በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤተሰባቸውን የተዉ አባቶች—ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ችግር

ቤተሰባቸውን የተዉ አባቶች—ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ችግር

ቤተሰባቸውን የተዉ አባቶች—ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ችግር

ቤተሰባቸውን የሚተዉ አባቶች ቁጥር በጣም እየተበራከተ መጥቷል። በ1990ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው ጋዜጣ ዩናይትድ ስቴትስ “በአባት አልባ ቤተሰቦች ብዛት የአንደኝነቱን ደረጃ የያዘች አገር” እንደሆነች ገልጿል። ይሁን እንጂ ቤተሰባቸውን የሚተዉ አባቶች ቁጥር እየተበራከተ የመጣው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ነው።

በብራዚል በ2000 በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ 44.7 ሚሊዮን ከሚያክሉ የአገሪቱ ቤተሰቦች መካከል 11.2 ሚሊዮን የሚሆኑት በሴቶች የሚተዳደሩ እንደሆኑ ታውቋል። በኒካራጓ ከጠቅላላዎቹ ልጆች 25 በመቶ የሚሆኑት ከእናቶቻቸው ጋር ብቻ የሚኖሩ ናቸው። በኮስታ ሪካ አባቶቻቸው የካዷቸው ልጆች ብዛት በ1990ዎቹ ዓመታት ከ21.1 በመቶ ወደ 30.4 በመቶ ከፍ ብሏል።

እነዚህ ከሦስት አገሮች የተገኙ አኃዛዊ መረጃዎች ለናሙና ያህል የቀረቡ ናቸው። አሁን ደግሞ ሌላውን የዚህ ችግር ገጽታ እንመልከት።

ቢኖሩም ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አባቶች

“አባዬ፣ ተመልሰህ የምትመጣው መቼ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። አሁን 23 ዓመት የሆናት ናኦ “አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊት አባቴን አይቼው አላውቅም ነበር ማለት እችላለሁ። አንድ ጊዜ ከቤት ሲወጣ ‘እባክህ ተመልሰህ ና’ ብዬ ለምኜው እንደነበረ ትዝ ይለኛል” ብላለች።

ፖላንዳዊው ፒዮትር ሽቸኬቪች “ብዙ ቤተሰቦች የጎደላቸው ጥሩ አባት ነው” ብለው ለመጻፍ የተነሳሱት ናኦ ከአባቷ ጋር የነበራትን ዓይነት የቤተሰብ ዝምድናዎች ከተመለከቱ በኋላ ነው። እርግጥ ነው፣ ብዙ አባቶች ከቤተሰባቸው ጋር እየኖሩ መተዳደሪያ እንደሚያቀርቡላቸው አይካድም። ሆኖም ካፒታል የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት እንዳለው “በጣም ብዙ አባቶች አስተማሪዎች መሆን እንደማያስፈልጋቸውና ዳቦ ይዘው ከገቡ በቂ እንደሆነ ያስባሉ።”

አብዛኛውን ጊዜ አባቶች የቤተሰቡ አባሎች ቢሆኑም የልጆቻቸውን አስተዳደግ አይከታተሉም። የእነርሱ ትኩረት ያለው ከቤተሰባቸው ውጭ ነው። ፋሚይ ክሬቲየን የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ “አባትየው በአካል ቤት ውስጥ ቢኖርም አእምሮው ግን ሌላ ቦታ ሊሆን ይችላል” ብሏል። በዛሬው ጊዜ ብዙ አባቶች በስሜትና በአእምሮ ከቤተሰባቸው የሚነጠሉት ለምንድን ነው?

ከላይ የጠቀስነው መጽሔት እንደገለጸው መሠረታዊ ምክንያቱ “አባት ወይም ባል ያለውን ኃላፊነትና ድርሻ ስለማይገነዘቡ ነው።” ብዙ አባቶች የአንድ ጥሩ አባት ድርሻ በቂ ደመወዝ ማምጣት ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዮዜፍ አውግስቲን የተባሉት ፖላንዳዊ ጸሐፊ እንዳሉት “ብዙ አባቶች ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ስለሚያመጡ ጥሩ ወላጆች እንደሆኑ ያስባሉ።” ይሁን እንጂ ይህ የአባትነት ኃላፊነት አንዱ ክፍል ብቻ ነው።

ልጆች የአባታቸውን ጥሩነት የሚለኩት በሚያመጣው የገንዘብ መጠን ወይም በሚሰጣቸው ሥጦታዎች ውድነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልጆች ከሚሰጣቸው ቁሳዊ ሥጦታ ይበልጥ የሚፈልጉት የአባታቸውን ፍቅር፣ ጊዜና ትኩረት ነው። ለእነርሱ ትልቅ ዋጋ ያለው ይህ ነው።

