በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባሕሩ ጋር ለመቀላቀል የሞከረ ተራራ

ከባሕሩ ጋር ለመቀላቀል የሞከረ ተራራ

ከባሕሩ ጋር ለመቀላቀል የሞከረ ተራራ

በቬንዙዌላ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

የቬንዙዌላ ዋና ከተማ በሆነችው በካራካስና በባሕሩ መካከል 2, 000 ሜትር ከፍታ ያለው ኤል አቢላ የሚባል አንድ ተራራ ይገኛል። በስተ ሰሜን በኩል ሕዝብ በብዛት የሰፈረበት ቀጭን የባሕር ጠረፍ አለ። ትልቁ የቬንዙዌላ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኘው በዚህ አካባቢ ሲሆን ጎብኚዎች ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ካራካስ ለማቅናት ከተራራው ሥር በተፈለፈለው የዋሻ መንገድ መጓዝ አለባቸው።

ባለፈው ታኅሣሥ ወር ዶፍ ዝናብ ሲጥል ከቆየ በኋላ ዝናብ የጠገበው የኤል አቢላ ተራራ ተጨማሪ ውኃ መቋጠር አልቻለም። በአሥር ሺህ ክዩቢክ ሜትር የሚለካ ውኃ ከተራራው ሲንዠቀዠቅ ላየ ሰው የተራራው ጎንና ጎን የተተረተረ ይመስል ነበር። አንድ ሰው እንደገለጸው ተራራው ከባሕሩ ጋር ለመቀላቀል እየሞከረ ያለ ይመስል ነበር። ከደሳሳ ጎጆ አንስቶ እስከ ትልልቅ ቪላዎች ድረስ ያሉ ቤቶች ጭቃ፣ አለትና ዛፍ በሞላው ጎርፍ ተጥለቀለቁ። አልጋዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣ ቴሌቪዥኖችና አልፎ ተርፎም ሰዎች በጎርፍ ተጠርገው ተወሰዱ። አንድ አረጋዊ ሰው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ ነበር የመሰለኝ ሲሉ ተናግረዋል።

ከጊዜ በኋላ ዝናቡ አቆመና ጎርፉ መጉደል ጀመረ። በአንድ ግምታዊ አኃዝ መሠረት ወደ 50, 000 የሚጠጉ ሰዎች አልቀዋል እንዲሁም 400, 000 ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል። ይህ ክስተት “በቬንዙዌላ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ የተፈጥሮ አደጋ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።

ከሞት አፋፍ የተረፉ ሰዎች

ታኅሣሥ 15 ቀን ሁዋን ካርሎስ ሎሬንሶ እና አባቱ ከአፍ እስከ ገደፋቸው ሞልተው በሚፈስሱ ሁለት ወንዞች ተከብበው መውጫ ቀዳዳ በማጣታቸው መኪናቸውን ትተው ሌሎች 35 ሰዎች ወደተጠለሉበት አንድ ሕንፃ ገቡ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ጎርፉ ወደ ሕንፃው መግባት በመጀመሩ የውኃው ከፍታ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሄደ። ሁሉም ጣሪያው ላይ ወጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የተገነደሱ ዛፎችና ትልልቅ ቋጥኞች ከሕንፃው ጋር እየተላተሙ ሕንፃውን ይንጡት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ የአንደኛውና የሁለተኛው ፎቅ ግድግዳዎች ፍርክስክሳቸው ወጣና ምሰሶዎቹና ጣሪያው ብቻ ቆመው ቀሩ። ብዙም ጥንካሬ የሌለው የሕንፃው መዋቅር ቋጥኞቹና ግንዶቹ በለተሙት ቁጥር ይንቀጠቀጣል።

አንዲት ሄሊኮፕተር ብቅ ብላ የነበረ ቢሆ​ንም ሊፈርስ ምንም ያህል ባልቀረው ሕንፃ ላይ ማረፍ አልቻለችም። ሄሊኮፕተሯ ተመልሳ ስትሄድ ሁዋን ካርሎስ እና አባቱ ሁሉ ነገር እንዳበቃለት በማመን እየተላቀሱ ተሰነባበቱ። ይህ ከሆነ በኋላ ሁለት ሄሊኮፕተሮች ደረሱ። ሙያቸውን በሚገባ የተካኑት አብራሪዎች አየር ላይ በማንዣበብ በጣሪያው ላይ የነበሩትን ሰዎች በሙሉ አንድ በአንድ ጭነው ወደ ደህና ቦታ አደረሷቸው። ልክ ሄሊኮፕተሮቹ እንደሄዱ ሕንፃው እንዳለ ተደርምሶ ጎርፉ ውስጥ ገባ። የተረፉት ለጥቂት ነበር!

