በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ተስፋዬ አልደበዘዘም

ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ተስፋዬ አልደበዘዘም

ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ተስፋዬ አልደበዘዘም

አንድሬ ሃናክ እንደተናገረው

ዓመቱ 1943 ሲሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሟል። ገለልተኛ አቋም በመውሰዴ ምክንያት ሃንጋሪ ቡዳፔስት በሚገኘው እስር ቤት ገባሁ። እዚያም አንድ ጢሙን ያሳደገ የኦርቶዶክስ ቄስ የሦስት ቀን የዳቦ ቀለቤን በመጽሐፍ ቅዱሱ እንድለውጠው ጠየቀኝ። ረሃቡ ቢያሰቃየኝም ጥሩ ምርጫ እንዳደረግሁ ተሰምቶኛል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች አገራችንን ሲቆጣጠሩ ንጹሕ ክርስቲያናዊ ሕሊና ይዞ መቆየቱ ከባድ ነበር። በኋላም በኮሚኒስታዊ አገዛዝ ሥር ባሳለፍናቸው ከ40 በሚበልጡ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሳንጥስ ፈጣሪያችንን ይሖዋን ማገልገል ከፍተኛ ትግል ይጠይቅ ነበር።

በወቅቱ አምላካዊ የአቋም ጽናትን መጠበቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከመግለጼ በፊት ስለ አስተዳደጌ ጥቂት ልንገራችሁ። በእነዚያ የቀድሞ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ችግሮችን ተቋቁመው እንዳለፉ ማወቅ እንደሚያስደስታችሁ እርግጠኛ ነኝ። በመጀመሪያ በአካባቢያችን ስለሚገኙት እውቅ ሃይማኖቶች እንዳስብ ስላደረገኝ አንድ ሃይማኖታዊ አጋጣሚ ልንገራችሁ።

ግራ የሚያጋባ ሃይማኖታዊ ጥያቄ

ታኅሣሥ 3, 1922 ፓትሲን በተባለች ከስሎቫክ ጠረፍ አቅራቢያ በምትገኝ አንዲት የሃንጋሪ መንደር ተወለድኩ። በዚያን ጊዜ ስሎቫኪያ የቼኮዝሎቫኪያን ምሥራቃዊ ክፍል ያጠቃልል ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቭየት ሕብረት ጦር አብዛኛውን የቼኮዝሎቫኪያን ክፍል ሲቆጣጠር ከዩክሬይን ጋር የሚያገናኘን ጠረፍ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ፓትሲን ዘልቆ ገባ።

ለሃይማኖቱ ካደረ አንድ ካቶሊክ ቤተሰብ ከተወለዱት አምስት ልጆች መካከል እኔ ሁለተኛው ነበርኩ። አሥራ ሦስት ዓመት ሲሞላኝ ስለ ሃይማኖት ይበልጥ እንዳስብ ያደረገኝ አንድ አጋጣሚ ተከሰተ። ሃንጋሪ ሞሪፖክ መንደር ውስጥ ወደሚገኘው 80 ኪሎ ሜትር በሚሆን ሃይማኖታዊ የእግር ጉዞ ከእናቴ ጋር አብሬ ተጓዝኩ። ይህን ጉዞ ያደረግነው ብዙ በረከት ያስገኝልናል የሚል እምነት ስለነበረን ነው። የሮማ እና የግሪክ ካቶሊኮች በዚህ ሃይማኖታዊ ጉዞ ይካፈሉ ነበር። ቀደም ሲል እነዚህ ሁለት ቤተ ክርስቲያናት አንድ ይመስሉኝ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አንድ እንዳልሆኑ ተረዳሁ።

በመጀመሪያ የተካሄደው የግሪክ ካቶሊክ ቅዳሴ ነበር። እኔም በዚያ ለመገኘት ወሰንኩ። በኋላ ግን እናቴ በግሪክ ቅዳሴ ላይ እንደተገኘሁ ስትሰማ በጣም ተበሳጨች። እኔም ግራ በመጋባት “የትኛውም ቅዳሴ ላይ ብገኝ ምን ለውጥ አለው? የምንወስደው የአንዱን የክርስቶስን ሥጋ አይደለም?” በማለት ጠየኳት።

