በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጅነት የሥራ ድርሻ

የወላጅነት የሥራ ድርሻ

የወላጅነት የሥራ ድርሻ

የሐርቫርድ ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፒተር ጎርስኪ “አንድ ልጅ የሚወደድና በጣም የተቀራረበ የአንድ ቤተሰብ አባል እንደሆነ እንዲሰማው ከተደረገ እንዲሁም ዓላማ ያለውና ተመራማሪ ከሆነ የዳበረ አእምሮ ያለው ሰው ይሆናል” ብለዋል። “የወላጅነት ግዴታችን የልጃችን አንጎል በላቀ ሁኔታ እንዲሠራ ማድረግ ሳይሆን ጤናማ አካልና አእምሮ ያለው እንዲሁም አሳቢ የሆነ ሰው ማሳደግ ነው።”

አንድ ልጅ አድጎ በሥነ ምግባር የታነጸና ለሌሎች አሳቢ የሆነ ሰው ሲሆን መመልከት ወላጆችን በጣም ያስደስታል! ወላጆች እንዲህ ያለውን ውጤት ማግኘታችሁ ጥሩ ምሳሌ፣ ጥሩ ባልንጀራና ጥሩ አስተማሪ ለመሆን እንዲሁም ከልጃችሁ ጋር ልብ ለልብ ለመተዋወቅ በምታደርጉት ጥረት ላይ የተመካ ነው። ሁሉም ልጆች ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ መሠረታዊ ዝንባሌ ኖሯቸው የሚወለዱ ቢሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ ደረጃ በደረጃ የሥነ ምግባር እሴቶችን ሊቀርጹባቸው ይገባል።

ልጆችን የሚቀርጸው ማነው?

ልጆችን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው ማነው በሚለው ጥያቄ ረገድ ተመራማሪዎች የተለያየ አስተያየት አላቸው። አንዳንዶች ልጆች በዋነኝነት የሚቀረጹት በእኩዮቻቸው እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ቤሪ ብሬዘልተንና ስታንሊ ግሪንስፓን ሕፃናትን በማሳደግ ረገድ ወላጆች ያላቸው ድርሻ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ያምናሉ።

አንድ ልጅ ካደገ በኋላ የሚያጋጥሙት ሁኔታዎችና የእኩዮቹ ተጽዕኖ ቀደም ሲል ባዳበራቸው ባሕርያት ላይ ተጨማሪ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ልጆች በቤተሰባቸው ክልል ውስጥ በርኅራኄና እንደ ባሕርያቸው ተይዘው ማደጋቸው አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ብስለት በሚንጸባረቅበት መንገድ ስሜታቸውን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ መማር ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያገኙ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ጋር ተግባብተው ለመሥራት፣ ርኅራኄ ለማሳየትና የሌሎችን ችግር ለመረዳት የተዘጋጁ ይሆናሉ።

ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን በጣም ከባድ ሥራ ነው። በተለይ አዳዲስ ወላጆች ከሆናችሁ በዚህ ረገድ የተሳካ ውጤት ለማግኘት ከእናንተ የተሻለ ልምድ ያላቸውን ሰዎች አመራር ብትጠይቁና አንድ ወጥ የሆነ አካሄድ ብትከተሉ ጥሩ ይሆናል። ስለ ልጆች አስተዳደግ የተጻፉ መጻሕፍት በጣም በርካታ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጡት ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ምክር ጋር ይስማማል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት አስተማማኝ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያሳድጉ አስችለዋል። የሚከተሉትን ተግባራዊ መመሪያዎች ተመልከቱ።

