በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዶርቃ ተወዳጅ የነበረችው ለምንድን ነው?

ዶርቃ ተወዳጅ የነበረችው ለምንድን ነው?

ልጆቻችሁን አስተምሩ

ዶርቃ ተወዳጅ የነበረችው ለምንድን ነው?

ሁላችንም ብንሆን ሰዎች እንዲወዱን እንፈልጋለን። አንተስ ሌሎች እንዲወዱህ አትፈልግም? * መጽሐፍ ቅዱስ በብዙዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ስለነበረች ዶርቃ የተባለች አንዲት ሴት ይናገራል።

ዶርቃ የምትኖረው በሜድትራንያን ባሕር አጠገብ ባለችው የኢዮጴ ከተማ ነበር። ኢዮጴ ከኢየሩሳሌም የምትርቀው 56 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነው። ዶርቃ ከጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዷ ነበረች።

ዶርቃ በሌሎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ የነበረችው ለምን ይመስልሃል?— መጽሐፍ ቅዱስ ዶርቃ ለሌሎች ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ታደርግና ስጦታዎችን ትሰጥ እንደነበር ይናገራል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዶርቃ ለመበለቶች ማለትም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች የሚያማምሩ ልብሶችን ትሠራላቸው ነበር። ከዚህም በላይ ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ለብዙ ሰዎች ትናገር ነበር።

ዶርቃ በአንድ ወቅት ምን መጥፎ ነገር እንደደረሰባት ታውቃለህ?— በጣም ታመመች፤ ከዚያም ሞተች። ጓደኞቿ በሙሉ በጣም አዘኑ። በመሆኑም ወደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሰዎችን ላኩ፤ በወቅቱ ጴጥሮስ የነበረው ከኢዮጴ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ አንዲት ከተማ ነበር። እነዚህ ሰዎች ጴጥሮስ በፍጥነት ከእነሱ ጋር እንዲሄድ ጠየቁት። ጴጥሮስ እዚያ እንደደረሰ ዶርቃ ወደምትገኝበት ወደ ላይኛው ክፍል ወጣ። በዚያ ያሉት ሁሉም ሴቶች እያለቀሱ ዶርቃ የሠራችላቸውን ልብሶች ያሳዩት ነበር።

ከዚያም ጴጥሮስ ሁሉም ክፍሉን ለቀው እንዲወጡ ነገራቸው። ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት ከዚህ በፊት የተለያዩ ተአምራትን ፈጽመዋል፤ ይሁንና ማናቸውም ቢሆኑ የሞተን ሰው አስነስተው አያውቁም ነበር። ታዲያ አሁን ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን?

ጴጥሮስ ከሞተችው ሴት አጠገብ ተንበርክኮ ወደ ይሖዋ ጸለየ። ከዚያም ዶርቃን “ተነሺ” አላት። ዶርቃም ከሞት ተነሳች! ጴጥሮስም እጇን ይዞ አስነሳት። ከዚያም መበለቶቹንና በዚያ ያሉትን ሌሎች ሰዎች ጠርቶ ከሞት መነሳቷን አሳያቸው። ሁሉም ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ?

ከሞት ስለተነሳችው ስለ ዶርቃ ከሚገልጸው ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ ለማሰብ እንሞክር። ይህ ታሪክ ለሌሎች መልካም ነገር የምታደርግ ከሆነ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደምትሆን ያስተምራል። ከሁሉም በላይ ግን አንዲህ በማድረግህ አምላክ ያስብሃል፤ እንዲሁም ይወድሃል። ለሌሎች ያደረካቸውን መልካም ነገሮች ፈጽሞ አይረሳም። እንዲሁም እሱ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም በደስታ እንድትኖር በማድረግ ውለታህን ይከፍልሃል።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።