እናቴ መልስ መስጠት ስላቃታት “ልጄ፣ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች መጠየቅ ኃጢአት ነው” አለችኝ። ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ በአእምሮዬ ውስጥ መጉላላታቸውን ቀጠሉ።

ለጥያቄዬ መልስ አገኘሁ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ከፈነዳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ17 ዓመቴ ከምኖርበት ቦታ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብላ አሁን በምሥራቃዊ ስሎቫኪያ ወደምትገኘው ከስትሪዳ ናድ ቦድሮጎም የተባለች ትንሽ ከተማ ሄድኩ። ወደዚያ የሄድኩት በአንድ ቀጥቃጭ ቤት ውስጥ የቅጥቀጣ ሞያን ለመማር ነበር። ይሁን እንጂ በቀጥቃጩ ቤት ከቀለጠ ብረት ለፈረሶች ጫማ ከመሥራትና ሌሎች ነገሮችን ከማዘጋጀት የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ተማርኩ።

ማሪያ ፓንኮቪክስ የተባለችው የቀጥቃጩ ባለቤት የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ስለዚህ ቀን ቀን ከባልዋ ቅጥቀጣን ስማር ማታ ማታ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን አጠና እና ምሥክሮቹ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር። ተለማማጅ ቀጥቃጭ እንደመሆኔ መጠን “በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው” የሚሉትን የመዝሙር 12:​6 ቃላት በተሻለ መንገድ ተረድቻቸዋለሁ። የይሖዋን ቃላት የምንመረምርባቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቼ የሚመለሱባቸው እነዚያ ምሽቶች ምንኛ አስደሳች ነበሩ!

ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተፋፋመ ሲመጣ አዲሱ እምነቴ እንደሚፈተን አልተገነዘብኩም ነበር።

በእምነቴ ምክንያት ታሠርኩ

የቀጥቃጭነት ሙያን መማር ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ የሃንጋሪ ወጣቶች በውትድርና እንዲካፈሉ ተጠየቁ። ይሁን እንጂ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም’ የሚለውን በኢሳይያስ 2:​4 ላይ የሚገኝ መሠረታዊ ሥርዓት ለመከተል ወሰንኩ። በዚህም ምክንያት የአሥር ቀን እስር ተፈረደብኝ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጠልኩ። ከዚያም ሐምሌ 15, 1941 ለይሖዋ ያደረግሁትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።

በወቅቱ ናዚ ጀርመን ሶቭየት ሕብረትን ወርሮ የነበረ ሲሆን ምሥራቅ አውሮፓም በጦርነት ተውጣ ነበር። የጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች በጋለ ስሜት ይነዙ የነበረ ከመሆኑም በላይ የብሔረተኝነት ስሜት በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነታቸው ጋር በመስማማት ገለልተኝነታቸውን ጠብቀዋል።

ነሐሴ 1942 ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተሰነዘረብን። ባለ ሥልጣናቱ አሥር የተለያዩ ጣቢያዎችን አዘጋጅተው ወጣት ሽማግሌ ሳይሉ ሁሉንም ምሥክሮች በእነዚህ ቦታዎች ሰበሰቧቸው። ባይጠመቁም እንኳ ከእኛ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሁሉ ወደ እነዚህ ቦታዎች ተወስደው ነበር። እኔም ከምኖርበት ከፓሲን መንደር 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው የሻሮሽፓታክ ከተማ እስር ቤት ተወሰድኩ።

