መጋቢት 23, 2022 | የታደሰው፦ ጥቅምት 11, 2024
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—የእስራት ፍርድ በይግባኝ ተሻረ | ይሖዋ ስድስት ታማኝ ወንድሞችንና እህቶችን ደግፏቸዋል
ጥቅምት 10, 2024 የካባረቭስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት፣ እህት ማያ ካርፑሽኪና፣ ወንድም ስታኒስላቭ ኪም፣ ወንድም ኒኮላይ ፖሌቭዶቭ፣ እህት ስቬትላና ሴዶቫ እንዲሁም ወንድም ቪታሊ ዡክና ባለቤቱ ታትያና ያቀረቡትን ይግባኝ ተመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል። በማያ፣ በስቬትላና እና በታትያና ላይ የተላለፈው የገደብ እስራት በአንድ ዓመት እንዲቀነስ ተወስኗል። በስታኒስላቭ ላይ ተላልፎ የነበረው የእስራት ፍርድ ደግሞ ወደ ሰባት ዓመት ከሁለት ወር የገደብ እስራት፣ የቪታሊ የእስራት ፍርድ ወደ ሰባት ዓመት ከአራት ወር የገደብ እስራት እንዲሁም የኒኮላይ ፍርድ ወደ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስራት ተቀይሯል። ወንድሞች ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት ከእስር ተፈትተዋል።
ሰኔ 20, 2024 በካባረቭስክ ክልል የሚገኘው የኢንደስትሪያልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት እህት ማያ ካርፑሽኪና፣ ወንድም ስታኒስላቭ ኪም፣ ወንድም ኒኮላይ ፖሌቭዶቭ፣ እህት ስቬትላና ሴዶቫ እንዲሁም ወንድም ቪታሊ ዡክና ባለቤቱ ታትያና ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ማያ የአራት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶባታል። ስቬትላና እና ታትያና እያንዳንዳቸው የአምስት ዓመት የገደብ እስራት ተበይኖባቸዋል። እህቶች በአሁኑ ወቅት እስር ቤት አይገቡም። ስታኒስላቭ የስምንት ዓመት ከሁለት ወር፣ ቪታሊ የስምንት ዓመት ከአራት ወር፣ ኒኮላይ ደግሞ የስምንት ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል። እነዚህ በ2017 ከተጣለው እገዳ ወዲህ ከተላለፉት የእስራት ፍርዶች ሁሉ ረጅም ናቸው። ወንድሞች ከፍርድ ቤት በቀጥታ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።
የክሱ ሂደት
ኅዳር 10, 2018
55 ገደማ ሰዎች አንድ ካፌ ውስጥ ተሰባስበው እየተጨዋወቱ ሳሉ ባለሥልጣናቱ አቋረጧቸው። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ጨምሮ በቦታው የነበሩት ሰዎች በሙሉ የወንጀል ምርመራ ተደረገባቸው፤ አሻራቸው ተወሰደ፤ እንዲሁም ፎቶግራፍ እንዲነሱ ተደረገ
ኅዳር 12, 2018
ስታኒስላቭ፣ ኒኮላይና ቪታሊ ወደ ማረፊያ ቤት ተላኩ። ማያ፣ ስቬትላና እና ታትያና የጉዞ ገደብ ተጣለባቸው
ጥር 14, 2019
ኒኮላይና ቪታሊ ከማረፊያ ቤት ተለቀው በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረጉ
ጥር 29, 2019
ስታኒስላቭ ከማረፊያ ቤት ተለቆ በቁም እስር እንዲቆይ ተደረገ
ሐምሌ 18, 2019
ክሱ በካባረቭስክ ክልል ወደሚገኘው የኢንደስትሪያልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ተወሰደ
ነሐሴ 2, 2019
ኒኮላይ ከቁም እስር ተለቀቀ
መስከረም 9, 2019
በስታኒስላቭና በኒኮላይ ላይ የተመሠረተው ሌላ ክስ በካባረቭስክ ወደሚገኘው የዢለዝናዳሮዥኒይ አውራጃ ፍርድ ቤት ተወሰደ
ኅዳር 5, 2019
ኒኮላይ የጉዞ ገደብ ተጣለበት
ጥር 18, 2020
ስታኒስላቭና ቪታሊ ከቁም እስር ተለቀቁ
የካቲት 4, 2020
ስታኒስላቭና ኒኮላይ በተመሠረተባቸው ሌላ ክስ ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ ተፈረደባቸው። በካባረቭስክ የሚገኘው የዢለዝናዳሮዥኒይ አውራጃ ፍርድ ቤት በሁለቱም ላይ የሁለት ዓመት የገደብ እስራትና የአመክሮ ቆይታ በየነባቸው
ነሐሴ 3, 2020
ለኢንደስትሪያልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ ተመለሰ፤ በመሆኑም አቃቤ ሕጉ ይግባኝ ጠየቀ
መስከረም 29, 2020
የካባረቭስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕጉ ያቀረበውን ይግባኝ ተመለከተ። ስታኒስላቭና ኒኮላይ በዳኛው ፊት ቀርበው እንዲናገሩ ተፈቀደላቸው። እነሱም እንደ አብዛኞቹ አገራት ሁሉ የሩሲያ ፌዴሬሽንም አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን እንደፈረመና የዜጎቹን የአምልኮ መብትና ነፃነት ላለመጣስ እንደተስማማ ገለጹ
ጥቅምት 12, 2020
የካባረቭስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት የኢንደስትሪያልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ያደረገውን ውሳኔ አጸና፤ በመሆኑም ክሱ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ ተመለሰ
ታኅሣሥ 15, 2021
ክሱ በድጋሚ ለኢንደስትሪያልኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀረበ
አጭር መግለጫ
ይሖዋ እነዚህን ውድ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም በዘመናችን ባለው “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ውስጥ የታቀፉትን ክርስቲያኖች በሙሉ መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 12:1