በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጥፎ ምኞቶችን ታግለህ ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

መጥፎ ምኞቶችን ታግለህ ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጥፎ ምኞቶችን ታግለህ ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

“በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ።”ሮሜ 7:21 አ.መ.ት

ከላይ የተጠቀሰውን የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎች ከፍተኛ የሆኑትን የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲከተሉ በማበረታታት ረገድ ከሌሎቹ ሐዋርያት የበለጠ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 15:9, 10) ያም ሆኖ ከላይ የተጠቀሰውን ሳይሸሽግ አምኖ ጽፏል። በአእምሮውና በመጥፎ ምኞቶቹ መካከል የማያቋርጥ ግጭት አጋጥሞታል። አንተስ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ተሰምቶህ ያውቃል? ፍጹማን ያልሆንን ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ያለ ውጊያ ያልገጠመው ማን አለ?

ሆኖም ብዙዎች ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ በጣም ከባድ ነው። አንዳንዶች ከሚሰማቸው ከፍተኛ የፆታ ስሜት ጋር በብርቱ ይታገላሉ። ሌሎች ደግሞ በቁማር፣ በትንባሆ፣ በአደገኛ ዕፆች ወይም በአልኮል ሱስ ተሸንፈው ለዚያ ባሪያዎች ሆነዋል። ጎጂና ርኩስ ምኞቶች በውስጣችን ሲቀሰቀሱ ታግለን ከውስጣችን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ትግል አሸናፊ ለመሆን ምን እርዳታ አለልን? ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የሚደረገው ውጊያስ ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

ፍቅር—መጥፎ ምኞቶችን ታግሎ ለማሸነፍ የሚረዳ ቁልፍ ባሕርይ

ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተጠቀሱት ትእዛዛት ሁሉ ሁለቱ አቻ የማይገኝላቸው መሆናቸውን ተናግሯል። የመጀመሪያው “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የሚለው ነው። (ማቴዎስ 22:37) ኢየሱስ እንደተናገረው አምላክን የምንወድደው ከሆነ ትልቁ ምኞታችን አምላክን ማስደሰት ሊሆን አይገባውም? ከሆነ እንዲህ ያለው ትክክለኛ ምኞት በጣም ከባድ የሚባለውን መጥፎ ምኞት እንኳን ሳይቀር ታግለን እንድናሸንፍ ሊረዳን ይችላል። ይህ እንዲያው ሐሳብ የወለደው ምኞት አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በየዕለቱ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር እየታገሉ ያሸንፋሉ። ታዲያ አንተስ ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ ጠንካራ ዝምድና መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው? በአምላክ ፍጥረት፣ በመጽሐፍ ቅዱስና ለእያንዳንዳችን በግል ባደረጋቸው ነገሮች ላይ በተንጸባረቀው ጥሩነቱ ላይ በአድናቆት በማሰላሰል ነው።—መዝሙር 116:12, 14፤ 119:7, 9፤ ሮሜ 1:20

ኢየሱስ የጠቀሰው ሁለተኛው ትልቁ ትእዛዝ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” የሚለው ነው። (ማቴዎስ 22:39) ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም [ጥቅም] አይፈልግም” ብሏል። እንዲህ ያለውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማዳበራችን ሌሎችን ሊጎዳ የሚችል ማንኛውንም መጥፎ ምግባር እንድናስወግድ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) ይህን ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ችግር እንደራሳችን ችግር አድርገን በማየትና ለስሜታቸው እንዲሁም ለዘላቂ ደህንነታቸው ከልብ በማሰብ ነው።—ፊልጵስዩስ 2:4

ምን እርዳታ አለልን?

አምላክ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ምን ያህል እንደሚያስቸግረን ስለሚያውቅ በተለያዩ መንገዶች እርዳታ ያቀርብልናል። መጥፎ የሆነውን ነገር እንድንጠላና ለእርሱ አክብሮት እንድናዳብር በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስተምረናል። (መዝሙር 86:11፤ 97:10) መጽሐፍ ቅዱስ ለመጥፎ ምኞት መሸነፍ የሚያስከትለውን ጉዳት የሚያሳዩ እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን ይዟል። በተጨማሪም አምላክን ከለመንነው በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ አቻ የማይገኝለትን ኃይል ማለትም መንፈስ ቅዱሱን እንደሚሰጠን ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) ሌላው ዝግጅት ደግሞ እንደኛው መጥፎ ምኞቶችን ለማሸነፍ ትግል ከሚያደርጉ ሌሎች ክርስቲያኖች የምናገኘው ድጋፍና ማበረታቻ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህ አዎንታዊ ተጽዕኖዎች አሉታዊ ተጽዕኖዎችን እያሸነፉ ሲሄዱ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በምናደርገው ውጊያ እገዛ አገኘን ማለት ነው። (ፊልጵስዩስ 4:8) ይህ ዘዴ በእርግጥ ይሠራል?

በሰካራምነቱ ይታወቅ የነበረውን ፊደል የተባለውን ሰው ሁኔታ ተመልከት። ሲጋራ ያጨስ፣ ቁማር ይጫወትና ሲሰክርም ከሌሎች ጋር ይጣላ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቱ እነዚህን ልማዶች እንዲያሸንፍ ረድቶታል። አሁን ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር ከበፊቱ በጣም የተሻለ ሕይወት ይመራል።

ሆኖም አንድ ሰው ‘መጥፎው ልማድ ቢያገረሽብኝስ?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ያለው ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ልጆቼ ሆይ፣ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋላሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) አዎን፣ የኢየሱስ መሥዋዕት ንስሐ የሚገባና አምላክን ለማስደሰት ሲል ለውጥ ለማድረግ በቅንነት የሚጥር ሰው የሚፈጽመውን ስህተት ይሸፍናል። ከዚህ ዝግጅት አንጻር ሲታይ አንድ ሰው ተስፋ ቆርጦ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ መዋጋቱን ለማቆም የሚያበቃ ምን ምክንያት ሊኖረው ይችላል?

መጥፎ ምኞቶች ድል ይደረጋሉ

ለአምላክና ለጎረቤት ያለንን ፍቅር ካሳደግንና አምላክ ባቀረበልን እርዳታ ከተጠቀምን አሁንም እንኳን ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ውጊያ ድል ልንቀዳጅ እንችላለን። ከዚህም በላይ ይህ ትግል ለዘላለም እንደማይቀጥል የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል። በቅርቡ በአምላክ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የሚጠቀሙ ሁሉ በአካልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይፈወሳሉ። (ራእይ 21:3-5፤ 22:1, 2) ከኃጢአት ቀንበርና ይህ ቀንበር ከሚያስከትለው ሞት ነፃ ይወጣሉ። (ሮሜ 6:23) በሌላ በኩል ግን ርኩስና ጎጂ የሆኑ ምኞቶችን ሆን ብለው የሚያስተናግዱ ሁሉ እነዚህን በረከቶች እንዲያገኙ አይፈቀድላቸውም።—ራእይ 22:15

ከመጥፎ ምኞቶች ጋር የምናደርገው ውጊያ ለዘላለም የሚቀጥል አለመሆኑን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! መጥፎ ምኞቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳሉ። እንዴት ያለ ግልግል ይሆናል!