እስር ቤት ከገቡት ሁሉ የመጨረሻ ትንሽ የሚባለው የሦስት ወር ሕፃን ሲሆን የታሠረው ምሥክር ከሆነች እናቱ ጋር ነበር። ቢያንስ ለልጁ ትንሽ ምግብ እንዲሰጡት ስንጠይቅ አንደኛው ጠባቂ “ተዉት፣ ያልቅስ። ጠንካራ ምሥክር እንዲሆን ይረዳዋል” በማለት በቁጣ መለሰልን። ልጁ እጅግ ቢያሳዝነንም የዚህ ወጣት ጠባቂ ልብ በብሔራዊ ፕሮፓጋንዳ ሳቢያ መደንደኑ ግን ይበልጥ አሳዘነን።

ፍርድ ቤት ከቀረብኩ በኋላ የሁለት ዓመት እስር ተፈረደብኝ። ከዚያም 85 ማርጊት ኮሩት ወደሚባለው የቡዳፔስት እስር ቤት ተዛወርኩ። አራት በስድስት ሜትር ስፋት ባላቸው ክፍሎች ውስጥ ከ50 እስከ 60 የሚጠጉ ሰዎች ታጭቀዋል። በእነዚያ ክፍሎች ውስጥ ያላንዳች ውኃና መጸዳጃ ቤት ለ8 ወራት ቆይተናል። ልብሳችንን ይቅርና ገላችንን እንኳ እንድንታጠብ አይፈቀድልንም ነበር። ሁላችንም ቅማል ወርሶን የነበረ ሲሆን ሌሊት ደግሞ በቆሸሸው ገላችን ላይ ተባዮች ይፈነጩብን ነበር።

ከሌሊቱ 10 ሰዓት መነሳት ነበረብን። ለቁርስ የሚሰጠን አንድ ትንሽ ስኒ ቡና ብቻ ነበር። በምሳ ደግሞ እኩል መጠን ያለው ሾርባ 150 ግራም ከሚመዝን ዳቦና ከጥቂት ንፍሮ ጋር ይቀርብልን ነበር። ማታ ግን ምንም አይሰጠንም ነበር። በጊዜው ጥሩ ጤንነት የነበረኝ የ20 ዓመት ወጣት ብሆንም ቀስ በቀስ ግን መራመድ እስኪያቅተኝ ድረስ እየደከምኩ መጣሁ። እሥረኞች በረሃብና በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት መሞት ጀመሩ።

በዚህ ጊዜ አንድ አዲስ እስረኛ ወደ ክፍላችን መጣ። ይህ ሰው በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት የኦርቶዶክስ ቄስ ነበር። ወደ እስር ቤት ሲገባ መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲይዝ ተፈቅዶለት ነበር። መጽሐፉን ለማንበብ ምንኛ ጓጉቼ ነበር! ሆኖም እንዲሰጠኝ ስጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ይሁን እንጂ ትንሽ ቆየት አለና “ማነህ አንተ ልጅ፣ መጽሐፉን መውሰድ ትችላለህ። እሸጥልሃለሁ” አለኝ።

“እሸጥልሃለሁ? በምን?” ስል ጠየቅኩ። “ምንም ገንዘብ የለኝም።”

ቄሱ መጽሐፍ ቅዱሱን በሦስት ቀን የዳቦ ቀለቤ የለወጠኝ በዚህ ጊዜ ነበር። ይህ ልውውጥ ምንኛ የሚክስ ነበር! በአካላዊ መንገድ ብራብም እኔም ሆንኩ ሌሎች በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ለመጽናት የሚያስችለንን መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል። መጽሐፉ እስከዛሬ ድረስ ከእኔ ጋር አለ።​—⁠ማቴዎስ 4:​4

ገለልተኝነታችን ተፈተነ

ሰኔ 1943 በመላው ሃንጋሪ የምንገኘው 160 የምናክል ወጣት ወንድሞች ያዝበራን ወደተባለች ከቡዳፔስት አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ ተወሰድን። የወታደር ቆብና እጅ ላይ የሚደረገውን አርማ ለማድረግ ፈቃደኞች ባለመሆናችን በእቃ መጫኛ ፉርጎ ተጭነን ወደ ቡዳፔስት-ኮባንያ ባቡር ጣቢያ ተወሰድን። እዚያም የጦር አዛዦቹ አንድ በአንድ እየጠሩ ለውትድርና ፈቃደኞች መሆናችንን ሪፖርት እንድናደርግ አዘዙን።

