በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጹሕ ቤት እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ

ንጹሕ ቤት እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ

ንጹሕ ቤት እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በንጹሕና ባልተበከለ አካባቢ መኖር ምንኛ አስደሳች ነው! ሆኖም በከተማዎች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ቆሻሻ ምክንያት አካባቢያችንን ንጹሕ ማድረግና ማሳመር ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል።

ማዘጋጃ ቤቶች ቆሻሻ የሚሰበሰብበት ዘዴ በማዘጋጀት መንገዶችን በንጽሕና ለመያዝ ቢጥሩም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ መጠራቀሙ አይቀርም። ይህ ደግሞ ለዓይን የሚያስቀይም ከመሆኑም በላይ ለኅብረተሰቡ ጤና ጠንቅ ነው። በየቦታው የተጠራቀመ ቆሻሻ ለአይጦች፣ ለበረሮዎችና በሽታ አስተላላፊ ለሆኑ ሌሎች ነፍሳት ምቹ የመራቢያ ስፍራ ይሆናል። ይህን ሁኔታ ለማስወገድ አንተ በበኩልህ ልታደርገው የምትችለው ነገር ይኖራል? አዎን፣ መኖሪያ ቤትህና አካባቢህ ንጹሕ እንዲሁም ያልተዝረከረከ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ።

ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር

አንዳንድ ሰዎች ድሆች ንጹሕ ቤትም ሆነ ሰፈር ሊኖራቸው አይችልም ብለው ያስባሉ። ሆኖም ሐቁ ከዚህ የተለየ ነው። እርግጥ ገንዘብ ማጣት አካባቢያችንን በንጽሕና መያዝ ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆንብን ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም አንድ የስፓንኛ አባባል እንደሚገልጸው “ድህነትና ንጽሕና እርስ በርሳቸው ጥል የላቸውም።” በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው በቂ ሀብት ስላለው ብቻ አካባቢውን በንጽሕና ይጠብቃል ማለት አይደለም።

ቤታችንም ሆነ አካባቢያችን ንጹሕ መሆኑ የተመካው በአመለካከታችን ላይ ነው፤ በዚህ ረገድ ተገቢውን አመለካከት ማዳበር ቤታችንን በንጽሕና ለመያዝ ያነሳሳናል። በእርግጥም፣ ቤትን በንጽሕና መያዝ በእጅጉ የተመካው በሁሉም የቤተሰብ አባላት አመለካከት ላይ ነው። በዚህም ምክንያት ቤታችንንና አካባቢያችንን በንጽሕና ለመያዝ እያንዳንዳችን ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደምንችል መመርመሩ ጥሩ ይሆናል።

ቋሚ የጽዳት ፕሮግራም

እናት በቤት ውስጥ የምታከናውነው ሥራ ማለቂያ ያለው አይመስልም። ምግብ ከማብሰልና ልጆችን ለትምህርት ቤት ከማዘጋጀት በተጨማሪ ቤቷንና አካባቢዋን በንጽሕና ለመያዝ ትጥራለች። ብዙ ጊዜ ልጆች ክፍላቸው ውስጥ ትተዋቸው የሄዱትን የቆሸሹ ልብሶች ወይም አንዳንድ የተዝረከረኩ ዕቃዎቻቸውን የምታነሳሳው እናት መሆኗን አስተውለህ ታውቃለህ? ቤተሰቡን በጠቅላላ የሚያሳትፍ ግልጽ የሆነ የጽዳት ፕሮግራም ማውጣት የእናትን ሸክም ለማቅለል ይረዳል።

አንዳንድ ሚስቶች የተወሰኑት ክፍሎች በየቀኑ ትኩረት እንደሚያሻቸውና ሊጸዱ እንደሚገባ ይሰማቸዋል፤ ከዚያም ሌሎቹን ነገሮች በየሳምንቱ ቀሪዎቹን ደግሞ በየወሩ ለማጽዳት ፕሮግራም አውጥተዋል። በዓመት አንድ ጊዜ ሊጸዱ የሚችሉ ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ በቤቴል ቤቶች ማለትም በየአገሩ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ ቁም ሳጥኖቹ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ ወጥቶ የተሟላ ጽዳት የሚደረገው በዓመት አንድ ጊዜ ነው። ይህም የማያስፈልጉትን ነገሮች ለማስወገድና ቁም ሳጥኑን በሥርዓት ለማስተካከል ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። የቤቱን ግድግዳ ለማጽዳትም ቋሚ የሆነ ፕሮግራም አለ።

