በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ፀጉርህ ትጨነቃለህን?

ስለ ፀጉርህ ትጨነቃለህን?

ስለ ፀጉርህ ትጨነቃለህን?

በርካታ ሰዎች የፀጉራቸውን ሁኔታ በመስተዋት እያዩ በየቀኑ ብዙ ሰዓት የሚያሳልፉ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንተም ትገኝበት ይሆናል። ስለ ፀጉር ማሰብ ወንድ ሴት የማይል ከመሆኑም በላይ ትልቅ ጭንቀት የሚፈጥርበት ጊዜም አለ።

ስለ ፀጉርህ አንዳንድ ሁኔታዎችን እወቅ

በራስ ቅልህ ላይ ስንት ፀጉሮች እንዳሉ ታውቃለህ? በአማካይ 100, 000 ይደርሳሉ። አንድ ነጠላ ፀጉር የሚያድገው ዕድሜ ልክ ሳይሆን ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ይረግፍና ከጥቂት የሽግግር ጊዜ በኋላ ከዚያው ቀዳዳ አዲስ ፀጉር መብቀል ይጀምራል። አንድ ነጠላ ፀጉር የራሱ የሆነ የአስተዳደግ ኡደት አለው። (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) በዚህ ኡደት ምክንያት ምንም ዓይነት የፀጉር ችግር ከሌለበት ሰው እንኳን በእያንዳንዱ ቀን ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ ፀጉሮች ይረግፋሉ።

የፀጉር ቀለም የሚለያየው በምን ምክንያት ነው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የፀጉር ቀለም በአብዛኛው የሚወሰነው ሜላኒን የተባለው ጥቁር ቡናማ ቀለም ባለው ሥርጭትና መጠን ነው።” ሜላኒን በፀጉር፣ በቆዳና በዐይን ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ቀለም ነው። የቀለሙ መጠን በጨመረ መጠን ፀጉርም ጠቆር እያለ ይሄዳል። የሜላኒን መጠን እያነሰ ሲሄድ ደግሞ የፀጉር ቀለም ከጥቁር ወደ ቡናማነት ወይም ወደ ቢጫነት ያደላ ይሆናል። ፀጉሩ ምንም ሜላኒን ከሌለው ግን ሙሉ በሙሉ ነጭ ይሆናል።

ከፎረፎር ሌላ ብዙዎችን የሚያሳስባቸው የፀጉር መርገፍ አለዚያም የፀጉር መሸበት ነው።

ፀጉርህ ሸብቷል?

ሽበት ብዙውን ጊዜ የእርጅና እና የአረጋዊነት ምልክት ተደርጎ ይታያል። እርግጥ ነው፣ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ፀጉር ይሸብታል። ይሁን እንጂ ሽበት የሚመጣው በእርጅና ምክንያት ብቻ አይደለም። በቂ ምግብ እንዳለመመገብ ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያሸብቱ ታውቋል። ሽበት ጠቆር ያለ ፀጉር ባላቸው ላይ ጎልቶ የሚታይ ይሁን እንጂ ጾታም ሆነ የፀጉር ቀለም አይመርጥም።

አንዳንዶች በመሸበታቸው ምክንያት ከዕድሜያቸው በላይ ያረጁ መስለው ሊታዩና ይህም አሳሳቢ ሊሆንባቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ባለመሸበታቸው ምክንያት ትክክለኛው ዕድሜያቸውና መልካቸው አለመመሳሰሉ የሚያሳስባቸው ሰዎች አሉ።

ፀጉር ከሸበተ ሞተ ማለት አይደለም። እርግጥ ነው በዓይን የሚታየው ውጪያዊ የፀጉር ክፍል በድን ነው። የእያንዳንዱ ፀጉር ሥር ከቆዳ በታች ጠልቆ ይገባል። ይህ ክፍል የፀጉር ሥር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሕይወት ያለው የፀጉር ክፍል ይህ ብቻ ነው። የፀጉር ሥር እንደ ፀጉር ፋብሪካ ሆኖ ያገለግላል። በሥሩ ውስጥ ያሉት ሴሎች በብዛት ተራብተው ፀጉር ሲፈጠር የቀለም ሴሎች የሚሠሩትን ሜላኒን ይቀባል። በዚህም የተነሣ የቀለም ሴሎች ሜላኒን መሥራት ካቆሙ ፀጉር ነጭ ይሆናል።