ፍቅራችሁን ለመግለጽ ወደኋላ አትበሉ

ሕፃናት ዘወትር ትኩረት ከተሰጣቸው፣ በተገቢ ሁኔታ ሲኮተኮቱና እንክብካቤ ሲደረግላቸው ፋፍተውና ለምልመው እንደሚያድጉ ዕጽዋት ናቸው። አንድ ለጋ ተክል ውኃና የፀሐይ ብርሃን ሲያገኝ ለምልሞና ጤናማ ሆኖ ያድጋል። በተመሳሳይም ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በቃልና በአካላዊ መግለጫዎች የሚገልጹ ወላጆች የልጆቻቸው አእምሯዊና ስሜታዊ እድገት ጤናማና የለመለመ እንዲሆን ያደርጋሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በቀላል አነጋገር “ፍቅር . . . ያንጻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 8:1) ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ከመግለጽ ወደኋላ የማይሉ ወላጆች ፈጣሪያቸውን ይሖዋ አምላክን ይመስላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት አባቱ እንደሚወደውና ደስ እንደሚሰኝበት የሚገልጽ ድምፅ ከሰማይ እንደሰማ ይተርካል። ኢየሱስ ሙሉ ሰው የነበረ ቢሆንም እንኳን ይህን መስማቱ በጣም ያጽናናዋል!—ሉቃስ 3:22

ለልጆቻችሁ የምታሳዩት ፍቅር፣ ሊተኙ ሲሉ የምታነቡላቸው ታሪክ እንዲሁም አብራችኋቸው የምትጫወቱት ጨዋታ እንኳን ሳይቀር በልጃችሁ አስተዳደግ ላይ ወሳኝ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዶክተር ፍሬዘር መስተርድ እንዲህ ይላሉ:- ‘ሕፃኑ የሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ በወደፊት ሕይወቱ ላይ የሚያስከትሉት ለውጥ ይኖራል። ልጃችሁ ለመዳህ በመጣጣር ላይ ከሆነ የምትሰጡት ማበረታቻና ድጋፍ አስፈላጊ ነው።’ የምትሰጡት ፍቅርና ትኩረት ልጃችሁ በጥሩ ሁኔታ አድጎ የበሰለና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው የሚሆንበትን ጠንካራ መሠረት ይጥልለታል።

ጥሩ ጓደኛ መሆንና እንደ ልብ መወያየት

ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በመካከላችሁ የቀረበ ትስስር እንዲፈጠር ያስችላል። ከዚህም በላይ ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታቸውን ያዳብርላቸዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች በቤት ውስጥም ሆነ በሌሎች ቦታዎች አመቺ በሆኑ ጊዜያት እንዲህ ያለው ቅርርብ እንዲኖር ያበረታታሉ።—ዘዳግም 6:6, 7፤ 11:18-21

የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያዎች ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ውድ ከሆኑ መጫወቻዎች ወይም ከማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ይስማማሉ። ብዙ ወጪ የማይጠይቁ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከልጆቻችሁ ጋር አስደሳች ጊዜ እንድታሳልፉ ያስችሏችኋል። ለምሳሌ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ተፈጥሮን ለማየት ወደ መናፈሻዎች ቢሄዱ ልጆቻቸውን ትርጉም ያላቸው ጥያቄዎች ለመጠየቅና ሐሳባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ለማበረታታት ጥሩ አጋጣሚ ሊከፍትላቸው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4) አዎን፣ አንድ ልጅ በአእምሮ፣ በስሜትና ከሌሎች ጋር ተግባብቶ በመኖር ረገድ የተሟላ እድገት እንዲያደርግ በነፃነት የሚጫወትበት ጊዜ ሊኖረው ይገባል። ዶክተር መስተርድ እንደሚሉት ጨዋታ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የግድ አስፈላጊም ነው። “ልጆች የአንጎላቸውን የነርቭ አውታሮች ለተለያዩ ተግባራት የሚያዘጋጁበት ዋናው መንገድ በሚጫወቷቸው ጨዋታዎች አማካኝነት ነው” ብለዋል። አንድ ልጅ ራሱ በሚፈጥራቸው ጨዋታዎች የሚጠቀምባቸው መጫወቻዎች እንደ ባዶ ካርቶን ያሉ ቀላል ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ጉዳት የማያስከትሉ ተራ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በጣም ውድ የሆኑ መጫወቻዎችን ያህል ያስደስቱታል። *

ልጆችን ትላልቅ ሰዎች በሚያዘጋጁዋቸው በርካታ እንቅስቃሴዎች ማጨናነቅ የፈጠራ ችሎታቸውን ይገድብባቸዋል። ልከኝነት አስፈላጊ ነው። ልጃችሁ የራሱን ዓለም እንዲመረምርና አቅሙንና ችሎታውን እንዲፈትን ፍቀዱለት። አንድ ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ራሱን የሚያዝናናበት እንቅስቃሴ አያጣም። እንዲህ ሲባል ግን ልጃችሁ በራሱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ምን እንደሚያደርግና የት እንደሚጫወት የማወቅ ኃላፊነት የለባችሁም ማለት አይደለም።