እንደ መታጠቢያ ቤት ያሉ አንዳንድ ቦታዎች መጽዳታቸው ለጤንነት ወሳኝ ነው። በየቀኑ ቀለል ያለ ጽዳት ቢያስፈልግም ባክቴሪያዎች እንዳይከማቹ በሳምንት አንድ ጊዜ በደንብ መጽዳት አለበት። አንዳንዶች የሽንት ቤት መቀመጫ ውስጥ የተጋገረ ቆሻሻ መኖሩ የማይቀር እንደሆነና ሊለቅ እንደማይችል አድርገው ያስባሉ። ሆኖም በጣም ንጹሕ መጸዳጃ ቤቶች ያሏቸው ቤቶች አሉ። መጸዳጃ ቤቱ ንጹሕ እንዲሆን አዘውትሮ ከማጽዳትና ትክክለኛውን የማጽጃ መሣሪያ ከመጠቀም ያለፈ ነገር አይጠይቅም።

ወጥ ቤትም ቢሆን ጥንቃቄ የተሞላበት ጽዳት ያስፈልገዋል። በየቀኑ ዕቃዎችን ከማጠብ እንዲሁም ምድጃውንና ምግብ የምንሠራበትን ቦታ ከማጽዳት በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ፣ ምናልባትም ቢያንስ በወር አንዴ ከምድጃውና ከማቀዝቀዣው ጀርባ እንዲሁም ከዕቃ ማጠቢያው በታች ያሉትን ቦታዎች በደንብ ማጽዳት አስፈላጊ ነው። በየጊዜው ጓዳውን ወይም የዕቃ መደርደሪያውን የምናጸዳ ከሆነ በረሮዎችና ሌሎች ጎጂ ነፍሳት አይኖሩም።

የቤተሰብ ትብብር

አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ ስለሚሰጧቸውና ስለሚያሠለጥኗቸው ልጆቹ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት አልጋቸውን ያነጥፋሉ፣ ቆሻሻ ልብሳቸውን በቦታው ያስቀምጣሉ እንዲሁም የግል ዕቃዎቻቸውን ሥርዓት ያስይዛሉ። “እያንዳንዱ ነገር የራሱ ቦታ ሊኖረውና ሁሉም ሰው ዕቃውን በቦታው ሊያስቀምጥ ይገባል” የሚለው መመሪያ ለማንኛውም ሰው ጠቃሚ ነው።

ለአንዳንድ የቤተሰቡ አባላት የተወሰነ ሥራ መስጠት ወይም በቤት ውስጥ አንዱን ክፍል እንዲያጸዱ ማድረግም ይቻላል። ለምሳሌ፣ አባትየው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ጋራዡን በተሟላ መልኩ በማጽዳት በሥርዓት ያደራጀዋል? ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ ከልጆቹ አንዱ ሊረዳው ይችል ይሆን? በግቢው ውስጥ የሚገኘውን ሣር የሚያጭድና የአትክልት ቦታውን የሚያርም ሰው ተመድቧል? ግቢው ጥሩ መልክ እንዲኖረው ሣሩ በየስንት ጊዜው ቢታጨድና ቢታረም ይሻላል? ቤቱ በጣሪያ ሥር ወይም በሌላ ቦታ ዕቃ ማስቀመጫ ክፍል አለው? ከሆነ አላስፈላጊ ኮተቶችን በማስወገድ ማን ሊያስተካክለው ይችላል? አንዳንድ ወላጆች እንደነዚህ ዓይነት ሥራዎችን ልጆቻቸው በየተራ እንዲያከናውኑ ይመድቡላቸዋል።

ስለዚህ ቤታችሁን በንጽሕና ለመያዝ ጥሩ ፕሮግራም አውጡ። የምታጸዱት ብቻችሁንም ሆነ ከቤተሰባችሁ ጋር ወይም ደግሞ የሚረዳችሁ ሰው ቀጥራችሁ ከሆነ ጥሩ ፕሮግራም ማውጣት ያስፈልጋችኋል። ቤቷን በንጽሕና የምትይዝ አንዲት እናት ቤተሰቡ ጠቅላላ እንዴት እንደሚተባበር ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “የቤቱን ሥራ ከሦስት ሴት ልጆቼ ጋር ሆነን ተከፋፍለነዋል። ኖርማ አድሪአና ሳሎን ቤቱን፣ ሁለት መኝታ ቤቶችን፣ በረንዳውንና በቤቱ ፊት ለፊት ያለውን መንገድ ታጸዳለች። አና ኮአኪና ወጥ ቤቱን ታጸዳለች። እኔ ልብሶችን ሳጥብና አንዳንድ ነገሮች ሳደርግ ማሪአ ዴል ካርመን ደግሞ ዕቃዎችን ታጣጥባለች።”

