በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ልታሟላ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ

መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ልታሟላ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ

መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ልታሟላ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ

ሰዎች ሃይማኖት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? የሰው ልጆች ወደ መንፈሳዊ ነገሮች የሚያዘነብሉት በዚህ ያልተረጋጋ ዓለም ውስጥ የሚታመኑበት ነገር ለማግኘት ስለሚፈልጉ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ምክንያቱ ይህ ብቻ አይደለም። አሜሪካን ሶሲኦሎጂካል ሪቪው በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “ሰዎች ወደ ሃይማኖት የሚሳቡት የሚተማመኑበት ነገር ማግኘት ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ አይደለም። የሰው ልጆች፣ ከየት ተገኘን? ወደፊትስ ምን ይገጥመናል? የም​ንኖረው ለምን ዓላማ ነው? እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል” ይላል።

እነዚህ እጅግ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው ቢባል እንደምትስማማ የተረጋገጠ ነው። ታዲያ እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች አስተማማኝ መልስ ማግኘት አስፈላጊ አይሆንም? እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች በጣም ከባድና ወሳኝ ከመሆናቸው የተነሣ እንደ ግል ምርጫችን ከዚያም ከዚህም ለቃቅመን የያዝናቸው እምነቶች መልስ ሊያስገኙልን አይችሉም። ስለ ሕይወት ለሚነሱ ጥልቀት ያላቸው ጥያቄዎች ጠንካራ መሠረት ያለው አስተማማኝ መልስ ለማግኘት ከፈለግን ከዚህ የተሻለ ዘዴ ማግኘት ይኖርብናል።

ታዲያ የተሻለ መንገድ ይኖራል? ፌራር ፌንተን የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተናገሩት አስደናቂ ነገር አለ። “የጽንፈ ዓለሙን ምሥጢርና የራሱን የሰውን ልጅ ምሥጢር ለሰው የሚገልጥ ብቸኛው ቁልፍ” ይህ መጽሐፍ ነው ብለዋል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስላለፈው፣ ስለአሁኑና ስለመጪው ጊዜ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ከየት እንደመጣን፣ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ፣ እንዴት ደስታ ልናገኝ እንደምንችልና የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘልን ይነግረናል። በታሪክ ዘመናት በሙሉ የዚህን መጽሐፍ ያህል በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ፣ የዚህን መጽሐፍ ያህል የተሰነዘረበትን ከፍተኛ ጥቃት በሙሉ ተቋቁሞ ያሸነፈ ሌላ መጽሐፍ የለም። ታዲያ ብዙ ሰዎች ስለ ሕይወት ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሲፈልጉ ይህን ወደር የማይገኝለት መጽሐፍ ችላ የሚሉት ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስና በሚያውቋቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል ልዩነት መኖሩን አስተውለው አያውቁም። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በአምላክ ስም እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉ ተመልክተዋል። ዘ ጋርድያን እንዳለው “በዛሬው ጊዜ ቀሳውስት የሚጨነቁት ገንዘብ ስለማግኘት እንጂ ለመንጎቻቸው የእረኝነት ጉብኝት ስለማድረግ አይደለም” ብለው የሚያማርሩ ሰዎች በርካታ ናቸው። ይህን የመሰለውን ባሕርያቸውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፍ ወይም የማያወግዝ ይመስላቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ ያዛል። ቃሉን ለሚሰብኩ ሰዎችም “በነጻ ተቀበላችሁ፣ በነጻ ስጡ” ይላል። (ዮሐንስ 13:​34፤ ማቴዎስ 10:​8) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን እናከብረዋለን እያሉ ትእዛዙን የማይከተሉ ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች መመዘን ተገቢ ነው?

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ያልሆነ፣ እርስ በርሱ የሚጋጭና ዘመን ያለፈበት መጽሐፍ ነው ብለው ያስባሉ። መጽሐፉን በጥልቅ ብንመረምር ግን የምንገነዘበው ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አለመሆኑ የሚካድ አይደለም። ሆኖም፣ ሕያዋን ፍጥረታት በምድር ላይ የተገኙበትን ቅደም ተከተል፣ የምድርን ቅርጽ ወይም ለተዛማች በሽታዎች ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ የመሳሰሉ ሳይንሳዊ ጉዳዮች በተመለከተ የሚናገረው ነገር ሁሉ ትክክል ነው። እንዲያውም በዚያ ዘመን ያልተደረሰባቸውን ሳይንሳዊ እውነቶች ይናገራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ 1, 600 በሚያክሉ ዓመታት ውስጥ የተጻፉ 66 መጻሕፍት ጥንቅር ቢሆንም እያንዳንዱ መጽሐፍ ከሌላው ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሰብዓዊ ፍጥረታትን ውስጣዊ ባሕርይ በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ ዘመን ያለፈበት መጽሐፍ አይደለም።

ይህ አስደናቂ መጽሐፍ ስለ አምልኮ የሚናገረው በጣም አስፈላጊ ነገርም አለ። አምላክ መመለክ የሚኖርበት ራሱ በወሰነው መንገድ እንጂ ሰው በፈለገው መንገድ አይደለም። (ዮሐንስ 5:​30፤ ያዕቆብ 4:​13–15፤ 2 ጴጥሮስ 1:​21) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት የተቀበሉና የተከተሉ ሰዎች ግን በጣም ጥቂት ናቸው። ከድሮ ጀምሮ ሰዎች ሃይማኖታቸው ከራሳቸው ዓላማ ጋር እንዲስማማ ሲያደርጉ ኖረዋል። እንጨት ቀርጸው ጣዖት ሲያመልኩ የኖሩት በዚህ ምክንያት ነው። ሃይማኖታዊ ተቋሞች ራሳቸው የፈጠሯቸውን መሠረተ ትምህርቶች የሚያስተምሩትም በዚህ ምክንያት ነው። የራሳቸውን ሃይማኖት ፈጥረው የሚይዙ ሰዎችም ከእነዚህ የተለዩ ናቸው ማለት ይቻላል?

ከዚህ የተለየ አማራጭ እንመልከት። የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ እንዳደረጉት ብናደርግስ? እኚህ ሰው ለፍርድ የቀረበላቸውን ጉዳይ ግራና ቀኙን አመዛዝነው ውሳኔ እንደሚሰጡ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ነው በሚልም ሆነ ሐሰተኛ ነው በሚል የሚቀርቡትን ማስረጃዎችም አንድ በአንድ መረመሩ። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው በላይ ከሆነ አካል ይኸውም ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ” ብለዋል።

አንተስ ይህን የመሰለ ምርምር ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች የሚሰጣቸውን መልሶች በመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓት ባለው መንገድ ልታጠና ትችላለህ። ይህን የመሰለ ጥናት ያደረጉ ስድስት ሚልዮን የሚደርሱ የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። ጊዜያቸውን በመሠዋት እነርሱ ያወቁትን ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን አለምንም ክፍያ በማስጠናት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በወረት ወይም በግል ምርጫ ከሚያዝ እምነት የበለጠ እምነት እንዲያገኙ መርዳት ችለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾልን የምናገኘው እውነተኛና ንጹሕ ክርስትና እንዲሁ ተራ ሃይማኖት አይደለም። ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እውነተኛውን ነገር የሚያስተምር ሃይማኖት ነው። ታዲያ ይህን የመሰለውን እውነት ለማግኘት መጣር አይገባንም?​—⁠ዮሐንስ 17:​17

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ማሟላት የምትችለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚሰጠውን ትምህርት በመማርና ከእውነተኛ አምላኪዎች ጋር በመገናኘት ነው