በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የበለጠ ተወዳጅነት የሚያገኙት ተግባቢ የሆኑ ልጆች ናቸው

“በጣም ውድ የሆነ ልብስ መልበስ ወይም በጣም ዘመናዊ የሆነ መሣሪያ መያዝ ተወዳጅነት የሚያስገኝ ነገር አልሆነም። በእኩዮች መካከል የበለጠ ዋጋ ያለው ሆኖ የተገኘው የኑሮ ደረጃ ሳይሆን ሰው ወዳድ መሆን ነው” ይላል ሳይኮሎጊ ሆይተ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ። በርሊን በሚገኘው በማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት ኦቭ ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሳይኮሎጂስት የሆኑት ዩዲት ሽረንክና ክርስቲን ጉርተር በአሥር የተለያዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሦስተኛና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች በሆኑ 234 ልጆች ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። የበለጠ ተደማጭነት ያላቸው ሆነው የተገኙት ከእኩዮቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም ተግባቢና ተጫዋች የሆኑት ልጆች እንደሆኑ ተረድተዋል። የሚማቱ ወይም በሌሎች ላይ የሚሳለቁ ልጆች በእኩዮቻቸው ዘንድ ተደማጭነትና ከበሬታ አላገኙም። ሪፖርቱ “አምሮ መታየት ወይም በዛ ያለ የኪስ ገንዘብ መያዝም እንኳ ብዙም ቦታ አልተሰጠውም” ይላል።

ከፍተኛ ጥቅም ያለው ፓርስሊ

አብዛኛውን ጊዜ ምግብን ለማጣፈጥና ለማስጌጥ ብቻ የሚውለው ፓርስሊ የተባለው ቅጠል በቪታሚኖችና በማዕድናት የበለጸገ እንደሆነ የአውስትራሊያው ሰንደይ ቴሌግራፍ ገልጿል። “አንድ ሲኒ ፓርስሊ ከአንድ ትልቅ ካሮት የሚበልጥ ቤታ ካሮቲን (ቫይታሚን ኤ)፣ በአንድ ብርቱካን ውስጥ ከሚገኘው እጥፍ የሚሆን ቫይታሚን ሲ እንዲሁም በአንድ ሲኒ ወተት ውስጥ ከሚገኘው የሚበልጥ ካልሲየም አለው። በተጨማሪም ተመሳሳይ መጠን ካለው ጉበት የሚበልጥ ብረት ያለው ሲሆን በቪታሚን ቢ1 እና ቢ2 በጣም የበለጸገ ነው።” በመድኃኒትነቱ ደግሞ “ፓርስሊ ብዙ የማሸናት ባሕርይ ስላለው በሰውነት ውስጥ የተጠራቀመ ፈሳሽ እንዲወጣ” እንደሚያደርግ ጋዜጣው ገልጿል። ከዚህም በላይ የጉበት፣ የጣፊያ፣ የሆድና የሽንት ችግር ላለባቸው ሰዎች ጠቃሚ ነው። ትኩሱን ተቀጥፎ ቢበላ “ብዙ ወጪ ሳያወጡ የትንፋሽ ጠረን ለማጥራት ይረዳል።” ይሁን እንጂ ጽሑፉ “እንደ እርግዝና ባሉ አንዳንድ ሁኔታዎች . . . በውስጡ በያዘው የኤስትሮጂን ቅመም ምክንያት አደገኛ ሊሆን ይችላል” በማለት ያስጠነቅቃል።

የሥራ ደረጃና አድራሻ የሚገልጹ ካርዶች ከአገልግሎት ውጭ ይሆኑ ይሆን?