የቀለም ሴሎች በድንገት ሜላኒን መሥራታቸውን የሚያቆሙት ለምን እንደሆነ ማንም የሚያውቅ የለም። በዚህም ምክንያት ለሽበት የሚሆን አስተማማኝ መድኃኒት ሊገኝ አልተቻለም። በተጨማሪም ሥራቸውን አቁመው የነበሩ የቀለም ሴሎች እንደገና መሥራት ሊጀምሩ እንደሚችሉ ሊታወቅ ተችሏል። ፀጉርን አስመልክተው የተነገሩ ብዙ አባባሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱ ስለ ነጭ ፀጉር ይናገራል። “አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልም” ብሏል። (ማቴዎስ 5:​36) እነዚህ ቃላት ሽበት ማስቀረትም ሆነ ማስወገድ ከሰው አቅም በላይ መሆኑ ከታወቀ ብዙ ዘመን ያለፈው መሆኑን ያመለክታሉ።

አንዳንዶች ሜላኒን እንደመወጋት ያሉትን አዳዲስ ሕክምናዎች ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ፀጉራቸውን ቀለም ይቀባሉ። ይህም ቢሆን ዛሬ የመጣ ልማድ አይደለም። የጥንቶቹ ግሪካውያንና ሮማውያን ፀጉራቸውን ቀለም ይቀቡ ነበር። የጥንት ግብጻውያን በበሬ ደም ፀጉራቸውን ያቀልሙ ነበር። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን ይኖር የነበረው ታላቁ ሄሮድስ ዕድሜውን ለመሸሸግ ሽበቱን ቀለም ይቀባ እንደነበረ ተመዝግቧል።

ይሁን እንጂ በየጊዜው ቀለም መቀባት ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ የአንዳንዶችን ቆዳ ሊያስቆጣ ወይም ሊያቆስል ይችላል። ሽበትህን በቀለም ለማጥቆር ብትወስንም መቀባትህን ለማቆም የምትፈልግበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ ከሥር የሚያድገውን ሽበት መሸሸግ አስቸጋሪ ይሆንብሃል። ሽበት በአዎንታዊ ጎኑ የሚያምርና ከዚህ በፊት ያልነበረህን ግርማ ሞገስ የሚያስገኝልህ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሸበተ ፀጉር በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” ይላል።​—⁠ምሳሌ 16:​31 NW

የፀጉር መሳሳትና ራሰ በራነት

ሌላው የተለመደ የፀጉር ችግር የፀጉር መሳሳትና ራሰ በራነት ነው። እነዚህም ችግሮች ቢሆኑ ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። በጥንቷ ግብጽ ለራሰ በራነት ከአንበሳ፣ ከጉማሬ፣ ከአዞ፣ ከድመት፣ ከእባብና ከዝይ ስብ የተቀመመ መድኃኒት ይሰጥ ነበር። በዛሬው ጊዜ ራሰ በራነትንና የፀጉር መሳሳትን ይከላከላሉ የሚባሉ በርካታ ሸቀጦች ሲኖሩ ለእነዚህ ሸቀጦች በየዓመቱ የሚፈሰው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው።

