በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገዳይ ከሆነው ጭስ ራስህን ጠብቅ

ገዳይ ከሆነው ጭስ ራስህን ጠብቅ

ገዳይ ከሆነው ጭስ ራስህን ጠብቅ

አኃዛዊው መረጃ እጅግ አስደንጋጭ ነው፤ በየቀኑ በእያንዳንዷ ደቂቃ ሦስት ሰዎች በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ይገደላሉ። ነፍሰ ገዳዩ ደግሞ የማገዶ ጭስ ነው።

እዚህ ላይ ማገዶ ሲባል ኩበት፣ ደረቅ እንጨት፣ ጭራሮ፣ ሣር ወይም ገለባ ሊሆን ይችላል። በኔፓል የሚታተመው ዘ ካትማንዱ ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ማለትም አንድ ሦስተኛው የዓለማችን ሕዝብ ለማብሰልና ሙቀት ለማግኘት ማገዶ ይጠቀማል። ብዙውን ጊዜ ማገዶ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ብቸኛ የኃይል ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።

የሚያሳዝነው ግን፣ ማገዶ በሚነድበት ወቅት አደገኛ ጭስ ከውስጡ ይወጣል። ታዲያ ምን ይበጃል? “በቤት ውስጥ የተበከለ አየር እንዳይኖር ማድረግ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል ነው፤ ይኸውም ጭስ ወደ ቤት እንዳይገባ ማድረግ አሊያም ከቤት ማስወጣት የሚቻልበትን መፍትሔ መፈለግ ነው” ሲል ኢንተርሚድየት ቴክኖሎጂ ዴቨለፕመንት ግሩፕ የሚባል ድርጅት ገልጿል። ይህ ድርጅት በብዙ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ በመርዳት ላይ ይገኛል።

ከቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል ቀዳሚ የሆነው ከቤት ውጪ ማብሰል ነው። ሆኖም ይህ የማይቻል አሊያም በብዙዎች ዘንድ የማይፈለግ ቢሆንስ? ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ድርጅት ንጹሕ አየር ቤት ውስጥ እንደ ልብ እንዲዘዋወር ማድረግ የሚቻልባቸውን ሁለት መንገዶች ይጠቁማል። እነዚህም በጣሪያና በግድግዳ መካከል ክፍተት ማበጀት (ትንንሽ ነፍሳት እንዳይገቡ ደግሞ ክፍተቶቹን በሽቦ ወንፊት መዝጋት) እንዲሁም በቂ መስኮቶች መሥራት (ገመና እንዳይታይ የመስኮት መከለያ ማበጀት) ናቸው። ይህ ንጹሕ አየር በቤት ውስጥ እንደ ልብ እንዲዘዋወርና ጭሱ እንዲወጣ ያደርጋል። ሆኖም ሙቀት ለማግኘት ሲባል እሳት በሚነድባቸው ቤቶች ውስጥ ጭሱን ለማስወጣት ግድግዳው ላይ ክፍተቶችን ከማበጀት ይልቅ ሌላ ቀለል ያለ መንገድ መጠቀሙ የተሻለ ነው።

ጭስን ከቤት ለማስወጣት የተለመደውና ውጤታማ የሆነው መንገድ ለምድጃው ኮፈን ወይም ከለላ መሥራት እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል። እንዲህ ያለውን ከለላ ከቆርቆሮ ካልሆነም ከጡብ ወይም ከጭቃ በቀላሉ መሥራት ይቻላል። ከዚያም የተሠራውን ሰፊ ከለላ ምድጃው ላይ ማድረግና አናቱ ላይ ቱቦ ቀጥሎ ከጣሪያው ጋር በማያያዝ ጭሱ በቀላሉ ከቤት እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል። በመስኩ የተሠማሩ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በግድግዳውና በጣሪያው መካከል ክፍተት ማበጀትና ጭስ ማውጫ የተገጠመለት ምድጃ መጠቀም ከማገዶ የሚወጣውን ጭስ 80 በመቶ ያህል ለመቀነስ ያስችላል። ጭስ ማውጫ ያለው ምድጃ የሚጠቀሙ ሰዎች ጤነኛ፣ ንጹሕ፣ ጠንካራና ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፤ ይህ ደግሞ ጥቂት ነገሮችን ብቻ በማስተካከል ኑሮን ማሻሻል እንደሚቻል የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግድግዳውና በጣሪያው መካከል ክፍተት ያለው እንዲሁም በቂ መስኮቶችና ባለ ጭስ ማውጫ ምድጃ ያሉት ኩሽና፤ ኬንያ

[ምንጭ]

ዶክተር ናይጀል ብሩስ/www.itdg.org