“ሃይል ሂትለር” እንድንል ታዘዝን። እያንዳንዱ ምሥክር የተባለውን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ክፉኛ ተደበደበ። በመጨረሻ ግን ደብዳቢዎቹ ስለደከማቸው ከመካከላቸው አንዱ “እሺ፣ ለመጨረሻ ጊዜ አንድ እንደግማለን። ይኼኛውን ግን መቋቋም አይችልም” በማለት ተናገረ።

ቲቦር ሃፍነር የተባለ አንድ የቆየ ምሥክር በወታደሮቹ እጅ ያለውን የምሥክሮች ስም ዝርዝር አግኝቶ ነበር። ስለዚህ ወደ ጆሮዬ ጠጋ አለና “ወንድም፣ ቀጥሎ አንተ ነህ። አይዞህ! በይሖዋ ታመን” በማለት ሹክ አለኝ። ወዲያው ተጠራሁ። ፉርጎው በር ላይ ስቆም እንድወርድ ተነገረኝ። ከወታደሮቹ አንዱ “ምኑ ይደበደባል” በማለት ተናገረ። ከዚያም “ለውትድርና ፈቃደኛ መሆንህን ሪፖርት ካደረግህ ምግብ ቤት እንድትመደብ እናደርጋለን። አለዚያ ግን ትሞታለህ” አለኝ።

“ለውትድርና ፈቃደኛ መሆኔን ሪፖርት አላደርግም” ስል መለስኩለት። “ወንድሞቼ ወዳሉበት ፉርጎ መመለስ እፈልጋለሁ።”

ወታደሩ ስላሳዘንኩት ማጅራቴን ይዞ ፉርጎው ውስጥ ወረወረኝ። ክብደቴ ከ40 ኪሎ ግራም ያንስ ስለነበረ እንዲህ ማድረጉ አልከበደውም። ከዚያም ወንድም ሃፍነር እጁን ትከሻዬ ላይ አድርጎ ፊቴን እየደባበሰኝ “በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ” የሚለውን መዝሙር 20:​1ን ጠቀሰልኝ።

የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ መቆየት

ከዚህ በኋላ በመርከብ ተጭነን በዳኑቢ ወንዝ በኩል ወደ ዩጎዝላቪያ ተወሰድን። ሐምሌ 1943 በአውሮፓ በመዳብ ምርቷ ከምትታወቀው ቦር ከተባለች ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኘው የጉልበት ሥራ መሥሪያ ካምፕ ደረስን። ከጊዜ በኋላ የካምፑ ነዋሪዎች ቁጥር 6, 000 አይሁዶችንና 160 የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ወደ 60, 000 ገደማ ደርሶ ነበር።

ምሥክሮቹን በአንድ ትልቅ ያረጀ ሕንፃ ውስጥ አስገቡዋቸው። በሕንፃው መካከል ጠረጴዛዎችና አግዳሚ ወንበሮች ስለነበሩ በሳምንት ሁለት ጊዜ ስብሰባዎቻችንን እናደርግ ነበር። በተጨማሪም ወደ ካምፑ በድብቅ የሚገቡ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን እናጠናለን እንዲሁም በዳቦ ቀለቤ የለወጥኩትን መጽሐፍ ቅዱስ እናነብብ ነበር። መዝሙር እንዘምርና አብረን እንጸልይም ነበር።

ከሌሎች እስረኞች ጋር ለመግባባት መጣራችንም ጠቅሞናል። አንድ ወንድማችን ከባድ የአንጀት መታወክ ገጠመው፤ ሆኖም ጠባቂዎቹ እርዳታ ማግኘት የሚችልበትን ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። ሕመሙ እየተባባሰበት ሲመጣ አንድ አይሁዳዊ እስረኛ የቀዶ ሕክምና ሊያደርግለት ተስማማ። ለወንድም አንዳንድ ጥንታዊ ማደንዘዣዎች ከሰጠው በኋላ በተሳለ የማንኪያ እጀታ የቀዶ ሕክምናውን አደረገለት። ወንድም ተሽሎት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ወደ ቤቱ ተመልሷል።