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው ወጡ። በትንንሽ አውሮፕላኖች፣ በተሽከርካሪዎችና በባሕር ዳርቻዎች መቆም በሚችሉ የጦር ሠራዊት ማጓጓዣ መርከቦች ተጭነው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተጓዙ። ሕፃናትን ትከሻቸው ላይ የተሸከሙ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በጎርፉ ውስጥ በገመድ እየተመሩ ጀልባ ላይ እንዲሳፈሩ ተደረገ። አንዳንዶች ጥቂት የግል ቁሳቁሶችን ማዳን የቻሉ ቢሆንም ብዙዎቹ ከለበሱት ልብስ በቀር ምንም የያዙት ነገር አልነበረም።

የእርዳታ እጅ ለመዘርጋት የተደረገ ጥረት

አደጋው መከሰቱን የሚገልጽ ወሬ እንደተሰማ ወዲያውኑ በቬንዙዌላ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እርዳታ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማካሄድ ጀመረ። ይሁን እንጂ መንገዶቹ አንድም በግባሶች ተሞልተዋል አለዚያም በጎርፍ ተወስደዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ አስቸኳይ የሆነ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል የዋናው አውራ ጎዳና አንደኛው መተላለፊያ ተከፈተ። የሕክምና ቁሳቁሶችንና ባለሙያዎችን የጫኑ የምሥክሮቹ ተሽከርካሪዎች እንዲያልፉ ተፈቀደላቸው። ከጊዜ በኋላ አንድ ባለሥልጣን “መንግሥት እርዳታ ለማድረስና ሰዎቹን ከአካባቢው ለማውጣት በቦታው ቀድመው ከሚደርሱት መካከል የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚገኙበት ያውቅ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ምሥክሮቹ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት የተጠናከረ ፍለጋ ማድረግ ጀመሩ። አካባቢውን እየለቀቁ የሚወጡትን ሰዎች ወደ ካራካስ ለመውሰድ የመጓጓዣ አገልግሎት ተዘጋጀ። ብዙዎቹ ወደ ከተማይቱ የገቡት ባዶ እጃቸውን ነበር። ችግር ላይ ለወደቁት ሰዎች ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ማከፋፈል ይቻል ዘንድ በከተማይቱ ውስጥ የእርዳታ ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች ተቋቋሙ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ከምግብና ልብስ በተጨማሪ ሌላ የሚያስፈልጋቸው ነገር ነበር። መጠለያም በእጅጉ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቲያን ወንድሞቻቸው በደስታ ተቀብለው አስጠጓቸው።

አደጋው ከተከሰተ በኋላ ወዳጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ረዘም ላለ ጊዜ በቤታቸው ያስጠለሉ ሰዎች ነበሩ። በፕዌርቶ ካቤዮ የሚገኙት ሆኤል እና ኤልሳ የተባሉ ምሥክሮች የሚኖሩት በአንድ አነስተኛ አፓርታማ ውስጥ ነው። ወዠቡ ከተከሰተ ከአንድ ወር በኋላም እንኳ 16 ሰዎች አብረዋቸው ይኖሩ ነበር። ብዙዎቹ ቤታቸውን ብቻ ሳይሆን ሥራቸውንም ጭምር ነበር ያጡት። መሥሪያ ቤቶቻቸው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

ቀደም ሲል ሰው ይተራመስባቸው የነበሩት የመዝናኛ ሥፍራዎችና የወደብ ከተሞች እንዳልነበሩ ሆነዋል። አንዳንድ መኪናዎች ከጭቃው ውስጥ ብቅ ብለው የሚታዩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከግድግዳ ጋር ተጣብቀው፣ ከምሰሶዎች ጋር ተላትመው ወይም በበሮችና በመስኮቶች መሃል ተወትፈው ይታያሉ። በአንዳንድ መንገዶች ላይ የተጋገረው ጭቃ እስከ 3 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያለው ሲሆን አንድ ሰው በጭቃው ላይ ቢራመድ ፎቅ ላይ አልፎ ተርፎም የቤት ጣሪያ ላይ የወጣ ያህል ሆኖ ሊሰማው ይችላል!

በቬንዙዌላ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች አደጋው በቁሳዊ ነገሮች መታመን እንደሌለባቸው ጥሩ ትምህርት ሰጥቷቸው እንዳለፈ ተናግረዋል። (ሉቃስ 12:​29-31) አንዳንዶች የሚከተለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምክር ያዘለውን ትርጉም መረዳት ችለዋል:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።”​—⁠ማቴዎስ 6:​19-21

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች/ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቬንዙዌላ

ካራካስ

የአደጋ ቀጣና

ኮሎምቢያ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩበን ሴራኖ ከፈራረሰው ቤቱ ጋር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1. በካራካስ ፈቃደኛ ሠራተኞች የእርዳታ ቁሳቁሶች አሰባስበዋል

2, 3. የማይኩቲያ ጉባኤ አባላት በመንግሥት አዳራሻቸው የተጋገረውን ሁለት ሜትር ጥልቀት ያለው ጭቃ አንስተዋል

4. እነዚህ ምሥክሮች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሲሆን ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች በፈቃደኝነት አዳዲስ ቤቶች ገንብተዋል

5. ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ከደረሱት በሳን ሰባቺያን ደ ሎስ ሬየስ ከሚገኙ ቤቶች አንዱ