በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ቀን

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ቀን

130ኛው የጊልያድ ምረቃ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ቀን

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ130ኛው ክፍል የምረቃ ፕሮግራም በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ቅዳሜ መጋቢት 12, 2011 በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተማሪዎቹን እንዲሁም የተማሪዎቹን ቤተሰቦችና ጓደኞች ጨምሮ ከ8,500 የሚበልጡ ሰዎች ተገኝተዋል። በዕለቱ የተገኙት በሙሉ በጣም ተደስተው ነበር፤ የደስታቸው ምክንያት ተማሪዎቹ ለዚህ ዕለት መብቃታቸው ብቻ ሳይሆን በሚገባ የሠለጠኑት እነዚህ ሚስዮናውያን ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር በቅርቡ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመሄድ ዝግጁ መሆናቸው ነው።

ይሖዋን “የሚጠባበቁ” ሁሉ ደስተኞች ናቸው

ከ⁠ኢሳይያስ 30:18 ላይ የተወሰደው ይህ የሚያጽናና ሐሳብ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባልና የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው ጄፍሪ ጃክሰን ያቀረበው ንግግር ጭብጥ ነው። ወንድም ጃክሰን ንግግሩን የከፈተው ሞቅ ባለና ፈገግ በሚያሰኝ መንገድ ነበር፤ ተማሪዎቹ ጭንቀቱ ሳይገድላቸው ጠጠር ያለውን የጊልያድ ኮርስ በማጠናቀቅ ለዚህ ቀን በመብቃታቸው ደስታውን የገለጸ ከመሆኑም ሌላ የዛሬውንም ቀን እንዲሁ ‘በሕይወት እንደሚያልፉ’ እርግጠኛ መሆኑን ገለጸ። ተማሪዎቹ ወደፊት ምን መጠበቅ ይችላሉ? በ⁠ኢሳይያስ 30:18-21 ላይ ተመሥርቶ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ሐሳቦችን አብራርቷል።

በመጀመሪያ ደረጃ ወንድም ጃክሰን “ይሖዋ ጸሎታችሁን እንደሚሰማ መጠበቅ ትችላላችሁ” በማለት ተናገረ። በቁጥር 19 ላይ የሚገኘውን “[አምላክ] ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁም!” የሚለውን ማረጋገጫ ጠቀሰ። ጥቅሱ አምላክ ምሕረት የሚያሳየው ለብዙ ሰዎች እንደሆነ አድርጎ ቢገልጽም በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅጂ ላይ ይህ ሐሳብ የተገለጸው በብዙ ቁጥር ሳይሆን በነጠላ ቁጥር መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ወንድም ጃክሰን ይህን ነጥብ በመጥቀስ ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን በቡድን ደረጃ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ መሆኑን ተናገረ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ አባት እንደመሆኑ መጠን ‘ለምንድን ነው እንደ እገሌ ጠንካራ የማትሆነው?’ አይለንም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳችንን ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጣል። መልስም ይሰጣል።”

በሁለተኛ ደረጃ ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ መጠበቅ እንዳለብን ተናገረ። “ይሖዋ ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ቃል አልገባልንም፤ ሊረዳን ግን ዝግጁ ነው።” ቁጥር 20 እንደሚያሳየው አምላክ እስራኤላውያን በጠላት እጅ በሚወድቁበት ጊዜ ጭንቀትና መከራ የእንጀራና የውኃ ያህል በየዕለቱ እንደማይለያቸው ትንቢት ተናግሮ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ይሖዋ ሕዝቡን ለመታደግ ምንጊዜም ዝግጁ ነበር። የጊልያድ ተማሪዎችም ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል! እርግጥ ነው፣ የሚያጋጥማቸው ሁኔታ የጠበቁት ዓይነት ላይሆን ይችላል። ወንድም ጃክሰን አክሎ “ሆኖም ይሖዋ የሚያጋጥማችሁን እያንዳንዱን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም እንድትችሉ እናንተን ለመርዳት ከጎናችሁ እንደሚሆን መጠበቅ ትችላላችሁ” በማለት ተናገረ።

በሦስተኛ ደረጃ ወንድም ጃክሰን ቁጥር 20⁠ን እና 21⁠ን በመጥቀስ ተማሪዎቹን “መመሪያ እንደምታገኙ መጠበቅ ትችላላችሁ፤ እንግዲያው ይህን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርጉ!” ሲል አበረታታቸው። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው በተዘጋጁ ጽሑፎች አማካኝነት የሚሰጠውን ምክርና መመሪያ በጥንቃቄ መከተል እንዳለበት ገለጸ። ወንድም ጃክሰን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ የሕይወት ጉዳይ እንደሆነ በመናገር ተማሪዎቹ ይህን እንዲያደርጉ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጣቸው።

