በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?

አምላክ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

አምላክ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?

“አምላክ የሚኖረው ሁሉም ነገር አስደሳች በሆነበት በሰማይ ነው፤ እኛ ግን እዚህ ቁም ስቅላችንን እናያለን።”ሜሪ *

የዛሬ ወጣቶች የተወለዱት ጭካኔ በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፉ አሳዛኝ የምድር መናወጦችና የተፈጥሮ አደጋዎች የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። በዜና ላይ በሰፊው የሚዘገበው ስለ ጦርነቶችና የሽብር ጥቃቶች ነው። ሕመም፣ በሽታ፣ ወንጀልና ድንገተኛ አደጋዎች የምናፈቅራቸውን ሰዎች በሞት ይነጥቁናል። ከላይ የተጠቀሰችው ሜሪ አሳዛኝ መከራ ደርሶባታል። እነዚህን ምሬት ያዘሉ ቃላት የተናገረችው አባቷን በሞት ባጣች ጊዜ ነበር።

በግለሰብ ደረጃ አሳዛኝ መከራ ሲደርስብን መበሳጨታችን፣ ማዘናችን ወይም መቆጣታችን ያለ ነገር ነው። ‘እንዲህ ያለ ነገር የሚደርሰው ለምንድን ነው?’ ‘ለምን በእኔ ላይ?’ ወይም ‘ለምን በዚህ ጊዜ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሻሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት ወደ ትክክለኛው ምንጭ ዞር ማለት አለብን። እርግጥ ነው፣ ተረል የተባለ ወጣት እንደተናገረው አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “ስሜታቸው በጣም ከመጎዳቱ የተነሳ ስለጉዳዩ ቆም ብለው ማሰብ አይችሉም።” ስለዚህ በምክንያታዊነት ለማሰብ እንድትችል ስሜትህን ትንሽ የምታረጋጋበትን መንገድ መሻት ያስፈልግህ ይሆናል።

አሳዛኝ እውነታዎችን መጋፈጥ

ማሰቡም እንኳን ደስ የማይል ሊሆን ቢችልም፣ ሞትና መከራ አይቀሬ የሕይወት ገጠመኞች ናቸው። ይህን ሁኔታ ኢዮብ “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” ብሎ በመናገር በትክክል ገልጾታል።—ኢዮብ 14:1

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጽድቅ የሚኖርበት’ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህ አስደሳች ሁኔታዎች እውን ከመሆናቸው በፊት ግን የሰው ዘር እስከዛሬ ታይቶ በማያውቅ ክፋት ውስጥ ማለፉ ግድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ” በማለት ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

ይህ አስጨናቂ ዘመን ምን ያህል ይቆይ ይሆን? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቀውት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህ በመከራ አዘቅት የተዋጠ ሥርዓት የሚያከትምበትን የተወሰነ ቀን ወይም ሰዓት ለይቶ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 13) የኢየሱስ ቃላት አርቀን እንድንመለከት ያበረታቱናል። ፍጻሜው እስኪመጣ ድረስ የሚያጋጥሙንን አሳዛኝ ሁኔታዎች በሙሉ ችለን ለመኖር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።

ተጠያቂው አምላክ ነው?

ታዲያ አምላክ ሥቃይ እንዲኖር በመፍቀዱ በእርሱ ላይ ማማረር ምክንያታዊ ነው? አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ሥቃይ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ቃል የገባ በመሆኑ በእርሱ ላይ ማማረሩ ተገቢ አይሆንም። መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱብን የሚያደርገው አምላክ ነው ብሎ ማሰብም ቢሆን ምክንያታዊ አይደለም። በርካታ አሳዛኝ አደጋዎች የሚከሰቱት በአጋጣሚ ነው። ለምሳሌ ያህል ንፋስ ዛፍ ገንድሶ አንድ ሰው ላይ ጉዳት አድርሷል እንበል። ሰዎች ይህ የአምላክ ቁጣ ነው ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዛፉን እንዲወድቅ ያደረገው አምላክ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉት ነገሮች የሚደርሱት “ጊዜና አጋጣሚ” በሚፈጥሯቸው ሁኔታዎች እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል።—መክብብ 9:11 NW

