በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተወዳጅነት ለማትረፍ የበቃው “የፍቅር ፖም”

ተወዳጅነት ለማትረፍ የበቃው “የፍቅር ፖም”

ተወዳጅነት ለማትረፍ የበቃው “የፍቅር ፖም”

ስፔይን የሚገኘው የንቁ ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት “የፍቅር ፖም” በደቡብ አሜሪካ በአንዲስ ተራራዎች አካባቢ አልፎ አልፎ ብቻ የሚታይ ተክል ነበር። ፍሬዎቹ ጥሩ ጣዕም ያላቸው ቢሆኑም የአገሩ ሕንዶች አይተክሉትም ነበር። ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ ተክል ባልታወቀ መንገድ ወደ ሜክሲኮ ተዛመተና አዝቴክ የሚባሉት የአገሩ ነዋሪዎች ሲቶማትል የሚል ስም አወጡለት። ቶማትል የሚለው ቃል ተመሳሳይ የሆኑና በአብዛኛው ብዙ ፈሳሽ ያላቸውን ፍራፍሬዎች ለማመልከት ይሠራበት ነበር። ብዙም ሳይቆይ የቲማቲም ድልህ ወይም ሳልሳ አዝቴኮች የሚያዘወትሩት ዋነኛ የምግብ ክፍል ከመሆኑም በላይ ቲማቲም ቀስ በቀስ ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘ መጣ።

የስፓኝ ቅኝ ገዥዎችም የቲማቲም ድልህ በጣም ጣፋጭ ሆኖ አግኝተውታል። በ1590 አብዛኛውን ዕድሜያቸውን በሜክሲኮ ያሳለፉ አንድ የካቶሊክ ቄስ ቲማቲም ሲበሉት የሚጣፍጥና ወጥ የሚያጣፍጥ ብዙ ጭማቂ ያለው ፍሬ እንደሆነ ተናግረዋል። ስፔናውያኑ የቲማቲም ዘሮችን ከሜክሲኮ ወደ ስፔይን እና በካሪብያንና በፊሊፕንስ ወደሚገኙ ቅኝ ግዛቶቻቸው ላኩ። ይሁን እንጂ ይህን በመሰለ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ መሰራጨት የጀመረው ቲማቲም በዓለም ወጥ ቤቶች መዘውተር የጀመረው ሦስት ምዕተ ዓመታት ያህል ቆይቶ ነው።

ሰዎች ያደረባቸው ጥላቻ

ሰዎች አንድን ነገር ከጠሉ ያንን ጥላቻቸውን እንዲያስወግዱ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ሁሉ አንድን ምግብ በተመለከተ የሚያድርባቸውንም ጥላቻ እንዲወገድ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ቲማቲም በሜክሲኮ ጥሩ ዝና ያተረፈ ቢሆንም በአውሮፓ ግን መጥፎ ስም ተሰጥቶታል። ለችግሩ መንስኤ የሆነው አውሮፓውያን የሥነ ዕፅዋት ባለሙያዎች ቲማቲምን መርዛማ ከሆነው የእንቧይ ዝርያ ውስጥ መመደባቸው ነው። በተጨማሪም የቲማቲም ቅጠል የሚሰነፍጥ መጥፎ ሽታ ያለው ከመሆኑም በላይ መርዛማ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። አንዳንድ መድኃኒት አዋቂዎች ደግሞ ቲማቲም ፍትወተ ሥጋ ይቀሰቅሳል ማለታቸው ሁኔታውን ይበልጥ አወሳስቦታል። ፈረንሳዮች ቲማቲምን ፖም ዳሙር ወይም “የፍቅር ፖም” ብለው የሰየሙት በዚህ ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑ አሉ።

ቲማቲም ያተረፈው መጥፎ ስም ወደ ሰሜን አሜሪካም ተዛምቷል። በ1820ዎቹ ዓመታት በማሳቹሴትስ ይኖር የነበረ አንድ አሜሪካዊ አትክልተኛ “[ቲማቲም] በጣም የሚያስጠላ ከመሆኑ የተነሣ በጣም ካልራበኝ በስተቀር ልቀምሰው እንኳን አልፈልግም” ብሏል። የቲማቲም ጥላቻ ያደረበት ይህ ሰው ብቻ አይደለም። አንድ ፔንስልቫንያዊ “ኮምጣጣ ጉድፍ” ብሎ ሲጠራው በዚያው ዘመን ይኖር የነበረ ብሪታንያዊ አትክልተኛ ደግሞ “ግም የሆነው ወርቃማ ፖም” ብሎታል።

በ16ኛው ምዕተ ዓመት ለቲማቲም ፖሞዶሮ (ወርቃማ ፖም) የሚል ስም የሰጡት ኢጣሊያ​ውያን ግን በጭፍን ከመጥላት ይልቅ መጀመሪያ መሞከር መርጠዋል። * በ17ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቲማቲም በኢጣሊያ ተወዳጅ ምግብ ሆነ። የአገሩም ፀሐያማ የአየር ሁኔታ ተክሉን በደንብ ለማልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ይሁን እንጂ የሰሜን አውሮፓ አትክልተኞች ለሁለት ምዕተ ዓመታት ያህል በምግብነት ሳይቀበሉት ቆይተዋል። ይተክሉት የነበረውም ለጌጥነትና ለመድኃኒትነት ብቻ ነበር።

ጥላቻው ተወግዶ ተወዳጅነት አተረፈ

ይሁን እንጂ ሰዎች አንዴ ቲማቲም መቅመስ ከጀመሩ በኋላ የነበራቸው ጥላቻ በሙሉ ይወገድና በሰፊው ቲማቲም ማልማት ይጀምራሉ። በመሆኑም በ1870ዎቹ ዓመታት አሕጉር አቋራጭ የባቡር ሐዲድ በመዘርጋቱ ትኩስ የካሊፎርኒያ ቲማቲም በኒው ዮርክ ይሸጥ ነበር። ይህ ከመሆኑ ጥቂት አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ የመጀመሪያው የፒሣ ቤት በኢጣሊያ አገር በኔፕልስ ከተማ ተከፍቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የቲማቲም ተፈላጊነት እየጨመረ መጣ። በ20ኛው ምዕተ ዓመት ደግሞ የቲማቲም ድልህ፣ የቲማቲም ጭማቂ፣ የቲማቲም ሾርባና የፒሣ ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ በጣም ይጠላ የነበረው ቲማቲም በመላው ዓለም ከፍተኛ ተወዳጅነት ሊያተርፍ ቻለ። (አባሪውን ሣጥን ተመልከት።) በሰፋፊ እርሻዎች የሚመረት ከመሆኑ በተጨማሪ ከመካከለኛው ምሥራቅ ምድረ በዳዎች እስከ ሰሜን ባሕር በሚገኙ አትክልተኞች የሚወደድ ተክል ሆኗል።

ከሲና እስከ ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎች

በሰሜን ባሕር ውስጥ በሚገኝ የነዳጅ ማውጫ ጣቢያ ፍራፍሬና አትክልት ይተከላል ተብሎ አይታሰብም። ይሁን እንጂ ቲማቲም ብዙ ምቾት የሚፈልግ ተክል አይደለም። የቲማቲም ዘር በቂ ውኃ ካገኘ አፈር ባይኖር እንኳን አስፈላጊዎቹ ንጥረ ነገሮች ተጨምረውበት ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ የፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ ሊያድግ ይችላል። በዚህ ምክንያት ከቧንቧዎችና ከመሣሪያዎች በስተቀር አንዳች ሕይወት ያለው ነገር በማይታይበት አካባቢ የሚሠሩት የነዳጅ ዘይት ሠራተኞች አረንጓዴ ነገር ማየትና ራሳቸው የተከሉትን ፍሬ ማዕዳቸው ላይ ማቅረብ ስለሚያስደስታቸው ቲማቲም ተወዳጅ ተክል ሆኖላቸዋል።

