውስጥ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።” ለምሳሌ ያህል፣ የሞተው ሰው ‘ተኝቷል’ ተብሎ የተነገረው ልጅ እሱም ከተኛ እንደማይነቃ በማሰብ ማታ አልተኛም ሊል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሞተው ሰው ሩቅ ቦታ “ሄዷል” ተብሎ የተነገረው ልጅ እንደማይፈለግ ወይም እንደተተወ ይሰማው ይሆናል።

በርካታ ወላጆች ለልጆች ስለ ሞት ሲያስረዱ ውስብስብ ሐሳቦችን ከመናገር ይልቅ ቀላልና ቀጥተኛ ቃላትን መጠቀማቸው የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። (1 ቆሮንቶስ 14:9) ልጃችሁ ጥያቄ እንዲጠይቅና የሚያሳስበውን ነገር እንዲናገር ማበረታታት ጠቃሚ መሆኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ከልጃችሁ ጋር አዘውትራችሁ መወያየታችሁ ግልጽ ያልሆኑለትን ነገሮች ለማስረዳትና እሱን ለመርዳት የሚያስችሏችሁን ሌሎች መንገዶች ለማስተዋል አጋጣሚ ይሰጣችኋል።

አስተማማኝ መመሪያ

በሐዘኑ ወቅት ልጃችሁ መመሪያ፣ ድጋፍና ለጥያቄዎቹ መልስ እንድትሰጡት ይፈልጋል። ታዲያ ሞትን በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የምትችሉት ከየት ነው? ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛና አስተማማኝ ተስፋ አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት አመጣጥ፣ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስላላቸው ተስፋ የማያሻማ መረጃ ይዟል። ልጃችሁ ‘ሙታን ምንም እንደማያውቁ’ መገንዘቡ በሞት ያጣው የሚወደው ሰው እየተሠቃየ እንዳልሆነ እንዲያስተውል ይረዳዋል። (መክብብ 9:5) መጽሐፍ ቅዱስ በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ እንደምናገኛቸው ተስፋ ይሰጠናል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ከቅዱሳን መጻሕፍት መመሪያ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ እንዲሁም ማጽናኛ ሊሰጥ የሚችል መሆኑን ልጅህ እንዲማር ይረዳዋል። እንዲህ ማድረጋችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ቃል ዞር እንደምትሉ እንዲያስተውል ይረዳዋል።—ምሳሌ 22:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15

ለአንዳንድ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች

ልጃችሁ የሚወደውን ሰው በሞት ማጣቱ ያስከተለበትን ሐዘን እንዲቋቋም ለመርዳት ስትጥሩ ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች ያጋጥሟችሁ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? * ብዙ ጊዜ ከሚያጋጥሙ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

ሐዘኔን በልጄ ፊት ከመግለጽ መቆጠብ ይኖርብኛል? ልጃችሁን ከጉዳት ለመጠበቅ መፈለጋችሁ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ልጃችሁ ስታዝኑ ማየቱ ስህተት ነው? በርካታ ወላጆች ሐዘናቸውን ለመደበቅ አለመሞከራቸው የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። ይህም ሐዘንን መግለጽ ምንም ስህተት እንደሌለው ልጃቸው እንዲረዳ ያስችለዋል። አንዳንድ ወላጆች፣ ሐዘናቸውን በሌሎች ፊት ስለገለጹ ሰዎች የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አንስተው ከልጆቻቸው ጋር ይወያያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ እንባውን ያፈሰሰ ሲሆን ስሜቱንም ለመደበቅ አልሞከረም።—ዮሐንስ 11:35

ልጄ በቀብር ሥነ ሥርዓት ወይም በቀብር ንግግር ላይ መገኘት ይኖርበታል? ልጁ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኝ ከሆነ እንዲህ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ጨምሮ በዚያ ምን ነገሮች እንደሚከናወኑ አስቀድሞ መንገሩ ጥበብ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ወላጆች በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ ልጆቻቸው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳይገኙ ይወስኑ ይሆናል። በይሖዋ ምሥክሮች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙ ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ ከሚሰጠው ንግግር ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በተገኙት ሰዎች መካከል የሚታየው ፍቅር ልጆችን ሳይቀር ሊያጽናናቸው ይችላል።—ሮሜ 12:10, 15፤ ዮሐንስ 13:34, 35

ስለሞተው ሰው ከልጄ ጋር ማውራት ይኖርብኛል? አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ ስለዚህ ጉዳይ ፈጽሞ የማታወራ ከሆነ ልጅህ ስለሞተው ሰው አንድ ነገር እየደበቅከው እንዳለህ አሊያም የሞተውን ሰው ሙሉ በሙሉ ለመርሳት እንደምትጥር ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ጁሊያ ራትኪ የተባሉ ደራሲ “ስለ ሟቹ ባላቸው ትዝታ ሳይረበሹና ሳይፈሩ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ልጆችን ማስተማር በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል። የሞተውን ሰው መልካም ጎን አንስቶ ማውራትን ጨምሮ ስለ ግለሰቡ በግልጽ መነጋገር ልጆች ሐዘናቸውን እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች፣ ሕመምና ሞት በማይኖርባት ገነት በሆነች ምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚኖር ስለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በመናገር ልጆቻቸውን ሊያጽናኗቸው ይችላሉ።—ራእይ 21:4

ልጄ ሐዘኑን እንዲቋቋም እንዴት መርዳት እችላለሁ? በሐዘን ምክንያት ልጃችሁ ጤናው ሊታወክ ይችላል። በዚህ ጊዜ እንደተተወ ስለሚሰማው ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለሚያድርበት ሊናደድ ወይም ሊረበሽ ይችላል። የጥፋተኝነት ስሜት ቢሰማው፣ ከአጠገባችሁ መለየት ባይፈልግ ወይም ዘግይታችሁ ስትመጡ አሊያም ስትታመሙ በጣም ቢረበሽ ሊገርማችሁ አይገባም። ታዲያ ልጃችሁን ማረጋጋት የምትችሉት እንዴት ነው? ልጃችሁ መረበሹን እንዳልተረዳችሁለት ሆኖ ሊሰማው አይገባም። በመሆኑም ስሜቱን ለመረዳት ንቁ መሆንና ሁኔታውን በትኩረት መከታተል ይኖርባችኋል። ልጃችሁ በሐዘኑ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት አቅልላችሁ አትመልከቱ። አዘውትራችሁ አጽናኑት እንዲሁም ጥያቄዎችን እንዲጠይቅና ሐሳቡን በግልጽ እንዲነግራችሁ አበረታቱት። ‘ቅዱሳን መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናኛ’ በመጠቀም የልጃችሁንም ሆነ የእናንተን ተስፋ ብሩህ ለማድረግ ጣሩ።—ሮሜ 15:4

ቤተሰቡ የተለመዱትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ማከናወን መጀመር ያለበት መቼ ነው? በሥራ መጠመድ ጥሩ እንደሆነ ምሑራን ይገልጻሉ። ጠቃሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ሐዘናችንን ለመቋቋም የሚረዳ ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ ይነገራል። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ በርካታ ወላጆች፣ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ መልክ አዘውትሮ ማጥናትንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ጨምሮ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመድ ቤተሰቡ እንዲረጋጋና ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያደርግ ተገንዝበዋል።—ዘዳግም 6:4-9፤ ዕብራውያን 10:24, 25

ይሖዋ አምላክ ሕመምንና ሞትን የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ልጆች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው በሚያስከትልባቸው ሐዘን መጎዳታቸው አይቀርም። (ኢሳይያስ 25:8) ይሁንና ልጆች ጥሩ ማጽናኛና ድጋፍ ካገኙ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች እንደ ሕግ ሆነው የሚያገለግሉ አይደሉም። ሁኔታዎችና ልማዶች እንደየአካባቢውና እንደየባሕሉ ሊለያዩ እንደሚችሉ ልብ ማለት ይገባል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልጃችሁ ጥያቄ እንዲጠይቅና የሚያሳስበውን ነገር እንዲናገር አበረታቱት

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ጨምሮ በሌሎች እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