በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 21, 2020
እስራኤል

እስራኤል ውስጥ በተደረገ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ

እስራኤል ውስጥ በተደረገ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ

አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው በጣም የተደሰቱ አባትና እናት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዘመናዊ ዕብራይስጥ ቋንቋ መውጣቱን ባበሰረበት ስብሰባ ላይ ንግግሩን የጀመረው “የበላይ አካሉ ልዩ ስጦታ አዘጋጅቶላችኋል” በማለት ነበር። ጥር 11, 2020 በሃይፋ፣ እስራኤል በሚገኘው የሮሚማ የስፖርት ማዕከል ውስጥ በተደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ 2,125 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።

የእስራኤል ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ዴቪድ ሲሞዝራግ እንዲህ ብሏል፦ “በክልላችን ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የዕብራይስጥ ተናጋሪዎች እንዳሉ ይገመታል። ታናክን a በዘመናዊ ዕብራይስጥ ቋንቋ ማቅረባችን ለእነዚህ ሰዎች ጠቃሚ እንደሚሆን እናምናለን።” ይህ ትርጉም ለዕብራይስጥ አንባቢዎች ከተዘጋጁት ጥቂት ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንዱ ነው።

አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ186 ቋንቋዎች ይገኛል። በጥንት ዘመን እንደነበሩት የማሶሬት ጸሐፍት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ዕብራይስጥ በመተርጎሙ ሥራ የተካፈሉ ወንድሞቻችንም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የትርጉም ቡድኑ ይህን ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም ከሦስት ዓመት በላይ ወስዶበታል። ከተርጓሚዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ የዕብራይስጥ አንባቢያን አንዳንድ ጥቅሶችን አልፎ ተርፎም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ለመረዳት ማመሣከሪያዎችን ወይም በሌላ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማየት አስፈልጓቸዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አንባቢያን የጥቅሶቹን ትርጉም በቀላሉ ማወቅ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።”

አንድ ቤተሰብ በዘመናዊ ዕብራይስጥ የተዘጋጀውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም እያሳዩ

አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ አንባቢያን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የታናክን አብዛኛውን ክፍል መረዳት ይከብዳቸው ነበር፤ አሁን ግን መልእክቱን በትክክልና ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መረዳት ይችላሉ።” በእስራኤል ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ሥር ከሚገኙት 2,000 አስፋፊዎች መካከል 603 የሚያህሉት ዕብራይስጥ ተናጋሪ ናቸው፤ እነዚህ አስፋፊዎች ይህን ልዩ ስጦታ “የይሖዋን ሕግ ለመመርመርና ተግባራዊ ለማድረግ” እንደሚጠቀሙበት እናምናለን።—ዕዝራ 7:10

a ታናክ የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሦስት ክፍሎች ይኸውም ኦሪት (ሕግ)፣ ኔቪም (ነቢያት) እና ኬቱቪም (መጻሕፍት) የሚጠሩበት ምህጻረ ቃል ነው፤ ታናክ ላይ መጻሕፍቱ የተዘረዘሩበት መንገድ ከአብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች የተለየ ነው። በአዲሱ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጻሕፍቱ የተዘረዘሩት ከታናክ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው።