በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ ይቻላል?

መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ ይቻላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ ይቻላል?

ማርክ ትዌይን የተባሉ ደራሲ በአንድ ወቅት “ሲጋራ ማጨስ ለማቆም በጣም ቀላል ነው። ምክንያቱም ሺህ ጊዜ ሞክሬዋለሁ” በማለት በምፀት ተናግረው ነበር። በትዌይን ቀልድ ለበስ አባባል ብዙ ሰዎች እንደሚስማሙ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ልማዶች ከሥነ ምግባር አንፃር ስህተት እንዲሁም ጎጂ መሆናቸውን ቢገነዘቡም እነዚህን ልማዶች መቋቋምና ማሸነፍ ግን እንደመናገሩ ቀላል እንዳልሆነም ያውቃሉ። ልማዶች በዓመታት ሂደት ሥር እየሰደዱ ሊሄዱና ለመተው የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በእጅጉ የሚፈታተኑ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ልማዶች የሚያስከትሉትን ሱስ እርግፍ አድርጎ መተው እልህ አስጨራሽ አልፎ ተርፎም ሥቃይ የሚያስከትል ሊሆን ይችላል።

ዶክተር አንቶኒ ዳንኤልስ የተባሉ በወህኒ ቤት የሚሠሩ አንድ ሐኪም ወንጀለኞች በአብዛኛው ለሚወዷቸው ነገሮችና ለልክስክስ ምኞቶቻቸው ተገዢዎች ከመሆን መላቀቅ እንደማይችሉ ሲናገሩ እንደሚደመጡ ገልጸዋል። አንድ ሰው የአንድ ነገር ሱሰኛ ሲሆን “ሊቋቋመው የማይችለው አምጣ አምጣ የሚል አስገዳጅ ስሜት ወጥሮ ይይዘዋል” በማለት ወንጀለኞቹ ይከራከራሉ። ይህ አስተሳሰብ እውነት ከሆነ አንድን ነገር እንድንፈጽም የሚያስገድደንን ውስጣዊ ስሜት ለማርካት ብለን ለምንሠራው ወንጀል ተጠያቂዎች ልንሆን አንችልም። ይሁን እንጂ ውስጣዊ ግፊቶቻችንንና ምኞቶቻችንን መቋቋም የማንችል ምስኪን ሰለባዎች ነን? ወይስ ጎጂ ልማዶችን በእርግጥ ማሸነፍ ይቻላል? ለዚህ ጥያቄ አስተማማኝ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።

ፍላጎትና ድርጊት

ለምናደርገው ማንኛውም ነገር በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሆንን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ሮሜ 14:12) በተጨማሪም ከጽድቅ የአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይጠብቅብናል። (1 ጴጥሮስ 1:15) ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ለእኛ ከሁሉ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ የሚያውቅ ሲሆን መሠረታዊ ሥርዓቶቹም በዚህ ዓለም የተስፋፉትን ብዙዎቹን ልማዶች የሚያወግዙ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ገላትያ 5:19-21) ይሁን እንጂ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች በሚጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊና ርኅሩኅ ነው።—መዝሙር 78:38፤ 103:13, 14

በመሆኑም መዝሙራዊው ሲጽፍ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቆጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” ብሏል። (መዝሙር 130:3) አዎን፣ ይሖዋ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። (ዘፍጥረት 8:21) ከወላጆቻችን የወረስነው የኃጢአት ዝንባሌና ያሳለፍነው ሕይወት ተዳምሮ መጥፎ ሐሳቦችንና ምኞቶችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ስለዚህ አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ ከእኛ ፍጽምና አይጠብቅም።—ዘዳግም 10:12፤ 1 ዮሐንስ 5:3

ይሁን እንጂ አምላክ ያለብንን የኃጢአት ዝንባሌ ከግምት የሚያስገባልን መሆኑ መጥፎ ምኞቶችን ለመቆጣጠር ካለብን ኃላፊነት ነፃ አያደርገንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር ትግል እንደነበረበት ሳይደብቅ ቢናገርም ተስፋ ቆርጦ ትግሉን አላቆመም። (ሮሜ 7:21-24) “ሰውነቴን እየጎሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ብሏል። ለምን ዓላማ? “እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) አዎን፣ መጥፎ ዝንባሌዎቻችንንና ልማዶቻችንን ለመዋጋት፣ ብሎም ድል ለማድረግ ራስን መግዛት አስፈላጊ ነው።

ለውጥ ማድረግ ይቻላል

የሰዎችን ባሕርይ የሚያጠኑ የሳይንስ ሊቃውንት መጥፎ ልማዶች እንደ ጥሩ ልማዶች ሁሉ በመማር የሚገኙና በጊዜ ሂደት የሚዳብሩ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህ ትክክል ከሆነ ከመጥፎ ልማዶች መላቀቅ ይቻላል ማለት ነው! እንዴት? ውጥረትን ስለመቆጣጠር የሚናገር አንድ መጽሐፍ የጻፉ ደራሲያን “ከተጠናወታችሁ ልማድ መላቀቅ የሚያስገኘውን ጥቅም አስቡት” ብለዋል። ከዚያም “የባሕርይ ለውጥ ማድረጋችሁ ሕይወታችሁን እንዴት እንደሚያሻሽለው በዝርዝር ጻፉ።” አዎን፣ ጎጂ ልማዶቻችንን መተዋችን በሚያስገኝልን ጥቅሞች ላይ ማተኮር ለውጥ ለማድረግ ሊያነሳሳን ይችላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በአእምሮአችን መንፈስ እንድንታደስ’ የሰጠንን ምክር አስቡት። (ኤፌሶን 4:22, 23) ይህ መንፈስ አእምሮአችንን የሚቆጣጠረው ዝንባሌ ነው። ወደ አምላክ በመቅረብና ለእርሱ የአቋም ደረጃዎች ያለህን እውቀት በማሳደግ ይህንን መንፈስ ማደስ ትችላለህ። ይሖዋን እንደምታስደስት ማወቅህ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ያነሳሳሃል።—መዝሙር 69:30-33፤ ምሳሌ 27:11፤ ቆላስይስ 1:9, 10

እርግጥ ለዓመታት ሕይወታችንን ሲቆጣጠሩት ከኖሩት መጥፎ ልማዶች መላቀቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ከፊታችን የሚጠብቀንን ትግል አቅልለን ማየት የለብንም። ልማዳችን ሊያገረሽብን ወይም ጥረታችን ከናካቴው ሊከሽፍብን ይችላል። ይሁን እንጂ ነገሮች እያደር እየቀለሉ እንደሚሄዱ እርግጠኛ ሁን። በጥረትህ በገፋህ መጠን ልታዳብረው የምትፈልገው አዲሱ ባሕርይ ይበልጥ እየተዋሃደህ ይሄዳል።

አምላክን የሚወድ ሰው የእርሱ እርዳታና በረከት እንደማይለየው እርግጠኛ መሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን . . . ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱንም ያዘጋጅላችኋል” በማለት ተስፋ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓትና ወራዳ ፍላጎቶቹን፣ ምኞቶቹንና አምሮቶቹን ሁሉ ይደመስሳቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:9-13፤ 1 ዮሐንስ 2:16, 17) ከዚህ ጥፋት በሕይወት የሚተርፉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ ቀስ በቀስ ከአካላዊ፣ ከአእምሯዊና ከስሜታዊ ቀውሶች ሙሉ በሙሉና ለዘላለም ይፈወሳሉ። “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” በማለት አምላክ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 65:17) “ያለፉት ነገሮች” ከተባሉት መካከል መጥፎ ምኞቶችና ፍላጎቶች እንደሚገኙበት ጥርጥር የለውም። ታዲያ ይህ ተስፋ በዛሬው ጊዜ መጥፎ ልማዶችን ለመቋቋምና ለመዋጋት የቻልነውን ሁሉ እንድናደርግ የሚገፋፋ ትልቅ ምክንያት አይደለም?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከመጥፎ ልማዶች መላቀቅ

1. ያለብህን መጥፎ ልማድ አምነህ ተቀበል። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ:- ‘ከዚህ ልማድ የምጠቀመው ነገር አለ? ሌሎችን የሚያበሳጭ ልማድ ነው? ጤንነቴን፣ ገንዘቤን፣ ደኅንነቴን፣ ቤተሰቤን ወይም የአእምሮ ሰላሜን ይነካል? ከዚህ ልማድ ብላቀቅ ሕይወቴ ምን ያህል ይሻሻላል?’

2. መጥፎውን ልማድ ጠቃሚ በሆነ ልማድ ተካው። ለምሳሌ ያህል በኢንተርኔት ገንቢ ያልሆነ ነገር በመመልከት ብዙ ጊዜ ታጠፋለህ? ከሆነ ይህን ጊዜ ገንቢ ለሆነ ንባብ፣ ጥናት ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ አውለው።

3. የምታደርገውን መሻሻል ተቆጣጠር። በየቀኑ ለጥቂት ደቂቃዎች ስላደረግኸው መሻሻል መለስ ብለህ አስብ። ልማዱ ካገረሸብህ ወደዚህ ያመራህ ሁኔታ ምን እንደሆነ ለይተህ እወቅ።

4. የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ እየጣርክ መሆኑን ለጓደኞችህና ለቤተሰብህ ንገራቸው፤ እንዲሁም ሊያገረሽብህ መሆኑን ሲገነዘቡ እንዲነግሩህ ጠይቃቸው። ይህን ልማድ በተሳካ ሁኔታ ታግለው ካሸነፉ ሰዎች ምክር ጠይቅ።—ምሳሌ 11:14

5. ሚዛናዊና ከእውነታው ያልራቅህ ሁን። አፋጣኝ የሆነ ስኬት አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ። ዓመታት የፈጁ ልማዶችን መተው አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል።

6. ወደ አምላክ ጸልይ። በአምላክ እርዳታ ከማንኛውም መጥፎ ልማድ ልትላቀቅ ትችላለህ።—መዝሙር 55:22፤ ሉቃስ 18:27