በማዕድን ማውጫው የሚሠራው ሥራ በጣም አድካሚ ሲሆን ከፍተኛ የምግብ እጥረትም ነበረ። ሁለት ወንድሞች በሥራ ላይ እንዳሉ በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት ሲሞቱ አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ በበሽታ ምክንያት ሞቷል። መስከረም 1944 የሩሲያ ጦር እየቀረበ ሲመጣ ካምፑን ባዶ ለማድረግ ተወሰነ። ከዚያ በኋላ የተፈጸመውን ነገር በገዛ ዓይኔ ባላየው ኖሮ መፈጸሙን ለማመን ያዳግተኝ ነበር።

በሥቃይ የተሞላ የሰልፍ ጉዞ

ከብዙ አይሁዳውያን እስረኞች ጋር ተሰልፈን አንድ ሳምንት የፈጀ አድካሚ ጉዞ ካደረግን በኋላ ቤልግሬድ ደረስን። ከዚያም ተጨማሪ ጉዞ በማድረግ ቼርቬንኮ የተባለ መንደር ደረስን።

ቼርቬንኮ ስንደርስ የይሖዋ ምሥክሮች አምስት አምስት ሆነው እንዲሰለፉ ታዘዙ። ከዚያም ከእያንዳንዱ ረድፍ አንድ ምሥክር ተወሰደ። ሊገድሏቸው ነው ብለን ስላሰብን እንባ ባቀረረ ዓይናችን ተመለከትናቸው። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተመለሱ። ምን ተፈጠረ? ወታደሮቹ የወሰዷቸው መቃብር ሊያስቆፍሯቸው ቢሆንም አንድ ሃንጋሪያዊ አዛዥ ለሳምንት ምግብ ስላልበሉ መሥራት እንደማይችሉ ተናገረ።

በዚያ ምሽት ምሥክሮች የሆንነውን በሙሉ ሸክላ ለማድረቅ በሚያገለግል የአንድ ሕንፃ ጣሪያ ሥር ወሰዱን። አንድ የጀርመን ወታደር “ዝም ብላችሁ እዚህ ቆዩ። ይህ የጭንቅ ምሽት ነው” አለንና በሩን ቆልፎት ሄደ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ “ፍጥነት! ፍጥነት!” የሚል የወታደሮች ድምፅ ሰማን። ከዚያም የመትረየስ ድምፅ ተሰማና ወዲያው ደግሞ አስፈሪ ጸጥታ ሰፈነ። እንደገና “ፍጥነት! ፍጥነት!” የሚል የወታደሮች ድምፅ ሰማን። ከዚያም የተኩስ ድምፅ ተከተለ።

ሁሉንም ነገር በጣሪያው በኩል እንመለከት ነበር። ወታደሮቹ አይሁዳውያኑን እስረኞች በቡድን በቡድን አድርገው ጉድጓዱ ጠርዝ ላይ እንዲቆሙ ካደረጓቸው በኋላ ይተኩሱባቸዋል። ከዚያም በተከመረው ሬሳ ላይ የእጅ ቦንብ ይጥላሉ። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ከስምንት አይሁዳውያን በስተቀር ሁሉም ተገድለው ነበር። በመጨረሻም የጀርመን ወታደሮች አካባቢውን ጥለው ሸሹ። በአእምሮም ሆነ በአካል ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶብን ነበር። ዛሬ በሕይወት ያሉት ያኖስ ቶሮክ እና ያን ባሊ የተባሉት ምሥክሮች በግድያው ወቅት በቦታው ነበሩ።