ቆም ብሎ ማጤን ያስፈልጋል

የጃፓን ማዕከላዊ የትምህርት ጉባኤ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት “አባቶች ከልክ በላይ ሥራ ላይ ብቻ ያተኮረውን አኗኗራቸውን ቆም ብለው ማጤን ይገባቸዋል።” ጥያቄው አንድ አባት ለልጆቹ ሲል አንዳንድ ማስተካከያዎች ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናል? የሚል ነው። ጊሰነ አልገማይነ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ አንድን ጥናት ጠቅሶ እንደዘገበው ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው አባቶች አብዛኞቹ ልጆቻቸውን ከሥራ እድገት ለማስቀደም ፈቃደኛ አይደሉም።

ልጆች አባታቸው ቸል እንዳላቸው ሲሰማቸው በጣም ያዝናሉ። አሁን 21 ዓመት የሆናት ሊድያ በፖላንድ ትንሽ ልጅ ሳለች አባቷ እንዴት ያለ ሰው እንደነበረ በደንብ ታስታውሳለች። “አናግሮን አያውቅም ነበር። በተለያየ ዓለም የምንኖር ሰዎች ነበርን። ትርፍ ጊዜዬን በዳንስ ቤቶች እንደማሳልፍ አያውቅም ነበር” ትላለች። ስፔይናዊቷ የ21 ዓመት ወጣት ማካሬናም በተመሳሳይ ልጅ ሳለች አባቷ “በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ከጓደኞቹ ጋር ለመደሰት ጥሏቸው እንደሚሄድና በተደጋጋሚ ለበርካታ ቀናት ጠፍቶ እንደሚቆይ” ትናገራለች።

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን ነገሮች መለየት

አብዛኞቹ አባቶች ለልጆቻቸው የሚሰጡት ጊዜና ትኩረት በቂ እንዳልሆነ ይገነዘቡ ይሆናል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ያለው አንድ ጃፓናዊ አባት “ልጄ ሁኔታዬን እንደሚረዳልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም ሥራ በሚበዛብኝ ጊዜ እንኳን ሳይቀር ስለ እርሱ አስባለሁ።” ይሁን እንጂ አባቱ የጠፋበትን ምክንያት ልጁ ይረዳል ብሎ መመኘት ብቻውን ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል?

የልጅን ፍላጎት ለማርካት ልባዊ ጥረት፣ እንዲያውም መሥዋዕትነት ያስፈልጋል። ልጆች ከምንም ነገር ይበልጥ የሚያስፈልጋቸውን ፍቅር፣ ጊዜና ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው . . . በእንጀራ [ወይም በምግብ] ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4) በተጨማሪም ልጆች በቁሳዊ ነገሮች ብቻ ጥሩ ሆነው ሊያድጉ አይችሉም። አባቶች፣ ለልጆቻችሁ ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት ስትሉ በጣም ውድ እንደሆነ የምትቆጥሩትን ነገር ማለትም ጊዜያችሁን ወይም የሥራ እድገታችሁን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ትሆናላችሁ?

ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ በየካቲት 10, 1986 እትሙ ከምንም ነገር ይበልጥ ለልጆቹ ቅድሚያ መስጠት እንደሚኖርበት ስለተገነዘበ አባት ተርኳል። “አንድ የጃፓን ብሔራዊ የባቡር ድርጅት ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ከቤተሰቡ ከመነጠል ይልቅ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ መርጧል” ይላል። ከዚያም ጋዜጣው ባለ ሥልጣኑ “ማንም ሰው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ይችላል። ልጆቼ ግን ከእኔ በስተቀር ሌላ አባት የላቸውም” ሲል መናገሩን ጠቅሶ ዘግቧል።

በእርግጥም ጥሩ አባት ለመሆን የመጀመሪያው እርምጃ ልጆች የሚያስፈልጋቸው ምን ዓይነት አባት እንደሆነ ማወቅ ነው። ጥሩ አባት መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል እንመርምር።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አባዬ፣ ተመልሰህ የምትመጣው መቼ ነው?”

ይህ ናኦ የተባለች የአምስት ዓመት ጃፓናዊት ልጅ አባቷ አንድ ቀን ወደ ሥራ ሲሄድ የጠየቀችው ጥያቄ ነው። በአንድ ቤት የሚኖሩ ቢሆኑም ብዙ ጊዜ አታየውም። አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ የሚመጣው ናኦ ከተኛች በኋላ ሲሆን የሚሄደው ደግሞ ከእንቅልፍ ከመነሳቷ በፊት ነው።