ይሖዋን “መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን”

የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ “እግዚአብሔርን መፍራት” የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው አባባል ምን ትርጉም እንዳለው አብራራ። (2 ዜና መዋዕል 19:7) ይህ አገላለጽ የሚያርበደብድ ዓይነት ፍርሃትን የሚያመለክት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ካለን ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭን እንዲሁም ጥልቅና ልባዊ ከሆነ አክብሮት የሚመጣን የፍርሃት ስሜት የሚያመለክት ነው። ወንድም ሞሪስ “በተመደባችሁበት ቦታ በምታገለግሉበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ፍርሃት ይኑራችሁ” በማለት ተማሪዎቹን መከራቸው። ታዲያ ተማሪዎቹ ለይሖዋ እንዲህ ያለ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ወንድም ሞሪስ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ነጥቦችን ጠቀሰ።

በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎቹ በ⁠ያዕቆብ 1:19 ላይ የሚገኘውን “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ አበረታታቸው። ተማሪዎቹ ለአምስት ወር በተከታተሉት ኮርስ ብዙ ነገሮችን እንደተማሩ ከገለጸ በኋላ ወደ ተመደቡበት ቦታ ሲሄዱ የተማሩት ነገር ለኩራት ምክንያት እንዳይሆናቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸው ነገራቸው። “በመጀመሪያ ማዳመጥ ይኖርባችኋል” አላቸው። ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የምታገለግሉበት ጉባኤና በአገሪቱ የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት የሚመሩት ወንድሞች የሚነግሯችሁን አዳምጡ፤ ስለ አገሪቱና ስለ ባሕሉ የሚነግሯችሁን ነገር አዳምጡ። ‘አላውቅም’ ማለት ሊያሳፍራችሁ አይገባም። የተማራችሁት ትምህርት በደንብ ገብቷችኋል የሚባለው ይበልጥ ባወቃችሁ መጠን የምታውቁት ነገር በጣም ኢምንት መሆኑን መገንዘብ ከቻላችሁ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ወንድም ሞሪስ ምሳሌ 27:21⁠ን ጠቀሰ፤ ጥቅሱ “ብር በማቅለጫ፣ ወርቅ በከውር እንደሚፈተን፣ ሰውም በሚቀበለው ምስጋና ይፈተናል” ይላል። ወርቅና ብር መፈተን ወይም መንጠር እንዳለባቸው ሁሉ እኛም የምንቀበለው ምስጋና ማንነታችንን እንደሚፈትን አብራራ። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ምስጋና ትክክለኛው ባሕርያችን እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል። በአንድ በኩል ኩራት እንዲሰማን በማድረግ ለመንፈሳዊ ውድቀት ሊዳርገን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች የአመስጋኝነት ስሜት እንዲያድርብንና የእሱን መሥፈርቶች ጠብቀን ለመኖር ይበልጥ እንድንነሳሳ ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም ወንድም ሞሪስ ተማሪዎቹ ምስጋና በሚቀርብላቸው ጊዜ ሁሉ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ይኸውም ‘ይሖዋን የሚፈሩ’ መሆናቸውን ለማሳየት እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገው እንዲያዩት አበረታታቸው።

“ተልዕኳችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ”

የበላይ አካል አባል የሆነው ጋይ ፒርስ የፕሮግራሙን ዋና ንግግር አቀረበ። ወንድም ፒርስ ከላይ የቀረበው ጭብጥ ላይ የተመሠረተውን ንግግር በሚያቀርብበት ጊዜ “ሚስዮናዊ” የሚለው ቃል “አንድን ተልዕኮ ለመፈጸም የተላከ” የሚል ትርጉም እንዳለው አብራራ። ከዚያም የተለያየ ተልዕኮ ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሚስዮናውያን መኖራቸው ምንም እንደማያስደንቅ ተናገረ። ብዙዎቹ ሚስዮናውያን ሰዎችን ከሕመማቸው በመፈወስ ላይ የሚያተኩሩ ከመሆኑም በላይ በዓለም ላይ ለሚታዩት ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲፈልጉ ይስተዋላል። ወንድም ፒርስ “የእናንተ ተልዕኮ ግን የተለየ ነው” አላቸው። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

ተማሪዎቹ ስለ አካላዊ ፈውስ የሚያወሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዘገባዎችን አጥንተዋል። ኢየሱስ አንዲትን ልጅ ከሞት ባስነሳበት ጊዜ የልጅቷ ወላጆች “የሚሆኑት እስኪጠፋቸው ድረስ በጣም [ተደስተው]” ነበር። (ማርቆስ 5:42) በተመሳሳይም፣ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ በተፈወሱ ጊዜ የተሰማቸው ደስታ ወደር አልነበረውም። ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን የፈጸመበት አንዱ ምክንያት በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ምን እንደሚያከናውን ለማሳየት ነበር፤ ይህ ሥርዓት በቅርቡ በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት የሚተርፈው ጻድቅ የሆነው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በዚህ ወቅት ከማንኛውም አካላዊ ሕመም ፈውስ ያገኛል። (ራእይ 7:9, 14) በትንሣኤ የሚቀበሏቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውም ቢሆኑ ፍጹም የሆነ አካላዊ ጤንነት ይኖራቸዋል። በዚያ ጊዜ ምን ያህል ደስታ ሊኖር እንደሚችል በዓይነ ሕሊናችሁ ይታያችሁ!

ይሁንና ወንድም ፒርስ እንደገለጸው ከምንም ነገር በላይ አንገብጋቢ የሆነው ፈውስ ሰዎችን በአካላዊ ሁኔታ ፈውስ እንዲያገኙ መርዳት አይደለም። ኢየሱስ ፈውሷቸው የነበሩ ሰዎች ውሎ አድሮ መታመማቸው አልቀረም። ከሞት ያስነሳቸውም ቢሆኑ ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። ዓይናቸውን ያበራላቸው ሰዎች በሕይወት እያሉ መልሰው ባይታወሩ እንኳ ሲሞቱ ብርሃናቸውን ማጣታቸው አይቀርም። በመሆኑም ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኢየሱስ ያከናወነው መንፈሳዊ ፈውስ ነው። በተመሳሳይም ከጊልያድ የተመረቁት ሚስዮናውያን መንፈሳዊ ፈውስ የማካሄድ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። ሰዎች ከሰማዩ አባታቸው ጋር እንዲታረቁ በመርዳት በመንፈሳዊ ሁኔታ ሕይወት እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋሉ። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት በመንፈሳዊ ሁኔታ የተፈወሱ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከዚያም ወንድም ፒርስ “ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጣው እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ፈውስ ነው። ይህን ስታደርጉ በአገልግሎታችሁ ስኬታማ ትሆናላችሁ” አለ።

በዕለቱ የቀረቡ ሦስት ተጨማሪ ንግግሮች

“የዛሬዋን ቀን በጥሩ ሁኔታ አሳልፍ ይሆን?” አስፈላጊ የሆነውን ይህን ጥያቄ ያቀረበው የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ሮበርት ሬንስ ነው። ተማሪዎቹ በተመደቡበት ቦታ በሚያገለግሉበት ወቅት ጊዜያቸውን በጥበብ የሚጠቀሙ፣ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ወደ አምላክ ቃል ዞር የሚሉ እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ የሚታመኑ ከሆነ እያንዳንዱን ቀን በጥሩ ሁኔታ ማሳለፍ እንደሚችሉ ነገራቸው።

“የቆየውን አዲስ ማድረግ ትችላላችሁ?” የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ማርክ ኑሜር ያቀረበው ንግግር ርዕስ ይህ ነበር። ወንድም ኑሜር 1 ዮሐንስ 2:7, 8⁠ን ያብራራ ሲሆን እዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ “አዲስ ትእዛዝ” ከጠቀሰ በኋላ ይኸው ትእዛዝ ራሱ “የቆየው ትእዛዝ” መሆኑን ገልጿል። ሁለቱም የሚያመለክቱት አንድን ትእዛዝ ይኸውም የክርስቶስ ተከታዮች የራሳቸውን ጥቅም በመሠዋት አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ ትእዛዝ ‘የቆየ’ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ትእዛዙን የሰጣቸው ከአሥርተ ዓመታት በፊት ስለሆነ ነው፤ ‘አዲስ’ የተባለው ደግሞ ክርስቲያኖች ተፈታታኝ የሆኑ አዳዲስ ሁኔታዎች ስላጋጠሟቸውና ፍቅራቸውን በአዲስ መልክ በተሟላ ሁኔታ ማሳየት ያስፈልጋቸው ስለነበር ነው። ሚስዮናውያንም በተመሳሳይ በርካታ አዳዲስ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸው ፍቅራቸውን በአዲስ መልክ ማሳየት ያስፈልጋቸው። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?