በራነት የሚጀምረው ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል ሲዛባ ነው። ትክክለኛው የፀጉር አበቃቀል በምግብ አለመመጣጠን፣ ረዥም ጊዜ በሚቆይ ትኩሳት ወይም በቆዳ በሽታ ባሉ ምክንያቶች የተነሳ ሊዛባ ይችላል። በተጨማሪም የፀጉር አበቃቀል እንደ እርግዝናና ልጅ መውለድ ባሉ ምክንያቶች ስለሚዛባ አዲስ ፀጉር መብቀል ከመጀመሩ በፊት ብዙ ፀጉር ሊረግፍ ይችላል። የፀጉሩን አስተዳደግ ያዛባው ምክንያት ሲወገድ ግን እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ ይቆምና ወደ መደበኛው ሁኔታ ይመለሳል።

ሌላው ዓይነት የፀጉር መርገፍ ደግሞ ላሽ ይባላል። * ይህ ችግር በሚኖርበት ጊዜ በአንድ አካባቢ ያለ በርካታ ፀጉር አንድ ጊዜ ይረግፋል። ላሽ የሚመጣው በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ በሚደርስ ቀውስ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር በቅርቡ የተደረጉ የሕክምና ጥናቶች ያመለክታሉ።

በጣም የተለመደው የፀጉር መርገፍ በወንዶች ላይ የሚደርሰው የራሰ በራነት ዓይነት ነው። ከፊት ያለው ፀጉር ገባ ገባ በማለት ወይም መሐል አናት ላይ ሳሳ በማለት ይጀምርና ቀስ በቀስ እየተባባሰ ይሄዳል። በነዚህ አካባቢዎች ያለው የፀጉር እድገት የተዛባ ሆኖ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ጨርሶ ወደማቆም ይደርሳል። ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “በራነት በጀመረው አካባቢ በነበረው ረዥም፣ ጠንካራና ባለቀለም ፀጉር ፋንታ አጭር፣ ለስላሳና የወየበ ቀለም ያለው ፀጉር መብቀል ይጀምራል።” የፀጉሩ እድገት እየቀጠለ ሲሄድ እየሳሳና ዕድሜው እያጠረ ሄዶ ምንም ፀጉር ከማይበቅልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። ይህ የሚሆነው በዘር ውርሻና በወንዶች ሆርሞኖች ምክንያት ነው።

የወንዶች ራሰ በራነት ከአፍላ የጉርምስና ዕድሜ አንስቶ ሊጀምር ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በ30ዎቹ ዓመታት መገባደጃና በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ነው። እንዲህ ያለው የፀጉር መርገፍ በብዙ ወንዶች ላይ የሚደርስ ቢሆንም መጠኑ ከዘር ወደ ዘርና ከግለሰብ ወደ ግለሰብ ይለያያል። ያም ሆነ ይህ ለዚህ ችግር የተረጋገጠ መድኃኒት ማግኘት አልተቻለም። አንዳንዶች በራቸውን ለመሸፈን ሰው ሠራሽ ፀጉር ለማድረግ ወይም በቀዶ ሕክምና ፀጉር ለማስተከል ይመርጡ ይሆናል። ለተቀረው ፀጉር ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ፀጉሩ እንዳይረግፍ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

የአንድ ሰው ፀጉር አንዴ መሳሳት ከጀመረ ጨርሶ ይመለጣል ማለት አይደለም። ነጠላ ፀጉሮች በመቅጠናቸው ምክንያት ሳስቶ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ የፀጉር ውፍረት ምን ያህል ነው? አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ50 እስከ 100 ማይክሮን ሊደርስ ይችላል። * አንድ ሰው እያረጀ ሲሄድ ፀጉሩ ይቀጥናል። የጥቂት ማይክሮኖች መቀነስ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ 100, 000 የሚያክሉ ፀጉሮች መኖራቸውን አትዘንጉ። ስለዚህ ነጠላ ፀጉሮች በትንሹ እንኳን ቢቀጥኑ በጠቅላላው የፀጉር ብዛት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ከፍተኛ ይሆናል።

ለፀጉርህ እንክብካቤ አድርግ

ፀጉር በየወሩ 10 ሚሊ ሜትር ያህል ያድጋል። ፈጣን እድገት ካላቸው የሰውነት ክፍሎች አንዱ ነው። የሰውነት ፀጉሮች እድገት በሙሉ አንድ ላይ ቢደመር በየቀኑ 20 ሜትር ያህል ያድጋል ማለት ነው።