ያማረ ግቢ

ስለ ግቢውስ ምን ለማለት ይቻላል? የምትኖሩት በትልቅም ሆነ መጠነኛ ስፋት ባለው ቤት ውስጥ ግቢው የሚጸዳበትና የሚስተካከልበት ፕሮግራም ያስፈልገዋል። ለምሳሌ የግቢው በር ማጠፊያው ወልቆ ይሆናል። በሩ ተገንጥሎ እስኪወድቅ ድረስ ባይጠገን ለእይታ ምን ያህል አስቀያሚ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። በቤቱ ደጃፍ ላይ ወይም ግቢው ውስጥ የተጠራቀመ ቆሻሻ ካለም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ቆርቆሮዎች፣ የተለያዩ መሣሪያዎችና ሌሎች ዕቃዎች ከቤቱ ውጭ በተዝረከረከ መልኩ ይቀመጣሉ፤ ይህም ለተባዮች መደበቂያ ይፈጥርላቸዋል።

አንዳንድ ቤተሰቦች እንደ አስፈላጊነቱ በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ ደጁን፣ ግቢውን እንዲሁም ከግቢው ውጭ ፊት ለፊታቸው ያለውን አካባቢ ያጸዳሉ። እርግጥ በአንዳንድ ቦታዎች መንግሥት አካባቢን የሚያጸዳበት በጣም ጥሩ አሠራር ሲኖረው በሌሎች ግን እንዲህ ዓይነት የጽዳት ፕሮግራም የለም። ሁላችንም አካባቢያችን ንጹሕ እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ካበረከትን የምንኖርበት ሰፈር ጥሩ መልክ እንደሚኖረውና ለጤና ጠንቅ የሚሆኑ ነገሮች እንደሚወገዱ ምንም ጥርጥር የለውም።

አንዳንድ ቤተሰቦች ከላይ የተጠቀሱትን ሥራዎች የሚያከናውኑበት ፕሮግራም ከማውጣታቸውም በላይ ፕሮግራሙን በወረቀት ጽፈው ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ላይ ይለጥፉታል። ይህም ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። እርግጥ በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ንጽሕና ማወቅ ያለባችሁን ሁሉንም ነገሮች አላካተትንም። ለምሳሌ ያህል፣ ለአካባቢያችሁ አመቺ የሆኑት የጽዳት ዕቃዎች ምን ዓይነት እንደሆኑና አቅማችሁ የሚፈቅደው የትኞቹን መሣሪያዎች ለመጠቀም እንደሆነ መወሰን ያለባችሁ እናንተ ናችሁ።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት አጠር ያሉ ሐሳቦች ቤትንና አካባቢን በንጽሕና መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ቤተሰቡ በጠቅላላ እንዲገነዘብ እንደሚረዱት እርግጠኞች ነን። ቤትንና አካባቢን በንጽሕና መያዝ የተመካው በገንዘብ አቅማችሁ ላይ ሳይሆን በአመለካከታችሁ ላይ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርባችሁም።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቤት ጽዳት ፕሮግራም

ክፍት የሆነው ቦታ ላይ የምትፈልጓቸውን ነጥቦች መጨመር ትችላላችሁ

አስፈላጊ ማሳሰቢያ:- የማጽጃ ኬሚካሎችን በተለይ ደግሞ በረኪናን አሞኒያ ከተባለው ኬሚካል ጋር መቀላቀል በጣም አደገኛ ነው

በየቀኑ

መኝታ ቤት:- አልጋ ማንጠፍና ዕቃዎችን በመልክ በመልኩ ማስቀመጥ

ወጥ ቤት:- የቆሸሹ ዕቃዎችንና የዕቃ ማጠቢያ ገንዳውን ማጣጠብ። ጠረጴዛውንና የዕቃ ማስቀመጫውን ማጽዳት። ወለሉን መጥረግ ካስፈለገም መወልወል

መታጠቢያ ቤት:- የእጅ መታጠቢያውንና የሽንት ቤት መቀመጫውን ማጠብ። ዕቃዎችን በየቦታቸው ማስቀመጥ

ሳሎን ቤትና ሌሎች ክፍሎች:- ዕቃዎችን በየቦታቸው ማስቀመጥ። ቀለል ያለ ጽዳት ማድረግ። አስፈላጊ ከሆነ ወለሉን መጥረግ ወይም መወልወል

ጠቅላላ ቤቱ:- ቆሻሻዎችን በተገቢው ቦታ መድፋት

በየሳምንቱ

መኝታ ቤት:- አንሶላ መቀየር። አስፈላጊ ከሆነ ወለሉን መጥረግ ወይም መወልወል። ከዕቃዎች ላይ አቧራ ማንሳት

ወጥ ቤት:- ምግብ ማብሰያውን፣ የዕቃ ማስቀመጫውንና ማጠቢያ ገንዳውን ማጽዳት። ወለሉን መወልወል

መታጠቢያ ቤት:- መታጠቢያ ገንዳውንና ቧንቧዎቹን እንዲሁም ግድግዳውን ማጠብ። ሽንት ቤቱን፣ የዕቃ መደርደሪያውንና ሌሎች ቦታዎችን በጀርም ማጥፊያ ማጽዳት። ፎጣዎችን መቀየር። ወለሉን መጥረግ ወይም መወልወል

በየወሩ

መታጠቢያ ቤት:- ግድግዳዎቹን በሙሉ በደንብ ማጠብ

ጠቅላላ ቤቱ:- የበሮቹን ክፈፍ እንዲሁም የወንበሮቹን መቀመጫዎች በደንብ ማጽዳት

የአትክልት ቦታው፣ ግቢውና ጋራዡ:- አስፈላጊ ከሆነ መጥረግና ማጽዳት። ቆሻሻ ወይም የማያስፈልጉ ነገሮች እንዳይጠራቀሙ ማስወገድ

በየስድስት ወሩ

መኝታ ቤት:- የአልጋ ልብሶችን ማጠብ ወይም በፋብሪካው መመሪያ መሠረት ማጽዳት

ወጥ ቤት:- ከማቀዝቀዣው ውስጥ ዕቃውን አውጥቶ በደንብ ማጽዳት

መታጠቢያ ቤት:- የዕቃ መደርደሪያዎቹንና መሳቢያዎቹን አጋብቶ ማጽዳት። የማያስፈልጉ ወይም ጊዜ ያለፈባቸውን ነገሮች መጣል።

ጠቅላላ ቤቱ:- አምፖሎቹን፣ ማብሪያ ማጥፊያዎቹን፣ ሶኬቶቹን እንዲሁም አየር ማቀዝቀዣውን ማጽዳት። በሮቹን፣ መስኮቶቹንና መስታወቶቹን መወልወል

በየዓመቱ

መኝታ ቤት:- ቁም ሳጥን ውስጥ ያለውን ልብስ አውጥቶ በደንብ ማጽዳት። የማያስፈልጉ ነገሮችን ማስወገድ። ብርድ ልብስ ማጠብ። ፍራሹንና ትራሱን እንዲነፍስበት ማድረግና ማጽዳት

ወጥ ቤት:- የዕቃ መደርደሪያዎቹና መሳቢያዎቹ ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች አውጥቶ በደንብ ማጽዳት። አላስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን መጣል። ዕቃዎችን በማንፏቀቅ ከኋላቸው ያለውን ግድግዳና መሬቱን ማጽዳት

ጠቅላላ ቤቱ:- ግድግዳዎቹን በሙሉ ማጠብ። የወንበሮቹንና የሶፋዎቹን መቀመጫዎች እንዲሁም መጋረጃዎቹን ማጽዳት

ጋራዡ ወይም መጋዘኑ:- በደንብ መጥረግ። የማያስፈልጉ ነገሮችን ማውጣት ወይም ማስተካከል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“እያንዳንዱ ነገር የራሱ ቦታ ሊኖረውና ሁሉም ሰው ዕቃውን በቦታው ሊያስቀምጥ ይገባል”

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የማትጠቀሙባቸውን ነገሮች ማስወገድ ቤታችሁን በንጽሕና ለመያዝ ሊረዳችሁ ይችላል