በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከአሥራ አምስቱ የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎች መካከል ሦስቱ ሽልማቶቻቸውን ይዘው

መስከረም 19, 2023
ጀርመን

አሥራ አምስት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች የናዚ ሰለባ የሆነችውን ቪልኼልሚነ ፐታን በተመለከተ ለሠሩት ፕሮጀክት እውቅና ተሰጣቸው

አሥራ አምስት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች የናዚ ሰለባ የሆነችውን ቪልኼልሚነ ፐታን በተመለከተ ለሠሩት ፕሮጀክት እውቅና ተሰጣቸው

ሐምሌ 6, 2023 በካስል፣ ጀርመን የሚኖሩ 15 ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን በመሆን ለሠሩት ፕሮጀክት አንደኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፤ ፕሮጀክታቸው ያተኮረው የድፍረት ምሳሌ በሆነችውና በናዚ በደረሰባት ግፍ ሕይወቷን ባጣችው በእህት ቪልኼልሚነ ፐታ ላይ ነበር።

ሽቶልፓሽታይነ ኢን ካስል የተባለው ተቋም በመላዋ የካስል ከተማ ለመታሰቢያነት የሚሆኑ አነስተኛ የመረማመጃ ድንጋዮች አስቀምጧል፤ ድንጋዮቹ በናዚ የግዛት ዘመን ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች መታሰቢያ ናቸው። በዚህ ተቋም ከተዘከሩት ሰዎች መካከል ቪልኼልሚነ እና ባለቤቷ ዩስቶስ ፐታ ይገኙበታል። ቪልኼልሚነ፣ የካስል አጎራባች በሆነችው በኒስተታል መንደር ውስጥም በስሟ መንገድ ተሰይሞላታል። በተቋሙ አሥረኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ከመላ ከተማዋ የተውጣጡ ተማሪዎች፣ የመረጧቸውን የናዚ ግፍ ሰለባዎች የሕይወት ታሪክ እንዲያቀርቡና ከተሞክሯቸው ያገኙትን ትምህርት እንዲያስረዱ ግብዣ ቀርቦ ነበር።

በቪልኼልሚነ ፐታ ስትራሰ (በእህት ቪልኼልሚነ ስም በተሰየመው መንገድ) ላይ በሚገኝ የአውቶቡስ ማቆሚያ ለእይታ የቀረቡት የእህት ቪልኼልሚነን ደብዳቤዎች የሚያሳዩ ፖስተሮች

ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 23 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ለፕሮጀክታቸው የቪልኼልሚነን ታሪክ መረጡ። አምላክን ብቻ ታዝዛለች በሚል ርዕስ የእሷን ሕይወት የሚተርክ የ24-ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ቪዲዮ አዘጋጁ። ቪዲዮው በ1937 ናዚዎች እስር ቤት እንዳስገቧትና በ1942 በራቨንስብሩክ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በ49 ዓመት ዕድሜዋ ሕይወቷ እንዳለፈ ይተርካል። በተጨማሪም ተማሪዎቹ ቪልኼልሚነ በእስር ላይ እያለች ለባለቤቷና ለቤተሰቦቿ የጻፈቻቸውን ደብዳቤዎች ፎቶግራፎች የያዙ ትናንሽ ፖስተሮችን አዘጋጅተዋል። ፖስተሮቹንም በስሟ በተሰየመው መንገድ ላይ በሚገኝ የአውቶቡስ ፌርማታ ለእይታ አቅርበዋል።

ቪልኼሚነ ሚያዝያ 25, 1937 ለባሏ በጻፈችው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “ውድ ዩስቶስ፣ ሁለታችንም ፍርዳችንን በሰማንበት ዕለት ተረጋግተን እንደነበረና ጠንካራ እምነት እንዳለን ያሳየን መሆኑ ደስ ብሎኛል። አሁንም ጌታ እንዲመራን ሁሉንም ነገር ለእሱ ትተናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እስከመጨረሻው ሁለታችንም ለእሱ ታማኝ ለመሆን የገባነውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል መንፈሳዊና አካላዊ ጥንካሬ እንዲሰጠን ጌታን በጸሎት እየለመንኩት ነው። መቼም ከምንቋቋመው በላይ የከበደ ፈተና እንድንሸከም አይፈቅድም። ስለዚህ በልበ ሙሉነት ጌታችንን እንጠባበቃለን።” ደግሞም ጸሎቷ ተሰምቶ ሁለቱም እስከ ሞት ድረስ ታማኞች ሆነዋል።

ቪልኼልሚነ ሚያዝያ 25, 1937 ለባለቤቷ ለዩስቶስ የጻፈችው ደብዳቤ

የ23 ዓመቷ እህት አሌክሳንድራ አልተማየ በቪዲዮው ላይ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ቪልኼልሚነ እና ባለቤቷ፣ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ተቃውሞን መጋፈጥ እንደሚጠይቅ ተረድተው ነበር። አምላክ ፈጽሞ እንደማይረሳቸው ስለሚያውቁ ስደትን፣ እስራትን ብሎም ሞትን እንኳ ሳይቀር ለእምነታቸው ሲሉ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል።” ለፕሮጀክቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተው የ18 ዓመቱ ወንድም ኦለ ሽሮደር ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “እህት ቪልኼልሚነ ለእኔ ምሳሌ ሆናኛለች። እምነቷ፣ ለአምላክ ያላት ታማኝነት፣ ጽናቷ እንዲሁም ደስታዋን አለማጣቷ ሊኮረጅ የሚገባው ነገር ነው። የእሷ ታሪክ ከአምላክ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ አስገንዝቦኛል።”

ሌሎች ተማሪዎችን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን፣ የከተማዋን ከንቲባ፣ የባሕል ጉዳዮች ኃላፊውን እና የትምህርት ጉዳዮች ዳይሬክተሩን ጨምሮ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት 180 ሰዎች ሙሉው ቪዲዮ ቀርቧል።

በፕሮጀክቱ ላይ እንደተሳተፉት ወንድሞችና እህቶች ሁሉ እኛም በዩስቶስና በቪልኼልሚነ የእምነትና የድፍረት ምሳሌ ተበረታተናል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይረሳቸው እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 6:10