ወንድም ኑሜር “በሰው ላይ የምትጠሉትን ነገር እናንተ ራሳችሁ ስታደርጉት እንዳትገኙ ተጠንቀቁ” በማለት መክሯቸዋል። ሌሎች ሰዎች የምንጠላውን ነገር ቢያደርጉብንና እኛም በተመሳሳይ መንገድ አጸፋውን ብንመልስ እኛው ራሳችን የምንጠላውን ነገር እያደረግን እንደሆነና ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ዞሮ ዞሮ እኛኑ እንደሚጎዳ አስጠንቅቋል። በአንጻሩ ግን እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን በአዲስ መልክ ፍቅራችንን የምናሳይ ከሆነ ‘እውነተኛውን ብርሃን’ በማብራት መንፈሳዊ ጨለማ እንዲወገድ እናደርጋለን።

“ሸክሙን ተሸከሙ።” ጠቃሚ በሆነው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ ንግግር ያቀረበው ሌላው የጊልያድ አስተማሪ ማይክል በርኔት ነበር። ወንድም በርኔት በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አገሮች በጣም ከባድ የሆኑ ሸክሞችን በጭንቅላታቸው የሚሸከሙ ሰዎች እንዳሉ ተናገረ። እነዚህ ሰዎች የተሸከሙት ነገር እንዳይቆረቁራቸውና ሚዛናቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ካታ ተብሎ የሚጠራ እንደ ማቶት ያለ ከጨርቅ የተዘጋጀ መሸከሚያ አናታቸው ላይ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ዘና ብለው እንዲራመዱ ይረዳቸዋል። ከጊልያድ የተመረቁት ሚስዮናውያንም ተመድበው በሚያገለግሉባቸው አገሮች ውስጥ ከባድ የሆነ የኃላፊነት ሸክም ይጠብቃቸዋል፤ ሆኖም ከካታ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ነገር አላቸው፤ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረት ጥልቅ ሥልጠና አግኝተዋል። እነዚህ ሠልጣኞች የተማሩትን ነገር ተግባራዊ ማድረጋቸው የኃላፊነት ሸክማቸውን በሚወጡበት ጊዜ ሚዛናቸውን ለመጠበቅና ውጤታማ ለመሆን ያስችላቸዋል።

ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች

በጊልያድ የሚሰጠው ሥልጠና በአካባቢው ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጋር ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መካፈልን የሚጨምር ነው። ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተለው ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ዊልያም ሳሙኤልሰን “እጅህ ሥራ አይፍታ” በሚል ጭብጥ ባቀረበው ንግግር ላይ ተማሪዎቹ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች ተናግሯል። (መክብብ 11:6) ተማሪዎቹ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች ሕያው በሆነ መንገድ በሠርቶ ማሳያ ያቀረቡ ሲሆን ይህም ወደ አየር ማረፊያዎች፣ ወደ ምግብ ቤቶችና ወደ ነዳጅ ማደያዎች በሚሄዱበት ጊዜ አጋጣሚውን ተጠቅመው ምሥራቹን በትጋት ይሰብኩ እንደነበር የሚያሳይ ነው። ተማሪዎቹ ከቤት ወደ ቤት፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድና በደብዳቤ ይሰብኩ ነበር። በእርግጥም እጃቸው ሥራ አልፈታም፤ በዚህም የተነሳ ግሩም ውጤቶች ተገኝተዋል።

በመቀጠል ደግሞ በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚያገለግለው ኬነዝ ስቶቫል በሚስዮናዊ አገልግሎት የካበተ ልምድ ላላቸው ሦስት ወንድሞች ማለትም በኢኳዶርና በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ላገለገለው ለባሪ ሂል፣ በኮት ዲቩዋር ላገለገለው ለኤዲ ሞብሊ እንዲሁም በሴኔጋል፣ በቤኒንና በሄይቲ ላገለገለው ለታብ ሃንስበርገር ቃለ ምልልስ አደረገ። ወንድም ስቶቫልን ጨምሮ በቃለ ምልልሱ የተካፈሉት ሁሉ ‘ይሖዋን ፈትኑ፤ የተትረፈረፈ በረከት ታገኛላችሁ’ በሚል ጭብጥ የቀረበውን ይህ ክፍል ሕያው አድርገውታል። (ሚልክያስ 3:10) ለምሳሌ ወንድም ሂል እሱና ባለቤቱ በኢኳዶር አቧራና ጭቃ የሚሆንባቸውን ወቅቶች መልመድ እንዲሁም ሞቃታማ የሆነውን የአገሪቱን የአየር ሁኔታ መቋቋም ተፈታታኝ ሆኖባቸው እንደነበር ተናግሯል። ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ገላቸውን የሚታጠቡት በባልዲ ውኃ እያመጡ ነበር። ሆኖም አገልግሎታቸውን ስለ ማቆም ፈጽሞ አስበው አያውቁም፤ የተሰጣቸውን ምድብ ከይሖዋ እንዳገኙት በረከት አድርገው ይመለከቱት ነበር። ወንድም ሂል “ሕይወታችን ይህ እንደሆነ ራሳችንን አሳምነን ነበር” በማለት ተናግሯል።

በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይ ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ ከትምህርት ቤቱ ላገኙት ሥልጠና የተሰማቸውን ከፍተኛ አድናቆት የሚገልጽ ልብ የሚነካ ደብዳቤ አነበበ። ደብዳቤው “እምነታችን ከመቼው ጊዜ ይበልጥ እንደጨመረ ይሰማናል፤ ሆኖም ገና ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ እናውቃለን” የሚል ሐሳብ ይዟል። ሁሉም ተማሪዎች ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ተለያዩ አገሮች ተመደቡ። ወንድም ጃክሰን ፕሮግራሙን ሲደመድም ተማሪዎቹ ወደፊት በሚጠብቃቸው ሕይወት በተለይ ደግሞ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለያቸው መጠበቅ እንደሚችሉ አረጋገጠላቸው። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ አዳዲሶቹ ሠልጣኞች ወደፊት ጥሩ ነገር እንደሚያከናውኑ ያላቸው ተስፋ ይበልጥ ተጠናክሯል። አዎ፣ ይሖዋም በእነዚህ አዳዲስ ሚስዮናውያን ተጠቅሞ ብዙ መልካም ነገሮችን እንደሚያከናውን ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ቻርት/​ካርታ]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

9 የተውጣጡባቸው አገሮች

34.0 አማካይ ዕድሜ

18.6 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፏቸው ዓመታት በአማካይ

13.1 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ተመራቂዎቹ በካርታው ላይ ወደሚታዩት አገሮች ተመድበዋል

ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገሮች

አርጀንቲና

አርሜንያ

ቡርኪና ፋሶ

ቡሩንዲ

ኮንጎ (ኪንሻሳ)

ቼክ ሪፑብሊክ

ሄይቲ

ሆንግ ኮንግ

ኢንዶኔዥያ

ኬንያ

ሊትዌኒያ

ማሌዥያ

ሞዛምቢክ

ኔፓል

ፓፑዋ ኒው ጊኒ

ሩማንያ

ሴኔጋል

ታንዛኒያ

ኡጋንዳ

ዚምባብዌ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ130ኛው ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ዜናይዳ ሞሊና፣ ሰማንተ ባሰሊኖ፣ ክሪስቲአና አላትሲስ፣ አራሴልያ አሮዮ፣ ሌነ ኒንዮ፣ ሼሪ መርክሊንግ፣ ሚሚ ክላርክ

(2) ሲንዲ ሊትል፣ ስቴፋንያ ቲበዶ፣ ሶፊያ ያኮፕሶን፣ ጃኔት ሞሬኖ፣ ኧማንደ ሮድሪገስ፣ ካረም ሊ፣ ሆሊ ካርዴናስ፣ ሊንደ አጊላር

(3) አንድሪአ ክሌርቡሽ፣ አንድሪአ ፖሊ፣ ሲልቭያ ኮልድዌል፣ ዋኒተ አዳሜ፣ ሽቴፋኒ ሂልደብራንት፣ ኢዘቤል ሹሜከር፣ ኔኦሚ ግሮመን፣ ግሪሴል ጋልቬስ

(4) ጄሲ ክላርክ፣ አንቶንዮ ባሰሊኖ፣ ካት ፓከም፣ ሆርሄ አዳሜ፣ ማክሲን ክናውስ፣ ማይክ ኒንዮ፣ ራሞን ሞሬኖ፣ ጄሰን ጋልቬስ

(5) ዴቪድ ሮድሪገስ፣ ሜ ዤኔ፣ ህዋን ሞሊና፣ አልበርት አጊላር፣ ኢሲዶረስ አላትሲስ፣ አላነ ማኖ፣ ሪገን ግሮመን፣ ጃኒ ፓከም

(6) ስቴፋን ዤኔ፣ ሚካኤል ካርዴናስ፣ ሴዛር አሮዮ፣ ክሪስቶፈር ማኖ፣ ጄሰን መርክሊንግ፣ ህዩ ሊ፣ ዛቪየር ክሌርቡሽ፣ ፓትሪክ ያኮፕሶን

(7) ጆኤል ሊትል፣ ቤርንት ሂልደብራንት፣ መታኔኧል ሹሜከር፣ ኬንት ክናውስ፣ ጆነተን ኮልድዌል፣ ፍራንክ ቲበዶ፣ ክሊንተን ፖሊ