በሕይወት መትረፍ

በሃንጋሪ ወታደሮች ታጅበን ወደ ምዕራብና ወደ ምሥራቅ የምናደርገውን ጉዞ ቀጠልን። በተደጋጋሚ ጊዜያት በጦር ኃይሉ ውስጥ እንድንካፈል ጥያቄ ይቀርብልን ነበር። ሆኖም ገለልተኝነታችንን መጠበቅና በሕይወት መትረፍ ችለናል።

ሚያዝያ 1945 ሃንጋሪንና አውስትራሊያን በሚያገናኛቸው ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ዞምባትሊ የተባለች ከተማ በጀርመንና በሩሲያ ወታደሮች መካከል ገብተን ነበር። የአየር ድብደባ እንደሚኖር ሲገለጽ እንዲጠብቀን የታዘዘ አንድ ሃንጋሪያዊ ካፒቴን “ጥበቃ ለማግኘት ከእናንተ ጋር እንድሄድ ትፈቅዱልኛላችሁ? አምላክ ከእናንተ ጋር እንደሆነ ማየት ችያለሁ” ሲል ጠየቀን። የቦምብ ድብደባው እንዳበቃ መሬት ላይ በተረፈረፈው የሰውና የእንስሳ ሬሳ ላይ እየተራመድን ከተማዋን ለቅቀን ወጣን።

የጦርነቱ ማብቂያ ሲቃረብ ያው ካፒቴን ሁላችንንም ሰበሰበንና “ስላከበራችሁኝ አመሰግናለሁ። ለእያንዳንዳችሁ የሚሆን ስኳርና ሻይ አለኝ። ከምንም ይሻላል” በማለት ተናገረ። አቅሙ የፈቀደውን ያህል በርኅራኄና በደግነት ስለያዘን አመሰገንነው።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሩሲያውያን ወታደሮች በመድረሳቸው በትንንሽ ቡድኖች ሆነን ወደ ቤታችን አቀናን። ሆኖም ፈተናችን ገና አላበቃም ነበር። ቡዳፔስት ከደረስን በኋላ በሩሲያውያን ወታደሮች አጃቢነት ለሌላ ወታደራዊ ምልመላ ማለትም ለሶቭየት ሕብረት ጦር ታጨን።

ጉዳዩን እንዲከታተል የተመደበው ሰው ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሩሲያዊ መኮንንና የሕክምና ዶክተር ነበር። ክፍሉ ስንገባ እኛ ባናውቀውም እርሱ ግን አወቀን። ቦር በሚገኘው የጉልበት ሥራ መሥሪያ ካምፕ ከእኛ ጋር የነበረና ከናዚ ጭፍጨፋ ከተረፉት ጥቂት አይሁዳውያን መካከል አንዱ ነው። ወዲያው እንዳየን “እነዚህ ስምንት ሰዎች ወደ ቤታቸው ይሂዱ፣ ተውአቸው” በማለት ጠባቂዎቹን አዘዛቸው። ለዚህም አመሰገንነው። ከሁሉም በላይ ግን ስላደረገልን ጥበቃ ይሖዋን አመሰገንን።

ተስፋዬ አሁንም አልደበዘዘም

በመጨረሻ ሚያዝያ 30, 1945 ፓሲን የሚገኘው ቤቴ ደረስኩ። ብዙም ሳይቆይ ሥልጠናዬን ለመጨረስ ስተሬዳ ናድ ቦድሮጎም ወደሚገኘው ቀጥቃጭ ቤት አመራሁ። የፓንኮቪክስ ቤተሰብ ራሴን ለመደገፍ የሚያስችለኝን ሙያ ብቻ ሳይሆን ሕይወቴን የለወጡ አስፈላጊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችንም አካፍሎኛል። አሁን ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ነገር ሰጠኝ። መስከረም 23, 1946 ዮላና የተባለችውን ውብ ልጃቸውን አገባሁ።