የደኅንነት አማካሪ የሆኑት ካርል ፓላዲኒ “በብራዚል ሰዎችን ማፈን በጣም እየተስፋፋ በመምጣቱ ሥራ አስኪያጆች የሥራ ደረጃቸውንና አድራሻቸውን የሚገልጽ ካርድ ባይዙ ይሻላቸዋል” ማለታቸውን የብራዚሉ የንግድ ጋዜጣ ኢዛም ገልጿል። እንዲህ ዓይነቱ መረጃ ወንጀለኞች የግለሰቡን የገንዘብ አቅም እንዲያውቁ ያስችላል። ክሮል የተባለው ትልቅ የደኅንነት ኩባንያ ዳይሬክተር የሆኑት ቫግነር ዳንጀሎ “በቦርሳህ የያዝከው ነገር ሕይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል” እስከማለት ደርሰዋል። ወንጀል በበዛባቸው አገሮች የሚኖሩ የንግድ ሰዎች ከካርዳቸው ላይ ማዕረጋቸውንና ደረጃቸውን የሚገልጹ ነገሮችን በሙሉ እንዲያጠፉና “በውድ ወረቀቶች ላይ ባሸበረቀ መንገድ የተጻፈባቸው [ካርዶችን] እንዲያስወግዱ” መክረዋል። አንዳንድ ሥራ አስኪያጆች ወንጀለኞች ይህንን ዘዴም ማወቃቸው እንደማይቀር በመፍራታቸው እስከነጭራሹ ካርድ መያዝ ትተዋል።

በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ፍንዳታ

አዮ የተባለችው የጁፒተር ጨረቃ “በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ከተከሰቱት ፍንዳታዎች በሙሉ የሚበልጥ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ” እንዳጋጠማት ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል። “በጣም ከፍተኛ የሆነው የጁፒተር የስበት ኃይል አዮ ላይ ከፍተኛ ሙቀት እንዲፈጠር ስለሚያደርግ አዮ እሳተ ገሞራ የሚበዛባት ጨረቃ ሆናለች። ይህች ጨረቃ በየዓመቱ አንድ ደርዘን ያህል ፍንዳታ ያጋጥማታል።” ይኸው ጽሑፍ እንዳለው “በዚህ ተወዳዳሪ ባልተገኘለት ፍንዳታ ምክንያት የተረጨው ፍንጥርጣሪ 1,900 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚያህል ስፋት የሸፈነ ሲሆን ይህም በምድር ላይ እሳተ ገሞራ ከሚበዛባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የጣሊያኑ የኤትና ተራራ በሚፈነዳበት ጊዜ የሚሸፍነውን ቦታ አንድ ሺህ ጊዜ ያህል ይሆናል።” ሳይንቲስቶች ይህን ፍንዳታ ሊያዩ የቻሉት ኬክ ሁለት በተባለውና በሃዋይ ደሴት በሚገኘው ማውና ኪያ የተባለ ተራራ ላይ በተተከለ ቴሌስኮፕ አማካኝነት ነው። ኬክ ሁለት ፍንዳታውን ለማሳየት የቻለው “በምድር ከባቢ አየር ላይ የሚፈጠረው ነውጥ የሚያስከትለውን ብዥታ አልፎ ጥርት ያለ ምስል ለማሳየት የሚያስችል” መነጽር ስላለው እንደሆነ ሳይንስ ኒውስ ገልጿል።

በክሬዲት ካርድ የሚሰጥ የሠርግ ስጦታ

በባሕላዊ የቱርክ ሠርጎች ላይ ለሙሽሮች መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹ ሰዎች ሙሽራዋን በጌጣጌጥ የሚያስውቡ ሲሆን ሙሽራውን ደግሞ በገንዘብ ስጦታ ያንበሸብሹታል። ይሁን እንጂ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ በቱርክም ክሬዲት ካርዶች በኅብረተሰቡ ዘንድ እየተለመዱ መጥተዋል። በቅርቡ በአንታሊያ በተደረገ አንድ ሠርግ ላይ ሙሽሮቹ ተንቀሳቃሽ የክሬዲት ካርድ ማንበቢያ ማሽናቸውን ወደ ድግሱ ቦታ ይዘው መጥተው እንደነበር ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ ዘግቧል። ወዳጆችና ዘመዶች በሙሽሮቹ የባንክ ሂሣብ ውስጥ ገንዘብ ለማስቀመጥ ክሬዲት ካርዳቸውን በማሽኖቹ ውስጥ በማሳለፍ ሙሽራዋንና ሙሽራውን በታተሙ ደረሰኞች አንበሸበሿቸው።