ለሽበትና ለራሰ በራነት ፍቱን የሆነ መድኃኒት ገና ያልተገኘ ቢሆንም ያለንን ፀጉር ለመንከባከብ ብዙ ልናደርግ የምንችለው ነገር አለ። በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብና የራስ ቅል በቂ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከመጠን በላይ ምግብ መቀነስ ወይም የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ሽበትና የፀጉር መሳሳት ሊያፋጥን ይችላል። አዘውትረን ፀጉራችንን መታጠብና የራስ ቅል ቆዳን በጥፍር ሳይቧጥጡ ጥሩ አድርጎ ማሸት ጥሩ እንደሆነ ባለሞያዎች ይመክራሉ። ይህን ማድረግ የራስ ቅል ጥሩ የደም ዝውውር እንዲያገኝ ያስችላል። ፀጉራችሁን በሣሙና ወይም በሻምፖ ከታጠባችሁ በኋላ ጥሩ አድርጋችሁ አለቅልቁት።

ፀጉራችሁን በኃይል አታበጥሩ። ፀጉራችሁ ረዥም ከሆነ መጀመሪያ ላይ ከሥር ጀምሮ እስከጫፍ አለማበጠር ጥሩ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ ፀጉራችሁን መሐል ላይ ይዛችሁ ጫፍ ጫፉን በማበጠር አፍታቱት። ቀጥላችሁ ከመሐል አንስታችሁ እስከጫፍ አበጥሩ። በመጨረሻም ፀጉራችሁን ወደታች ልቀቁትና ከሥር እስከ ጫፍ አበጥሩት።

ፀጉራችሁ ሸብቶ ስታዩት ወይም ሲረግፍ ሊያሳስባችሁ ይችላል። ቢሆንም የፀጉራችሁ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ እናንተን የሚያሳስባችሁን ያህል ሌሎችን እንደማያሳስብ አስታውሱ። ፀጉራችሁን ቀለም መቀባት፣ ሰው ሠራሽ ፀጉር ማድረግ ወይም ሕክምና ማድረግ ትፈልጉ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ለእናንተ የተተወ ነው። የፀጉራችሁ ቀለም ምንም ዓይነት ይሁን ወይም ምንም ያህል ፀጉር ይኑራችሁ ዋና አስፈላጊው ነገር በንጽሕናና በሥርዓት መያዛችሁ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 የሚያዝያ 22, 1991 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12 ተመልከት።

^ አን.20 አንድ ማይክሮን የሚባለው የአንድ ሚሊ ሜትር አንድ ሺኛ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]

የፀጉር አስተዳደግ

የፀጉራችን አስተዳደግ የራሱ ኡደት አለው። ፀጉር የማደጊያ፣ የመሸጋገሪያና የማረፊያ ጊዜ አለው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ፀጉር በማረፊያ ጊዜ ማደጉን ያቆማል። በዚህ ጊዜ አሮጌው ፀጉር የማደጊያው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሥሩ ላይ እንዳለ ይቆያል። በማደጊያ ጊዜ አሮጌው ፀጉር ይረግፍና አዲስ ፀጉር ከሥር ይወጣል።” በማንኛውም ወቅት ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚደርስ ፀጉር በእድገት ላይ ሲሆን ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው በማረፊያ፣ 1 በመቶ የሚሆነው በመሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ይሆናል።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የፀጉር ግንድ

ዘይት አመንጪ እጢ

የደም ሥሮች

የፀጉር ቀዳዳ

እድገት የጀመረ ፀጉር

በእድገት ላይ ያለ ፀጉር

የቀጨጨ ፀጉር

በዕረፍት ላይ ያለ ፀጉር

ዳግመኛ ማደግ የጀመረ ፀጉር

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]