ልጃችሁን ለማስተማር ጊዜ መድቡ

ማስተማር ለልጆች እንክብካቤ የማድረግና የተስተካከለ ስብዕና ያላቸው ልጆች የማሳደግ ዋነኛ ክፍል ነው። ብዙ ወላጆች በቀኑ ውስጥ ለልጆቻቸው ጮክ ብለው የሚያነቡበት ጊዜ ይመድባሉ። ይህም ስለ መልካም ባሕርያት ለማስተማርና ፈጣሪያችን በሚናገራቸው ነገሮች ላይ የተመሠረተ የሥነ ምግባር እሴት እንዲያዳብሩ ለማስቻል አጋጣሚ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ አስተማሪና ሚስዮናዊ የነበረው ጢሞቴዎስ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን ከሕፃንነቱ ጀምሮ’ ያውቅ እንደነበረ ያመለክታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15

ለሕፃን ልጃችሁ ማንበብ በአንጎሉ ነርቮች መካከል ያሉትን ግንኙነቶች ወይም የሲናፕስስ ትስስሮች ያጠናክራል። ቁልፉ አንባቢው ትኩረት የሚሰጥና በአሳቢነት የሚያነብብ መሆኑ ነው። የትምህርት ፕሮፌሰር የሆኑት ሊንዳ ሲገል ስለሚነበበው ነገር ይዘት ሲያስጠነቅቁ “ልጆች ሊረዱትና ሊደሰቱበት የሚችሉት ዓይነት መሆን አለበት” ብለዋል። በተጨማሪም የምታነቡላቸው በየቀኑ፣ በተወሰነ ሰዓት እንዲሆን ጥረት አድርጉ። እንዲህ ከተደረገ ልጁ ንባቡን በናፍቆት መጠባበቅ ይጀምራል።

ትምህርት ዲስፕሊን ወይም ተግሣጽ መስጠትን ይጨምራል። ትናንሽ ልጆች በፍቅር ከሚሰጣቸው ተግሣጽ ጥቅም ያገኛሉ። ምሳሌ 13:1 [NW] “አባት ተግሣጽ የሚሰጥ ከሆነ ልጅ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። ይሁን እንጂ ተግሣጽ መቅጣት ብቻ እንዳልሆነ አስታውሱ። ለምሳሌ ያህል ተግሣጽ፣ በቃል እርማት በመስጠት አሊያም አንዳንድ መብቶችን በመከልከል ወይም በሌሎች መንገዶች በመቅጣት ሊሰጥ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ብሬዘልተን ተግሣጽ የሚባለው “አንድ ልጅ ስሜቱን እንዲቆጣጠርና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ባሕርይ እንዳያሳይ ማስተማር ነው። ሁሉም ልጅ ገደቦቹን ማወቅ ያስፈልገዋል። ከፍቅር ቀጥሎ ለልጆች ሊሰጥ የሚገባው በጣም አስፈላጊ ነገር ተግሣጽ ነው።”

ወላጅ እንደመሆናችሁ የምትሰጡት ተግሣጽ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? አንደኛ ነገር ልጆቻችሁ ተግሣጽ የሚሰጣቸው ለምን እንደሆነ መረዳት ይገባቸዋል። እርማት በምትሰጡበት ጊዜ ልጆቻችሁ ደጋፊና አፍቃሪ ወላጅ መሆናችሁ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ሊሆን ይገባል።

የተሳካ ውጤት የሚያስገኙ ጥረቶች

ፍሬድ ለሴት ልጁ ከሕፃንነቷ ጀምሮ በየቀኑ ማታ፣ ማታ ከመተኛትዋ በፊት ያነብላት ነበር። ከጊዜ በኋላ የሚያነብላትን አብዛኞቹን ታሪኮች በቃል እንደያዘች እንዲሁም እርሱ ሲያነብ ተከትላው ቃሎቹን አስታውሳ እንደምትጠራ አስተውሏል። ክሪስ ለልጆቹ በማንበብ ረገድ ትጉህ የሆነ ሌላ ወላጅ ነው። የሚያነብላቸውን ነገር ለመቀያየር ይጥር ነበር። ልጆቹ በጣም ትንሽ ሳሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እንደሚሉት ባሉ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ሥዕላዊ መግለጫዎች በመጠቀም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ትምህርቶች ይሰጣቸው ነበር። *

ሌሎች ወላጆች ደግሞ ከንባቡ በተጓዳኝ ሥዕል እንደ መሳል፣ ቀለም እንደ መቀባት፣ ሙዚቃ እንደ መጫወት እንዲሁም መናፈሻና ፓርኮች የመሰሉ ቦታዎችን እንደ መጎብኘት ያሉ እንቅስቃሴዎችን ያቀናጃሉ። እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎችን ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማካፈል እንዲሁም ጥሩ የሥነ ምግባር እሴቶችንና መልካም ጠባዮችን በቀላሉ ሊቀበል በሚችለው የልጃቸው ልብና አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።

ታዲያ ይህ ሁሉ ልፋትና ጥረት በእርግጥ ዋጋ ያስገኛል? ከላይ የዘረዘርናቸውን ተግባራዊ መመሪያዎች ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ሥራ ላይ ለማዋል የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ወላጆች ጥሩ ዝንባሌና አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ልጆች የማሳደግ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ልጆቻችሁ ከትንሽነታቸው ጀምረው የማሰብና ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታ እንዲያዳብሩ ብትረዷቸው ለሥነ ምግባራዊና ለመንፈሳዊ ስብዕናቸው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላላችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በምሳሌ 22:6 ላይ “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ብሏል። ወላጆች ልጆችን በማሠልጠን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የተረጋገጠ ነው። ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅር ከመግለጽ ወደኋላ አትበሉ። ከእነርሱ ጋር ጊዜ አሳልፉ፣ ተንከባከቧቸው እንዲሁም አስተምሯቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ ለእነርሱም ሆነ ለእናንተ ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላችኋል።—ምሳሌ 15:20

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 በዚህ መጽሔት የመጋቢት 22,1993 (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “በነፃ የሚገኙ የአፍሪካ መጫወቻዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.23 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው መጽሐፍም ትናንሽ ልጆችን በማስተማር ረገድ ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከልጃችሁ ጋር ተጫወቱ

▪ ሕፃናት በተፈጥሯቸው በጣም ስልቹ ናቸው፤ በመሆኑም ማጫወት ያለባችሁ ደስ በሚላቸው ጊዜ ብቻ ነው።

▪ መጫወቻ የምትሰጧቸው ከሆነ መጫወቻው አደጋ የማያስከትልና የልጁን አእምሮ የሚያሠራ ዓይነት ይሁን።

▪ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠይቁ ጨዋታዎች አጫውቷቸው። ሕፃናት እነርሱ የጣሉትን አሻንጉሊት እንደ ማንሳት ያሉ ነገሮች አሁንም አሁንም ስታደርጉ ማየት ያስደስታቸዋል።

[ምንጭ]

ምንጭ:- Clinical Reference Systems

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለልጃችሁ በምታነቡበት ጊዜ

▪ የቃላቶቹን ትክክለኛ አጠራር በመጠቀም በግልጽ እንዲሰማ አድርጋችሁ አንብቡ። አንድ ሕፃን ቋንቋ የሚማረው ወላጆቹ ሲናገሩ በመስማት ነው።

▪ በጣም ትንንሽ ለሆኑ ልጆች በመጽሐፋቸው ላይ ያሉትን ሰዎችና ዕቃዎች በጣታችሁ እያመለከታችሁ ስማቸውን ንገሯቸው።

▪ ልጁ ከፍ እያለ ሲሄድ የሚወዳቸውን ነገሮች የያዙ መጻሕፍት ምረጡ።

[ምንጭ]

ምንጭ:- Pediatrics for Parents

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከልጆቻችሁ ጋር የምትዝናኑበትና የምትደሰቱበት ጊዜ ይኑራችሁ