በተጨማሪም ቲማቲም መጠነኛ እንክብካቤ ከተደረገለት በበረሃም ሊበቅል ይችላል። በግብጽ አገር በሲና ተራሮች ተበታትነው የሚኖሩ አንዳንድ ዘላን አረቦች እርከን ሠርተው የምንጭ ወይም የጉድጓድ ውኃ እያጠጡና አልፎ አልፎ በሚዘንበው የዝናብ ውኃ እየተጠቀሙ አትክልት ያለማሉ። ውኃ በደንብ የሚጠጣው የአትክልት ቦታቸው በጣም ብዙ ቲማቲም ያመርታል። ይህንኑ ምርታቸውን በፀሐይ አድርቀው በክረምቱ ወራት ይመገቡታል።

ይሁን እንጂ ቲማቲም በመላው ዓለም ሊታወቅና ሊለማ የቻለው ከተለያየ የአፈርና የአየር ሁኔታ ጋር ሊላመድ በመቻሉ ብቻ አይደለም። አብዛኞቹ የቲማቲም ዝርያዎች እርስ በርሳቸው ሊራቡ በመቻላቸው የተለያየ ጣዕም ያላቸው ብዙ ዝርያዎችን ማዳቀል ይቻላል። ባሁኑ ጊዜ አትክልተኞች 4, 000 ከሚያክሉ የተለያዩ ዝርያዎች መካከል የፈለጉትን ሊያማርጡ ይችላሉ። ትንሿና ቀላ የምትለው ቲማቲም ብዙ ውኃ ያላት ስትሆን ለሰላጣ ጥሩ ጣዕምና ውበት ትሰጣለች። ሞላላ የሆነው ጣፋጭ ቲማቲም ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በቆርቆሮ ይታሸጋል። ትልቁና ባለብዙ ሥጋው ቲማቲም ደግሞ የስፓኞች ዋነኛ ምግብ ሲሆን ለሰላጣና ለወጥ መስሪያ በጣም ይወደዳል።

ቲማቲም ውሎ አድሮ ተወዳጅነት ሊያተርፍ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ግን ጣዕሙ ነው። እጅ የሚያስቆረጥመው ጣዕሙ ለፒሣ፣ ለሰላጣ፣ ለስጎም ሆነ ለጭማቂ ማጣፈጫነት ያገለግላል። ቲማቲም “የፍቅር ፖም” ሊሆን ባይችልም የመላውን ዓለም ፍቅር ያተረፈ ፍሬ ሆኗል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ቲማቲም ይህ ስያሜ ሊሰጠው የቻለው ኢጣሊያውያን ይተክሏቸው የነበሩት የመጀመሪያዎቹ የቲማቲም ዝርያዎች ቢጫ ስለነበሩ እንደሆነ ይታሰባል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ጋዝፓቾምርጥ የቲማቲም ሾርባ

በሞቃት ጊዜ ቀዝቀዝ የሚያደርግ ጥሩ ጣዕም ያለው ቀዝቃዛ ሾርባ ለመቅመስ ትፈልጋለህ? በስፔን አገር በአንዳሉዥያ አካባቢ በየቀኑ ማለት ይቻላል፣ ከዋናው ምግብ ጋር ጋዝፓቾ የሚባል ሾርባ ይቀርባል። ጋዝፓቾ፣ በቀላሉ ሊገኙ ከሚችሉ አትክልቶች የሚዘጋጅና አዘገጃጀቱም ከባድ ያልሆነ፣ የምግብ ፍላጎት የሚከፍት ለጤና ተስማሚ የሆነ ሾርባ ነው። ለአምስት ሰው የሚበቃ ጋዝፓቾ እንደሚከተለው ማዘጋጀት ይቻላል።

ተፈላጊ አትክልቶችና ቅመሞች

600 ግራም ቲማቲም

350 ግራም ኪያር (ኩከምበር)

250 ግራም ቀይ የፈረንጅ ቃሪያ

60 ግራም ደረቅ ዳቦ

30 ሚሊ ሊትር ኮምጣጤ

30 ሚሊ ሊትር የወይራ ዘይት

ጨው

አንድ ፍንካች ነጭ ሽንኩርት

ትንሽ ቁንጣሪ ከሙን

አዘገጃጀት የቃሪያዎቹ ፍሬ ይወጣል፣ ኪያሩና ቲማቲሙ ይላጣል። ከዚያ በኋላ ሁሉም አትክልቶች በደቃቁ ይከተፋሉ። በጎድጓዳ ሣህን ውስጥ ጨምርና አንድ ሊትር ውኃ (አትክልቶቹን ለመሸፈን የሚበቃ ውኃ) ጨምርበት። ዳቦው፣ ነጭ ሽንኩርቱና ቅመሙ፣ እንዲሁም ኮምጣጤውና ዘይቱ ይጨመራሉ። ሾርባው ሌሊቱን በሙሉ እንዳለ ካደረ በኋላ በሚቀጥለው ቀን በእጅ መምቻ ተመትቶ በማጥለያ ይጠላል። አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ ቅመም መጨመር ይቻላል። ሾርባው እስከሚቀርብበት ጊዜ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቆያል። ጋዝፓቾው በደቃቁ ከተከተፈ ቲማቲም፣ ኪያርና የፈረንጅ ቃሪያ ጋር ሊቀርብ ይችላል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቲማቲምን አስመልክቶ የቀረቡ መረጃዎች

ቲማቲም በመላው ዓለም ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ ፍሬ ሆኗል። በየዓመቱ የሚመረተው የቲማቲም ብዛት አንድ ቢልዮን ኩንታል የሚደርስ ሲሆን ይህም ከሌሎቹ ዋና ዋና ፍራፍሬዎች (ከፖም፣ ከሙዝ፣ ከወይንና ከብርቱካን) የምርት መጠን በእጅጉ ይበልጣል።

ቲማቲም አንዳንድ ጊዜ ከአትክልት የሚመደብ ቢሆንም ዘሩ የሚገኘው በሚበላው የተክሉ ክፍል ውስጥ በመሆኑ በዋነኛነት የሚመደበው ከፍራፍሬዎች ነው። (አብዛኛውን ጊዜ አትክልት የሚባሉት ግንዳቸው፣ ቅጠላቸውና ሥራቸው የሚበሉት ተክሎች ናቸው።)

ዘ ጊነስ ቡክ ኦቭ ሪከርድስ እንደሚለው ከሆነ እስከ ዛሬ ከተመዘገቡት ቲማቲሞች መካከል በትልቅነቱ አንደኛ የሆነው በኦክላሆማ፣ ዩ ኤስ ኤ የተተከለውና 3.5 ኪሎ ግራም የተመዘነው ቲማቲም ነው።

ሰዎች በተክሉ አጠገብ ትምባሆ የሚያጨሱ ከሆነ ወይም ባጨሱበት እጃቸው የሚነካኩት ከሆነ ተክሉ ሊጎዳ ይችላል። በትንባሆ ውስጥ ቲማቲም የሚያጠቃ ቫይረስ ይገኛል።

ቲማቲም ቪታሚን ኤ እና ሲን ከመያዙም በላይ ላይኮፒን የሚባል በኦክሲጅን ሳቢያ የሚከሰትን ኬሚካላዊ ለውጥ የሚከላከል ንጥረ ነገር አለው። ብዙ ቲማቲም መብላት ካንሰር ሊከላከል እንደሚችል አንዳንድ የምርምር ጥናቶች ያመለክታሉ።