ዮላና እና እኔ አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንንና መስበካችንን ቀጠልን። ከዚያም በ1948 የአንድሬ ወላጆች የመሆን ተጨማሪ በረከት አገኘን። ሆኖም ያገኘነው ሃይማኖታዊ ነጻነት ብዙም አልዘለቀም። ብዙም ሳይቆይ ኮሚኒስቶች አገራችንን ሲቆጣጠሩ ሌላ የስደት ማዕበል ጀመረ። በ1951 በቺኮዝሎቫክ ኮሚዩኒስታዊ ባለ ሥልጣናት ለውትድርና ተመለመልኩ። በዚህ ጊዜ ያው ያለፈው ታሪክ ተደገመ:- ፍርድ ቤት፣ የእስር ፍርድ፣ የጉልበት ሥራና ረሃብ ተፈራረቀብኝ። ሆኖም በአምላክ እርዳታ እንደገና በሕይወት መትረፍ ቻልኩ። በ1952 በአመክሮ ከእስር ተፈታሁና ላድሞቭሲ ስሎቫኪያ ከሚገኘው ቤተሰቤ ጋር ተቀላቀልኩ።

አርባ ለሚያክሉ ዓመታት በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ እገዳ ቢጣልም ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችንን አላቋረጥንም። ከ1954 እስከ 1988 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አገኘሁ። ቅዳሜና እሁድ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች በመጎብኘት ወንድሞችና እህቶች ጽኑ አቋማቸውን እንዲጠብቁ አበረታታቸው ነበር። በሳምንቱ ቀናት ደግሞ ቤተሰቤን በቁሳዊ ለመደገፍ ሰብዓዊ ሥራ እሠራለሁ። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት የይሖዋ ፍቅራዊ መመሪያ እንዳልተለየን ተሰምቶናል። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ ቃላት እውነት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ:- “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፣ ቍጣቸው በላያችን በነደደ ጊዜ፣ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር።”​—⁠መዝሙር 124:​2, 3

ከጊዜ በኋላ ዮላና እና እኔ አንድሬ የተባለው ልጃችን ሲያገባና በመጨረሻም የጎለመሰ ክርስቲያን ሽማግሌ ሲሆን በመመልከታችን ተደስተናል። ባለቤቱ ኤልሺካ እንዲሁም ራዲምና ዳንኤል የተባሉት ሁለቱ ወንዶች ልጆቹ ጭምር ንቁ ክርስቲያን አገልጋዮች ሆነዋል። ከዚያም በ1998 ውዷ ዮላና ስትሞት ከፍተኛ ኀዘን ላይ ወደቅሁ። ከደረሱብኝ ፈተናዎች ሁሉ ለመቋቋም የከበደኝ ይሄኛው ነበር። ዮላና በየቀኑ ትናፍቀኛለች። ሆኖም ድንቅ በሆነው የትንሣኤ ተስፋ እጽናናለሁ።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

አሁን በ79 ዓመት እድሜዬ ስሎቫኪያ በሚገኘው ስሎቬንስኪ ኖቬ ሜስቶ መንደር ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ። እዚህ ውድ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለጎረቤቶቼ በማካፈል እጅግ እደሰታለሁ። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ60 የሚበልጡ ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስታውስ በእርሱ እርዳታ ሁሉንም ዓይነት መሰናክሎችና ፈተናዎች ማለፍ እንደምንችል ተገንዝቤአለሁ። ፍላጎቴና ተስፋዬ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ” ከሚሉት የመዝሙር 86:​12 ቃላት ጋር ተስማምቶ መኖር ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዳቦ ቀለቤ የለወጥኩት መጽሐፍ ቅዱስ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲቦር ሃፍነር በፈተናዎቼ እንድጸና አበረታቶኛል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቦር የጉልበት ሥራ መሥሪያ ካምፕ የነበሩ ምሥክሮች

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጀርመን ወታደሮች በተገኙበት በቦር ካምፕ የተደረገ የአንድ ምሥክር የቀብር ሥነ ሥርዓት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መስከረም 1946 ዮላናን አገባሁ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጭፍጨፋው ወቅት የነበሩት ያኖስ ቶሮክ እና ያን ባሊ (በስተቀኝ)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከወንድ ልጄ፣ ከባለቤቱና ከልጅ ልጆቼ ጋር