በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእንቅልፍ ዕዳ እየተባባሰ የመጣ ችግር ነው?

የእንቅልፍ ዕዳ እየተባባሰ የመጣ ችግር ነው?

የእንቅልፍ ዕዳ እየተባባሰ የመጣ ችግር ነው?

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ “ዕዳ” ውስጥ ተዘፍቀዋል። ይህ ዕዳ በመኪኖቻቸው ላይ ለሚደርሰው አደጋ፣ ለሥራ እድገታቸው መገታትና ለትዳራቸው መፍረስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ጤንነታቸውን ሊያውክና ዕድሜያቸውን ሊያሳጥር ይችላል። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክምና ለተለያዩ የኢንፌክሽን በሽታዎች የሚያጋልጥ ዕዳ ነው። የስኳር በሽታ፣ የልብ በሽታ፣ ቅጥ ያጣ ውፍረትና ሌሎች የጤና ችግሮች ከዚህ ዕዳ ጋር ዝምድና እንዳላቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተጠቂዎች ይህ ዕዳ እንዳለባቸው እንኳን አይታወቃቸውም።

የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ አንድ ሰው ለጥሩ ጤንነት የሚያስፈልገውን በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ሲቀር የሚፈጠረው የእንቅልፍ ውዝፍ ነው። ይህ ችግር አንድ ሰው በራሱ ፈቃድ በሚከተለው አኗኗር ምክንያት አለበለዚያም በበሽታ የተነሳ በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ሲቀር የሚመጣ ሊሆን ይችላል።

የሕክምና ተመራማሪዎች በአሁኑ ጊዜ ጠቅላላው የዓለም ሕዝብ በአማካይ ማግኘት ከሚያስፈልገው የእንቅልፍ መጠን በአንድ ሰዓት ያነሰ እንቅልፍ እንደሚያገኝ ይገምታሉ። ይህ አሐዝ ትንሽ ቢመስልም በየሌሊቱ የሚያጋጥመው የስድስት ቢሊዮን ሰዓቶች ውዝፍ ብዙ ተመራማሪዎች ከእንቅልፍ ማጣት ጋር በሚዛመዱ በሽታዎችና በቂ እንቅልፍ አለማግኘት በሰዎች ሕይወት ላይ በሚያስከትለው ተጽዕኖ ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

በአንድ ወቅት የሕክምናው ዓለም የእንቅልፍ ማጣትን ችግር ኢንሶምኒያ በሚባል አንድ የጤና እክል ብቻ ፈርጆት ነበር። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ያቋቋመው አንድ ኮሚሽን 17 ዓይነት የእንቅልፍ ማጣት ችግሮችን ለይቷል። ያም ሆነ ይህ ትኩሳት አንድ ዓይነት ኢንፌክሽን መኖሩን የሚጠቁም ምልክት እንደሆነ ሁሉ እንቅልፍ ማጣትም በጣም በርካታ ምክንያቶች ያሉት በመሆኑ ብዙውን ጊዜ የሌላ ችግር ምልክት እንደሆነ ይታሰባል።

አልፎ አልፎም እንኳ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ቶም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ብዙ ልምድ ያለው የከባድ መኪና አሽከርካሪ ቢሆንም ያሽከረክረው የነበረው ባለ ተሳቢ ከባድ መኪና መንገድ ስቶ ከግምብ ጋር በመላተሙ ጭኖት የነበረው 400 ሊትር የሚያክል ሰልፊውሪክ አሲድ አውራ ጎዳና ላይ ሊፈስ ችሏል። ቶም “እንቅልፍ ወስዶኝ ነበር” በማለት የእምነት ቃሉን ሰጥቷል። በሁለት የአሜሪካ ዋና ጎዳናዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከተከሰቱት ከባድ አደጋዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት የደረሱት እንቅልፍ ባሸለባቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት ነው።