የልጆች መሞት በወላጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት እንደገለጸው በዴንማርኩ የኦርሁስ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች “ከ18 ዓመት በታች የሚገኝ ልጃቸውን በበሽታ፣ በድንገተኛ አደጋ፣ በግድያ ወይም ራስን በማጥፋት ምክንያት በሞት ያጡ 21,062 ወላጆችን ሕይወት ተከታትለዋል።” እነዚህን ወላጆች 300,000 ከሚያክሉ ልጆች ያልሞቱባቸው ሰዎች ጋር አወዳደሩ። “ልጃቸውን በሞት ካጡ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት እናቶቹ በድንገተኛ አደጋ ወይም የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት የመሞታቸው አጋጣሚ በአራት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የአባቶቹ የመሞት አጋጣሚ ደግሞ በ57 በመቶ ጨምሯል።” ተመራማሪዎች ይህ ሊሆን የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረትና ጭንቀት ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የቀፎ ማሞቂያ

ንቦች ቀዝቃዛውን የክረምት ወቅት ተቋቁመው ለማለፍ “ክንፋቸውን በማርገብገብ” ሙቀት ያመነጫሉ በማለት ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ ዘግቧል። ይሁን እንጂ በቀፎው ውስጥ ያለው ሙቀት አንድ ዓይነት አይደለም። በቀፎው መካከል ያሉት ንቦች የሰውነታቸው አማካይ ሙቀት 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲሆን በቀፎው ዳር ያሉት ንቦች አማካይ የሙቀት መጠን ግን 12 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ወይም ከዚያ በታች ነው። በርዷቸው የሚንቀጠቀጡት ንቦች ዳር ላይ የሚገኙት ሳይሆኑ መሃል ያሉት እንደሆኑ በኦስትሪያ፣ ግራዝ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት ደርሰውበታል። በዚህ መንገድ ንቦቹ ከቀፎው ወደ ውጭ የሚወጣውን የሙቀት መጠን ብሎም በክረምት የሚያስፈልጋቸውን የምግብ ፍጆታ መቀነስ ይችላሉ። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘ሙቀት ባለበት የቀፎው መካከለኛ ክፍል ያሉት ንቦች ዳር ላይ ካሉት ይበልጥ ሙቀት ማመንጨት እንዳለባቸው የሚያውቁት እንዴት ነው?’ የሚለው ነው።

የኤድስ ወረርሽኝ በካረቢያን አገሮች

በኤድስ ወረርሽኝ መስፋፋት ከአፍሪካ ቀጥሎ በዓለም ውስጥ የሁለተኛነት ደረጃ የያዙት የካረቢያን አገሮች እንደሆኑ ዘ ማያሚ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ ዓለም አቀፍ እትም ገልጿል። “አንዳንድ ግምቶች እንደሚያመለክቱት በካረቢያን አገሮች ለአቅመ አዳም ከደረሱ ሰዎች መካከል 2.4 በመቶ የሚሆኑት [በኤች አይ ቪ] የተለከፉ” ሲሆኑ በከተሞች አካባቢ ከሕዝቡ መካከል 12 በመቶ የሚሆነው በበሽታው ተይዟል። “ፍርሃት፣ ሰዎች በበሽታው መለከፋቸውን ማመን አለመፈለጋቸው እንዲሁም በቂ የሕክምናና የጤና አገልግሎት አለመኖሩ ወረርሽኙ ምን ያህል እንደተስፋፋ ሙሉ በሙሉ ለማወቅ እንዳይቻል አድርጓል” ይላል ሄራልድ። “በካረቢያን አገሮች በ2001 ብቻ 40,000 የሚያህሉ ሕፃናትና ትላልቅ ሰዎች በበሽታው እንደሞቱ ይገመታል።” በካረቢያንና በላቲን አሜሪካ አገሮች በዓለም ባንክ የጤና ባለሞያ የሆኑት ፓትሪሽዮ ማርከዝ ኤድስ “በጣም ምርታማ በሆነ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተለ ነው። . . . አንድ ትውልድ በሙሉ ተጠራርጎ የሚጠፋ ይመስላል” ብለዋል። በጣም የተጎዳችው ሄይቲ ስትሆን ከ6 በመቶ የሚበልጠው ሕዝቧ በቫይረሱ ተለክፏል። “የጤና ባለሞያዎችና የፖለቲካ መሪዎች ወረርሽኙ . . . ውስን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ባላቸውና ኢኮኖሚያቸው የተመካው በቱሪዝም ላይ በሆነባቸው ትናንሽ አገሮች ላይ የሚያደርሰው ውድመት በጣም ከባድ እንደሚሆን” ጋዜጣው ገልጿል።