መከራ ከማስተዋል ጉድለትም ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የተወሰኑ ወጣቶች የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ ጠጥተው መኪና ሲያሽከረክሩ ከባድ አደጋ ደረሰባቸው እንበል። ተጠያቂው ማን ነው? አምላክ ነው? በፍጹም። ምክንያቱም ወጣቶቹ ያጨዱት ማስተዋል የጎደለው እርምጃ መውሰዳቸው ያስከተለባቸውን መዘዝ ነው።—ገላትያ 6:7

ይሁን እንጂ ‘አምላክ መከራን አሁኑኑ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ኃይል አለው አይደለም እንዴ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ታማኝ ሰዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተው ነበር። ነቢዩ ዕንባቆም “አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ?” በማለት አምላክን ጠይቆ ነበር። ቢሆንም ዕንባቆም ከድምዳሜ ለመድረስ አልቸኮለም። ከዚህ ይልቅ “ምን እንደሚለኝ . . . ለማወቅ እጠባበቃለሁ” ብሏል። በኋላም አምላክ ‘በወሰነው ጊዜ’ መከራን እንደሚያስወግድ ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (ዕንባቆም 1:13፤ 2:1-3) ስለዚህ እኛም አምላክ ክፋትን እርሱ በወሰነው ጊዜ እስኪያስወግድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ አለብን።

አምላክ መከራ እንዲደርስብን ይፈልግ ይሆናል ወይም እርሱ ራሱ እየፈተነን ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መቸኮል አይኖርብህም። መከራ ውስጣዊ የሆኑ ግሩም ባሕርይዎቻችን እንዲታዩ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስም አምላክ እንዲደርስብን የሚፈቅዳቸው ፈተናዎች እምነታችንን ሊያጠሩልን እንደሚችሉ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:7) ከባድ ችግሮች ወይም አሳዛኝ ሁኔታዎች የደረሱባቸው ሰዎች ይበልጥ ታጋሾች ብሎም አዛኞች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። ቢሆንም የደረሰባቸው መከራ አምላክ ያመጣው ነው ብለን ማሰብ የለብንም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የአምላክን ፍቅርና ጥበብ ያገናዘበ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” በማለት በግልጽ ይናገራል። በአንጻሩ ግን፣ ከእርሱ የሚመነጨው “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት” ብቻ ነው!—ያዕቆብ 1:13, 17

አምላክ ክፋትን የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

ታዲያ የክፋት ምንጩ ማን ነው? አምላክ ተቃዋሚዎች እንዳሉት አትርሳ፤ ከእነሱም ቀንደኛው ‘ዓለምን ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው’ ነው። (ራእይ 12:9) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን አዳምንና ሔዋንን ያስቀመጣቸው ከመከራ ነጻ በሆነ ዓለም ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን ሔዋንን ከአምላክ አገዛዝ ብትወጣ እንደሚሻላት አሳመናት። (ዘፍጥረት 3:1-5) የሚያሳዝነው ደግሞ ሔዋን የሰይጣንን ውሸት አመነችና የአምላክን ትእዛዝ ጣሰች። አዳምም በዓመጽ ድርጊቷ ተባበራት። ውጤቱስ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ” በማለት ይናገራል።—ሮሜ 5:12