በተጨማሪም እንቅልፍ ከተጫጫነው የሥራ ባልደረባ ጋር አብሮ መሥራት ምን አደጋ እንዳለው ተመልከት። አን ዊልያምሰን የተባሉት አውስትራሊያዊት ተመራማሪ “[ጥናት የተደረገባቸው ሰዎች] ከ17 እስከ 19 ሰዓት ለሚያክል ጊዜ እንቅልፍ ሲያጡ በደማቸው ውስጥ ያለው አልኮል መጠን 0.05 በመቶ የሆነባቸውን ሰዎች ያህል ወይም ከእነሱ የባሰ ደንዝዘው ታይተዋል” ብለዋል። በሌላ አባባል ጥናቱ የተደረገባቸው ሰዎች በአንዳንድ አገሮች ለአሽከርካሪዎች ከሚፈቀደው የአልኮል መጠጥ በላይ እንደጠጡ ያህል ሆነው ነበር ማለት ነው። በየዓመቱ እንቅልፍ በማጣት ምክንያት በተሽከርካሪዎች ላይም ሆነ በሥራ ቦታ የሚደርሱትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አደጋዎች ስንመለከት በምርት ላይ የሚከሰተው ኪሳራም ሆነ በቤተሰብ ላይ የሚደርሰው ችግር በጣም ከፍተኛ እንደሆነ እንገነዘባለን። *

ለእንቅልፍ ዕዳ ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? አንደኛው ምክንያት በአንዳንድ ኅብረተሰቦች ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው በቀን 24 ሰዓትና በሳምንት ሰባት ቀን በሥራ ተወጥሮ የማሳለፍ ባሕል ነው። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው መጽሔት ይህን ሁኔታ “የአኗኗር ዘይቤያችንን በመለወጥ ላይ የሚገኝ ባሕላዊ ነውጥ” ሲል የገለጸው ሲሆን “ቀንና ሌሊት በመሥራት ትርፍ የሚያጋብሱ ቸርቻሪዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር እንደ አሸን እየፈላ ነው” ብሏል። በብዙ አገሮች በርካታ ሰዎች መተኛት ሲኖርባቸው ሙሉ ሌሊት ቴሌቪዥን ወይም ኢንተርኔት ላይ አፍጥጠው ያድራሉ። በዚህ ሳቢያ የሚፈጠረው የእንቅልፍ ዕዳ ከፍተኛ ውጥረትና ጭንቀት ያስከትልባቸዋል። በተጨማሪም አንድ ሰው እንቅልፍ እንዲያጣ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ አካላዊ ሕመሞች አሉ።

ብዙ ዶክተሮች በሽተኞቻቸውን እንቅልፍ ማጣት ምን ያህል ከባድ ችግር እንደሆነ ማሳመን እንደሚቸግራቸው ይናገራሉ። አንድ ዶክተር ለረዥም ጊዜ የቆየ ድካም በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ታታሪ ሠራተኛ የሚያስቆጥርና “አድናቆት የሚያስገኝ ነገር” እንደሆነ ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ አለ ብለዋል። በተጨማሪም ሁኔታቸው እየተባባሰ የሚሄደው በጣም ቀስ ብሎ ስለሆነ እንቅልፍ የማጣት ችግር ያለባቸው ሰዎች ከባድ ችግር እንዳለባቸው እንኳን ላይታወቃቸው ይችላል። ብዙዎቹ ‘እርጅና ነው’ ወይም ‘የኑሮን ጫና መቋቋም ስላቃተኝ ነው’ አሊያም ደግሞ ‘በቂ እረፍት ማግኘት ስላልቻልኩ ሁልጊዜ ይደክመኛል’ ይላሉ።

ይህን የእንቅልፍ ዕዳ ከፍሎ መጨረስ በጣም ውስብስብና ፈታኝ ችግር ነው። ይሁን እንጂ ጤናማ የሆነ የእንቅልፍ ዑደት ምን እንደሚመስልና የእንቅልፍ ዕዳ ምልክቶች ምን እንደሆኑ ማወቅ ለውጥ ለማድረግ ሊያነሳሳ ይችላል። ከባድ የሆነ እንቅልፍ የማጣት ችግር ምልክቶች ምን እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ ሕይወትን ሊታደግ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በ20ኛው መቶ ዘመን ለደረሱት በጣም አስከፊ አደጋዎች አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ድካም እንደሆነ ይታመናል። የየካቲት 8, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 6 ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልፎ አልፎም እንኳ ቢሆን በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል