በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጭፍን ጥላቻ የተለያዩ ገጽታዎች

የጭፍን ጥላቻ የተለያዩ ገጽታዎች

የጭፍን ጥላቻ የተለያዩ ገጽታዎች

“ጭፍን ጥላቻን በበር ብታስወጣው ተመልሶ በመስኮት ይገባል።—ታላቁ ፍሬድሪክ፣ የፕራሻ ንጉሥ

ራጄሽ የሚኖረው ፓሊያድ በምትባል የሕንድ መንደር ውስጥ ሲሆን ዝቅ ተደርገው እንደሚታዩት ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ውኃ የሚቀዳው 15 ደቂቃ ያህል በእግሩ ሄዶ ነው። “ጨዋዎች የሚባሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚቀዱበት የመንደሩ ቧንቧ እንድንቀዳ አይፈቀድልንም” በማለት ይገልጻል። ራጄሽ ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ ሌሎች ልጆች የሚጫወቱበትን ኳስ በእጁ እንኳን እንዲነካ አይፈቀድለትም ነበር። “እኛ የምንጫወተው በድንጋይ ነበር” ይላል።

ክርስቲና የምትባል ከሩቅ ምሥራቅ መጥታ በአውሮፓ የምትኖር ወጣት “ምክንያቱን ባላውቅም ሰዎች እንደሚጠሉኝ ይሰማኛል” ትላለች። “በጣም ያበሳጫል። ብዙውን ጊዜ ራሴን ማግለል እንደሚሻለኝ ባስብም ብስጭቴን ግን ሊቀንስልኝ አልቻለም” በማለት አክላ ተናግራለች።

በምዕራብ አፍሪካ የሚኖረው ስታንሊ “ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ጭፍን ጥላቻ ያወቅኩት 16 ዓመት ሲሆነኝ ነበር” ይላል። “ከዚያ በፊት አይቻቸው እንኳን የማላውቃቸው ሰዎች ከከተማችን ውጣ አሉኝ። የእኔ ጎሣ አባላት የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ቤታቸው ተቃጥሎባቸዋል። የአባቴ የባንክ ሂሣብ እንዳይንቀሳቀስ ታገደበት። በዚህ የተነሣ እኛን ይጠላ የነበረውን ጎሣ መጥላት ጀመርኩ።”

ራጄሽ፣ ክርስቲናና ስታንሊ የጭፍን ጥላቻ ሰለባ ሆነዋል። እንዲህ ዓይነት ጥላቻ እየደረሰባቸው ያሉ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኮይቺሮ ማትሱራ “ዛሬ በዘር ጥላቻ፣ በአድልዎ፣ በባይተዋርነትና በመገለል ምክንያት የሚሰቃዩ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ” ብለዋል። “እንዲህ ያለው ሰብዓዊነት የጎደለው ልማድ በድንቁርናና በጭፍን ጥላቻ በመታገዝ በበርካታ አገሮች የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲቀጣጠሉና እጅግ ከፍተኛ የሆነ መከራና ሥቃይ በሰዎች ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።”

ጭፍን ጥላቻ ደርሶብህ የማታውቅ ከሆነ ምን ዓይነት የስሜት ቁስል እንደሚያስከትል ላይገባህ ይችላል። “አንዳንዶች ሆድ ይፍጀው እያሉ ለራሳቸው አምቀው ይዘውት ይኖራሉ። ሌሎች ደግሞ ጥላቻውን በጥላቻ ይመልሳሉ” ሲል ፌስ ቱ ፌስ አጌንስት ፕረጀዲስ የተባለው መጽሐፍ አስተያየቱን ሰጥቷል። ጭፍን ጥላቻ የሰዎችን ሕይወት የሚጎዳው በምን መንገዶች ነው?

የሚናቅ ወይም የሚጠላ የኅብረተሰብ ክፍል አባል ከሆንክ ሰዎች እንደሚርቁህ፣ እንደሚገላምጡህ ወይም ባሕልህን የሚያንቋሽሽ አስተያየት እንደሚሰጡ ታስተውላለህ። ሌላው ሰው ንቆ የተወውን ሥራ ካልሆነ ሌላ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንብሃል። ምናልባትም ተስማሚ ቤት ማግኘት ያቅትሃል። ልጆችህን የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ያገልሏቸዋል።

ከዚህ ሲብስ ደግሞ ጭፍን ጥላቻ ሰዎችን ለጠብና ለግድያ ያነሳሳል። በእርግጥም የታሪክ ገጾች በጭፍን ጥላቻ ምክንያት በተቀጣጠሉ እልቂቶች፣ ጭፍጨፋዎችና የጎሣ ምንጠራ ዘመቻዎች የተሞሉ ናቸው።

ባለፉት መቶ ዘመናት የታየ ጭፍን ጥላቻ

በአንድ ወቅት ዋነኞቹ የጭፍን ጥላቻ ዒላማዎች ክርስቲያኖች ነበሩ። ለምሳሌ ኢየሱስ እንደሞተ አካባቢ በጣም አሰቃቂ የሆነ የስደት ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 8:3፤ 9:1, 2፤ 26:10, 11) ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ክርስቲያኖች ነን ይሉ በነበሩ ሰዎች ላይ ብዙ ግፍ ተፈጽሟል። የሦስተኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ተርቱልያን “አንድ ወረርሽኝ ቢነሳ ወዲያው ‘ክርስቲያኖች ለአንበሶች ይጣሉ’ የሚል ጩኸት ይነሳል” ሲል ጽፏል።

ከ11ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግን በመስቀል ጦርነት ምክንያት በአውሮፓ ዋነኞቹ የጥላቻ ዒላማዎች አይሁዳውያን ሆኑ። የቡቦኒክ ወረርሽኝ መላዋን አውሮፓ አዳርሶ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአህጉሪቱን አንድ አራተኛ ነዋሪዎች በገደለ ጊዜ አይሁዳውያን ቀድሞውንም በብዙዎች ይጠሉ ስለነበር በሽታውን ያመጡብን እነሱ ናቸው ተባለ። ጀኔት ፋረል ኢንቪዚብል ኢነሚስ በተባለው መጽሐፋቸው “ወረርሽኙ ለጥላቻው ሰበብ ሲሆን ጥላቻው ደግሞ በፍርሃት ተውጠው የነበሩት ሰዎች ለወረርሽኙ ተጠያቂ አድርገው የሚወነጅሉት ወገን እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗቸዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

በኋላም በደቡባዊ ፈረንሣይ የሚኖር አንድ አይሁዳዊ በደረሰበት ሥቃይ ምክንያት በውኃ ጉድጓዶች ውስጥ መርዝ በመጨመር ወረርሽኙን ያመጡት አይሁዳውያን መሆናቸውን “አመነ።” የሰጠው የእምነት ቃል ውሸት እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም እንደ እውነት ተደርጎ በመላ አህጉሪቱ ተሰራጨ። ብዙም ሳይቆይ በስፔይን፣ በፈረንሣይና በጀርመን የሚኖሩ አይሁዳውያን ተጨፈጨፉ። የበሽታው ትክክለኛ ምክንያቶች አይጦች መሆናቸውን ዞር ብሎ ያየ ሰው አልነበረም። በተጨማሪም አይሁዳውያንም እንደሌሎቹ ሰዎች በዚህ ቸነፈር መሞታቸውን ያስተዋለ አልነበረም።

ጭፍን ጥላቻ እንደ ሰደድ እሳት አንዴ ከተያያዘ ለብዙ መቶ ዘመናት እየተቀጣጠለ ሊቆይ ይችላል። በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ አዶልፍ ሂትለር ጀርመን በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተሸነፈችው በአይሁዳውያን ምክንያት ነው በማለት ፀረ ሴማውያን እንቅስቃሴ እንዲፋፋም አደረገ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማለቂያ ላይ የኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ የናዚዎች አዛዥ የነበረው ሩዶልፍ ኾስ “የተሰጠን ወታደራዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ሥልጠና ጀርመንን ከአይሁዳውያን መጠበቅ እንዳለብን ያስገድደን ነበር” ሲል የእምነት ቃሉን ሰጥቷል። ኾስ “ጀርመንን ለመጠበቅ” 2,000,000 ሰዎችን ያስገደለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ነበሩ።

የሚያሳዝነው ግን ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳን እንደነዚህ ያሉት የጭካኔ ድርጊቶች አለመቅረታቸው ነው። ለምሳሌ በ1994 በምሥራቅ አፍሪካ በቱትሲዎችና በሁቱዎች መካከል በተፈጠረው የጎሣ ግጭት ምክንያት ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች ተገድለዋል። ታይም መጽሔት “ምንም ዓይነት መሸሸጊያ ማግኘት አልተቻለም” ሲል ዘግቧል። “ብዙዎቹ ተሸሽገን እናመልጣለን ብለው በገቡባቸው አብያተ ክርስቲያናት ወለሎች ላይ ደም እንደጎርፍ ፈሷል። . . . ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ የተደረገ ውጊያ ሲሆን የነበረው ጭካኔና የደም ጥማት ከሞት ሊያመልጡ የቻሉትን በድንጋጤና በፍርሃት ክው ብለው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል።” ሕፃናት እንኳን በጭካኔ ከመገደል አላመለጡም። አንድ የአገሪቱ ነዋሪ “ሩዋንዳ በጣም ትንሽ አገር ብትሆንም የዓለምን ጥላቻ በሙሉ ይዘናል” ብሏል።

ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መፈራረስ ጋር በተያያዘ በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት 200,000 የሚያክሉ ሰዎች ሞተዋል። ለበርካታ ዓመታት በሰላምና በጥሩ ጉርብትና አብረው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተገዳድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተገደው ሲደፈሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የጎሣ ምንጠራ በተባለ ጨካኝ ፖሊሲ ምክንያት ከቤታቸውና ከቀዬአቸው ተባርረዋል።

ጭፍን ጥላቻ አብዛኛውን ጊዜ እስከ መገዳደል ባያደርስም በሰዎች መካከል መለያየትና መቃቃር ማስከተሉ አይቀርም። አንድ በቅርቡ የወጣ የዩኔስኮ ዘገባ የዓለም ሕዝብ በጣም እየተቀራረበ የመጣ ቢሆንም ዘረኝነትና የዘር ጥላቻ “በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ሥር እየሰደደ ሄዷል” ሲል ገልጿል።

ታዲያ ጭፍን ጥላቻን ለማስወገድ ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖራል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጭፍን ጥላቻ በሰዎች አእምሮና ልብ ውስጥ ሥር የሚሰድደው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጭፍን ጥላቻ ባሕርያት

ጎርደን ደብሊው አልፖርት ዘ ኔቸር ኦቭ ፕረጀዲስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በጭፍን ጥላቻ ምክንያት የሚፈጠሩ አምስት ዓይነት ባሕርያትን ዘርዝረዋል። አብዛኛውን ጊዜ ጭፍን ጥላቻ ያለበት ሰው ከእነዚህ ባሕርያት አንዱ ወይም ብዙዎቹ ይታዩበታል።

1. አፍራሽ አስተያየቶች። ሰውየው በጭፍን የሚጠላቸውን ሰዎች የሚያዋርድና የሚያቃልል አስተያየት ይሰጣል።

2. ማግለል። የሚጠላው ቡድን አባል የሆነን ማንኛውም ሰው አያቀርብም።

3. ማዳላት። የሚጠላቸው ሰዎች አንዳንድ የሥራ ዓይነቶችን፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን ወይም መብቶችን እንዳያገኙ በማድረግ መድልዎ ይፈጽምባቸዋል።

4. አካላዊ ጥቃት። የሚጠላቸውን ሰዎች ለማስፈራራት በሚካሄዱ የጠብ ወይም የዓመጽ ድርጊቶች ይካፈላል።

5. ማጥፋት። በድብደባ፣ በግድያ ወይም ጨርሶ በማጥፋት ዘመቻዎች ይካፈላል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤናኮ የስደተኞች መጠለያ፣ ታንዛኒያ ግንቦት 11, 1994

በውኃ መቅጃ ዕቃዋ አጠገብ የተቀመጠች ሴት። ከ300,000 የሚበልጡ ስደተኞች ወደ ታንዛኒያ የተሻገሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ሁቱ ሩዋንዳውያን ናቸው

[ምንጭ]

Photo by Paula Bronstein/Liaison