አምላክ ሰይጣንንና ተከታዮቹን ወዲያውኑ በመደምሰስ ይህን ዓመጽ ከማስቆም ይልቅ ጊዜ እንዲፈታው ማድረግ እንደሚሻል አሰበ። ጊዜ መፍቀዱ ምን ውጤት ይኖረዋል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥ ያስችላል! እንዲሁም ከአምላክ አገዛዝ ነጻ መውጣት ከጉዳት በስተቀር ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ይረዳል። በገሃድ የታየውስ ይኸው አይደለም? ‘መላው ዓለም በክፉው ቁጥጥር ሥር’ ወድቋል። (1 ዮሐንስ 5:19) ከዚህም በላይ ‘ሰው ሰውን የሚገዛው ለመጉዳት ነው።’ (መክብብ 8:9) የዓለም ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት እርስ በርሱ የሚጋጭና የተወሳሰበ ነው። ሥነ ምግባር ከምንጊዜውም የበለጠ ዘቅጧል። ሰብዓዊ መንግሥታት አለ የሚባለውን አገዛዝ ሁሉ ሞክረዋል። ውሎችን ይፈራረማሉ እንዲሁም ሕጎችን በሥራ ላይ ያውላሉ። ይሁን እንጂ ተራው ሕዝብ አሁንም ፍላጎቶቹ አልተሟሉለትም። ጦርነቶች ደግሞ ችግሩን አባብሰውታል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ጣልቃ ገብቶ ክፋትን እንዲያስቆምልን እንፈልጋለን! ይህ የሚሆነው ግን አምላክ በወሰነው ጊዜ ብቻ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመታዘዝ የእርሱን አገዛዝ የመደገፍ ልዩ መብት አለን። መጥፎ ነገሮቸ ሲደርሱብን ከመከራ ነጻ የሆነ ዓለም እንደሚመጣ በተገባልን እርግጠኛ ተስፋ ልንጽናና እንችላለን።

መከራ የሚደርሰው በእኛ ላይ ብቻ አይደለም

የሆነ ሆኖ መከራ ሲደርስብን ‘በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ “እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ” በመግለጽ ክፉ የሚደርስብን እኛ ብቻ እንዳልሆንን አሳስቦናል። (ሮሜ 8:22) ይህን ሐቅ ማወቅህ የሚደርስብህን መከራ እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኔኮል በመስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ ከተማና በዋሽንግተን ዲ ሲ በደረሰው የሽብር ጥቃት ሳቢያ የስሜት ቀውስ አጋጥሟት ነበር። “በጣም ተሸብሬና ተደናግጬ ነበር” በማለት የተሰማትን ተናግራለች። ይሁን እንጂ ሌሎች ክርስቲያኖች ይህን አሳዛኝ መከራ እንዴት እንደተቋቋሙት የሚገልጹ ታሪኮችን ስታነብ አመለካከቷ ተቀየረ። * “መከራ የደረሰው በእኔ ላይ ብቻ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ቀስ በቀስ ከደረሰብኝ ሥቃይና ኀዘን ማገገም ጀመርኩ” በማለት ተናግራለች።

አንዳንድ ጊዜ የውስጣችሁን አውጥታችሁ የምትነግሩት ሰው፣ ወላጅም ይሁን የጎለመሰ ወዳጅ ወይም ክርስቲያን ሽማግሌ መፈለጉ ጥበብ ነው። ለምታምኑት ሰው ስሜታችሁን አውጥታችሁ መንገራችሁ የሚያበረታታ “መልካም ቃል” እንድታገኙ ያስችላችኋል። (ምሳሌ 12:25) አንድ ብራዚላዊ ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ይላል:- “ከዘጠኝ ዓመት በፊት አባቴን በሞት አጣሁ። ይሖዋም አንድ ቀን እንደሚያስነሳው አውቃለሁ። ሆኖም ኀዘኔን ለመቋቋም የረዳኝ የተሰማኝን በጽሑፍ ማስፈሬ ነበር። በተጨማሪም ስሜቴን ለክርስቲያን ወዳጆቼ አወያያቸው ነበር።” አንተስ የልብህን ልታካፍላቸው የምትችላቸው እውነተኛ ‘ወዳጆች’ አሉህ? (ምሳሌ 17:17) ከሆነ ከሚያደርጉልህ ፍቅራዊ እርዳታ ልትጠቀም ትችላለህ! ለማልቀስም ሆነ ስሜትህን ለመግለጽ አትፍራ። ኢየሱስም እንኳ ወዳጁን በሞት ባጣ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል’!—ዮሐንስ 11:35

መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ‘ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥተን ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረ ነጻነት የምንደርስበት’ ቀን እንደሚመጣ ያረጋግጥልናል። (ሮሜ 8:21) እስከዚያ ድረስ ብዙ ጥሩ ሰዎች መከራ ሊደርስባቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነና ከአሁን ወዲያ ብዙ እንደማይቆይ በማወቅ ተጽናና።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.20 በጥር 2002 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “በአደጋ ወቅት የታየ ድፍረትና ቆራጥነት” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኀዘንህን መግለጽ ሊረዳህ ይችላል